Wednesday, December 21, 2011

የአቡነ ገሪማ አምላክ አባ ጳውሎስ ይሆኑ?

በሉልሰገድ እረታ lulsegedrt@gmail.com
          ክርስትና የመከራ ህይወት ነው እንደሚባለው ሆኖ እንደሆነ እንጃ በየትኛውም ዘመን የተፃፈ የትኛውንም የታሪክ መጽሐፍ የተመለከተ ሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከፈተና እና ከመከራ የተላቀቀችበት ዘመን እንደሌለ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ በ10ኛው መቶ ክ/ዘመን የዮዲት ወረራ፣ በ16ተኛው ክ/ዘመን የአህመድ ግራኝ ጭፍጨፋ፣ በ17ተኛው ክ/ዘመን የሱስንዮስ ካቶሊካዊ ወረራ፣ በ18ኛው ክ/ዘመን የዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ ክፍፍል፣ በጣም በቅርብ ጊዜ እንኳን የወታደራዊ መንግስት ደርግ ኮሚንስታዊ ተጽእኖ በግምባር ቀደምነት የሚጠቀሱ የቤተክርስቲያን ፈተናዎች ናቸው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ግን ቤተ-ክርስቲያን እነዚህን ሁሉ መከራዎች በምን መንገድ እና በማን መስዋዕትነት ተወጣቻቸው የሚለው ሲሆን ለዚህ ጥያቄ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጋራ የሚሰጠው ምላሽ አንድ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ፡፡
እነዚያ ሁሉ መከራዎች ታሪክ ሆነው የቀሩት ቤተ-ክህነቷ ባፈራቻቸው ልጆቿ በተለይም ደግሞ በአስተዳዳሪዎቿ ብርታት እና መስዋዕትነት መሆኑን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ምናልባትም ከአንድ ሰው እድሜ ባልዘለለ አመት ውስጥ እንኳን በአንባገነኑ የደርግ መንግስት ስለ እምነታቸው እና ስለሀገራቸው ሰላም መስዋዕት የሆኑትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን፣ ወይም ለፋሽስት ሐገሬን ባርኬ አልሰጥም በማለት ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡትን ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን የሚዘነጋቸው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
 ዛሬስ ———
  ዛሬ ዛሬ ይሄ ታሪክ ፈጽሞ እየተገለባበጠ እንደመጣ ሁሉም የሚረዳው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ብዙ አባቶች መስዋዕት የሆኑላት ቤተ-ክርስቲያን ዛሬ ብዙዎቹ አባቶቿ ለባእዳን መስዋዕት አርገው ሊያቀርቧት የሚሯሯጡባት ቤት ሆናለች፡፡ ክርስቶስን የሚያውቁ ክርስቲያኖች፣ የክህነት ምንጩ ማን እንደሆነ ያልተረዱ ካህናት፣ በተለይም ደግሞ ከመናፍቅ ያነሰ ምግባር የያዙ ጳጳሳት መከማቻ ከሆነች ይህ ነው የማይባሉ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ምን እንዲህ ለማለት ደፈረ ልትሉ እንደምትችሉ ወይም ስርዓት አልባ ደፋር አድርጋችሁ እንደምትስሉኝ አስባለሁ፡፡ በቅርቡ የሆነውን ነገር አስተውላችሁ ስትመለከቱት ግን ምን ያህል የዘመኑን አባቶች መግለጫ የሚሆን ቃል እንዳጠረኝ ትረዱኛላችሁ፡፡
ብዙዎቻችሁ በተለያዩ የብዙሐን መገናኛዎች እንደሰማችሁት አንዲት ጀርመናዊት የፊልም ባለሙያ ነኝ በማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ በፊልም መልክ ለማዘጋጀት ወደ ሀገራችን ትመጣለች፡፡ ፊልሙ የጌታችንን ታሪክ ቀርቶ የአንድን ጨዋ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ሊገልጽ በማይችል መንገድ ፍፁም ከስርዓት የወጣ እንደሆነ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ምንጮች ያትታሉ፡፡ ከነዚህ ሁሉ ድክመቶቹ እና ድፍረቶቹ ጋር ግን ‘The Abode of God’ ፊልም በቅዱሳን ገዳማት በተለይም በይምርሐነ ክርስቶስ፣ በአሽተን ማርያም እና በጉንዳ ጉንዲ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ላይ እንዲቀረጽ ቤተ-ክርስቲያንን ይጠብቃሉ ተብለው ከተሾሙት የቤተ-ክህነት ‘አባቶች’ ፈቃድ አገኘ፡፡ እንግዲህ ክርስቶስን ያህል ታላቅ ጌታ ክብር ይግባውና ከይሁዳ ጋር የዝሙት ፊልም( Erotic movie) ተዋናይ ወይም እንደ ደፋር ግብረ ሰዶማዊ (Homo-sexual) ከንፈር ለከንፈር ገጥሞ ሲሳሳሙ በሚያሳይ ፊልም ላይ፣ ማርያም መግደላዊት የኢየሱስ ክርስቶስ ሚስት መሆኗን ከሚገልጽ ደፋር እና ‘ጋጠ ወጥ’ ፊልም ፈቃድ የሚሰጡትን የዘመናችን ‘ጳጳሳት’ ወረራ ሳይመጣ እጃቸውን የሰጡ ——- ብዬ ብገልጻቸው፡፡ እኔ ራሴ ጋጠ ወጥ እባል ይሆን ——?
የኔ ጥያቄ ከፍቃዱ ሳይሆን ከዛ ቀደም ብሎ ይጀምራል፡፡
ጀርመናዊቷ ለምን ኢትዮጵያን መረጠች?
እንደ ጀርመናዊቷ አገላለጽ ከሆነ ኢትዮጵያ የተመረጠችበት ምክንያቶች ሁለት ናቸው
  1. ‘የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም እስከ አሁን በጥቁር ሕዝቦች አልተሰራም’ የሚል የዘር  (Race) መብት ጥያቄ
  2. የኢትዮጵያን ቅድስት ሀገርነት አረጋግጫለሁ የሚል ‘ዶሮን ሲደልሏት’ የሚለውን አባባል የሚያስታውስ ፌዝ መሰል ምክንያት ነው፡፡
በእኔ እምነት ግን ሁለቱም ምክንያቶች እውነትን የመሰሉ ነገር ግን ‘ሆን’ ተብለው ለማስመሰል የተሰጡ ይመስሉኛል እና ምክንያቷ ምንድን ነው? እንደኔ ምክንያቱ የሀገራችን የኢትዮጵያ የታሪክና የቅርስ ማዕከል የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሶስት ሺ አመታት በጎበኘችበት ወቅት የተገነዘበቻቸው ሁለት ሐቆች አሉ፡-
  1. ገዳማቱ ያለ ጠባቂ የቀሩ እና አስታዋሽ ያጡ መሆናቸውን፤
  2. የቤተክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ ነን የሚሉት አባቶች ከቤተክርስቲያኗ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ጥቅም ፈላጊዎች መሆናቸውን አሳምራ የተረዳችው በመሆኑ፡፡
የፍቃድ ሰጭው ማንነት
ጀርመናዊቷ የፊልም ባለሙያ ነኝ ባይ ይዛው የተገኘችው ፈቃድ ላይ የሰፈረው የድሬዳዋ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት የብፁእ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) መሆኑ ብዙዎች ላይ ግርምትን አጭሯል፡፡ ጥያቄው እንግዲህ ይህ ነው፤ ለምን በአቡነ ገሪማ ፊርማ ይህ ክስተት ለኔ አንድ ፍጥጥ ያለ እውነት እንዳለ ይጠቁመኛል፡፡ ፓትሪያርኩ ቤተ-ክርስቲያንን የሚነካ እና ለተቃውሞ የሚዳርግ ክስተት ሲገጥማቸው ብዙ ጊዜ በኝህ አባት በኩል መጠቀምን ይመርጣሉና፤ ለምን?
ከ 3 አመታት በፊት በቤተክርስቲያኗ እውቅና ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ እና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር ኬንያ ላይ መኪና ሰርቋል ብለው ማስወራታቸውን ብዙዎቻችን የምንዘነጋው አይመስለኝም፡፡ እነዚህ አሉባልታዎች አልበቃ ብለው የተመደቡበትን ሐገረ-ስብከት ያለ መሪ ትተው ከፓትሪያርኩ ላለመራቅ አዲስ አበባ ላይ ከከተሙ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሚያስተዳድሩት የድሬዳዋ ሐገረ-ስብከት ከአንድ ጅምር ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ 5 ሚሊየን ብር መጉደሉን አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው ከሌላው ምዕመን እኩል በሚዲያ ሲሰሙት ስናይ አንድ ጥያቄ መጠየቃችን አልቀረም፡፡
‘እውነት ግን እኝህ ሰው ጳጳስ ናቸው?’
ፓትሪያርኩ ያሉትን ሁሉ አሜን ብሎ መቀበል፡፡ አንድ ተራ ደብዳቤ በደረሳቸው ቁጥር ‘አባታችን’ ካልፈቀዱ አይሆንም የሚለው መራር ምላሽ እና ተግባር ሲደጋገምልን ደግሞ ሌላ ጥያቄ አስከተልን ‘እውነት ግን የአቡነ ገሪማ አምላክ ማን ነው? እግዚአብሔር ወይስ  አቡነ ጳውሎስ?’
          አሁን መፈፀማቸው የተሰማው ድርጊት ግን ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች አጥርቶ የመለሰ ይመስለኛል፡፡ ጳጳስ ቀርቶ አንድ ተራ ክርስቲያን ከህሊናው በላይ የሚሆንበት የክርስቶስን የባህሪ አምላክነት ከሚነቅፍ ተግባር ጋር መደራደር እንደ እኔ እምነት ‘ጳጳስነቱን ተውት እና እኔ ክርስትና የሚባለውን ሐይማኖት እንኳን አላውቀውም’ ብሎ ከመናገርም በላይ ግልፅ መልስ ይመስለኛል፡፡
ግን ብፁዕ አባቴ የተወሰኑ ጥያቄዎች እንድጠይቅዎት ይፈቀድልኝ እና (ምናልባትም እነዚህንም ‘ከአባታችን’ ጋር ልማከርባቸው ካላሉ)——
       ‘ክርስቶስ አልተሰቀለም በእርሱ ምትክ መላዕኩ ነው የተሰቀለው’ ——- የሚል ፊልም በቅዱሳን ገዳማት ውስጥ እንዲሰራ እየፈቀዱ እንዴት የክርስቶስ ስጋ እና ደም ሲፈትቱ ይውላሉ?
  ክርስቶስ የማርያም መግደላዊት አባወራ መሆኑን ካመኑ (መቼም ያላመኑበትን አይፈቅዱም ብዬ ነው) እርስዎስ ምን በወጣኝ ብለው ስለ እርሱ ጃንደረባ ሆኑ (ምናልባት ከሆኑ)? ወይም ነኝ ይላሉ?
      አሁን ክርስቲያን ይሆኑ ወይ? ክህነትስ ይኖራቸው ይሆን ወይ? የሚለውን ጥያቄያችንን እድሜ ለሰሞኑ ዜና በትክክል መልሰውልናል፡፡ —— እናም የአሁኑ ጥያቄያችን ሌላ ነው? —-
     ገና ሩጠው ያልጠገቡ በወጣትነት እድሜ መግቢያ ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክርስቶስ ላይ አንደራደርም ብለው አልሰራም ያሉትን ፊልም ሲፈቅዱ የክርስትናን እምነት የማይከተሉ ባለስልጣኖች እንኳን ‘የክርስትናን እና የሐገርን ገጽታ ያበላሻል’ ብለው በእርስዎ ፈቃድ የተጀመረውን ፊልም ሲያስቆሙ —— አብሮን የከረመ ጥያቄያችንን እየመለሱ እግረ መንገድዎትን ግን ሌላ ጥያቄ በውስጣችን መጫርዎት አልቀረም —– እውነት ግን እርስዎ ኢትዮጵያዊ ነዎት?
     በመጨረሻ አንድ ነገር ልል ወደድኩ፡፡ እርስዎ የሰሩትን ክህደት ይቅርታ ከዚህ የከበደ ቃል ስላጣሁ ነው) ስመለከት ያለንበት ዘመን የሳሙኤልን የልጅነት ታሪክ አስታወሰኝ፡፡
     በዛ በመከራ ወራት እግዚአብሔርን የሚያውቁ የእግዚአብሔር ሰዎች ነን ባዮች ልክ እንደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሁሉ በመቅደሱ በሞሉ እና መቅደሱን ባረከሱበት ዘመን የነ ኤሊ ስህተት የተገለፀለት ብቸኛ ሰው ቢኖር ሕፃኑ ሳሙኤል ነበር?
    ዛሬም የእርስዎ ስህተት በህፃናት ተማሪዎች ሲስተካከል ስመለከት ነገሩ ግጥምጥሞሽ ይሆን ወይስ ዘመኑ ራሱ የነ ኤሊን ዘመን ሆኗል ማለቴ አልቀረም፡፡
    ነገሩንስ እግዚአብሔር ራሱ በመረጣቸው ሰዎቹ በኩል ፈታው ግን እርስዎ በኤሊ ላይ የደረሰውን ያውቁታል? ምናልባት አንብበውት የሚያውቁ ከሆነ ቦታውን ልጠቁምዎት ‘በአንደኛ ሳሙኤል’ ላይ ያገኙታል፡፡
  እግዚአብሔር የተቆጣ ጊዜ አገልጋይህ ነኝ ብለው እንደ የዋሁ ሕዝብ የማይሸውዱት አምላክ እንደሆነ ቅዱሱ መጽሐፍ በታሪኩ እያዋዛ ይነግርዎታል እና አባክዎትን ያንብቡት፡፡ —– ማን ያውቃል ምን አልባት መንጋው ከሚነዳቸው የዚህች  ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን የዚህ ዘመን እረኞች መሀከል ተለይተው ያለ ጠባቂ የቀረውን ምስኪን ምዕመን የሚያገለግሉ መልካም እረኛ ይሆኑልን ይሆናል፡፡ የቀረውን ስህተትዎትን ያኔ ንሰሐ እንደሚገቡበት ተስፋ በማድረግ —- ብቻ ከመፃፍ ተቆጥቤያለሁ፡፡
     እግዚአብሔር የቀሩንን ጥቂት እውነተኛ አባቶች ይጠብቅልን፡፡ ለሌሎችም ልቦናን ያድልልን አሜን ያድለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከገብረ ኄር ታማኝ አገልጋይ የተገኘ

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ
 

1 comment:

  1. abetu yetsihonen degoch asmamrat kitrua lifers newna tadegat endenehmiya yale yemicheneklat fiterlat !!agelgayochua fikir attewal , abatochua bedlewal , yemikomlat attalechina ante direslat !!amen

    ReplyDelete