Wednesday, February 27, 2013

ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ራሳቸውን ከዕጩነት አገለሉ!!


  • አስመራጭ ኮሚቴው የብፁዕነታቸውን ውሳኔ ለመራጮች በይፋ ያሳውቅ ይኾን?
  • አብዛኞቹ የብፁዕነታቸው መራጮች ለአቡነ ዮሴፍ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ይገመታል
His Grace Abune Mathewos
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ


የወላይታና ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ራሳቸውን ከዕጩነት በማግለል ከምርጫው ለመውጣት መወሰናቸው ተሰማ፡፡
ለአስመራጭ ኮሚቴው ቅርበት ያላቸው ሐራዊ ምንጮች እንደገለጹት÷ በዕጩ ፓትርያሪክነት መካተታቸውን እንዳልተቀበሉት ቀድሞውንም በግልጽ ያስታወቁት ብፁዕነታቸው÷ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ከተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፍጻሜ በኋላ የት እንደሚገኙ ለማወቅ አልተቻለም፡፡
አንዳንድ ምንጮች ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በራቸውን ዘግተው መቀመጣቸውን የሚናገሩ ሲኾን ሌሎች ምንጮች ደግሞ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ወጥተው መሄዳቸውን ይገልጣሉ፡፡
ነገ፣ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጠዋቱ 1፡00 ጀምሮ በሚከናወነው የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ዕጩ ፓትርያሪክነታቸውን ያልተቀበሉት፣ በምርጫውም ዙሪያ እንደሌሎች ዕጩዎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያልታዩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከዕጩ ተወዳዳሪነት ይሰረዙ እንደኾን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ይኹንና ብፁዕነታቸው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት እንዲኾኑ ለሚሹ መራጮቻቸው ዜናው የመርዶ ያህል መኾኑ አይቀርም፡፡
ከዚህ የተነሣ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አንጻር ተሰልፈው የነበሩ መራጮች የአቋም ለውጥ በማድረግ ምርጫቸውን÷ በጽኑ መንፈሳዊነታቸው፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔና ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ባሳዩት ተገዥነታቸው፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንንና ሕገ ወጦች በመቋቋም በሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ላይ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡
ሌሎች የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ መራጮችም ለብፁዕ አቡነ ማትያስና ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ድጋፋቸውን ሊሰጡ እንደሚችሉ ተዘግቧል፡፡ ይህ ሊኾን የሚችለው ግን የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ወቅታዊ አቋም ለመራጮች በሰዓቱ ከተገለጸ ነው፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው በነገው ዕለት በወድድሩ ውስጥ በሌሉት አባት ሳቢያ የድምፅ መባከንን/መከፋፈልን ለማስቀረት ምን ውሳኔ ያሳልፍ ይኾን? አብረን የምናየው ይኾናል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስ ራሳቸውን የማግለላቸው ዜና ቀድመው አረጋግጠው ሳያውቁት አልቀሩም የሚባሉት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል÷ በከፋ ሸካ ቤንች ማጂ፣ በደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ፣ በኢሉባቦርና በጋምቤላ፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ፣ ከሀገር ውጭም በአፍሪካና በካናዳ (የብፁዕ አቡነ ያዕቆብና የብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ) አህጉረ ስብከት በቀራቢዎቻቸው አማካይነት የምር ቅስቀሳቸውን አጠናክረው መሰንበታቸውን፣ በአንዳንድ ኹኔታዎችም ‹ድላቸውን› ከወዲሁ ሲያውጁ መደመጣቸው ታውቋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ በኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም ነው፡፡ አሁን ወላይታና ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከመኾናቸው በፊት የዋግህምራ እና የምዕራብ ሐረርጌ (አሰበ ተፈሪ) አህጉረ ስብከትን በየተራ መርተዋል፤ ከብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሲኾኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለሦስት ዓመት ሠርተዋል፡፡ በአብነት ትምህርት ይኹን በዘመናዊ ትምህርት ከቀረቡት ዕጩዎች የተሻለ እንጂ ያነሰ ደረጃ አልነበራቸውም፡፡
ብፁዕታቸው እንደተናገሩት በቀድሞ አባቶች ገዳማዊ ሥርዐት ዕጩነቱ አይገባኝም ማለታቸው ከትሕትና (አትሕቶ ርእስ) የመነጨና በአርኣያነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ በስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ዙሪያ የሚታየው ውጫዊ ተጽዕኖ እና የውስጥ ቡድኖች ሽኩቻ ራሳቸውን ከዕጩነት ለማግለላቸው ሌላው ምክንያት ሳይኾን እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

Source: http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment