የድሬዳዋ ሳባ ደ/ኀ/ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን |
- በቅ/ሲኖዶሱ አቋም የተደሰቱት የደብሩ ካህናት፣ ምእመናንና የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት አጣሪ ኮሚቴውን ለማገዝ ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
- ኮሚቴው ማጣራቱን እስኪያጠናቅቅ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ሥ/አስኪያጅ እና የደብሩ አስተዳዳሪ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ታግደው እንዲቆዩ ተወስኗል።
- ጉድለቱ ከብር 1.8 ሚልዮን አሁን ከብር 5.6 ሚልዮን በላይ ደርሷል።
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 1/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 11/2012/ READ IN PDF)፦ ከቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመዋቅር ማሻሻያዎች፣ በዕርቀ ሰላም እና በቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፎች ላይ አበክሮ እየሠራ የሚገኘው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው ፀረ - ሙስና አቋም ያላቸውን አገልጋዮች ለበለጠ ተጋድሎ የሚያነሣሣ፣ ምእመኑም በአመራሩ ላይ ያለው እምነት ይጠናከር ዘንድ ታላቅ ተስፋ የሚሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ይህ ውሳኔ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም በተመረጡት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና በዚሁ ዕለት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቱን ለማገዝ በተጨመሩት ስምንት ብፁዓን አባቶች የተጠናከረው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዐበይት መዋቅራዊ ችግሮች ተለይተው አስፈላጊው የተቋማዊ ማሻሻያ ርምጃዎች እስኪወሰዱ ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ይኹን በአህጉረ ስብከት ደረጃ የሚፈጸም ማንኛውም ቅጥር፣ የደረጃ ዕድገት እና የደመወዝ ጭማሪ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲቆም በማድረግ ለሚያካሂደው እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚሰማና የሚዳሰስ መልእክት ነው፡፡
ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ዛሬ ከቀትር በፊትና በኋላ ባካሄደው ስብሰባ ከቀድሞው ፓትርያርክ ጀምሮ ሲንከባለል የቆየው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንደሰፈነ የሚነገረው የአስተዳደር በደል በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብለት ወስኗል፡፡ የሕግ ተጠያቂነትንና አስተዳደራዊ ርምጃን ሊያስከትል እንደሚችል የተጠቆመውን የማጣራት ሥራ ሠርቶ ሪፖርት የሚያቀርበው በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ በአቶ ተስፋዬ ውብሸት የሚመራ ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴም አቋቁሟል፡፡
አጣሪ ኮሚቴው ነገ ዓርብ ወደ ድሬዳዋ በማምራት በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑና በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በሚኖረው ቆይታ በሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመልአከ ኀይል አባ ገብረ ሥላሴ ቸኮል እና በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በአባ አረጋዊ ነሞምሳ ከአንድም ሁለት ጊዜ የታገዱትን የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የሀ/ስብከቱን አስተዳደር ጉባኤ አባላት እንደሚያነጋግር ይጠበቃል፡፡ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ ደስታቸውን እየገለጹ የሚገኙት የደብሩ ምእመናን፣ ካህናትና የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ከአጣሪ ኮሚቴው ጋራ ለመተባበርና ተልእኮውን ለማገዝ ዝግጁ መኾናቸው ተዘግቧል፡፡
ኮሚቴው የማጣራት ሥራውን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጁና የደብሩ አስተዳዳሪ ምንም ዐይነት እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት እንዳያደርጉ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ታዝዘዋል፡፡ ይኸው ትእዛዝ ሥራ አስኪያጁ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ የአቤቱታ ፊርማ ሰብስበው የሚጠባበቁት የሰባት አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በተቃውሟቸው ሳቢያ በሕገ ወጥ ዝውውርና ከደረጃ ዝቅ መደረግ ለተሠቃዩትና በቀጣይም ርምጃ እንደሚወሰድባቸው ዛቻ የደረሰባቸው የአድባራት ጸሐፊዎች፣ ካህናትና ምእመናን በነጻነት ከኮሚቴው ጋራ ለመተባበር እንዲችሉ በማሰብ እንደ ኾነ ተመልክቷል፡፡
ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ከዚህ አቋም ላይ የደረሰው ባለፉት ሁለት ዓመታት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ኾነው የቆዩት ብፁዕ አቡነ ገሪማ እንዲያስረዱ በተጠሩበት ጉዳይ በጽሑፍ ያቀረቡትን ምላሽ ካደመጠ በኋላ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ሒሳብ፣ የግንባታ ጥራትና ተያያዥ አስተዳደራዊ በደሎች ዙሪያ ስለቀረበው አቤቱታ በጽሑፍ ያቀረቡት ምላሽ የተጠየቁባቸውን ጉዳዮች ፍሬ ነገር የማይመለከትና ጨርሶ የሚክድ፣ አቤቱታ አቅራቢዎችንና ደጋግ ምእመናንን እንደ ግለሰብ የሚተች ዘለፋ እንደ ነበር ተገልጧል፤ “እኔንና የሀ/ስብከቴን ስም ለማዋረድና ለማጥፋት የተቀነባበረ ሤራ ነው” በሚል አቤቱታውን ያጣጣሉበት ጽሑፍም በእርሳቸው ምትክ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ኾነው ሀገረ ስብከቱን ‹በሚመሩት› በልዩ ጸሐፊያቸው መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም እና በሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ ሊቀ መንበር በአቶ ብርሃኔ መሐሪ የተዘጋጀ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ጉዳዩን እንዲያስረዱ የተጠሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳ የደብሩን አስተዳዳሪ፣ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብርሃኔ መሐሪ፣ የሀ/ስብከቱን ጸሐፊ እና የሕግ ክፍል ሓላፊ አስከትለው አዲስ አበባ በመምጣት የቀረቡ ሲኾን በስብሰባው ላይ እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ግን አልነበሩም፡፡ ፍላጎቸታቸው ከጉዳዩ ጋራ ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች በገንዘብ በመደለል አጣሪ እንዳይመደብ መከላከል፣ “ኬዙን መዝጋት”ና መመለስ የነበረ ሲሆን ለዚህም ግለሰቡ ከጉዞው በፊት በአንድ የድሬዳዋ የግል ባንክ ቅርንጫፍ ከሚገኘው የዘረፋ ድልቡ (ተቀማጩ) በርከት ያለ ብር አውጥቶ እንደነበር ተነግሯል፡፡
እነ አቶ ብርሃኔ በዚህ ባይሳካላቸውም በቀድሞው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ ተሠርቶ፣ በሀ/ስብከቱ ቁጥጥር ታምኖበት የተፈረመበትን የብር 1.8 ሚልዮን ጉድለት የሚያሳየውን የኦዲት ረፖርት በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ ተለውጦ በተሠራ ሌላ ሪፖርት ወደ ተራ “የአሠራር ግድፈት” ተለውጦ ታይቷል፡፡ ይኹንና ኦዲቱ የተለወጠበት ኹኔታ በምርመራ ወቅት ሪፖርቱ በተመሠረተባቸው ሰነዶች ለማስተያየት በመቻሉ የቁጥጥር አገልግሎቱ ባልደረባ ክፉኛ ከመወቀስ አልፎ ርምጃ ሊወሰደበት እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ ሀ/ስብከታቸውን በአግባቡ/በቅርበት ሳይከታተሉ የቆዩት ብፁዕ አቡነ ገሪማ በትችት ላይ በማተኮር አንዳችም ስሕተት እንዳልተፈጸመ በማስመሰላቸው ከቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ አባላት ጠንከር ያለ ተግሣጽ አግኝቷቸዋል፡፡
ከቀትር በኋላ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ አቡነ ገሪማ ባቀረቡት የጽሑፍ ምላሽ፣ ስድስት የአገልጋዩና የምእመኑ ተወካዮች ያቀረቡትን አቤቱታ እና የቁጥጥር አገልግሎቱ የኦዲት ሪፖርት በአንድነት በማቅረብ ክርክር አድርጎበታል፡፡ በዚህም የደብሩ አስተዳዳሪና የሀ/ስብከቱ ሥ/አስኪያጅ እንዲነሡ፣ ሊቀ ጳጳሱም ታግደው እንዲቆዩ ከሚለው ጀምሮ ጠንካራ ሐሳቦች የቀረቡ ቢኾንም በመጨረሻ አጣሪ ኮሚቴው እንዲላክና እስከ ሰኞ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በአስቸኳይ የውሳኔ መነሻ ሐሳብ እንዲያቀርብ መወሰኑ ታውቋል፡፡ በስብሰባው ሂደትና ውሳኔ የተደናገጡት አባ አረጋዊ “ከላይም ከታችም እሳት እየነደደብኝ” ነው ሲሉ ከላይ ጫና እየፈጠሩ እሳት ከሚያነዱባቸው አንዱ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለ “ጥፋቱ ጥፋት ነው፤ ልማቱ ልማት ነው፤ ከእኛ አቅም በላይ ነው፤ እንዲህ ባንቀሳቀሱት ሰዎች ላይ መሥራት አለባችኹ፤” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የአጣሪ ኮሚቴው የትኩረት ነጥቦች እንደሚኾኑ ከሚጠበቁት መካከል፡- የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ በተደጋጋሚ በአለቃውና በሥራ አስኪያጁ መታገዱና ከቃለ ዐዋዲው ውጭ የራሳቸውን ሰዎች በሓላፊነት ማስቀመጣቸው፤ የሕንጻ ሥራውን በአነስተኛ ዋጋ ለመሥራት ቃል የገቡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የተፈራረሙበት የሥራ ስምምነት እያለ ከቃለ ዐዋዲው በተፃራሪ ራሱን ለቀድሞው ፓትርያርክ ተጠሪ ያደረገው ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በፊርማቸው እንዲጸድቅ አለመደረጉ፤ ከውለታ ጊዜውና ከውለታ ስምምነቱ ውጭ የደብሩ ሰበካ ጉባኤና የፕሮጀክቱ አማካሪ መሐንዲስ ሳያጸድቅ ክፍያ መፈጸሙ፤ የዋጋ ግሽበት ከሚመለከታቸው ሲሚንቶ፣ ነዳጅና ብረት ውጭ የአጠቃላይ ነጠላ ዋጋ ማሻሻያ በማድረግ ሰበካ ጉባኤው ያላጸደቀው፣ ገለልተኛ መሐንዲስ ያላየው ክፍያ በወቅቱ የናረ ዋጋ መፈጸሙና ያስከተለው ብክነት፤ የሕንጻ ግንባታው የምሕንድስና ጥራት፤ ሙስናን በመቃወማቸው ከነበሩበት ደብር ወደ ሌላ በግዳጅ ስለተዘዋወሩ ወይም ከደረጃ ዝቅ ስለተደረጉ አገልጋዮች . . . የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment