Tuesday, May 15, 2012

በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ያተኮረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አራተኛ ቀን ውሎ

READ THIS IN PDF.
·        አባ ጳውሎስ ጉዳዩ አጀንዳ እንዳይኾን ተቃውመው ነበር
· እትሙ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ክብር የሚያቃልልና መጥፎ አርኣያነት ያለው መኾኑ በጉባኤው አባላት አጽንዖት ተሰጥቶበታል
·        የጋዜጣው ተጠሪነት ለማን እንደ ኾነ አልታወቀም
·        የጋዜጣው ዋና እና ምክትል አዘጋጆች፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና እና ምክትል ሓላፊዎች ዛሬ ቀርበው ይጠየቃሉ
·      የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ንብረት ጉዳይ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ተይዞ ለቋሚ ሲኖዶስ ተመርቶ ነበር
·  ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ቅ/ሲኖዶስ ፍርድና ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል

(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 7/2004 ዓ.ም፤ May 15/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በትናንት፣ ግንቦት 6 ቀን 2004 ዓ.ም አራተኛ ቀን ውሎው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በ56 ዓመት ቁጥር 125፣ ሚያዝያና ግንቦት 2004 ዓ.ም እትሙ ይዞት በወጣው ርእሰ አንቀጽና ጽሑፍ ዙሪያ ሲነጋገር ውሏል፡፡ የጋዜጣው ጽሑፎች ኾነ ብለው በያዙት ቅን ያይደለ አሳብና ዓላማ (Intents and purposes) ሳቢያ ባጸደቃቸው አጀንዳዎች ዙሪያ የጀመረው ውይይት ሂደት የተስተጓጎለበት ምልአተ ጉባኤው÷ ጉዳዩን በርእስነት ይዞ እንዳይነጋገር ከርእሰ መንበሩ አባ ጳውሎስ ተቃውሞ ገጥሞት እንደ ነበር የጉባኤው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ሄዶ ሄዶ የጉዳዩ ሥር ፓትርያርኩ ራሳቸው በመኾናቸው ከተጠያቂነት ለመዳን ሚያደርጉት ጥረት መኾኑ ታምኖበታል፡፡

በምልአተ ጉባኤው እምነት ‹የቤተ ክርስቲያን ልሳን› የኾነው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ “የአባቶች ገበና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጋለጥ” በሚል ርእስ ያወጣው አቋም፣ በቀዳሚ ገጹ “ቤተ ክርስቲያንንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ከግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ የህልውና ውሳኔ” በሚል ርእስ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ በማተኰር ያተመው ጽሑፍ፡- አባ ጳውሎስ በተመሳሳይ ጉዳዮች ለሚታዩባቸው ግዙፍ ተጠያቂነቶች አንዳች ትኩረት ያልሰጠና ሌሎችን ለማሸማቀቅ በመሣርያነት ያገለገለ፣ ፓትርያርኩ አላግባብ የሚጠቀሙበትን ሥልጣናቸውን የማጠናከር ዝንባሌ ያለው፣ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳነት ቀርቦ እልባት እንዲሰጠው በማሰብ ቋሚ ሲኖዶስ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብበት በተመራው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ንብረት ጉዳይ ዕድል ያልሰጠ፣ በአጠቃላይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ክብር የሚያቃልልና መጥፎ አርኣያነት የሚታይበት ነው፡፡


በስብሰባው ላይ አባ ጳውሎስ ጉዳዩ አጀንዳ እንዳይኾን ያደረጉትን ጥረት በዚህ አረዳድ የተከላከሉት የምልአተ ጉባኤው አባላት በመቀጠል የተነጋገሩበት በጋዜጣው ጽሑፍ በቅዱስ ሲኖዶሱ ፊት ወይም ደረጃ ቀርበው መጠየቅ ያለባቸው እነማን ናቸው? አቅርበን መጠየቅስ ያስፈልገናል ወይ የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡

“አቅርበን መጠየቅ አያስፈልገንም፤ በጋዜጣው ላይ በተቀመጡት የዋና እና ምክትል አዘጋጆች ስሞች መሠረት ውሳኔ እንሰጣለን” በሚል ውይይቱ የቀጠለ ሲኾን ጽሑፉ ስለተዘጋጀበት ዓላማና ሂደት (የጽሑፉ ምንጭ ስለሆኑ አካላት ማንነት) በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ውሳኔ ለመስጠት የሚረዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ተጠሪ የኾነለትን አካል ይጠይቃል፤ ለዚህ ጥያቄ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሰጡት ምላሽ ጋዜጣው ቀደም ሲል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር እንደነበር በኋላ ደግሞ ወደ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንደተዛወረ በመጥቀስ ለይተውና ወስነው ለማሳወቅ አልቻሉም፡፡
በመኾኑም ምልአተ ጉባኤው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፣ ምክትል አዘጋጅ መ/ር ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር፤ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ፣ ም/ሓላፊው መ/ር ሣህሉ አድማሱ ቀርበው መጠየቃቸውን አስፈላጊ ኾኖ አግኝቶታል፡፡ በዚህም መሠረት የተጠቀሱት አዘጋጆች እና ሓላፊዎች በዛሬው ዕለት በቅዱስ ሲኖዶሱ ፊት እንዲቀርቡ መወሰኑ ተዘግቧል፡፡

ስለ ውሳኔው ምንነት በተደረገ ውይይት “አስተዳደራዊ ይኹን” “የለም፣ በቀኖናዊ ቅጣት እንለፈው” የሚሉ አማራጮች መነሣታቸው የተገለጸ ሲኾን በአመዛኙ የተያዘው ስምምነት ወደ አስተዳደራዊ ውሳኔ ያደለ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡ አስተዳደራዊ ርምጃ ይወሰድ የሚለው አማራጭ ከታየ ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ከጋዜጣው ሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ያገለገሉት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ከሓላፊነታቸው የመሰናበት ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸው ተመልክቷል፤ “እስኪ እርሱም ይብቃው” ይላሉ ስለ ውሳኔው ከወዲሁ ሐሳብ የሚሰጡ የጉዳዩ ተከታታዮች፡፡

ከጋዜጣው መውጣት በኋላ “ዜና ቤተ ክርስቲያን ስም ብቻ ይዞ ቢቀር” በሚል ባለ ዘጠኝ ገጽ ጽሑፍ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅጽር እየተሠራጨባቸው የሚገኙት ዋና አዘጋጁ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ከ1967 ዓ.ም አንሥቶ በያዙት የዋና አዘጋጅነት ሓላፊነት የጋዜጣውን ዓላማ በመለወጥ “የግል ሰዎች ስም ማወዳሻ፤ የስድብና የሐሜት መናኸርያ፤ የባለሥልጣናት ማጥመጃና መደለያ” የሚል ክስ እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡

“ቤተ ክርስቲያናችን ሕግ እያላት በሕግ አልተመራችም፤ ሲኖዶስ እያላት በሲኖዶስ አልተዳደረችም፤ በገጠር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በመዘጋት ላይ ስለኾኑ መፍትሔ ይፈለግላቸው፤ በውጭም ኾነ በውስጥ መለያየት እየተፈጠረ ስለኾነ መፍትሔ ይፈለግላት፤ ምእመናንና ካህናት አስፈላጊውን አመራር ባለማግኘታቸው ተስፋ እየቆረጡ ነው” ብለው ማሳሰባቸውን የሚገልጹት የጽሑፉ አዘጋጆች፣ ይህን በመናገራቸው ግን “በወልደ ሩፋኤል አፍ” መሰደባቸውን ይገልጻሉ - በገዛ ገንዘባችን፣ በገዛ ጋዜጣችን፣ በገዛ ቤተ ክህነታችን በወልደ ሩፋኤል አፍ ቤተ ክርስቲያንና አባቶች ተሰድበናል፡፡ እኛን የሚያሳዝነን የዓለም ምሳሌና አብነት የነበረች ቤተ ክርስቲያን የእበላ ባይ መጫወቻ ኾና መቅረቷ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 28 (4) (ከሀ - ሐ) በግልጽ ከተደነገገው ውጭ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች እንደተገለጸው “አዳዲስ ሠራተኞችን በባለውለታነት እየሾሙ በአዲሶቹ ሹመኞች እየተደገፉ ብዙ የከፉ ተግባራትን መሥራት ለሚፈልጉት” አባ ጳውሎስ አንድ ማሳያ የኾነው በእስክንድር ገብረ ክርስቶስ የሚመራው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከመዋቅር የማስወገድ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽና ሐተታዊ ጽሑፍ እንደ አጠቃላይ በያዛቸውና በሚያመለክታቸው እውነታዎች ሳይኾን በአቀራረቡ አድሏዊና የማጥቂያ መሣርያ መኾኑ ከቤተ ክርስቲያን ልሳንነቱ አኳያ አደጋ እንዳለው አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጳጳሳት ንብረት መያዝና ከሞተ ዕረፍት በኋላ ስላለው ውርስ ቀደም ሲል የነበረው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በ1991 ዓ.ም እንዲሻሻል በተደረገበት ወቅት አሁን በዜና ቤተ ክርስቲያን በተገለጸው አኳኋን (ለቤተ ክርስቲያን ማውረስ) እንዳይካተት በከፍተኛ ደረጃ የተቃወሙት ፓትርያርኩ ራሳቸው እንደነበሩ፣ ለዚህም ከደቡብ አፍሪካ እስከ አሜሪካ እንደገዟቸው ከሚነገሩት ቪላዎች ውጭ በትውልድ ቦታቸው ለወላጅ እናታቸው አሠርተውታል የሚባለው ቤት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

የቅርቡን ትተን ከ1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል በፊት በኅዳር ወር 1990 ዓ.ም የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ለወቅቱ ቋሚ ሲኖዶስ ባቀረበው ባለ53 ገጽ ሪፖርት በቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር ዙሪያ በተፈጸመው የአድልዎ አሠራር፣ የአስተዳደር በደል፣ የገንዘብ ምዝበራ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስን በተጠያቂነት ያስቀመጠ መኾኑም ተገልጧል፡፡

ከ14 ዓመት በፊት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከምእመናንና ከመንግሥት አካላት (በታዛቢነት) በተውጣጡ ሰባት አባላት የተጠናቀረው የኮሚሽኑ ሪፖርት “ሲኖዶስ በስም እንጂ በግብር የለም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይ አካልነት በቅዱስ ፓትርያርኩ ዓምባገነናዊ አመራር ሰጭነት መተካቱ ተረጋግጧል፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከሚፈቅደው ውጭ በዘፈቀደ ይሠራል” የሚሉት የወቅቱ ስሞታዎች የተመረመሩበትና አግባብነት ያለው ቅሬታ እንደነበርም የተገለጸበት ነበር፡፡

ኮሚሽኑ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን መጣስን አስመልክቶ ስለ ቀረቡና መፈጸማቸውንም ስላረጋገጣቸው የውዝግብ ነጥቦች ይታረሙ ዘንድ ባቀረበው እምነቱና ሐሳቡ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣንና ተግባር በሚገባ በሚወስን መልኩ ተደራጅቶ ቀርቦ በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲጸድቅና ሥራ ላይ እንዲውል፤ በሥራ ላይ ያለውም ይኹን ወደፊት ተሻሽሎ የሚጸድቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተከብሮና ተጠብቆ በሥራ እንዲተረጎም ሌሎች ችግሮች ሁሉ እንደሚፈቱ መክሮ ነበር፡፡

ከ14 ዓመታት በኋላስ? ፓትርያርኩን ከቅዱስ ሲኖዶሱ በላይ አመራር ሰጪ በማድረግ በአባ ጳውሎስ ዓምባገነናዊ አሠራር ለተፈጸሙ በደሎች ሽፋን የነበረው የ1988 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን በ1991 ዓ.ም ሲሻሻል ችግሮቹ እንደሚቀረፉ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የሚጠቀሱ ውጤቶች የተገኙ ቢኾንም በብዙ መልኩ ከቀድሞው የባሰ የትምህርተ ሃይማኖት መፋለስ፣ የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፣ ሙስና እና የአስተዳደር በደል ተባብሶ መታየቱ አልቀረም፡፡

ይህ ኾኖ ሳለ ዜና ቤተ ክርስቲያን “አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ” ይሉት ሙግት ይዟል፡፡ ከጠቀሳቸው የሚወሰዱ ነጥቦች በላይ “ለፓትርያርኩ መብት መገፋት፤ ጳጳሳቱ ሽቅብ መልስ ለመስጠታቸው” ይዋቀሳል፤ ዋና አዘጋጁም እንዳሉት ርእሰ አንቀጹና ጽሑፉ በተለያየ መንገድ ቀድሞ ሲባሉ የነበሩ ነገሮች [አሁን የወጣውና በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ የተቀነባበረው ጽሑፍ ቀደም ሲል በአባ ገሪማ፣ በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ገ/ዐማኑኤል፣ በዶ/ር አግደው ረዴ እና በልዩ ጸሐፊያቸው በመጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም ‘update’ የተደረጉበት ነው] ተመልሶ በጋዜጣዊ አቋም የቀረቡበትና በርግጥም ሊጤኑ የሚገባቸው ነጥቦች ቢኾኑም በመሠረታዊ አሳቡ ቅንነት ይጎድለዋል፤ የማጥቂያ ብትር ኾኗል የሚያሰኘው ቅሉ ይህ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ በቅንነት የሚፈጽሙትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማደናቀፍ አባ ፋኑኤል በፈጸሙባቸው የክፋት ተግባር እንዲሁም አባ ፋኑኤል ከግብር አበራቸው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንና ከዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ አዘጋጆች ጋራ “ቤተ ክርስቲያን መሪና ተቆጣጣሪ የሌላት የጥቂት ግለሰቦች መፈንጫ የኾነች በሚያስመስል መልኩ በዜና ቤተ ክርስቲያን  እኔን በተመለከተ የተሳሳተ እና በሐሰት ላይ የተመሠረተ ዘገባና የስም ማጥፋት ተግባር” በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲጠየቁላቸውና በመንፈሳዊ አግባብ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ከ14 ያላነሱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተመርጠው ሀገረ ስብከቱን በፀሐፊነት የሚያገለግሉት ቀሲ ዶ/ር መስፍን አባ ፋኑኤል በእርሳቸው ላይ ደብዳቤ የጻፉባቸውና የስም ማጥፋት ዘመቻ የያዙባቸው፣ “አባ ፋኑኤል ለሚፈጽሙት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን የወጣና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የማፍረስ ተግባራቸው ተባባሪ ባለመሆኔ የተነሣ በክፋት እና በጥላቻ መንፈስ ተይዘው ነው” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባ ፋኑኤል በቀሲስ ዶ/ር መስፍን ላይ የተከተሉት አካሄድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቀ፣ በጋዜጣው ዘገባ ላይ እንኳ ግልጽ ኾኖ ያልተቀመጠ በመኾኑ ስሐተቱን በማረም ረገድ “ቅንና ትጉህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው” ካሏቸው ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ጎን እንደሚሰለፉ፣ ለስሕተቱም መታረም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ 

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment