Monday, February 25, 2013

ታሪክን የኋሊት “ፓትርያርኩን አትምጡ ስንላቸው መጥተው እኛንም በገማ እንቁላል አስደበደቡን” አቡነ ማቲያስ


  • አቡነ ማቲያስ አቀድሳለሁ ነው የምልዎት  እንዲህ አይነቱ ቤተ ክርስቲያን ቢፈርስ ምን ይጎዳል” አቡነ ጳውሎስ
  • እንደ ፖሊሶቹ ቁጥር ማነስና ጥንቃቄ ጉድለት የፓትርያርኩ ተቃዋሚዎች  የፈለጉትን ዓይነት ወንጀል በላያችን ላይ ከመፈጸም የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም” አቡነ ማቲያስ በጊዜው የተነሳውን ተቃውሞ  ሲገልፁ
  • “ፓትርያርኩን አጅበን ከዋሽንግተን ዲሲ ተነስተን ቦልቲሞር ስንደርስ ፤ ተዘጋጅቶ ሲጠብቅ የነበረው ተቃዋሚው የፖለቲካ ቡድን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በድንገት ወጥቶ ወረረን ፤ በጣም ቀፋፊ የሆነ ስድብ ውርጅብኝ አወረደብን፡፡
  • አቡነ ጳውሎስ ይጎበኙታል የተባለው ሕንጻ ውስጥ ፈንጂ ተቀብሯል ስለተባለ እርሳቸውና ከእሳቸው ጋር ያሉት 9 ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡


(አንድ አድርገን የካቲት 18 2005 ዓ.ም)፡- “አንድ አድርገን”በየጊዜው ወደ ኋላ መለስ በማለት በበቤተክርስቲያናችን ላይ የሆነው እና የተደረገውን ነገር አሁን ያለው ትውልድ ያውቀው ዘንድ ፤ ከባለፈ ታሪክ ተምሮም የተሻለ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ ታሪካችንን መልካምም ይሁኑ መጥፎ ጥሬ ሀቃቸውን ታሪክን የኋሊት እያለች እንደምታቀርብ ይታወቃል፡፡  አቡነ ማቲያስ የዛሬ 14 ዓመት በርካታ ህዝቡ ሊያውቅ ይገባል ያሏቸውን ታሪኮችን በስምንት የተለያዩ ጉዳዮች ከፋፍለው ከ20 ገጽ የማያንስ በጊዜው በህትመት ላይ ለነበረችው ለ”ኢትኦጵ” መጽሔት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአቶ ተስፋዬ ተገኝ በአስቸኳይ የፖስታ አገልግሎት የላኩት ጽሁፍ ላይ ስለ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  የአሜሪካን አገር ጉብኝት ሁኔታዎቸ ያሰፈሩትን ጽሁፍ ለአንባቢያን ለማድረስ ወደድን ፡፡ አቡነ ማቲያስ ለ”ኢትኦጵ” መጽሔት በላኳት ደብዳቤያቸው ብዙ ነገር ያወጉናል፡፡

 


የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የአሜሪካን አገር ጉብኝት
እ.ኤ.አ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 8  ቀን  1986 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካን አገር የተደረገው  ፓትርያርካዊ ጉብኝት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ያስደፈረ ፤ ተዳፍኖ የነበረውን ፖለቲካዊ እሳት እንዲጋጋል ያደረገ  የቤተክርስቲያኒቱን ዘውድ  ያስደበደበ እጅግ መጥፎ ገጽታ የታየበት ጉብኝት ነበር፡፡ መቼም ክፉም ይሁን ደግ ታሪክ ነውና መጻፍ አለበት፡፡

የፓትርያርኩ ጉብኝት የታቀደበት ወቅት በውጭ አገር የሚገኝውን ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ አዲሱ የፖለቲካ ማዕበል ሞረድ ንፋስ እንደበረታበት የባህር መርከብ ክፉኛ ያማታው ስለነበር ፤ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ “ለጉብኝት መምጣቴ ነው” ብለው በቴሌፎን ሲያስታውቁን በጊዜው “አሁን ባይመጡ ይመረጣል” ብለናቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳ አሜሪካ ከገቡ በኋላ እንደታየው ከተገመተው በላይ ገንፍሎ አስቀያሚ የሆነ የስድብ ውርጅብኝ ፤ የድንጋይ ፤ የቲማቲምና የእንቁላል ውርወራ  የተቀላቀለበት ኃይለኛ የሆነ ሕዝባዊ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል ብለን ባናስብም መጠነኛ የሆነ ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው አልተሰወረንም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ምክሩን ሳይቀበሉ ትዕዛዙን እንደሚከተለው አስተላለፉልን

መስከረም 15 ቀን 1986 ዓ.ም
ቁጥር 31/86
ለ ፡- ብጹዕ አቡነ ማትያስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካና የካናዳ ሊቀ ጳጳስ
በአሜሪካ አገር የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተክርስቲያናት አገልጋይ ካህናት በሙሉ በማለት በኒውዮርክ ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ፤ በአትላንታ ፤ በሳንዲኤጎ ፤ በሎስ አንጀለስ ፤ በሳንሆዜ ፤ በፍሎሪዳ በዳላስና በሌሎችም ያሉት ሁሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  ከብጹዕን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ቅዳሜ መስከረም 29 ቀን 1986 ዓ.ም ኒውዮርክ ከተማ ሲገቡ በኬኔዲ ኤርፖርት እንዲገኙ በጽሁፍ እንዲያስታውቁ፡፡
ፊርማ
ተወልደ ገ/ዮሐንስ (የአቡነ ጳውሎስ ወንድም)
ልዩ ጸሀፊ

በማለት ነበር ደብዳቤው የተላከው ፡፡ ምንም እንኳን የትዕዛዙ አሰጣጥ  የአዲስ አበባ አድባራትን  ካህናት ወደ ቦሌ ኤርፖርት እንደመጥራት ዓይነት ቀላል ቢያስመስሉትም ካህናቱ መምጣት ቻሉም አልቻሉም ውሳኔው የእነሱ ይሁን ብለን በትዕዛዙ መሰረት ጥሪውን ለሁሉም አስተላልፈናል፡፡ ይህን ትዕዛዝ የአሜሪካ አገር ስቴቶች አንዱ ከሌላው ምን ያህል እንደሚራራቁና የካህናቱ የኢኮኖሚ አቅምና ሁኔታ ምን እንደሚመስ የማያውቅ ሰው አስተላልፎት ቢሆን አይፈረድበትም ነበር፡፡ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፈላቸው ወንድምየውም ሆነ ፓትርያርኩ ይህን ሁሉ ጠንቅቀው እያወቁ እንዲህ አይነቱን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የሚገርም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ የተዘረዘሩትን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተባበሩን የሳንዲያጎው አባት ብቻ ነበሩ፡፡ 

በፖለቲካው ምክንያት በርቀት የነበሩት ይቅርና በቅርብ የነበሩት ጭምር አብዛኛዎቹ ካህናት ለመቀበል ፍቃደኛ  ባለመሆናቸው ሳይመጡ ቀርተዋል፡፡ እንኳን ኬኔዲ ኤርፖርት ድረስ ሊመጡ ቀርቶ መጥቶ በአካል ያገኛቸው አንድም አልነበረም፡፡ ፍቃደኞች የሆኑት ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ስቴቶቹ በጣም የተራራቁ ስለሆኑ የመጓጓዣ የአውሮፕላን ቲኬት ለመግዛት የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ በቂ ጊዜ ባለመገኝቱ ሳይቀበሏቸው ቀርተዋል፡፡ ለምሳሌ ከሎሳጀለስ ካሊፎርኒያ እስከ ኒውዮርክ ያለው ርቀር በአውሮፕላን የ6 ሰዓት በረራ ነው ፤ የቲኬት ዋጋውም በርቀቱ መጠን ይወሰናል፡፡

አንድ የአቡነ ጳውሎስ የድሮ የቅርብ ወዳጅ ካህን ያሉኝን አስታውሳለሁ፡፡ መቼም የበላያችን ትዕዛዝ በማክበር ካህናቱን ለማስተባበር ያደረግነው ጥረት በደብዳቤ ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን በሌለን በጀት በቴሌፎን ጭምር በማስተጋባት ስለነበር ፤ ቴሌፎን ደውዬ “ ቄስ አገሌ እባክዎን ፓትርያርኩን ለመቀበል ዝግጅት ያድርጉ ፤ ንዋየ ቅድሳትን ይዘው ለኦክቶበር 10 ኢንተር ቸርች ቻፕል እንዲገኙ” አልኋቸው፡፡ በመጀመሪያ “በሚገባ አባቴ እኮ ናቸው” አሉኝ ፡፡ ጥቂት ሰንበት ብዬ ነገሩን ለማጠናከር “ቀሲስ ቀኑ እየደረሰ ነው ተዘጋጅታችኋል ወይ ?” ብዬ ስጠይቃቸው  የተቃዋሚውን ሕዝብ ሁኔታ ሲያዳምጡ ሰንብተው ኖሯል መሰለኝ የሰጡኝ መልስ ከመጀመሪያው ፈጽሞ የተለየ ሆነ “እኔ እንኳን ልቀበላቸው ካሉበት አካባቢ ለመታየት እንኳን አልፈልግም፡፡  እንዴ! በዚህ በእሳት ጊዜ ለምን መጡ ? እኔን አሳት ውስጥ ከተው አሳቸው ፎቶግራፍ ተነስተው ሊሄ አይደለም ? ከራስ በላይ ንፋስ ነው አልመጣም” አሉኝ ፡፡ ካህኑ ትክክል ናቸው ምንም አልፈርድባቸውም፡፡ ማንም ቢሆን የማያስልግ መስዕዋትነትን ለመክፈል ተወርውሮ እሳት ውስጥ መግባት የሚፈልግ የለም ፤ እኛ ግን ኃላፊነት ሆኖብን ምርጫ ስላልነበረን ገባንበት፡፡ ድሮውንም “አሁን ባይመጡ ይመረጣል” ያልናቸው ይህን በመፍራት ነበር፡፡ ነገር ግን አቡ ጳውሎስ የሰውን ሃሳብ ስለማይቀበሉ በስራ ላይ አላዋሉትም፡፡


ፓትርያርኩ በተሾመ በሁለተኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ አሜሪካንን ለመጎብኝት የተነሱበት ዋናው ምክንያት የመታየት ሱስ ስላለባቸው  በስደት በነበሩበት አገር ላይ በፓትርያርክነት ደረጃ ለመታየት  ነው የሚል ግምት ቢኖርም ፤ ለጉብኝቱ ምክንያት እንዲሆን የተፈጠረው ዘዴ ባልቲሞር ሜሪላንድ(Baltimore Maryland) ተዘጋጅቶ የነበረውን ኤግዚቢሽን መርቆ ለመክፈት የኤግዚቢሽኑ ባለቤት የሆነ አንድ አሜሪካዊ ድርጅት ጋብዞኛል በሚል ሰበብ ነበር፡፡

በኋላ ቀረብ ብለን ስናጠናው ድርጅቱ በጣም ከማነሱ የተነሳ ስንኳን አንድ ፓትርያርክ ያውም ከኢትዮጵያ ድረስ ተጉዞ  ስምንት ሊቃነ ጳጳሳትንና ሌሎችንም ውሉድ ካህናትን አስከትሎ ለመጎብኝት  የሚበቃ ደረጃ ያለው መሆኑ ቀርቶ አንድ ቄስ ቢወከል እንኳን  የሚበዛበት ከመሆኑ በላይ በኢግዚቢሽኑ ውስጥ የሚታዩት እቃዎች ደግሞ በተለያዩ ጊዜያቶች ከኢትዮጵያ ተሸጠው ወይም በልዩ ልዩ ዘዴ የወጡ  ቅርሳ ቅርሶች አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ ተከማችተው ሲገኙ አብዛኛው ግን የኢትዮጵያ ያልሆነ እኛን የማይመለከት ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

 ኢግዚቢሽኑ ተመርቆ በሚከፈትበት ቀንና ሰዓት ፓትርያርኩን አጅበን ከዋሽንግተን ዲሲ ተነስተን ቦልቲሞር ስንደርስ  ፤ ተዘጋጅቶ ሲጠብቅ የነበረው ተቃዋሚው የፖለቲካ ቡድን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በድንገት ወጥቶ ወረረን ፤ በጣም ቀፋፊ የሆነ ስድብ ውርጅብኝ አወረደብን፡፡ የነበረው የፖሊስ ኃይል ሊቆጣጠረው ስላልቻለ  ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል በራዲዮ ተጠርቶ ተተራመሰ፡፡ ሁኔታው ከባድ የእሳት አደጋ ይመስል ነበር፡፡ ጋባዦቹም ጥግ ጥጋቸውን ይዘው ትርምሱን ይመለከቱ ስለነበር የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ከፍተኛ መደናገጥ ይታይባቸው ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ያሳዩት ኢትዮጵያዊ ባህልና ግብረ-ገብነት የጎደለው እጅግ አሳፋሪ የሆነ ትርኢት ከመሆኑም በላይ  ፤ ከዚያ አልፈው ደም ቢያፈሱ አካል ቢያጎድሉ በሰላም የመኖር ዋስትናቸውን የሚጻረር ወንጀል ስለሚሆንባቸው አላደረጉትም እንጂ እንደ ፖሊሶቹ ቁጥር ማነስና ጥንቃቄ ጉድለት የፈለጉትን ዓይነት ወንጀል በላያችን ላይ ከመፈጸም የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም፡፡

ሁኔታውን እንደምንም በፖሊስ ኃይል ከተቃዋሚዎቹ ተላቅቀን ኢግዚቢሽኑ ወደሚታይበት ሕንጻ እንደተጠጋን ባለጉዳዮቹም በተራቸው “አናስገባችሁም ወደ መጣችሁበት ተመልሳችሁ ሂዱ” አሉን፡፡ ለምን ? ቢባል “ሕንጻው ውስጥ ፈንጅ ተቀብሯል የሚል ማስጠንቀቂያ ከተቃዋሚዎች በኩል በጣም ብዛት ያለው ጥሪ ስለደረሰን ለእኛም ሆነ ለእናንተ ሕይወት አስጊ ስለሆነ በምንም አይነት አናስገባችሁም”ብለው መለሱን፡፡ ፓትርያርኩ “ጸጥታን የመጠበቅ ኃላፊነት የእናንተ እንጂ የእኔ አይደለም ለዚህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ድረስ ጋብዛችሁ አምጥታችሁናል ስለዚህ ገብቼ የመጣሁበትን ጉዳይ መፈጸም አለብኝ” ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ክርክር ገጠሙ፡፡ ባለጉዳዮቹም “የፈለገው ዓይነት ርቀት ቢጓዙ እኛ መሞት አንፈልግም እርስዎም እንዲሞቱ አንፈልግም ፤ እቃዎችዎም ሆነ ህንጻው እንዲወድም አንፈልግም እባክዎ ይቅርታ አድርገውልን ወደ ቤትዎ በሰላም ይመለሱልን” ብለው ቢለምኗቸው አቡነ ጳውሎስ  “ይህን ሳላደርግ ከምመለስ ብሞት ይሻለኛል” ብለው ለአንድ ሰዓት ያልህ ክርክራቸውን ቢቀጥሉ ነገሩ ውጤት አልባ ሆኖ ቀርቷል፡፡

በመሰረቱ በባለጉዳዮቹ ላይ ሽብር ፈጥሮ እንዳይሳካ ለማድረግ የተፈጠረ ዘዴ ነበር እንጂ ምንም ዓይነት የተቀበረ ፈንጂ አልነበረም፡፡ ያም ሆነ ይህ ፓትርያርኩ ከኢትዮጵያ ድረስ የመጡበት ጉዳይ በእንዲህ አይነት አሳፋሪ ሁኔታ ተፈጸመ፡፡ በወቅቱ ስለነበረው አሳዛኝ ሁኔታ  አብረው የነበሩት ሊቀ ጳጳሳት የዓይን ምስክሮች ናቸው፡፡

ወደ ቦልቲሞር ከመሄዳቸው ሶስት ቀን ቀደም ብሎ የጸጥታ ክፍሎች ፓትርያርኩ ወዳረፉበት ዋሽንግተን ካቴድራል መጥተው “የሀገረ ስብከቱ ሃላፊ ማነው?” ብለው ሲጠይቁ “እኔ ነኝ አቡነ ማቲያስ እባላለሁ” አልኋቸው፡፡ “ፓትርያርኩ ወደ ባልቲሞር እንዳይሄዲ ንገሯቸው” አሉኝ፡፡ ለምን? ብዬ ብጠይቀው “እዚያ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ እንደሚያደርሱባቸው ደርሰንበታልና አደጋ ሊያደርሱባቸው ስለሚችሉ በፍጹም እንዳይሄዱ ፤ ድርጅቱም ሊያድናችሁ አይችልም”  አሉኝ ፡፡ እኔም እሺ ብዬ ፓትርያርኩ እና ስምንት ጳጳሳት በተሰበሰብንበት  ጉባኤ ላይ ጉዳዩን አቀረብሁት ፤ ምንም እንኳን አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ብንወያይበት ይሻላል ቢሉም ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ግን ጭራሹንም አፌዙብን፡ “አቡነ ማቲያስ ይቀልዳሉ ? አስር ሺህ ማይልስ አቋርጬ የመጣሁት አኮ ለዚህ ጉዳይ ነው” በሚል ሃይል የተመላበት አነጋገር በመሰንዘር ጉዳዩ ለውይይት እንዳይቀርብ አደረጉትና ሁላችንም ተከትለናቸው ሄድን ፤ ያው ቀጨኔ መድኃኒአለም የተከሰተው ዓይነት የሆነ ችግር አጋጠመን፡፡ “ተዓገሣ ለመዓት ወድኅረ ታሥተፌሥሐከ” የሚለውን መንፈሳዊ ምክር በመከተል ፈንታ በገቢረ ተዓምር ራሳቸውን ለማዳን የተማመኑ ይመስል ወደሚነድ እሳት ተወርውሮ መግባት ሰማዕትነት አይሉት አርበኝነት ፤ ጽድቅ አይሉት ኩነኔ ፤ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለመረዳት ከቶ አልተቻለኝም፡፡

በጣም የከፋው የቦልቲሞሩ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ብሎ ኦክቶበር 10 1993 እሁድ በኒውዮርክ ኢንተር ቸርችል ቻፕል ውስጥ ጸሎተ ቅዳሴ ሲያካሂዱ ተመሳሳይ ሕዝባዊ ተቃውሞ አጋጥሟችዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከሜሪካ አገር ሲኖዶሱ በቤተክርስቲያኖች አካባቢ በሚንቀሳቀሱባቸው ጊዜያቶች የጸጥታ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጸጥታ ክፍሎችን ጠይቀን ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰጠን መልስ “እኛ ጥበቃ የምናደርገው ለዲፕሎማቶች እንጂ ለሃይማኖት መሪዎች  ጥበቃ የማድረግ ባህል የለንም” የሚል ነበር ፡፡ በኋላ ግን በኒውዮርክ ኢንተር ቸርች በመግቢያ እና መውጫ ላይ ብጥብጥ እንደተነሳ ሲታወቅ የአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ፓትርያርኩ በተለይ ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በቆዩበት ወቅት መጠነኛ የሆነ ጥበቃ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ዋሽንግተን ዲሲ ለስድስት ቀን ሲሰነብቱ ምንም እንኳን በዞሩበት አካባቢ ሁሉ ተቃዋሚ ባይጠፋም እንደ ኒውዮርክ ፤ ቦልቲሞር ፤ ሜሪላንድ ፤  አትላንታ እና ጆርጂያ ዓይነት የጎላ ችግር አልነበረም፡፡ 

አቡነ ጳውሎስ አትላንታ ጆርጂያን ለመጎብኝት የሄዱበት ዋና ዓላማ ከቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት  ጂሚ ካርተርና ከአትላንታ ከንቲባ ጋር ለመገናኝት ሲሆን በየሄዱበት የሚያደርጉት ሁሉ እዚያ ያሉትን ምዕመናን ቀድሼ  ማቁረብ ስላለብኝ ዝግጅት አድርልኝ  አሉን፡፡ እኛም ትዕዛዛቸውን ተቀብለን  አትላንታ ጆርጂያ ቅድስት ማርያር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ያሉት ካህናት ለኦክቶበር 17 1993 እሁድ ቅዳሴ እንዲያዘጋጁላቸው ትዕዛዝ አስተላለፍን፡፡ ዳሩ ግን ካህናቱ ፍቃደኞች ሲሆኑ በፖለቲካው ተቆጥቶ የኖረው ህዝብ ግን ፓትርያርኩ ቢመጡ ቤተክርስቲያናችንን እንዘጋለን በምንም አይነት አናስገባቸውም ብሎ አደመ፡፡ “እናንተ ተቀብለን እናስገባለን ብትሉ ጠባችን ከእናንተ ጋር ይሆናል” ብሎ ከካህናቱ ጋርም ጠብ ገጠመ፡፡

ካህናቱ ሲጨንቃቸው ወደ እኔ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ደውለው “አቡነ ማቲያስ እባክዎን ሕዝቡ አድሟልና ቅዱስ ፓትርያርኩ ቅዳሴ መቀደስ እንዲቀርባቸው ይለምኑልን ፤ ያለበለዚያ ከሕዝብ ጋር መጣላታችን ነው” ብለው አምርረው ነገሩኝ፡፡ እኔም “ቅዱስ አባታችን ኒውዮርክና ዋሽንግተን ዲሲ ቀድሰዋልና ይበቃዎታል የአትላንታው ቅዳሴ ይቅርብዎ ያለዚያ ካህናቱንና ህዝቡን ከፋፍለው ቤተክርስቲያኑ ይፈርሳል” አልኋቸው፡፡  አሳቸው ግን አሁንም “አቡነ ማቲያስ አቀድሳለሁ ነው የምልዎት  እንዲህ አይነቱ ቤተክርስቲያን ቢፈርስ ምን ይጎዳል” ብለው  እንደመብረቅ ሲጮሁብኝ  ጊዜ  ወደ አትላንታ ቴሌፎን ደውዬ  “ነገሩ አልተቻለም ፤ ፓትርያርኩ ሀሳቡን አልተቀበሉትምና የሚመስላችሁን አድርጉ” አልኋቸው ፡፡ ካህናቱም ከህዝቡ ተደብቀው ሌላ ቤተክርስቲያን ለምነው ፓትርያርኩን ተቀብለው ቅዳሴ እንዲቀድሱ አደረጓቸው፡፡ ተቃዋሚዎቹ ግን እዛ ድረስ ሄደው ሲሳደቡ ዋሉ፡፡ ካህናቱም በዚሁ ሰበብ ከዚያ ቀን ጀምሮ ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ሳይመለሱ በዚያው እንደወጡ ቀሩ፡፡ ካህናቱም ፓትርያርኩን በዚህ ሁኔታ ከሸኙ በኋላ ካደመው ሕዝብ ጋር መስማማት ስላልቻሉ ብዙ ሳይቆዩ ሌላ ቤተ ክርስቲያን አቋቋሙ፡፡ በዚህ ምክንያያት ቤተክርስቲያኗ ለሁለት ተከፈለች፡፡

ፓትርያርኩ ከአትላንታ ወደ እንግሊዝ አገር ጉዟቸውን ቀጠሉ ፡፡ የእንግሊዝ ሕዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ ከአሜሪካ እጅጉን የከፋ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ሌላው አስገራሚ ታሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት አንዱንም የሃይማኖት መሪ አለማነጋገራቸው ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አንዱም አልተሳካም እንጂ አጀንዳቸው ከአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ጋር  ለመገናኝት ብቻ ነበር፡፡  ይህ ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የማይጠበቅ እንግዳ ነገር ነበር፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው ፡-
1.     በዚያን ጊዜ የዩናይትድ ኔሽን  ሴክሬተሪ የነበሩት ፑጥሮስ ፑጥሮስ ጋሊ ፤ ዋሽንግተን ዲሲ
2.    የኒውዮርክ ከንቲባ ፤ ኒውዮርክ
3.    የተማሩበት የፕሪስተን ሴኒናሪ ፤ ኒውጀርሲ
4.    ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ፤ ኋይት ሃውስ ዋሽንግተን ዲሲ
5.    የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ
6.    የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃሚ ካርተር ፤ አትላንታ ጆርጂያ
7.    የአትላንታ ከንቲባንና ሌሎችንም ነበር፡፡
ከዚህ ሁሉ የተገናኟቸው ጂሚ ካርተርን ብቻ ነበር፡፡ ሌሎችን ግን ማግኝት ፈጽሞ አልቻሉም ነበር፡፡ የሃገሩ የሃይማኖት መሪዎች “ፓትርያርካቹ መጥተው እንደነበር ሰማን እውነት ነውን?”  ብለው በጥያቄ ሲያፋጥጡን ከማፈር በቀር የምንመልሰው መልስ አልነበረንም፡፡
ቀጣይ 6ተኛው ፓትርያርክ ከዚህ የቀድሞ ታሪካችን ብዙ ነገር ይማራሉ ብለን እንጠብቃለን ፤ የሰውን ምክር አለመስማት ለእንደዚህ አይነት ችግር ይዳርጋል ፤ እኔ ብቻ አውቃለሁ ማለት ቁልቁለት ያወርዳል ፤ ጆሮን ለሌሎች አለማዋስ የገማ እንቁላል ያስወረውራል ፤  የገማ እንቁላል ክብርን ያሳንሳል ፤ ሞገስን ያሳጣል ፡፡ ቀጣዩ ፓትርያርክ ሌላ የገማ እንቁላል እንዳያስተናግድ ምርጫው እግዚአብሔርን በመፍራትና በህገ ቤተክርስቲያን ብቻ መጓዝ መቻል አለበት ፡፡ “ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ነውና መጠንቀቁ አምላክን መፍራቱ ተገቢ ነው፡፡ አቡነ ጳውሎስ የገማ እንቁላል ያስተናገዱት ከተመረጡ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት በኋላ ነበር ፤ ዋናው ምክንያትም ሹመቱ ህገ ቤተክርስቲያንን የሚጥስ ፤ ከኢህአዴግ ተበረከተላቸው ገጸበረከት ነው በማለት ህዝቡ ስላመነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በውጭ የሚገኝው ህዝብ ክፉኛ ውስጡ ስላረረ እና ስላልተቀበላቸውም ጭምርና መንግሥት ሆን ብሎ የሾማቸው አባት ናቸው ብሎ ስላመነ ነው፡፡ አሁንም ከህገ ቤተክርስቲያን ውጪ የሚካሄድ የፓትርያርክ ምርጫ ከባለፈው የገማ እንቁላል የባሰ እንደማያስወረውር እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ፡፡ አቡነ ማቲያስ በጊዜው እንዲህ ብለው የአቡነ ጳውሎስን ስራ በመጻፍ ለመጽሄት አብቅተው ህዝቡ እንዲያውቅ አድርገውት ነበር ፤ አሁን ደግሞ እሳቸው ፓትርያርክ ቢሆኑ ይህ ታሪክ እሳቸው ላይ ያለመደገሙን ማን እርግጠኛ ይሁንልን ? ፡፡  ሹመት ከቤተመንግሥት ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስስ ለምን ያስፈልጋል? ፤ ለምንስ ጉባኤ ያደርጋል? ፤ ለማንኛውም ይህን ታሪክ አቡነ እንዲያስታውሰት አስፍረነዋል፡፡ ወርቃማ ታሪኮች እንዳሉን ሁሉ ይህን የመሰለ ታሪክም ቤተክርስቲያናችን አሳልፋለች ፡፡ መልካሙን ብቻ ሳይሆን ይህንም የማወቅ ኃላፊነት አለብን ብለን እናስባለን ፤ አቡነ ማቲያስ በጊዜው ይህን የመሰሉ በርካታ ህዝቡ ሊያውቃቸው የሚገባቸውን ታሪኮች ከ20 ገጽ የማያንሱ ለ”ኢትኦጵ” መጽሄት ዋና ሥራ አስኪያጅ በአስቸኳይ የፖስታ አገልግሎት የላኩትን ጽሁፍ በእጃችን ይገኛል ፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ሌላውን ወደፊት የምንመለስበት ይሆናል፡፡

ሌላ የገማ እንቁላል እንዳታስተናግዱ አካሄዳችሁን በሕገ- ቤተክርስቲያን እና እግዚአብሔርን በመፍራት አድርጉ፡፡


ታሪክን ማወቅ መልካም ነው፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment