- ብፁዓን አባቶችን በጎጥ በመከፋፈል ቀጣዩን ፓትርያርክ በብሔር ማንነት ለማስመረጥ በየሆቴሉ፣ በየመናፈሻው እና በየግለሰቡ ቤት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ የሚገደዱበት አቋም እንዲወሰድ ለአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊዎች ጥሪ ቀርቧል።
- በሪፖርት የተካተተው የዋልድባ ጉዳይ በንባብ መዘለሉ ጥያቄ አሥነስቷል።
በውጭና በሀገር ውስጥ ከሚገኙ 49 አህጉረ ስብከት የተውጣጡ 750 የካህናት፣ ሊቃውንት፣ ሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን ተወካዮች የሚሳተፉበትና እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ይኸው መደበኛ ስብሰባ የሚመራው በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ርእሰ መንበርነት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሰብሳቢነት ነው፡፡
አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በሥራ ላይ በሚቆይባቸው ስድስት ተከታታይ ቀናት÷ የቤተ ክርስቲያናችንን የማእከልና የአህጉረ ስብከት የ2004 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያዳምጣል፤ በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አስተባባሪነት በባለሞያዎች የተዘጋጁ፣ ቤተ ክርስቲያናችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ችግር የሚዳስሱና የሁለንተናዊ ተቋማዊ ለውጥ አቅጣጫን በሚያመላክቱ ስምንት ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርቡለታል፤ በመጨረሻው ቀንም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመምሪያ ሓላፊዎች በሚረዱና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሩ 12 ምድቦች ተከፍሎ በሰሞናዊ ውሎው በተነሡ ዐበይት ጉዳዮች ላይ የቡድን ውይይት ያደርጋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ በረፋዱ የጉባኤው የሻይ ዕረፍት ላይ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ለጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መነሻና ግብአት የሚኾኑ ውሳኔዎችን፣ የአቋም መግለጫዎችንና አቅጣጫ አመላካች ጥናቶችን አዳብሮ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ እሑድ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚካሄድ የመክፈቻ ጸሎት የሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ለአጠቃላይ ጉባኤው ባቀረቡትና በጥልቀት እንዲመከርባቸው በጠየቁት አምስት ነጥቦች ላይ እንደሚመክር አመልክተዋል፡፡
49ኙ አህጉረ ስብከት አብያተ ክርስቲያንና ሰበካ ጉባኤያትን ስለማጠናከር፣ አብነት ት/ቤቶችን፣ ስብከተ ወንጌልን፣ የሰንበት ት/ቤቶች እንቅስቃሴን፣ መልካም አስተዳደርን፣ የገዳማትና ቅርሳቅርስ አጠባበቅን፣ የራስ አገዝ ልማትንና ምግባረ ሠናይን፣ የገንዘብና ንብረት አያያዝን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና የወደፊት ዕቅዶችን በማካተት በዋና ሪፖርታቸው በስፋት ያቀረቡትን አጠቃለውና አሳጥረው በንባብ ያሰሙት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት÷ አጠቃላይ ጉባኤው በጥልቀት መክሮ ለቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጋቢ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብባቸው የጠየቁባቸው አምስቱ ነጥቦች፡-
- ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ድረስ የሚገኙ ካህናትና ሠራተኞች በሙሉ በሰበካ ጉባኤ ተመዝግበው አስተዋፅኦ መክፈላቸው በትክክል ስለሚረጋገጥበትና ለምእመናን መልካም አርኣያ ስለሚኾኑበት፤
- የመላው ካህናትና ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ማለትም የጡረታ መብትስለሚከበርበት፤
- የቤተ ክርስቲያኒቱ መላው ገቢ በአንድ ካዝና ተሰብስቦ የበጀት ማእከላዊነት እንዲኖር ስለሚቻልበት፤
- የአብያተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ሁሉ በዐቅም መጠን ተጀምረው በተወሰነ ጊዜ ስለሚጠናቀቁበት ኹኔታ፤
- ገዳማት ናቸው በሚል ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ ተነጥለው ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች የበላይ አስተዳደር ውጭ ያሉ አንዳንድ ገዳማት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የበላይ አስተዳደር ስለሚታቀፉበት ኹኔታ የሚሉ ናቸው፡፡
በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አስተባባሪነት በባለሞያዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡትና አጠቃላይ ጉባኤው የቡድን ውይይት የሚያካሂድባቸውን ስምንቱን ርእሰ ጉዳዮች አቶ እስክንድር ሲዘረዝሩ፡-
- ስትራተጅክ ዕቅድ ለቤተ ክርስቲያን ልማት የሚኖረው ጠቀሜታ፤
- በቤተ ክርስቲያን ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የፋይናንስ ሲስተም የማደራጀት ጠቀሜታ
- የዘመናችንን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማብቃት የአባቶች ሚና፤
- ቤተ ክርስቲያን በድኅነት ቅነሳ ላይ ልታበረክት የምትችለው አስተዋፅኦ፤
- ፍሬያማ አመራር ለቤተ ክርስቲያን ልማት ያለው ድርሻ፤
- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊ ሚና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ታሪክ ውስጥ፤
- መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥቱ ያለው ድርሻ፤
- ግጭት፣ የግጭት መንሥኤና አፈታት የሚሉ እንደኾኑ
በመግለጽ ቤተ ክርስቲያናችን ከምትገኝበት የተቋማዊ ለውጥ ኹኔታ አኳያ የጥናቶቹ ቁጥር መብዛት፣ ፋይዳቸውን ይበልጥ ለማጎልበትም ተሳታፊዎች የቡድን ውይይት እንዲካሄድባቸው መደረጉ የዘንድሮውን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከቀድሞው እንደሚለየው አስረድተዋል፡፡
ከጥናታዊ ጽሑፎቹ መካከል “ግጭት፣ የግጭት መንሥኤና አፈታት” የሚለው ጽሑፍ ትናንት ከቀትር በፊት በአዘጋጁ በአቶ ይልቃል ሽፈራው የቀረበ ሲኾን የልማት ኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ውይይቱን መርተዋል፡፡ በጥናት ጽሑፉ መሠረት ግጭት የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ክሥተት ቢኾንም መልካም አስተዳደርን በማስፈንና በይቅርባይነት ሊፈታ እንደሚችል ዝርዝር የግጭት ባሕርያትንና የአፈታት ስልቶችን በመተንተን ያስረዳል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊውን አጭር መግለጫ ተከትሎ ጋዜጠኞች ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ውስጥ በጽሑፍ ሰፍሮ ሲያበቃ በንባብ የተዘለለው የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ከገዳማትና ቅርሳቅርስ አጠባበቅ ጉዳይነቱ ይልቅ በመልካም አስተዳደር ንኡስ ርእስ ሥር ተጠቃሎ የቀረበው በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ ስለተጋረጠው ችግር በአጭሩ የተመለከተው ዐረፍተ ነገር÷ “በዋልድባ አብረንታንት አንድነት ገዳም በግድብ ምክንያት የተነሣው ውዝግብ በተቀናጀ የቡድን ተልእኮ መረጋጋት ችሏል” በሚል ሰፍሯል፡፡ አቶ እስክንድር በአሁኑ ወቅት ስለ አካባቢው አስተማማኝ መረጃ መኖሩን ተናግረው ይህም ቀደም ሲል በተለይም በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘንድ የታየው የአስተሳሰብ መዛባት በውይይት በመፈታቱና ችግሩ በነበረበት ደረጃና መጠን የሌለ በመኾኑ፣ የሌለን ችግር ደግሞ አጉልቶ ማውጣት ባለማስፈለጉ እንደ ኾነ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ ከሰዓት በኋላ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የቀረበው ሪፖርትም በዛሬማ ወንዝ መገደብ ሳቢያ በዋልድባ አንድነት ገዳም ውዝግብ መነሣቱንና በሕዝበ ክርስቲያኑም ላይ የሥነ ልቡና ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው÷ “ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከፌዴራል መንግሥት የተውጣጣ ልኡክ ከቦታው ድረስ ሄዶና አይቶ የዐይን ምስክርነት የሰጠውን ቡድን ሐሳብ መነሻ በማድረግ በጎንደር፣ በደባርቅ፣ በዛሬማና በዓዲ አርቃይ ከተማዎች በተካሄዱ የሕዝብ ኮንፈረንሶች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማረጋጋትና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተችሏል፡፡”
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊውና የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት እንዲህ ይበሉ እንጂ ሌሎች የሀገረ ስብከቱ ምንጮች እንደሚሉት ከወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ጋራ በተያያዘ በዓዲ አርቃይ ወረዳ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከጠቅላላ ገቢያቸው የሚጠበቅባቸውን የ20 በመቶ ፈሰስ ለወረዳ ቤተ ክህነቱ ባለማድረግ በተቃውሟቸው እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ከፐርሰንት ክፍያ ጋራ የሚገናኘው ውዝግብ በፕሮጀክቱ ሳቢያ የተነሣው ተቃውሞ አካል ሳይሆን ፈሰሱን አናደርግም ያሉትን አብያተ ክርስቲያን ባለቤትነት በተመለከተ በዋልድባ ገዳምና በሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት መካከል ጥያቄ በመነሣቱ ምክንያት መኾኑን አቶ እስክንድር “በሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት የሚገኙት አብያተ ክርስቲያን ሞፈር ቤትና ምግብ ማዘጋጃ ሰበካዎች በመሆናቸው የገዳሙ አካል ናቸውና ፐርሰንት ለመክፈል አይገደዱም ሲል ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ በሥሬ ናቸውና ይከፍላሉ ይላል እንጂ ከፕሮጀክቱ ጋራ አይገናኝም፡፡” ሲሉ ያስረዳሉ። ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በፊናቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ የዋልድባ ገዳምን ከግማሽ በመቶ በላይ የኑሮ መሠረት የሚደግፉ በመኾናቸው ውዝግቡ ከታላቁ ገዳም ህልውና በአግባቡ ሊጤን እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡
በሌላ በኩል አጠቃላይ ጉባኤው ስለ ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫና ማንነት ፍንጭ የሚታይበት አጀንዳ ይኖር እንደኾን ከጋዜጠኞች ስለቀረበው ጥያቄ አቶ እስክንድር÷ ጉባኤው የቤተ ክርስቲያኒቱን የ2004 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም፤ በማኅበራዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ልማታዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማመላከት እንጂ በፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ላይ የመወያየት ይኹን የመወሰን ሥልጣን እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የፓትርያርክ ምርጫ መቼና እንዴት ይኹን የሚለውን መወሰን የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊው፣ ቅ/ሲኖዶስ በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤው ጉዳዩን ሊያነሣውም ላያነሣውም እንደሚችል፣ አጠቃላይ ጉባኤውም የፓትርያርክ ምርጫን የሚመለከት አጀንዳ የሚነሣበት እንዳልኾነ አስረድተዋል፡፡
ይኹንና አቶ እስክንድር በሓላፊነት የሚመሩት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ወቅታዊ ጉዳይን በሚመለከት ለ31ኛው ዓለም አቀፉ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጉባኤተኞች መልእክት አስተላልፏል፡፡ መልእክቱ አጠቃላይ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያናችን የምትገኝበትን የሽግግር ወቅት በመጠቀም በየሆቴሉ፣ በየመናፈሻውና በየግለሰቡ ቤት በመዞር ብፁዓን አባቶችን በትውልድ ማንነታቸው በመከፋፈል÷ “የእገሌ ዘር ከእገሌ ዘር ይሻላል፤ ቀጣዩ ፓትርያርክ እንደ ፖሊቲካ ፓርቲ ምርጫ በዘርና በመንደር መመረጥ አለበት በማለት ደፋ ቀና የሚሉ” የተሐድሶ መናፍቃን ግንባር ቀደም መሪዎች ያደራጇቸው ጥቅመኛ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያደርግ የጋራ አቋም እንዲወስድ ይጠይቃል፡፡
የመልእክቱ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች የሰፈረው ነው፡፡ እርሱን እንድትመለከቱ በመጋበዝ የ31ኛውን ዓለም አቀፍ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሂደት የተመለከቱ ቀጣይ ዘገባዎችን እንዳስፈላጊነቱ እንደምናቀርብ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
ሳይቃጠል በቅጠል
(የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ)
አንጋፋዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ተከታይ ምእመናን እንዳሏት ይታመናል፡፡ ይህች አንጋፋና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ጥንተ ሥልጣኔ መሠረት ስትኾን ለኢትዮጵያ የቱሪስት መዲናነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እና መሠረት እንደኾነችም ማንም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነቱን እንዲያከብር፣ ባህሉንና ቅርሱን እንዲከባከብ በሥነ ምግባር በግብረ ገብነት የታነጸ እንዲኾን ያበረከተችው አስተዋፅኦም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖቱን ጠባቂነትና ባህሉን አክባሪነት በምስክርነት እንድትጠቀስ አድርጓታል፡፡ በዚህ መስክም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ውጭ የኾኑ ወገኖችንም በፍቅርና በክብካቤ በመያዝ ፍቅርን፣ አንድነትንና መቻቻልን በተግባር የሰበከች ስትኾን በውጤቱም ለኢትዮጵያ የእምነቶች መቻቻል ቁልፍ ሚና የተጫወተች አንጋፋና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡
ብሔራዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን ለመላው ሕዝብ ከማዳረስ አንጻር በከተማ ያልተወሰነች፣ በየገጠሩ የሚገኙ ሕዝቦችን በስብከተ ወንጌል በመማረክ ተከታዮቿ ያደረገች በውጤቱም በመላ ሀገሪቱ ለመስፋፋት የቻለች ስትኾን በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ ወገኖችም በሰላም፣ በመፈቃቀርና በመቻቻል ከሌሎችም ወገኖች ጋራ መኖር እንዲችሉ ያስተማረች እናት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡
ይህም ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በብሔር ትምክህተኝነት የምትገለጽ ስትሆን ለኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት መሆን የምትችል ብሔራዊት እናት ነች፡፡ ይኹንና የቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ተምሳሌትነት ያልተመቻቸውና ከመጠን በላይ መስፋፋቷ ያሰጋቸው አንዳንድ ወገኖች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመበታተን፣ ለማዳከም አቋራጩ መንገድ በብሔር፣ በጎጥ በዘርና በመንደር እንድትከፋፈል በማድረግ ማዳከም እንደሚቻል በመገመታቸው በዚህ ስሌት አንዳንድ የዋህ ሰዎችን በመቀስቀስና በማስተባበር ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማመስና ለመበታተን ታጥቀው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡
ይህ ቀላል የሚመስል ነገር ግን እጅጉን አደገኛ የኾነው የመበታተንና የማፈራረስ ስትራቴጂ ለጥቅመኞች፣ አሉባልተኞች እና ሥራ ፈቶች እጅግ የሚመች ሲሆን ለምስኪኑ ምእመን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንዲህ ከኾኑ እኛ ምን አገባን? ብለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥለው እንዲኾኑ ጥቂቶቹም ከመናፍቃን ጎራ እንዲሰለፉ ሰበብ ኾኗቸዋል፡፡
ይህ በዘርና በጎጥ የመከፋፈል ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰው አልባ የሚያደርጋት መኾኑን በመረዳትም በዚህ መሠሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማስተማር፣ በማረምና በመምከር መመለስ ግድ ይላል፡፡ በተለይ ካለፉት ኻያ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መሰባሰብ፣ መደራጀትና መንቀሳቀስ የጀመሩት የተሐድሶ መናፍቃን ስብስብ ይህን የመሰለ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፈራረስ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህንኑ በመረዳት ቡድኑ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች፣ ያቀጣጠላቸውን እሳቶች በማጥፋት ከዚህ እኵይ ዓላማው እንዲታቀብ ማድረግና የማያዳግም ርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን ከጥቅምቱ 31ኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ ጉባኤ ተሳታፊዎችም የሚጠበቅ ይኾናል፡፡
በተለይም ከአምስተኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ኅልፈተ ሕይወት ወዲህ በቀጣይ የፓትርያርክ ምርጫና በምርጫው መመረጥ ይገባቸዋል በሚሏቸው አባት ዙሪያ በየሆቴሉ፣ በየመናፈሻውና በየግለሰቡ ቤት በመዞር÷ ‹የእገሌ ዘር፣ የእገሌ ዘር› በማለት በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስና በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመረጠው ቅዱስ አባት እንደ ፖሊቲካ ፓርቲ ምርጫ በዘርና በመንደር መመረጥ አለበት በማለት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ፡፡
አንዳንዶቹ በዘር የሚመስሏቸውን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማነጋገር፣ በማደራጀት እና በመቀስቀስበማይመለከታቸው ጉዳይ እንዲገቡ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ እዚህ ላይ በየትኛውም የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኝ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዲህ ዐይነት አደገኛ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ በእሳት መጫወት እንደማይገባው የቡድን አደራጆቹ ያውቃሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስም የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ውጤቱ ሊመጣጠን የማይችል መኾኑን ማስላት ባለመቻላቸው አልያም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንዲህ ዐይነት እንቅስቃሴ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለው ማሰባቸው በእጅጉ የዋሆች እንደ ኾኑ የሚያመላክት ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሌሎች የዋሆችንና አላዋቂዎችን ሊያስትና ሊያሰናክል ስለሚችል ወሰንና ዳርቻ ተበጅቶለት እዚህ ላይ ይብቃ ሊባል ይገባዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪዎች በመምሰል ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማመስ፣ አባቶችን ከአባቶች በማለያየት መተማመንና መቀራረብ እንዳይፈጠር ሲሠሩ የነበሩ የተሐድሶ መናፍቃን ግንባር ቀደም መሪዎች በአባቶች እርስ በርስ መለያየትና መጋጨት ምንኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳጋበሱ ያውቃሉ፡፡ አሁንም አንዱን ከአንዱ ለማለያየት ጥሩ መንገድ የሚኾነው “አባቶችን በብሔር መከፋፈል ሲቻል ነው” በሚል የአላዋቂነት ስሌት በመንቀሳቀስ “ብፁዕ አቡነ እገሌ ከእነ ብፁእ አቡነ እገሌ ይሻላሉ፤ እርሳቸውን ለማስመረጥ ብንቀሳቀስ መልካም ነው፤ ከብሔርም ከትምህርትም አንጻር የተሻሉ ናቸው”ተሰብስበው ሲያቦኩና ያልበላቸውን ሲያኩ ሰንብተዋል፡፡
እነዚህ ኀይሎች መቼም ቢኾን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ደንታ የሌላቸው፣ በመከፋፈሉና በመለያየቱ መሀል እንዴት መጠቀም እንደሚችሉና እንደሚገባቸው ከማስላት የዘለለ ሕልም የሌላቸው በቀጥታ ከመናፍቃን በሚሰጥ አመራርና ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና እየተንቀሳቀሱ ያሉ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ያለውን የሽግግር ወቅት በመጠቀም የተሐድሶ መናፍቃንና ጥቅመኞች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማመስ፣ ለመበታተንና ሀብት ለማጋበስ ወቅቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር እየተንቀሳቀሱ እንደ ኾነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ስለሆነም ብፁዓን አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ሓላፊዎች፣ የ31ኛው ዓለም አቀፋዊ ሰበካ ጉባኤ ተሳታፊዎች፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎችና የጸጥታ ተቋማት “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በዚህ ደረጃ በውስጥም በውጭም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ነቅቶ መጠበቅ፣ መከታተልና ማረም እንደሚገባ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ዐዋጅ ነጋሪ፤ 5ኛ ዓመት ቁጥር 8፤ 2005 ዓ.ም
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment