Wednesday, December 21, 2011

ብፁዕ አብነ አብርሃም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

በሕግ አክባሪነታቸው፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በመጠበቅ እና በማስጠበቅ እንዲሁም በብዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የሚወደዱት እና የሚከበሩት ብፁዕ አብነ አብርሃም የምሥራቅ ሐረርጌ እና የጅጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተሰየሙበት ካለፈው የጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም. በኃላ ወደ ሀገረ ስብከታቸው ለመሔድ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተገልጿል። ብፁዕ አብነ አብርሃም ከአሜሪካ መዲና ከሆነችው ከዋሽንግተን ዲሲ ሲነሱ በርካታ ካህናትና ምዕመናን በእንባና በልቅሶ ሸኝተዋቸዋል። ብፁዕነታቸው በበርካታ የአካባቢው ምዕመናን እና አድባራት በአይነቱ ልዩ የሆነ የመሸኛ ምሽት አዘጋጅተውላቸው እንደነበር ከቦታው የደረሰን ሪፓርት ይገልጻል። ብፁዓን አባቶች፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ካሕናት፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ዲያቆናት፣ እንዲሁም በርካታ ከተለያየ ጠቅላይ ግዛት የመጡ ምዕመናን በዚህ የመሸኛ ምሽት ተገኝተው መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። ብፁዕነታቸውም በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ የዋሽንግተን እና አካባቢውን ምዕመናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ምንም አይነት ድርድር ውስጥ ማስገባት እንደሌለባቸው እና ማንኛውንም የቤተክርስቲያን አባት ሊመረመር እና ሊመዘን የሚችለው በሕገ ቤተክርስቲያን እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደሚታወቀው በዚሁ የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ  አነጋጋሪው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እንደገቡ የሚታወቅ ሲሆን በዚሁ ለብፁዕ አቡነ አብርሃም በተደረገ የመሸኛ ምሽት እለት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በበኩላቸው የራሳቸውን ስብሰባ እያደረጉ እንደነበር የደረሰን ሪፓርት ጨምሮ ይገልጻል። ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸውም በፊት ብፁዕ አብነ ፋኑኤል ነባሩን ሀገረ ስብከት ወይም ሥራዎች ለማየት እና ለመረካከብ ፈቃደኝነታቸውን ባለማሳየታቸው እንደገና እንደ አዲስ የተለየ ሀገረ ስብከት ሊመሠርቱ እና ሊሰሩ እንዳሰቡ በስብሰባው ላይ የተገኙ ምዕመናን የነገሮችን ብልሽትሽት ያለ አካሄድ እያነሱ ሲያማርሩ ተሰምቷል። እንደምንጮቻችን አነጋገር ከሆነ በስብሰባው ላይ የነበሩት ጥቂት ተሰብሳቢዎች፣ የተስፋ መቁረጥ እንዲሁም የመሰላቸት ስሜት ይታይባቸው እንደነበር ተነግሯል ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልም የአካባቢውን ምዕመናን ስደተኛውንም፣ ገለልተኛውንም፣ መጻተኛውንም በጋራ በአባትነት እመራለሁ ሲሉ መሰማታቸውንም አንዳንዶች በግርምት ተመልክተውታል።

ቸር ወሬ ያሰማን

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

1 comment:

  1. Happy that we got one more blog. Great! I hope you'll be as informative and educational as Deje Selam and other blogs like it.

    ReplyDelete