Monday, May 7, 2012

ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ ኃላፊነታችን ነው" የሰሜን አሜሪካን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ


 

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሕገ ወጥ አካሄድ ያሳደረባቸውን ስጋት በመግለጽ ወጣቶች የአቋም መግለጫ አውጥተዋል:: የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ጋር አብሮ ለመሥራት በስልክና በደብዳቤ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳያገኝ እንደቀረ መግለጫው ያትታል ።  መሉ መግለጫውን ለማንበብ ይህንን PDF ይጫኑ::

ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ  ኃላፊነታችን ነው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 
በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ : ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን: በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን:: ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኅይል አትግዙ “ ፩ ጴጥ ፭፥ ፪-፫


ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አጽንዖት  ሰጥታ ከምታስተምረው ትምህርት መካከል አንዱ በሃይማኖት የተሰጠንን ኃላፊነት እንዴት መወጣት አንደሚገባን ነው ። ይህ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት የእምነቱን ተከታዮች በሙሉ የሚመለከት ሲሆን ፤ ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ፤በማስተማር ፤ በመዘመር ፤ እውነትን በመመስከር ፤ ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ፤የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በመጠበቅና በማስጠበቅ ፤ ደሃ እንዳይበደል ፤ ፍርድ እንዳይጓደል በቅንነት ውሳኔ በመስጠትና  ተመሳሳይ  የሆኑ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በመፈጸም የሚገለጽ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም  “ ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር እንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግእዞሙ ወተመሰሉ በሃይማኖቶሙ ፦ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” ዕብ 13፡7  ያለው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የተወጡ አባቶቻችንን በመመልከት እነርሱንም በሃይማኖት ፤በበጎ ምግባር እና ኃላፊነትን በመወጣት መስለን እንድንገኝ የተሰጠንን አደራ የሚያሳስብ ነው። ለዚህም ነው በሁሉም ቦታ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጉዳየ ብለው የቤተ ክርስቲያንን ነገር በመከታተል የቤተ ክርስቲያን አምነት ሥርዓትና መዋቅር በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይፋለስና ሰዎች የሚሰናከሉበት ችግር እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ለማድረግ መነሳት የሚገባቸው። ቤተ ክርስቲያን ከውስጥና ከውጭ ችግር ቢገጥማትም ፤ ከባድ የሚሆነው ከውስጥ የሚፈጠር ችግር ነውና በግልጽ እየተነጋገሩ ፤እውነትን  በመያዝ ለተፈጠረውም ችግር ሥር ሳይሰድ መፍትሔ እየሰጡ መሄድ  በተለይም  ቤተ ክርስቲያንን በኃላፊነት ከሚመሩ አባቶች የሚጠበቅ ነው ። 
ይህንን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ለመወጣት የቀደሙት ክርስቲያኖች የከፈሉትን መስዋዕትነት ስንመለከት እራሳችንን እንድንመረምርና አውቀንም ይሁን ሳናውቅ በምንፈጽመው ስህተት የቱን  ያህል ቤተ ክርስቲያንን  እንደምንጎዳ ፤ ጸጋና በረከት እንደምናጣ ፤እግዚአብሔርንም እንደምናዛዝን  ያስገነዝበናል ። የተሰጣቸውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ለመወጣት ሲሉ ብዙዎች ሰማዕትነት ከፍለዋል።ሐብትና ንብረታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ( ሐዋ 2፡45  )፤ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀንና ሌሊት ያገለገሉ ፤ እምነት የሌላቸውን ነገሥታትና መኳንንት ጭምር ሳይፈሩ  እውነትን የመሰከሩ ፤ የተገረፉ፤ በሰይፍ የተመተሩ ፤ ለአውሬ የተሰጡ ፤ በድንጋይ የተወገሩ ፤የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞረው ያስተማሩ  ፤ የዓለም ክብር ይቅርብን ብለው በዋሻና በምድረበዳ በጸሎት ተጠምደው የኖሩ  እነዚህ ሁሉ መከራን የተቀበሉት ፤ የቤተ ክርስቲያንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት የሚያስገኘውን ክብር ፤ ችላ ብለው ደግሞ ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ የሚጠብቃቸውን ፍርድ በመመልከት ነው ። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከተኛል ኃላፊነትም አለብኝ ብለን ለእውነተኛ አገልግሎት የምንነሳው በእግዚአብሔር የፍርድ ሚዛን ቀለን እንዳንገኝ ነው ። የኑሮአቸውንም ፍሬ ተመልከቱ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው የሰዎችን ስም  ሳይሆን  ምግባራቸውንና የእምነታቸውን  ፍሬ  ለይተን እና ትክክለኛነቱን አረጋግጠን እንድንከተላቸው ማሳሰቡ ነው ። 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ የተመሰረተውም ይህንን  የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ለመወጣት የሰንበት ት/ቤት አባላት ድርሻቸውን በመረዳት ለቤተ ክርስቲያን መዋቅር እምነትና ሥርዓት  መጠበቅ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ለማበረታታት ነው ። የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ከተመሰረተ 12 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ከአኅጉረ ስብከት ጋር አብሮ በመስራት የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲጠናከር፤ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ፤ገዳማትና አድባራት ያለባቸው ችግር እንዲቃለል ድጋፍ በማድረግ እና በመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎቶች እየተሳተፈ ይገኛል። ለአብነትም ያህል በምዕራብ ጎጃም ዞን የዋሻ አምባ ቅ/ተ/ኃይማኖት ገዳም የወፍጮ ተከላ ፕሮጀክት:በጅማ እና አካባቢው በአክራሪ እስላሞች ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተክርስቲያናት እና ምዕመናን መልሶ ማቋቋሚያ $11,000 (አስራ አንድ ሺህ የአሜሪካን ዶላር)፤ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የፅርሃ ጽዮን ማህበር ጋር በመተባበር በጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ሰባክያንን በቋንቋቸው ለማሰልጠን የተነደፈውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ በመሸፈን፤ በሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት በሆሳዕና ከተማ የሚገኘውን የንባብ እና የቅዳሴ ት/ቤት ፕሮጄክት በማስፈጸም፤ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ሶስቱ አኀጉረ ስብከቶች መካከል  የዋሽንግተን ዲሲ እና የካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከትን ለማጠናከር በሚደረገው እንቅስቃሴ በገንዘብ እና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በማገዝ፤ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ካከናወናቸው መልካም ስራዎች ከፊሎቹ ናቸው። የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሚተዳደርበትን ደንብ  በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ታይቶ የጸደቀ ሲሆን በየጊዜው የሚያደርገውንም እንቅስቃሴ ለብፁዓን አባቶች እና ለአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት በመግለጽ  ለአሠራር የሚጠቅሙ ሀሳቦችንም በመቀበል ሲሠራ ቆይቷል።በተለያየ ጊዜ ከቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው ከመጡ ብፁዓን አባቶች ጋር  እና ከሚመሯቸው አኅጉረ ስብከት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት   በርካታ ዓመታትን አሳልፏል።
ካለፉት 6 ወራት ማለትም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዋሽንግተን ዲሲና የካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ ወዲህ ያሉትን ነገሮች ስንመለከት ግን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ኅብረት : ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ : ለምዕመናን ፍቅርና ሰላም የሚደክሙትን ሁሉ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችን እየተመለከትን መጥተናል ። ለመጥቀስም ያህል ላለፉት 12 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ የሚገኘውን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አላውቀውም የማለት ፤ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር መጠበቅ የማያመላክቱ ሹመቶችን ሲሰጡ ማየት ፤ ለቤተ ክርስቲያን ቃለ ዓዋዲ የሚሰጠውንና ሊሰጠው የሚገባውን ትኩረት የሚቀንሱ ደብዳቤዎችንና  ፤ ያለ አግባብና ያለ ሥርዓት ሥልጣነ ክህነትን ለመያዝ የሚደረጉ ሙከራዎችን በማየታችን የበለጠ ግራ እየተጋባን እንድንሄድ  በማድረጉ ለቤተ ክርስቲያን  መዋቅር እና ለሥልጣነ ክህነት የተሰጠው ክብር  እያነሰ መጥቷል የሚል አመለካከት አሳድሮብናል ።
 በተለይም በአባቶች የተፈረሙ ደብዳቤዎች የቅዱሳን ክብር በሚዋረድበት አባ ሰላማ በተባለ ብሎግ (የመጻጻፊያ መድረክ) ላይ በተደጋጋሚ ሲወጣ ማየታችን  ከፍተኛ ሀዘን ፈጥሮብናል፤እንዴት ይህ ሊከሰት ቻለ ? የሚል ጥያቄ አሳድሮብናል።  የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት  የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ጋር አብሮ ለመሥራት በስልክና በደብዳቤ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል ።
በአጠቃላይ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ  አሁን የምንመለከተው ችግር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገንዝበናል ። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅርና ሥርዓት የሚያዳክሙ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆናቸውንና የመናገር መንፈሳዊ ኃላፊነት  እንዳለብን በመገንዘብ ብዙዎቻችንን ግራ እያጋባ ያለው አካሄድ በአስቸኳይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አናምናለን ። በዚህም መሰረት ፦
1.              ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜን አሜሪካ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርን ጠብቆ ስለመሥራት  ግልጽ  የሆነ መመሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን
2.             ከዚህ በፊት የነበሩት ብጹዓን አባቶች ያደርጉት እንደነበረው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና ሥርዓትን የበለጠ እንዲጠናከር የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚጠናከርበት መንገድ እንዲመቻችልን
3.             የቤተ ክርስቲያንን ደረጃ ያልጠበቁ ፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን  ተጽዕኖ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ደብዳቤዎችና አሠራሮች ሥርዓት እንዲይዙ እንዲደረግ  እንጠይቃለን።
4.             በቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች የሚጻፉ ደብዳቤዎች የቅዱሳን ክብር በሚነቀፍበት ብሎግ እንዳይወጣና የቤተ ክርስቲያንን እና አባቶችን ክብር ዝቅ እንዳያደርግ  ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን።
የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን
                                        ሚያዝያ 23 2004 ዓ. ም            
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ስራ አመራር
ሰሜን አሜሪካ
ግልባጭ:
·                     ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ፣
·                     ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት 
·                     ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት  
·                     በሰሜን አሜሪካ ላሉ ሶስቱም አህጉረ ስብከት
·                     ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት ፣
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment