Saturday, February 23, 2013

ለዕጩ ፓትርያሪክነት ከተለዩት አባቶች ሁለቱ በዕጩነት መካተታቸውን አልተቀበሉትም

  • አቡነ ማትያስ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን የመለሱበትን ሰርቲፊኬት እንዲያቀርቡ ይጠበቃል
  • የእነንቡረ እድ ኤልያስን ጫና አንቀበልም ያሉ መራጮች እንዲቀየሩ እየተደረገ ነው
  • የጨለማው ቡድን በአቅምና በሰው ኀይል ተጠናክሮ በአራራት ሆቴል ዳግም እየተደራጀ ነው
  • የአስመራጭ ኮሚቴው አንዳንድ አባላት በተናጠል ማስፈራሪያ ተደርጎባቸዋል
  • ‹‹በሃይማኖት አክራሪነት ለኦርቶዶክስ የበላይነት ብቻ የሚቆሙ ናቸው፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የመንግሥትን ድጋፍ ያጡበት ምክንያት/
  • ‹‹አዲስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ተመርጦ ምርጫው ለሌላ ጊዜ መተላለፍ አለበት፡፡›› /አስተያየት ሰጭዎች/
የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ለዕጩ ፓትርያሪክነት የለያቸውን አምስት ሊቃነ ጳጳሳት ነገ፣ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያቀርባል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው የካቲት 14 ቀን ለይቶና አጣርቶ ከተፈራረመባቸውና በነገው ዕለት ለቅዱስ ሲኖዶሱ ለማቅረብ ካዘጋጃቸው አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች መካከል ሁለቱ ግን በዕጩነት በመካተታቸው እንደማይስማሙ ነው ከወዲሁ እየተነገረ የሚገኘው፡፡ በዕጩነት መካተታቸውን እንደማይቀበሉት የተነገረላቸው ሁለቱ የኮሚቴው ዕጩ ፓትርያሪኮች የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ የወላይታና ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡

የዜና ምንጩ እንደሚለው፣ ሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በኮሚቴው ዕጩነት መካተታቸውን የተቃወሙበት ምክንያት አንድና ተመሳሳይ ነው፤ እርሱም÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ለማስመረጥ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የፅልመት ቡድን የመንግሥት የደኅንነት ኀይሎች ናቸው በተባሉ ግለሰቦች እየታገዘ በመራጮች ላይ ያካሄደውና አሁንም ያላቋረጠው ኀይል፣ ዛቻና ማስፈራራት የተቀላቀለበት ግልጽ ዘመቻ ነው፡፡ በአዲስ አበባ አራራት ሆቴል እየተሰበሰበ ይመክራል የተባለው ይኸው የጨለማ ቡድን በአህጉረ ስብከት ደረጃ ከመንግሥት የዞን ደኅንነት መዋቅር ጋራ የሚሠራ ቅርንጫፍ ያለው ሲኾን ለመራጭነት የተመዘገቡ ካህናትን፣ የሰንበት ተማሪዎችንና ምእመናን ስም ዝርዝርና አድራሻ ከአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች እየወሰደ በመራጮች ውሳኔ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡
ጫናው ቀደም ሲል ሲዘገብ እንደቆየው፣ ‹‹መንግሥት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በፓትርያሪክነት እንዲመረጡ ይፈልጋል፤ ድምፅ መስጠት ያለባችኹ ለብፁዕ አቡነ ማትያስ ነው፤ አቡነ እገሌ እንዲህ ናቸው፤ አቡነ እገሌ ደግሞ እንዲያ ናቸው፤ ለአቡነ ማትያስ ድምፅ የማትሰጡ ከኾነ እናስራችኋለን፤ ከሥራ እናባርራችኋለን፤›› የሚል ነው፡፡ የጫናው መጠንከርና የብፁዕ አቡነ ማትያስ በፓትርያሪክነት መመረጥ ከምርጫው ቀን አስቀድሞ የተረጋገጠ መምሰሉ በዕጩነት የተካተቱት ሌሎች አባቶች ‹‹አጃቢ፣ አሯሯጭ፣ አዳማቂ›› እንዲባሉ አድርጓቸዋል፡፡ በአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ምርጫ ወቅት በዕጩነት ቀርበው ከነበሩት አንዱ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣‹‹ፊትም አሟይ ነበርኹ፤ አሁንም ማሟያ አልኾንም፤›› ማለታቸው የተዘገበ ሲኾን፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስም ‹‹አጫፋሪ አይደለኹም፤›› በማለት የምርና ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም በሚባለው ምርጫ ሐዘናቸውን ገልጸዋል ተብሏል፡፡
ከየአህጉረ ስብከቱ የሚወጡት ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ የጨለማው ቡድን የመንግሥትን የደኅንነት መዋቅር/ኀይል በመጠቀም በጫና ያወረደውን መመሪያ ባለመቀበል በራሳቸው ምርጫና ውሳኔ ለመጽናት የቆረጡ መራጮች በሌሎች እንዲቀየሩ እየተደረገ ነው፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት በሀገር ውስጥ የሚገኙ 53ቱም አህጉረ ስብከት በምርጫ ሕጉ በተወሰነው መሠረት÷ በየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ሰብሳቢነት በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ከካህናት አራት፣ ከምእመናን አራት፣ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አራት በድምሩ 12 መርጠው የሀ/ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ 13 አባላት ዝርዝራቸውን እስከ ነገ የካቲት 16 ቀን በአካል ወይም በፋክስ እንዲልኩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ እንግዲህ ሰሞኑን በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና ጽ/ቤቶቻቸው ላይ የመራጮችን ዝርዝር እንዲሰጡ፣ እነርሱም ራሳቸው መራጮቹን እየሰበሰቡ የጫናውን መልእክት እንዲያስተላልፉ ርብርብ የተደረገው÷ ይህ ቀነ ገደብ አልቆ በወጣው ፕሮግራም መሠረት መራጮች የካቲት 19 ቀን አዲስ አበባ የሚገቡበት ቀን ከመድረሱ በፊት ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዘንድም መንግሥት በፓትርያሪክነት ሊያስመርጣቸው ነው በሚባሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ላይ አለ የሚባለውየተከፋፈለ አቋም ቀደም ሲል ለተገለጸው የውስጥ ሕገ ቡድኖች ዘመቻና የውጭ አካል የከፋ ተጽዕኖ የተመቸ ኾኗል፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ያሉ አንድ አባት፣ ‹‹የእኛው መከፋፈል ተመቸ›› ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስ በፓትርያሪክነት ቢመረጡ በእጅጉ የሚደግፉትና ቢኾኑ በሚል የማይቃወሙት÷ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ባላቸው ከፍተኛ መቀራረብ የብፁዕነታቸውን ደመወዝ ላለፉት ኻያ ዓመታት በውክልና ሲቀበሉ እንደነበር ተነግሯል)፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (በብፁዕነታቸው ምትክ በኢየሩሳሌም መመደብ ይፈልጋሉ፤ ከዚህ ቀደም ለመመደብ ሞክረው አልተሳካላቸውም፤ የወ/ሮ እጅጋየሁን የጉዞ ወኪል ቢዝነስ ለማጧጧፍ ይኾን?) ናቸው፡፡
በአንጻሩ የሚጠቀሱ በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ የብፁዕ አቡነ ማትያስ በፓትርያሪክነት መመረጥ ቅር ያሰኛቸዋል፤ ለምን? ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ከአገሩ ርቀው በሂደት ለተለዋወጡት ኹኔታዎች እንግዳ መኾናቸውን መሠረት ያደርጋል፡፡ አንድ ብፁዕ አባት እንዲህ ይላሉ÷ ‹‹የአገር ቤቱን ወቅታዊ ኹኔታ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ችግር የረሳ ሰው እንዴት ይመረጣል? እዚህ ፓትርያሪክ የሚኾን ጠፍቶ ነው ወይ?›› ሌሎቹም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕነታቸው ለኻያ ዓመት ይዘውት የቆዩትን አሜሪካዊ ዜግነትና ዕድሜያቸው ምናልባት ከ75 ያልፋል በሚል ጥርጣሬ ብፁዕነታቸው ከፓትርያሪክነቱ መመዘኛ መስፈርት በመፃረር በጫና መሾማቸውን ይቃወማሉ፡፡ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 5/1 እና 2 መሠረት በዕጩ ፓትርያሪክነት የሚቀርብ ተወዳዳሪ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ መኾን አለበት፤ የውጭ አገር ዜግነት ያለው ከኾነም የውጭ ዜግነቱን ሰርዞ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ የተመለሰ መኾን አለበት፤ ይህም ኢትዮጵያዊነትና ኦርቶዶክሳዊነት ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት በማመንና ኢትዮጵያዊነት በራሱ እሴት መኾኑን በመቀበል የሰፈረ ድንጋጌ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በዕጩነት የተካተቱት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዕጩነታቸው የተስማሙ ከኾነ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ይዘውት የቆዩትን አሜሪካዊ ዜግነት የመለሱበትን ሰርቲፊኬት በዛሬው ዕለት ለአስመራጭ ኮሚቴው እንዲያቀርቡ መጠየቃቸው ነው የተሰማው፤ እንደሚባለው የብፁዕነታቸው ሰነዶች ጠፍተዋል የሚል ማመኻኛ ካልተሰጠ በቀር፡፡
የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩን በዕድሜ መግፋት፣ ጥቂት የማይባሉ አሠራሮችና ውሳኔ ለውጭ ተጽዕኖ ይበልጥ እንዲጋለጥ ማድረጉን በሰበብነት የሚጠቅሱ የተወሰኑ ብፁዓን አባቶች በበኩላቸው፣ ‹‹የሚፈለገው የሚሠራ ሰው ነው፤ የሥራ ሰው ነው፤ መንግሥትማ ፓትርያሪክ ሊመርጥልን አይችልም፤ ሌላ ዐቃቤ መንበር ተሠይመው ምርጫው በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ መደረግ ይኖርበታል፤ ይህንንም አገልጋዩና ምእመኑ ሁሉ እንዲያውቀው መደረግ ይኖርበታል፤›› ይላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን የደኅንነት መዋቅር እየተጠቀመ በአቅሙ ተጠናክሮ፣ በሰው ኀይሉ ጨምሮ የተደራጀው የጨለማው ቡድን በዕጩነት ሊካተቱ ይችላሉ የተባሉ ብፁዓን አባቶችን ሳይቀር ግልጽ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸውና ‹‹ዐርፈው እንዲቀመጡ›› አድርጓል፤ ቀጥተኛ ማስፈራሪያ ከደረሳቸው አንዱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ከእርሳቸውም ጋራ ለብፁዕነታቸው የምርጫ ድጋፍ እንቅስቃሴ አድርገዋል የተባሉ፣ በፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቋማቸው የሚታወቁ የሐዋሳ ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል የሰላምና ልማት ኮሚቴ ታዋቂ ምእመናን ይገኙበታል፡፡
በዕጩዎች ዝርዝር ቢካተቱ ከትምህርት ዝግጅታቸው፣ ከችሎታቸውና ልምዳቸው አንጻር ከሌሎች ጋራ ሲነጻጸሩ ‹‹ውጤቱ የማይፈለግ ይኾናል››በሚል እንዲወጡ የተደረጉት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል÷ ከካህናትና ምእመናን በተሰበሰቡ ጥቆማዎች ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በመቀጠል ከፍተኛውን ብልጫ ያገኙ አባት ናቸው፡፡ የጨለማው ቡድን ብፁዕነታቸውን ከዝርዝሩ እንዲወጡ ሲያደርግ ብፁዕነታቸው በአሜሪካ ቆይታቸው ነበራቸው የሚለውን ‹ፖሊቲከኝነት›ና መሰል ምክንያቶች በመንሥኤነት በማጋጋል መኾኑ ተገልጧል፡፡
አካሄዱን ተቃውመዋል የተባሉትን የአስመራጭ ኮሚቴውን አባላት በተናጠል በማስፈራራትና ተስማምተው እንዲፈርሙ በማድረግ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከዕጩነት ዝርዝር እንዲወጡ የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ብፁዕነታቸው ‹‹በሃይማኖት አክራሪነት ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የበላይነት ብቻ ነው የሚሠሩት›› የሚለው የተዛባ አመለካከት፣ ቂምና ጥላቻ የወለደው ክሥ ነው፡፡ የመንግሥትን የደኅንነት መዋቅር የሚታከከው የጨለማው ቡድን ይህን ክሡን ያጠናከረው ብፁዕነታቸው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት በጅማና በኢሉ አባ ቦራ በጽንፈኞች የተፈጸመውን አሠቃቂ ሽብር በሀ/ስብከቱ ጋዜጣ – ኆኅተ ጥበብ – እንዲዘገብ አድርገዋል፤ በሃይማኖት መቻቻልና በእስላማዊ አክራሪነት ዙሪያ ያሳተሟቸውን መጻሕፍት በመጥቀስ ነው፡፡
የጨለማውን ቡድን እኒህን ክሦቹን በማጠናከር፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከዕጩዎች ዝርዝር ተካተው በፓትርያሪክነት ለመመረጥ ከበቁ‹‹የሃይማኖት መቻቻል እንዳይኖር ያደርጋሉ›› የሚል ለመንግሥት የሚስብ መስሎ የሚታይ፣ በሐቀኛ ገጹ ግን አንድም÷ የአድርብዬ ጠባይ የተጠናወተው፣ አንድም በቡድኑ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ድጋፍ የሚሰጡ ሕገ ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች መሠሪ ተንኰል በተገፋ አቋሙ ለጊዜውም ቢኾን ያሰበው የተሰካለት መስሎ ታይቷል፡፡ ታድያ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ቡድን ነፍስ ዘርቶ ሊጠናከርበት ያደባበት የምርጫ ሂደትና የምርጫ ውጤት አካል አንኾንም፤ አናደምቅም ቢሉ ቅር ያሰኛልን? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment