Monday, May 14, 2012

በጀርመን የሚገኙ ምእመናን በአካባቢው በሚገኝ መናፍቅ ቄስ ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካላት አሁንም ምላሽ እየጠበቁ ነው


 (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 6/2004 ዓ.ም፤ May 14/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ለረጅም ዓመታት በጀርመን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን አቤቱታ ሲቀርብበት የነበረው ከመናፍቅነት “ተመልሻለሁ” የሚለው የ”ቀሲስ” ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ  እስካሁን ድረስ መፍትሄ አለማግኘቱ በአካባቢው ምእመናን ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን እያስነሣ ይገኛል። ሕዝበ ክርስቲያኑ ቅሬታቸውን ምንም እንኳን በተደጋጋሚ በጀርመን ካለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊ አንስቶ ጠቅላይ ቤተክህነት ድረስ ቢያሰሙም የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት አስገብቶ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው የቻለ አንድም አካል አለማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያስረዳል።


የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በነሐሴ ወር ፳፻፫ ዓ/ም  እኚህኑ ግለሰብ ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ በአጥቢያቸው ብቻ እንዲወሰኑ እገዳ ጥለውባቸው ከሄዱ በኋላ ግለሰቡ ምእመናንን የማሰናከል ሥራቸው እየከፋ ከመሄዱ በፊት በአስቸኳይ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ በጀርመን የሚገኘው የምእመናን ኅብረት የአቤቱታ ደብዳቤ በጥቅምት ለዋለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በብፁዕነታቸው በኩል ቢያቀርብም የሚጠበቀው ውሳኔ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።
በወርኃ ታኅሣሥ ፳፻፬ ዓ/ም የቅዱስ ገብርኤል በዓል በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሚከበርበት ጊዜ ምእመናን በድጋሚ ጥያቄውን ከሌሎች በጀርመን ከሚገኙ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት አስተዳደራዊ ችግሮች ጋር አንድ ላይ አድርገው ቢያነሱም “ጊዜ ስጡን” ከሚል ምላሽ ውጭ ተግባራዊ ነገር አለማየታቸው ወደ ተስፋ መቁረጡ እያስገባቸው እንደሆነ ጠቁመውናል። በሙኒክ በነበረው ንግግር ጉዳዩ በምእመናኑ በኩል በሰፊው የተነሳ ሲሆን ሊቀ ጳጳሱ የምእመናኑን ችግር ለማዳመጥ መድረክ መስጠታቸው ከጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ እና ከፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በኩል ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን በተለይ ከፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ከአባ ሲራክ ወልደሥላሴ ከአንድ የሃይማኖት አባት የማይጠበቁ ከሥርዓት ውጪ የሆኑ ንግግሮች እንዲሰሙ ምክንያት ሆኗል።

ሊቀ ጳጳሱን በምእመናኑ ፊት የዘለፉት አባ ሲራክ በአጥቢያቸው “ሰበካ ጉባዔው እንዳይጠናከር፤ ስብከተ ወንጌልም ተዳክሞ እንዲቆይ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቱም በአግባቡ እንዳይሠራ፤ ህጻናት ልጆቻችንም ተገቢውን መንፈሳዊ ትምህርት እየተማሩ እንዳያድጉ” ምክንያት ሆነዋል የሚል አቤቱታ ቀርቦባቸው ሳለ መናፍቁን ቄስ መከላከሉ ላይ መግባታቸው፣ ከማዕረገ ክህነታቸው ወደ ላይ ከፍ ብለውም ሊቀ ጳጳሱን መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል።  በሌላ በኩል በዋዜማው ዕለት የምእመናኑን ሮሮ ካዳመጡ በኋላ “በምትፈልጉት ጊዜ መጥቼ አብረን እንነጋገራለን” ብለው የነበሩት ሊቀ ጳጳሱ በበነጋታው ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ አሳባቸውን መቀየራቸው በጉዳዩ ጠንካራ አቋም መያዝ አለመቻላቸውን ከማሳየቱም በላይ በጀርመን ባሉት ኃላፊ እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ ያመላከተ አጋጣሚም ነበረ።

የሊቀ ጳጳሱን እገዳ ከቁብም ያልቆጠሩት ኃላፊውን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙት አንዳንድ ካህናት ከሁለት ሳምንታት በፊት በሚያዚያ ፳፩ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም መናፍቁ ቄስ በአጥቢያቸው ባከበሩት የንግሥ በዓል ላይ መገኘታቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሱ እገዳውን ያስተላለፉት ግለሰቡ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ምእመናንን በኑፋቄ ትምህርታቸው እንዳያሰናክሉ መሆኑ እየታወቀ ግለሰቡ በሚገኙበት ቦታ ምእመናንን አስተባብሮ ለመሄድ መሞከሩ ይህን ያደረጉት ካህናት ለሃይማኖት ጉዳይ ያለ ቸልተኝነተን ያሳየ ነው። በዕለቱ የተገኙት በጣም ጥቂት ምእመናን ሲሆኑ በዑደት ጊዜ ታቦቱን እንዲያጅቡ ከውጡት ሥዕላት ውስጥ የእመቤታችን ሥዕል አለመውጣቱን በቦታው ተገኝተው የነበሩ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ?” በሚል ርዕስ በዛው በጀርመን በሚገኝ የካስል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በመምህር ኅሩይ ኤርምያስ ተዘጋጅቶ በኅዳር ወር ፳፻፬ ዓ/ም ታትሞ ለአንባቢዎች የቀረበውና በ”ቄስ” ገዳሙ ደምሳሽ ለተፃፉት ሦስት መጻሕፍተ ኑፋቄ ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ምላሽ የሰጠው መጽሐፍ ራሳቸውን የቤተ ክርስትያናችን አባት ነኝ ብለው የዋህ ምእመናንን በማሰናከል ላይ ያሉትን የ”ቀሲስ” ገዳሙን ማንነት በማጋለጥ ደረጃ ትልቅ አስዋጽኦ እንዳለው መጽሐፉን አንብበው አስተያየታቸውን የሰጡን ምእመናን ገልጸውልናል።

በመጽሐፍ የገባን ኑፋቄ በመጽሐፍ መመለስ እንዲገባ ተረድተው ምላሹን ያቀረቡት መምህር ኅሩይ ልክ እንደቀደሙት ሊቃውንት ማለትም ኰኵሐ ሃይማኖትን እና መድሎተ አሚንን እንዳቀረቡልን እንደ ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፣ “መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና”ን እንዳስነበቡን ዓይናማው ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በሚጥም አንደበት የነሱን ፈለግ ተከትለው ያዘጋጁት መጽሐፍ ምላሽ ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ትምህርት ነው ሲሉ መጽሐፉን ያነበቡ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በምላሽ መጽሐፉ አቀራርብ እና ጥልቀት በጣም እንደተደሰቱ ቢያሳውቁንም በአንጻሩ የሊቃውንት እጥረት በሌለባት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የዋህ ምእመናን እንደ “ቀሲስ” ገዳሙ ላሉ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች ተላልፈው መሰጠታቸው እጅጉን እንዳሳዘናቸው፤ ጉዳዩ በሚመለከታቸው በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ኃላፊዎች ዝምታና ቸለተኝነትም  ቅር መሰኘታቸውን ጨምረው ገልጸውልናል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ምእመናን እየተነበበ ያለውና 219 ገጾች ያሉት ይኸው መጽሐፍ “ቀሲስ” ገዳሙ ደምሳሽ በሦስቱ መጽሐፎቻቸው ያቀረቡትን ኢኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች ነቅሶ በማውጣት በቀደሙ አባቶች ለዛ እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምረውን ትምህርት ያሳየ ሲሆን ምእመናንም ይኽንን የምላሽ መጽሐፍ በማንበብ አባቶቻችን መምህራን የሃይማኖት ቅንጣትን በዘሩበት በወንጌል እርሻቸው ላይ ሐሰተኛ መምህራን የኑፋቄ ትምህርታቸውን እንዳይዘሩባቸው፤ ራሳቸውን እና ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ ያሳስባል።

በጀርመን ሀገር በቪዝባደን ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት “ቀሲስ” ገዳሙ ደምሳሽ በ1997 ዓ.ም “ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቀደመች ቤተ ክርስቲያናቸው ተመልሰዋል” ከመባላቸው በፊት በይፋ በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግሉ የነበሩና በአጠቃላይ አራት የኑፋቄ መጻሕፍትን የጻፉ ሰው ናቸው። ሁለቱን ቀደም ብለው ቀሪ ሁለቱን ደግሞ “ተመልሰዋል”  ከተባሉ በኋላ ያቀረቡ  ሲሆን ከአራቱ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የሚያተኩሩት ሁለቱ አንዱ ከአንድኛው በይዘት ካለመለያየታቸውም በተጨማሪ በመጨረሻ የወጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሁለተኛ ክፍል ቀድሞ በመናፍቃኑ ጎራ በግላጭ እያሉ በጻፉት በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ የነበረውን ሕጸጽ አርሞ ያልወጣ ይልቁንም ያንኑ ስህተት አጠናክሮ ይዞ የቀረበ ነው።

ግለሰቡ ከሚያስተዳድሩት ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው እየኮበለሉ ወደመናፍቃን አዳራሽ የሚነጉዱት ምእመናን ቁጥር ያሳሰባቸው፤ ይህም ሲሆን እያየ ምንም ዓይነት ርምጃ ሊወስድ ያልቻለውን በጀርመን ሀገር ያለውን የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተቃወሙ በጀርመን ሀገር የሚገኙ ምእመናን በጥቅምት 2004 ዓ.ም ቅ/ሲኖዶስ እኚህኑ ግለሰብና ያለውን የአስተዳደር ችግር በተመለከተ ፊርማቸውን ያሰፈሩበት አቤቱታ ከመረጃዎች ጋር ለመንበረ ፓትርያርክ ውጪ ጉዳይ መምሪያ እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ያስገቡ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸው ይታወቃል። የዝግጅት ክፍላችን ከዚህ ቀደም በዚሁ ጉዳይ ላይ የዘገበ ሲሆን በቀጣይም ሁኔታውን እየተከታተለ ላንባቢዎች የሚያሳውቅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን። ከዚህ በፊት ያቀረብነውን ዘገባ ለመመልከት እዚህ ጋር  እዚህ ጋር ይጫኑ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment