በወረዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ115 በላይ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውና ከ16 በላይ ዐብያተ ክርስቲያናት መዘጋታቸው ታውቋል።
ጥቅምት ፲፱/፳፻፲፰ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን በደረሰው መረጃ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከለሊቱ 4:00 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ ሄላ ዘባባ ቀበሌ አርሴማ አጥቢያ የሚኖሩ ምእመናን በታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ ደግሞ መታገታቸው ተገልጿል።
ከተገደሉት ምእመናን ውስጥ የአንዱ ሟች አባትና ወንድም መታገታቸው በመረጃው የተገለጸ ሲሆን ታፍነው የተወሰዱት ምእመናን ስለሚገኙበት ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል፡፡
በመረጃው እንደተነገረው የሞቱት ሦስቱ ኦርቶዶክሳውያን በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2016 ዓ.ም መስከረም 02 ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለማቋረጥ በወረዳው ከ115 በላይ ምእመናን የተገደሉ ሲሆን 27 ኦርቶዶክሳዉያን ደግሞ አሁንም ድረስ ታግተው ያሉበት እንደማይታወቅ ነዋሪዎቹ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በግድያ ያላበቃው መከራና ስቃይ በሽርካ ወረዳ ብቻ በዘጠኝ ቀበሌዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኦርቶዶክሳዉያን መፈናቀላቸውንም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

