ትጉህ እና ቅን ለበጎቹ አሳቢ መሪ ይስጠን |
(ደጀ
ሰላም፤ መስከረም 9/2004 ዓ.ም፤ ሰምቴፕር 19/2012/ READ
THIS ARTICLE IN PDF)፡-
ከአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማለፍ በኋላ በመንበረ ተክለ ሃይማኖት መቀመጥ የሚገባውን ቀጣይ አባት ከመሾም አስቀድሞ የአራተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ዕጣ ፈንታ መወሰን፣ ከዚህም ጋራ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት እንዲሁም የመዋቅር ማሻሻያ የሚመለከቱ ርምጃዎች መውሰድ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ኾኖ ወጥቷል፡፡ በአሜሪካው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሂደት በተጨማሪ በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሓቅ የሚመራውና ከዐሥር ያላነሱ ልሂቃንን የያዘው የአገር ሽማግሌዎች ቡድን ሰሞኑን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በመወያየት በቅርቡ ቡድኑ በቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የሚነጋገርበት ኹኔታ እንዲመቻች መደረጉ ተዘግቧል፡፡
በሌላ
በኩል የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባናል፤ የቅ/ሲኖዶስን የሰላምና የተቋማዊ ማሻሻያ ርምጃዎች በማገዝ ረገድ የበኩላችንንም ለማበርከት ተዘጋጅተናል የሚሉ የአገልጋዮችና ምእመናን ስብስቦችም ይበጃል በሚሏቸው ሐሳቦች ዙሪያ የሚመለከታቸውን አካላትና ሰፊውን ምእመን በተደራጀ መንገድ እያወያዩ ናቸው፤ ለውይይትና ግንዛቤ የሚረዱ ጽሑፎችም በተለያዩ መድረኮች እየቀረቡና እየተሠራጩ ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም መካከል ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ የተሰኘውና በዋናነት ለመረጃ፣ ለግንዛቤና ለውይይት የሚረዱ ጽሑፎችን መዘርጋት የጀመረው የአገልጋዮች መድረክ አንዱ ነው፡፡
መድረኩ
ባዘጋጀውና ለደጀ ሰላም መድረስ በጀመረው በዛሬው ሁለተኛ ጽሑፉ ከቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ አስቀድሞ መከናወን በሚገባቸውና ‹‹መንገድ ጠራጊዎች ናቸው›› በሚላቸው መሠረታዊ ሥራዎች ላይ ሐሳቡን በዝርዝር አቅርቧል፤ እኒህ መሠረታዊ የቅድመ ሢመተ ፓትርያሪክ ተግባራት ለቤተ ክርስቲያናችን፣ ለአገራችንና ለዓለም ሁሉ ያላቸውን በረከት በማመላከትም ተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው ይከራከራል፡፡ ደጀ ሰላማውያን ሁሉ በመድረኩ የጽሑፍ አበርክቶዎች ላይ ሐሳባቸውን በማቅረብ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ በባለቤትነት ለመወያየት እንችል ዘንድ ደጀ ሰላም ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡
ቸር
ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
+++
ቀጣዩ
ፓትርያርክ ማን ይሁን? የወቅቱ የቤተክርስቲያን ፈተና!
(ከውሉደ
አበው ዘተዋሕዶ)፦ ወደ ዐቢይ ርእሳችን ከመግባታችን በፊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ልትሠራቸው ከሚገባት ዐበይት ሥራዎች አንዱ የሆነውን ጉዳይ ልናስቀድም ወደድን።
ሕግጋት፣
ደንቦች እና መመሪያዎች
ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን በረዥሙ መንገዷ ውስጥ ስትገለገልባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ሕግጋት አሏት። ቀኖና ቤተክርስቲያን የሚጠበቀው ከቀደምት አበው ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚነሡ አበው ዘመኑን እየዋጁ ቤተ ክርስቲያን ከእነ ተከታዮቿ ተጠብቃ የምትኖርበትን ሁኔታ እያገናዘቡ ፣ ክፍተት እንዳይፈጠር በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየመከሩ ቀኖና እንዲደነግጉ ፣ ሕግጋትን እንዲያወጡ ሥርዓት እንዲሠሩ የሚቻልበትም ጭምር ነው። ይህም አዲስ ነገር ሳይሆን በ፶ ዓም ከተካሄደው ከመጀመሪያው የቅዱሳን ሐዋርያት ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከዚያም ወዲህ በርካታ ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ተደንግገዋል። በፈለገ አበው የምትጓዘው አናት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም በዚያው በቅዱሳኑ አሠረ ፍኖት በመጓዝ ተልአኮዋን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ሕግጋትን ደንቦችን እና መመሪያዎችን ለማውጣት ሥልጣን አላት ።
ይህ
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ከሰማይም ከምድርም ከሁለት ወገን የተሰጣት ነው። ሰማያዊው ሥልጣን የታወቀ እና የተረዳ ሲሆን በኢትዮጵያ ሀገራችን ሕግ በግልጽ በታወቀ በተረዳ መንገድ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ብቸኛ የሀገራችን መንፈሳዊ ተቋም ናት። ይኽም በ፲፱፻፶፪ ዓም በወጣው አስካሁንም በሥራ ላይ ባለው የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ ፫፻፺፰ ላይ ተገልጦ ይታያል። እርሱም እንዲህ ይላል፥
ቁ
፫፻፺፰ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን
፩.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው የምትቆጠር ናት
።
፪.
እንዲህ እንደመሆኗ በመሥሪያ ቤቶቿ አማካይነት በአስተዳደር ሕጎች የተፈቀዱትን መብቶች ሁሉ ልታገኝና ልትሠራባቸው ትችላለች።
ቁ
፫፻፺፱ የጳጳስ ሀገረ ስብከት አድባራት እና ገዳማት
በአስተዳደር
ሕጎች ሁኔታዎችና ወሰኖች በተሰጡ ውሳኔዎች መሠረት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክፍል የሆኑ የጳጳስ ሀገረ ስብከት ፤ አድባራትና ገዳማት በሕግ በኩል ግዴታ ያለባቸውና መብት ያላቸው ናቸው ።
ቁ
፬፻፯ ሃይማኖታዊ ጠባይ ያላቸው ስብሰባዎች
፩.
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በቀር ሌሎች አብያተ ክርስቲያኖች፤ ሃይማኖቶች እና ማኅበሮች የሚተዳደሩት እነዚህኑ በሚመለከቱ ልዩ ሕጎች ነው።
ከእነዚህ
ወሳኝ የሕግ አናቅጽ የምንረዳው ቤተ ክርስቲያን በራሷ ወሰን ለተልእኮ የሚያስፈልጋትን ማንኛውም የሥራ ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያ ለማውጣት ሕጋዊ ሰውነት አላት ማለት ነው። ይኽ ሥልጣን ከፍ ባለ ደረጃ ሕግ ነክ የሆኑ ደንቦች እና መመሪያዎች እንድታወጣ ይፈቅድላታል። በተለይም በአስተዳደር ሕጎች የተፈቀዱትን መብቶች ሁሉ ልታገኝና ልትሠራባቸው ትችላለች የሚለው በአንቀጽ ፫፻፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪ ላይ የተገለጠው መጠነ ሰፊ መብት በሚገባ ሊጤን እና ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው እጅግ ከፍ ያለ ዕድል መሆኑ አያከራክርም። መነሣት የሚገባቸው ነጥቦች ሥልጣኑን ወይም መብቱን ምን ያኽል ተጠቅማበታለች? የሚለው ሲሆን ያወጣቻቸው ሕግጋት፣ ደንቦች እና መመሪያዎችስ ከዚህ ሥልጣን አንፃር የቱን ያኽል አብረው ይሄዳሉ? በምንስ ደረጃ ላይ ናቸው? የሚሉት ይሆናሉ።
አሁን
በቤተ ክርስቲያን እየተሠራባቸው ካሉት መካከል በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ደንቦች እና መመሪያዎች መነሻ ከኾነውና ሊኾን ከሚገባው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ፡-
- · ቃለ ዓዋዲ፣
- · ፍትሕ መንፈሳዊ፣
- · የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብ ያሉት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በሚገባ ተፈትሸውና ተገምግመው፣
፩. ሊያሟሉ የሚገባቸው አርእስት ካሉ በማካተት፣
፪. ሊታረሙ የሚገባቸውንም በማርታት፣
፫.
ከአኀት አብያተ ክርስቲያናት ሕግጋት እና ከሌሎች ቅቡል ዘመናዊ አሠራሮች አንፃር የሚያስፈልጉ አናቅጽን
በመጨመር ፣
፬.
ሊቋቋሙ የሚቸሉ እና የተቋቋሙ ተቋማትን [ለምሳሌ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የልማት ተቋማት፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ ማኅበራት … ወዘተ] በሚመለከት ክትት እና ጥርት ያለ የማያወላዳ ጠቋሚ የመመሥረቻ አንቀጽ ወይም ክፍል ተቀርጾ እንዲገባ በማድረግ፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ባለ ደረጃ ፣ ብቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ እና የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናቸው የማያጠራጥር የሕግ ባለሙያዎች እና እንደየዘርፉ ልምድ እና ሙያ ያላቸው ምእመናንን አሰባጥሮ የሚሠራ አካል በአስቸኳይ ማቋቋም ይጠበቃል።
የዋለ
ያደረ ነገር እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችል ለብልኅ አይመክሩ /ለአበው አይነግሩ/ ለአንበሳ አይመትሩ ነውና ከመጠቆም ያለፈ ብዙ ሐተታ አያሰፈልግም።
ሕገ
ቤተ ክርስቲያኑን እንደ ላዕላይ ሕግ (Church
Constitution) መሠረታዊ
እና መነሻ አድርጎ እርሱን ለማስፈጸም የወጡ እና የሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎችን በመዳሰስ የማያዳግም ሥራ መሥራት ይገባል። በተለያየ ምክንያት ዓለማዊውን ፍርድ ቤት ያጣበቡ ግን በቤታችን እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው ፋይሎች የሚዘጉት ብቃት ያለው ሕግ ፣ ደንብ እና መመሪያ ከአፈጻጸም ሥርዓት ጋር (Judiciary) ሲዋቀር እንዲሁም በአግባቡ የተደራጀ ፈጻሚ አካል (Executive) በማቋቋም ብቻ ነው።
ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን ሕግ አውጭ (Legislative)፣ ሕግ አስፈጻሚ (Executive) እና ሕግ ተርጓሚውን (Judiciary) በአግባቡ ለይታ እና አደራጅታ ለማዋቀር አቅሙ እንዳላት ሁሉ ፍላጎቱ እና ቁርጠኝነቱ ሊኖራት ይገባል። እጅግ በጣም ብዙ ልጆቿ የነፃ ሙያ አገልግሎት እስከማበርከት ድረስ ፍላጎት እና ተነሳሽነት እያሳዩ ባለበት በዚህ ወሳኝ ምእራፍ ታሪካዊ ሥራ እንዲሠራ መደረግ ይገባዋል። ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው እንዲል መጽሐፍ። መዝ ፻፲፱፥፻፳፮ ። ቅዱስ ሲኖዶስ የሕግ አውጭውን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የሚመራው መንበረ ፓትርያርክ የሕግ አስፈጻሚውን ድርሻ ይወስዳል። ነገር ግን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት ሀገረስብከት እና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሚኖራቸው የሥራ ተዋረድ እና ግንኙነት በአግባቡ ግልጽና የማያሻማ ኾኖ ሊቀረጽ ይገባዋል።
ከዚህም
በተጨማሪ የሕግ አስፈጻሚውን ሥልጣን እና ተግባር ተንትኖ በማስቀመጥ አቅሙን የማሳደግ ሥራ ሊሠራ ያስፈልጋል። ወደታች የሚዋቀሩ አካላት ግልጽ ካለ የተጠሪነት እና የሓላፊነት መዘርዝር ጋር ተሰናስሎ መቀመጥ ይኖርበታል። ከሥራ አስፈጻሚው በላይ የሕግ ተርጓሚው ጉዳይም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ከማቋቋም ጀምሮ ከሊቃውንት ጉባኤ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በጥንቃቄ ማሰብ እና መስመሩን መዘርጋት ይጠበቃል። ከትዳር ጉዳይ ጀምሮ እስከ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ድረስ በዓለማዊ ፍርድ ቤት ያለው ግርግር መፍትሔ የሚያገኘው ይህ የአሠራር ሥርዓት ሲዘረጋ ብቻ ነው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገበና በየአደባባዩ እንደተራ ጉዳይ ሲናኝ ማየት እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው። መሄጃ ወይም አማራጭ ከማጣት የተነሣ ጉዳያቸውን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ለመውሰድ የተገደዱ ብዙዎች ናቸው። ይኽንን ለማስቆም፣ የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም፣ ክብር እና ዝና ለማስጠበቅ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ ወደፊትም እስከ ወረዳ ቤተክህነት ደረጃ መቋቋሙ አንድ እና ሁለት የሌለው ቀዳማዊ መፍትሔ ነው።
የፓትርያርክ
ምርጫ
የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁን በ፭ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እረፍት ማግስት ላይ ትገኛለች። ከዛሬ ፳ ዓመት በፊት በተፈጠረው የአስተዳደር ልዩነት ምክንያት ከሁለት በተከፈለ ሲኖዶስ ፣ ካህናት፣ ምእመናን እና አስተዳደሯ ችግር ላይ ወድቀዋል። ይኽ ወቅተ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችን እና ስህተቶችን ካለመድገም በተጨማሪ አስተማሪ እና ፈዋሽ የሆነ ተግባር የሚከናወንበት ነውና ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር ከታላላቅ ገዳማት እስከ ገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሱባኤ የሚታወጅበት፣ ከግለሰባዊ ፍላጎት ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን የምናደላበት ፥ ይህን ወይም ያንን ብናደርግ መመዘኛችን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ምን ይፈይድላታል? በሚል እንጂ እኔ ልሁን፣ የእኔ ይሁን ፣ ያልሁት ከሚቀር ከምላሴ ጠጉር ይነቀል ወይም ሞቼ ብቀበር ይሻለኛል እያልን የምንሟገትበት አይደለም።
የማን
ማንነት የሚፈተንበት፣ ራስን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ መስጠት የሚተረጎምበት፣ እግዚአብሔር እና ቅዱሳኑ የሚደሰቱበት፣ ምእመናን አንገታቸውን ቀና አድርገው በእርካታ የሚያመሰግኑበት ጊዜ ሊሆን ይገባዋል። ራስን መካድ የሚለው የጌታችን ትምህርት በተግባር የሚታይበት እንዲሆን ሁሉም ተስፋ አድርጓል። ስለሆነም መቻኮልን አዘግይቶ፣ ቅድሚያ ለጸሎት፣ ለምሕላና ለሱባኤ ሰጥቶ፣ በቂ እና አሳማኝ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ አዘጋጅቶ የሚሠራበት መሆኑ ከሐሜት ነጻ፥ ከጣልቃ ገብነትም ነጻ በሆነ አፈጻጸም የሚከናወን እንዲሆን የሁሉም ዓይኖች ተስፋ ያደርጋሉ ።
በተቻኮለ
እና በተጣደፈ ሒደት ተከታዩን ፓትርያርክ መሰየም ከፍተኛ የሆነ የውዝግብ በር ከፍቶ ለሌላ አሳዛኝ ንትርክ ቤተ ክርስቲያንን አሳልፎ መስጠት ይሆናል። ለተጨማሪ ኀዘን እና ውርደት የተዘጋጀ ግለሰብም ኾነ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ እንደሌላትና እንደማይኖራት ቢታወቅም በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱና የሚያስመስሉ ግለሰቦችና አካላት እንደአሉና እንደሚፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ትገነዘባለች። በመኾኑም ከወቅቱ አንጻር በዝምታ የማታልፈው ነው ተብሎ ይጠበቃል። መስከን እና ማሰብ ከብዝኀ ጸሎት እና ጾም ጋር እጅግ ያስፈልጋል ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ ጾም ወጸሎት ነውና። ለእግዚአብሔር የቀረቡ ገዳማውያን በሚገባ ሊሳተፉበት የሚችል መድረክ መፈጠሩ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ የሚሆንበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል። ስለሆነም ትዕግስት በተላበሰ ሂደት በሰከነ መንፈስ በሃይማኖታዊ ርጋታ የሚያቻኩሉ ቢኖሩ እንኳ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በጸሎት እየጠየቀች መሆኑን በማስረዳት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ መጠባበቅ ላይ መሆናችንን ማሳወቅ ይጠበቅብናል።
ከስህተት
ወደ ስህተት ለመሄድ መፍጠን አያስፈልግም። ካለፈው ለመማር የምንችልበት በቂ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሰጠን እናስተውል። “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” የሚባለው ብኂል የሚያስተምረን ብዙ ነገር አለው። “የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች” የሚለውም እንዲሁ ። በየገዳሙ እና በረሃው ዓለምን ንቀው በተጋድሎ ጸንተው ያሉ አባቶች ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑበት የሱባኤ ጊዜ ያስፈልጋል። ከእነርሱ የሚላከውን መልእክት ለመስማት ዕድሉ መመቻቸት ይኖርበታል። ይኽም ጊዜ ይፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ከምርጫው በፊት መንገድ ጠራጊ የሆኑ መሠረታዊ ሥራዎች እንዲሠሩ ጊዜ ያስፈልጋል። ሁሉም የሚሠራው በጊዜ ነውና! ይኽም ሲባል የተንዛዛ እና የተራዘመ ጊዜ ይፍጅ ማለት አይደለም። የተመጠነ አና በቂ ሥራ የሚሠራበት ጊዜ ይሰፈርለት ለማለት ነውና ሳይረዝምም ሳያጥርም በልኩ የተሰፋ የጊዜ ምጣኔ ይመደብለት የሚለው የተወደደ ሀሳብ ነው ማለት ይቻላል።
ጊዜ
ከሚፈልጉት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ተግባራት ጥቂቶቹ ሲሆኑ የማይታለፉ እና በቅድመ ምርጫ ሊከናወኑ የሚገባቸው ናቸው። በአጭር በአጭሩ ለማየት ያኽል እንደሚከተለው ተቀምጠዋል።
፩.
እርቀ ሰላሙን መፈጸም
በሁለቱ
ሲኖዶሶች መካከል ያለው አለመግባባት ከመጠናቀቁ በፊት የፓትርያርክ ምርጫ ባይደረግ እጅግ የተሻለ ተቀዳሚው ይሆናል። ቀጣዩ ምርጫ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም በሚመሩት ሲኖዶሶች ያሉት ቁጥራቸው ፷፮ የሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት በጉዳዩ ላይ ያላቸው የምንታዌ ሀሳብ በተዋሕዶ ተለውጦ ኹሉም የሚሳተፉበት ምርጫ መሆኑ ሂደቱን ከማሳመር ባሻገር አሳማኝነቱ ላቅ ያለ ደረጃ እንዲይዝ የበኩሉን ጉልህ አስተዋጽኦ ይወጣል። አሁን የተፈጠረው እርቀ ሰላሙን ስለመፈጸም የሚደረገው ርብርብ ምቹ ሁኔታ በመሆኑ ከዚህ አካሄድ ጋር እንዲሰምር መደረጉ የበለጠ ድጋፍ ይሆናል።
በቀጣዩ
የፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ በአንድነት መሳተፍ ውሕደቱን የእውነት በማድረግ በኩል የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚለካ አይደለም። አንድ አካል ባለቤት ሆኖ በወሠነበት ጉዳይ አብሮ በተጓዘው ጉዞ ውስጥ የተለየ ተቃራኒ ሀሳብ የማምጣቱ ነገር እጅግ ሩቅ ነው። ሁለቱም አካላት ከሁለትነት ወደ አንድነት ከመጡ በኋላ በጋራ ተስማምተው የሚያደርጉት የእገሌ ወእገሌ የማይባል ተጠያቂነትም ቢኖር በጋራ ተመስጋኝነትም በጋራ የሚሆንበት ሥርዓት ስለሚፈጠር ይህ እጅግ የሚናፈቅ መንፈሳዊ ተግባር መቼ ሆኖ ዐይተነው የሚያሰኝ ምግባረ ሰናይ ነው።
አምሀ
ወይም መባዕ ተቀባይነት የሚኖረው አስቀድሞ የተቀየመ ወይም ያዘነ ወይም የተበደለ ሰው ካለ እርሱን ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ እንደሆነ ጌታችን በማያሻማ ሁኔታ በወንጌል ተናግሮታል። “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። “ እንዲል። ማቴ ፭፥፳፫−፳፬። ይኽ የጌታ ቃል ሁል ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ድምጽ እንደሆነ ይኖራል መኖርም አለበት። መሥዋዕት የሚያርገው ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርሰው ቅድሚያ የሚሰጠው ቅድሚያ ሲሠራ ብቻ ነው። መለያየት መከፋፋት እያለ አላየሁም አልሰማሁም ብሎ በራስ መንገድ እና በተጽእኖ ሥር በመውደቅ ምክንያት ገለል ብሎ መሄድ ከጌታ መንገድ ማፈንገጥ ለመሆኑ ሌላ ምስክር ማምጣት አያስፈልግም።
ቤተ
ክርስቲያን ከተቀበለቻቸው ሓላፊነቶች አንደኛው እና ቀዳሚው ፍቅርን መስበክ ነው። ፍቅር ደግሞ በቃል ብቻ የሚነገር ወይም የሚሰበክ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽ የሚጠይቅ በሃይማኖት ለመኖር ዋነኛው ምልክት መሆኑ በመጽሐፍ ታውጇል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ ።” ማቴ ፲፫፥፴፭። የክርስቶስ ነን ለማለት መለያ መታወቂያችን ፍቅር ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ቃል የተነገረ ነውና ልንሸሸው አይገባም። እስከዛሬ የቆየንበትን እየኮነንን የሚመጣው ዘመን ላይ የጠላነውን ላለመድገም መከፈል ያለበትነ መሥዋዕትነት ልንከፍል ይገባል። አበው ሊቃነ ጳጳሳት በአማን የክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆናቸው የሚታወቀው ታሪክ እና ጊዜ ያበረከቱትን ይኽን መልካም አጋጣሚ ሲጠቀሙበት ብቻ ነው። ስለሆነም መቅደም ላለበት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። አካሄዱ ሀሳባዊ ሳይሆን መጽሐፋዊ ነውና። ፍቅር የሕግ ፍጻሜ በመኾኑ። ሮሜ
፲፫፥፲።
“ትንቢትም
ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ ።… እንዲህም ከሆነ ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” ፩ቆሮ ፲፫፥፪፣፲፫። ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ላይ ታንጻ በፍቅር ተገንብታ በፍቅር የተጠናቀቀች ፍቅርን የተጎናጸፈች ሁለመናዋ ፍቅር የሆነች የክርስቶስ አካል ናት። ከሁሉ ምግባረ ሃይማኖት ይልቅ ከፍተኛውን ስፍራ የያዘውን ተግባር ችላ ብሎ ቤተ ክርስቲያንን እመራለሁ አስተዳድራለሁ ብሎ ማሰብ እመቀመቅ ወርዶ የተራራው ጫፍ ላይ ነኝ እንደማለት ይሆናል።
ቅዱስ
ጴጥሮስም ከሥራዎች ሁሉ ፍቅርን ማስቀደም እንደሚገባ ከጌታው የተማረውን አብነት ይዞ በመልእክቱ እንዲህ ጽፎልናል። “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።” እንዲል። ፩ጴጥ ፬፥፰። ሐዋርያው ከሁሉ በፊት በማለት ያስቀመጠው ሌላው ሁሉ መንፈሳዊ ሥራ እና አገልግሎት ፍቅርን ወደ ስፍራዋ ከመመለስ በኋላ የሚከተል መሆኑን ያለጥርጥር ያመለክተናል። የፓትርያርክ ሹመትም እንዲሁ ከፍቅር በኋላ መደረግ ያለበት ምንም አጣዳፊ ችግር የማያስከትል መሆኑን መላው የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ልጆች ያውቃሉ እና ለዚሁ ለምንመራበት የእግዚአብሔር ቃል በመገዛት እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጅነታችንን ልናስመሰክር ያስፈልጋል። “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” ፩ዮሐ ፬፥፰።
ስለሆነም
በተጥባበ ሰብእ ብቻ እንነጉዳለን ብሎ የእግዚአብሔርን ቃል በመተው በሌላ አካሄድ ለመሄድ ፈጽሞ መታሰብ የለበትም። ልዩነቱ ሁሉ በፍቅር ከከሰመ በኋላ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ መምጣት ተገቢ ይሆናል። ከዚህ ሀሳብ ባፈነገጠ መንገድ ለመሄድ ማሰብ አንድም ሥጋዊ አሠራር እና ጸረ ክርስትና ነው አንድም ለመሾም ከመሻኮት የሚመጣ ክፉ አመል ነው። ከመንገድ የወጣውን አስተሳሰብ በመደገፍ ላይና ታች የሚወርዱ አካላት ካሉም አጃቸውን ሰብስበው የእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ረዥሙ እጃቸው ገብቶ እንዳይፈተፍት ሊታቀቡ ያስፈልጋል ካልኾነ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቃወም የሚያስከትለውን መዘንጋት ይኾናል። ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያን ነውና ብቻዋን እግዚአብሔርን ይዛ የማትወጣው ዳገት የማትወርደው ቁልቁለት ስለሌለ የማንንም ችሮታ እና በጎ አሳቢነት እንዲሁም እገዛ በዚህ ጉዳይ አትጠይቅም አትፈልግምም።
እርቀ
ሰላሙ ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ለዓለምም ይዞት የሚመጣው በረከት ብዙ ነውና አስቀድመን የእርሱን የቤት ሥራ ለመሥራት እንትጋ። አስቀደማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም እሹ የቀረው ሁሉ ይጨመርላችኋል ተብለናልና በምድር ያለችው የእግዚአብሔር መንግሥት አንድነቷ እንዲጸና እንሻ እግዚአብሔር ደግሞ የሚጨምረውን ይጨምራል። ማቴ ፮፣፴፫።
፪.
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጉዳይ እልባት መስጠት
ይህ
ጉዳይ መታየት ያለበት ለቤተ ክርሰቲያን ለቤተ ክርሰቲያን ከማድላት ብቻ እንጂ በሌሎች ጉዳዮች በመታጠር መሆን የለበትም። ላለመስማማት ሺህ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሁሉ ለመሰማማትም ሺህ ምክንያቶች አሉ ። ምክንያቶች ሁሉ ግን ውኃ ሊያነሡ የሚችሉት የሚታዩባቸው መነጽሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያሳዩ ከሆነ ብቻ ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በተመለከተ ሊኖሩ የሚገባቸውን አማራጮች በዝርዝር ማየት የአበው ሊቃነ ጳጳሳት የመላው ካህናትና ምእመናን ወቅታዊ የቤት ሥራ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔርን ተማጽነን የሚመጣውን በጎ ነገር እንጠባበቃለን።
እርሳቸውን
በተመለከተ ሊታዩ ከሚገባቸው አማራጮች የሚከተሉት ትኩረት ተደርጎባቸው የሚነሡና ሊሠራባቸው የሚገባቸው
ናቸው።
ሀ.
ፓትርያርክነቱን ለአቡነ መርቆሬዎስ መስጠት
ይህንን
ሀሳብ የሚደግፉ አባቶች እና ምእመናን እንዳሉ የታወቀ ነገር ነው። በተቃራኒውም የሚቃወሙም እንዲሁ አሉ። ጉዳዩ በደጋፊ እና በነቃፊ መካከል የሚደረግ ሽኩቻም አይደለም። ተልእኳችን ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና እግዚአብሔር የወደደውን እንዲያደርግ በአንቃዕዶ ኅሊና በተመስጦ ልቡና ወደ እርሱ ማመልከቱ ላይ ትኩረት መደረጉ የበለጠ ይበጃል። ምንም እንኳ ቅድሚያ የምንሰጠው ለፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆንም እርሱ የሚሆነውን እስኪያሳየን ድረስ ሁላችንም በያለንበት መጨነቃችን አይቀርም። ጉዳዩ የሚታየው ለቤተ ክርሰቲያን ከሚያመጣው ጥቅም አንፃር ነውና እርሳቸው ወደ ቀደመ ሥልጣናቸው ቢመለሱ የሚል ሲኾን የዚህም ሐሳብ አመክንዮ፡-
አንደኛው
፦ ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተከሰተው አሳዛኝ ክስተት የተፈጠረው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ ጥፋቱ የጋራ ነውና። አንዱ ሞጋች ሌላው ተሞጋች ሊኾን አይገባውም። ጉዳዩ የጋራ ስህተት የወለደው ነውና ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለን ሊታለፍ ይገባዋል፤ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ከመስጠት አንጻር ይህንን ካላደረግን በየአቅጣጫው በሚፈጠረው መሳሳብ ወደ ባሰ ችግር ሊያመራና የቤተ ክርስቲያን ነቀርሳ ኾኖ ሊቀጥል ይችላልና የሚለው ሲሆን፤
ሁለተኛው፦
እስከ አሁን ድረስ በተደረገው የእርቀ ሰላም ጥረት ትልቁ እንቅፋት ኾኖ ቆየው የሁለቱ ቅዱሳን አባቶች ለአንድ መንበር የተሠየሙ ኾነው መቆየታቸው ሲኾን እግዚአብሔር ባወቀ የተፈጠረውን ድንገተኛ አጋጣሚ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ከመጠቀም አንጻር ብቻ አጋጣሚው አሸናፊነትና ተሸናፊነት ጽድቅና ኀጢአት ተደርጎ ሳይታይና ሳይቆጠር ይቅር ለእግዚአብሔር ፍርዱን ለእግዚአብሔር እንተወው ብሎ መቋጨት ይቻላል የሚል ነው፡፡
ለ.
ፓትርያርክ ሆነው ግን ከአስተዳደር በአፍአ እንዲሆኑ ማድረግ
ብፁዕ
ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የፓትርያርክነቱን ክብሩን ከነሙሉ መንፈሳዊ ማዕረጉ ይዘው ነገር ግን ከአስተዳደራዊ ጉዳይ ርቀው በሕይወት እስካሉ ድረስ በመረጡት ቦታ በቡራኬ እና በጸሎት ተወስነው፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለአንድ ፓትርያርክ በሚገባ ክብር እንዲቀመጡ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቅዱስነታቸውን ጨምሮ ኹሉም አባት የመከረበትና የተስማማበት እንደራሴ እንዲሰይም ማድረግ የሚለው ሁለተኛው አማራጭ ነው። ይኽኛው አማራጭ ፓትርያርኩ ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሌላ ፓትርያርክ መሾምን አይቀበልም።
በአንድ
ቤተ ክርስቲያን የሁለት ፓትርያርክ መኖር ምን እንዳመጣ ይታወቃልና ያለፈውን ስህተት ከመድገም መቆጠብ ያስፈልጋል ይላል። እንደራሴው ፬ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ በሕይወት እስከ
አሉ ድረስ ቅዱስ ሲኖዶሱን በሊቀመንበርነት እየመራ አስተዳደሩን እያከናወነ እንዲቀጥል ማድረግ የሚል ሲኾን የዚህም ሐሳብ አመክንዮ፡-
አንደኛው
፦ ያኔ እርሳቸው እንዲሰደዱ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው መንግሥት አሁንም በሥልጣን ላይ ያለው እርሱ ነው። በአስፈላጊ እና በተገቢ ሁኔታዎች ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር የመሥራት ሓላፊነት አንዳለባት ይታወቃል። በእነዚህ ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያበቃ ከቂም በቀል እና ከኩርፊያ ነፃ የመሆናቸው ነገር እስከ የት ድረስ ይሆናል? የሚል ሲኾን፣
ሁለተኛው
፦ እስከ አሁን ድረስ ለ፳ ዓመታት ሁለቱ ፓትርያርኮች ለአንድ መንበር የተሠየሙ ኾነው መቆየታቸውን ተከትሎ የነበረው እሰጥ አገባ፣ አላስፈላጊ ውዝግብና ትንቅንቅ ጥሎት ያለፈው የልዩነት መንፈስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንዳያገኝ እና ቁሰሉ እንዲሽር ለወደፊቱም የቤተ ክርስቲያን ጉዞ እንቅፋት ሆኖ እንዳይቀር የሆነ ቦታ ላይ መሳሳቡ መቆም ይኖርበታል። ተሰዳጅና አሳደጅ በሚል መፈራረጅ ማክተም ይገባዋል። ለዚህም ይኽኛው
አማራጭ የነበሩትን ልዩነቶች ሁሉ ማንም ወደ ማንም ሳይጠቁም ተከስቶ የነበረውን ችግር የጋራ በማድረግ እልባት ለመስጠት አቡነ መርቆሬዎስ ከአስተዳደር በአፍአ ሆነው ሲኖዶስ በእንደራሴ ቢመራ የተመቸ ነው ይላል።
ሦስተኛው፦
በአሁኑ ወቅት ቅዱስነታቸው ካለባቸው የጤንነት ችግር አንጻር ሙሉ በሙሉ የቤተ ክርስቲያንን ሓላፊነት ለመሸከም የፍላጎት ሳይሆን የአቅም እጥረት እንዳለባቸው ይታወቃል። እዚያው ባሉበት ሀገርም እንደሚታየው አጠቃላይ
የጤና እና የአመራር ሁኔታ ውስብስብ የሆነውን ወቅታዊ የቤተክርስቲያን አስተዳደር የመምራት ሓላፊነት በአግባቡ ሊወጡት ይችላሉ ማለት እጅግ በጣም አዳጋች ይሆናል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸሎት ተጸምደው መኖርን ከመምረጣቸው አንጻር በዚሁ መቀጠላቸው ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም ወደር የለሽ ይሆናል የሚል ነው፡፡
ሐ.
ዐዲስ ፓትርያርክ መምረጥ
ይኽኛው
አማራጭ ጥንቱን አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክነቱን የተዉት ተጽዕኖ ቢኖር እንኳ የመቋቋም ግዴታቸውን በመወጣት ፋንታ ትተው በመሄዳቸው ምክንያት የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ፈቅደው እና ፈልገው ነው ይላል። ምክንያቱም በቀደሙት አበው ዘንድ ተጽዕኖ በመጣ ጊዜ ከቅዱስ አትናቴዎስ ጀምሮ በሌሎችም ላይ ምን እንደተደረገ እነርሱም ምን እንዳደረጉ ይታወቃልና። እነ ቅዱስ አትናቴዎስ በጽናት የመጣባቸውን ተጽእኖ በመቋቋም የእግዚአብሔርን አደራ ጠብቀው በፈቃደ እግዚአብሔር ተመልሰው ወደ መንበራቸው እንዲመጡ ሆነዋል። ቀድሞውንም በቃልም በተግባርም አልተዉትም ነበርና። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም አሞኛል ከማለት የሚመጣባቸውን ጫና ከመጋዝ ጀምሮ እሰከ መሰደድ አይበለውና እስከሞትም ቢሆን በመጋፈጥ የአባቶቻቸው ወራሽ መሆናቸውን ማስመስከር ይጠበቅባቸው ነበር። በሕመም ምክንያት መምራት አልችልም ብለው በቃል መናገራቸው በፈቃዳቸው ሥልጣኑን እንደተዉት ያስተረጉማልና።
ይሁን
እንጂ እንደ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትነታቸው የሚጠበቀውን ባለማድረጋቸው እና ሌላ ሲኖዶስ በማዋቀር ቤተ ክርስቲያንን የሚከፍል አሠራር በመፍጠራቸው ሌላ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም የሚል ሲኾን የዚህም ሐሳብ አመክንዮ፡-
አንደኛው፦
ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው በራሳቸው አንደበት በሕመም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱን መምራት እንደማይችሉ ተናግረዋልና እርሱን መሠረት አድርጎ በጊዜው የነበረው ሲኖዶስ ጉዳዩን ተቀብሎ ካስተናገደው በኋላ ይህንን ጥያቄ ማንሣት ማለትም የአቡነ መርቆሬዎስን ፓትርያርክነት መመለስ ተገቢ ነውን? ብሎ የሚሞግት ሲሆን፣
ሁለተኛው፦
እዚህ አገር ቤት ሳሉ መምራት አልቻልሁም ብለው የነበሩት አባት በኬንያ በኩል ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ እርሳቸው ሕጋዊ የሚሉትን ሲኖዶስ በማቋቋም ትክክለኛው ፓትርያርክ እኔ ነኝ የሚል አቋም ይዘዋል። እንደ ሃይማኖት አባት እርሳቸው እንደሚሉት ሥልጣናቸውን የተዉት በተጽዕኖ ቢሆን እንኳ ሰማዕትነቱን እዚሁ መቀበል ሲገባቸው ገለል ካሉ በኋላ ልጆቻቸውንም በትነው ከተሰደዱ ወዲያ እዚህ ሌላ ፓትርያርክ እንደተመረጠ እያወቁ ‘ሕጋዊው ፓትርያርክ እኔ ነኝ ማለታቸው የቱን ያኽል ቅቡል ያደርጋቸዋል?’ የሚል የመከራከሪያ ነጥብ በማከል ሌላ ሦስተኛ ጥያቄ ይጨምራል፣
ሦስተኛው፦
በመጀመሪያ በማንኛውም ምክንያት ይሁን መንበሩን ትቻለሁ ማለታቸው አንድ ስህተት ነው። ቀጥሎ ደግሞ ከሀገር ከወጡ በኋላ ደግሞም ፓትርያርክ ከተመረጠ በኋላ ሕጋዊው ፓትሪያርክ እኔ ነኝ ማለታቸው ሌላ ስህተት ነው። አሁን እርሳቸውን ወደ ፓትርያርክነት ማምጣት ሌላ ሦስተኛ ስህተት መሥራት አይሆንምን? ደግሞስ እርሳቸው
እንደሚሉት በተጽዕኖ ከተሰደዱ ሌላ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ቢመጣ የመቋቋም አቅማቸው የቱን ያኽል ያሳምናል? አንድ ጊዜ ተፈትነው ታይተዋልና የሚለው ሲኾን፣
እርቀ
ሰላሙ ተፈጽሞ ፷፮ቱም ሊቃነ ጳጳሳት ራሳቸውን አቡነ መርቆሬዎስን ጨምሮ በጋራ በአንድ መንበር በአንድ ጉባኤ ተቀምጠው ዐዲስ ፓትርያርክ መሰየም አለባቸው በማለት ይቀጥላል። በተጨማሪም ዐዲስ ፓትርያርክ ይመረጥ ሲባል የግድ አሁን በማዕርገ ጵጵስና ካሉት አባቶች ብቻ ማለት ሳይሆን የሚዘጋጀው የምርጫ ሕግ የሚፈቅድ ወይም የማይከለክል ከሆነ ከመናንያን ገዳማውያን መካከል ፣ በቅድስና እና በንጽሕና ከሚኖሩ አበው እግዚአብሔር ባመለከተው መጠን በዕጩነት እስከማቅረብ ሊደርስ ይችላል የሚል ነው።
መ.
አቡነ መርቆሬዎስ ራሳቸውን ቢያገልሉ፤
ይኽኛው
አማራጭ ደግሞ አቡነ መርቆሬዎስ ዕድሜያቸው መግፋቱን ጤናቸው መታወኩን እንዲሁም ውዝግቡ እንዳበጣበጠ እንዳይቀጥል ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው ራሳቸውን ፓትርያርከ ከመሆን ወይም ተብሎ ከመጠራት ቢያገልሉ ሦስተኛውን አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል የሚል የሚል ሲኾን የዚህም ሐሳብ አመክንዮ፡-
አንደኛው
፦ እስከ አሁን ድረስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በጽሑፍም ይሁን በቃል በይፋ የሰጡት አባታዊ መግለጫ ወይም መልእክት ካለመኖሩም በተጨማሪ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች እርሳቸው ሥልጣኑን እንደማይፈልጉትና ሌሎች ለራሳቸው ዓላማ ብቻ በእርሳቸው ስም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው ብለው የሚሰጡትን ማብራሪያ በመጥቀስ እሳቸው በአካል ተገኝተው ቢጠየቁ ይህንኑ ሊያረጋግጡ ይችላሉ የሚለው ሲሆን፣
ሁለተኛው፦
ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ፍቅረ ሲመት የጠፋለትና እንደ አባታችን እንደ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት እኔ ይቅርብኝ ማለትንና እንኳን አጨቃጫቂ በኾነ ኹኔታ ቀርቶ ከጤናና ከዕድሜ የተነሣ በሰላማዊም መንገድ ሓላፊነትን ማስረከብ በዓለማዊውም መንገድ እየተከሰተ የሚታይ ታላቅነትና እራስን በትውልድና በታሪክ ወስጥ በወርቃማ መዝገብ አስመዝግቦ ማለፍን የሚያጎናጽፍ በመኾኑ ባያስቡት እንኳን ልናግባባቸው ይገባል የሚል ነው፡፡
፫.የምርጫ ሕግ
ከላይ
የተገለጸው ችግር የሚፈታበት መንገድ የሚመራውን የመፍትሔ ሐሳብ በማጠቃለያ ላይ የምንመለስበትና የሚቋጭ ኾኖ የምርጫ ሕግን ጉዳይ ስንመለከት ትንታኔ ከተሰጠበት ሐሳብ ጋር ካለው ቁርኝትና ተያያዥነት በመነሣት አንዱ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነውና በዚሁ ጋር
አያይዘን የምንመለከተው ነውና እንደሚከተለው ይታያል፡፡
ምንም
እንኳ በቂ ነው ባይባልም የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ የለም ማለት አይቻልም። በቂ ካልሆነ ደግሞ በቂ እንዲሆን ማድረግ የማይቻልበት ምንም ዓይነት ስጋት የለም። ይሁን እንጂ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ድኅረ ምርጫ ድረስ ያለውን ዝርዝር ሁኔታ የሚያመለክት ሕግ መውጣቱ ሊመጡ ከሚችሉት ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎች ለመዳን የተመቸ አሠራር ይሆናል።
የአስመራጭ
ጉባኤ ወይም ኮሚቴ እንዴት ይዋቀራል? በምን መመሪያ ይሠራል? በምርጫው ውስጥ መሳተፍ ያለባቸው (ከመራጭነት እስከ ተመራጭነት) እነማን ናቸው ? እጩዎች በምን መመዘኛ ይቀርባሉ ? ጥቆማው እንዴት ይሰጣል? የማወዳደሪያው ሥርዓት ምንድን ነው ? ከእጩዎች መካከል የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች እንዴት ይለያሉ ? የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ከተለዩ በኋላ ምን ያኽል ጊዜ ያስፈልጋል በምንስ መንገድ ፓትርያርኩ ይመረጣል? የአኀት አብያተ ክርስቲያናት፣ የገዳማት፣ የሊቃውንት፣ የካህናት፣ የምእመናን ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና የማኅበራት ተሳትፎ እስከ ምን ድረስ ነው? የሚሉትን የማይቀሩ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚመልስ ደረጃውን የጠበቀ የምርጫ ሕግ እንዲወጣ ይጠበቃል።
በተለያየ
ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከአኀት አብያተክርስቲያናት ጋር በምታደርገው የትብብር ግንኙነት (ecumenical
relation) የተፈራረመቻቸው
ስምምነቶች በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ድርሻ እንደሚኖራቸው ያመለክታል እና የእነርሱ ጉዳይ እንዲሁም የተሳትፎ ሁኔታቸው መታየት ካለባቸው አካላት ውሰጥ ተካትተዋል። የምርጫ አስፈጻሚውን ከማዋቀር በፊት የሚመራበት ደንብ መዘጋጀቱ ቅድሚያ የሚሰጠው የቤት ሥራ መሆኑ አያጠያይቅም። ገለልተኛነቱ የሚረጋገጥበት ሥርዓትም መዘርጋት ይኖርበታል። ጣልቃ ሊገባ የሚችል አካልን እንዴት መከላከል እንደሚቻልም መንገድ ማበጀት ያስፈልጋል። ተሰሚነቱ እና ቁጥጥሩ እስከምን ድረስ ይሆናል? ካስመረጠስ በኋላ እንዴት ይሰናበታል? የተሰየመው ፓትርያርክ እንዴት ሥራ ይጀምራል? ከመጀመሩስ በፊት ምን ይጠበቅበታል?...ወዘተ ጥያቄዎች የሚመልስ የምርጫ ሕግ ቢሠራ ብዙ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ማቃለል እና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስጠብቅ መሆኑ አያጠራጥርም።
ስለሆነም
የምርጫ ሕጉን የማዘጋጀቱ ነገር ነገ ለሚሆነው ዐቢይ ክስተት ዛሬ የመሠረት ድንጋይ እንደማኖር ይቆጠራል። ብዙ ተወራዋሪ እና ጣልቃ ገብነት የሚያጓጓቸው አካላት ቢመጡ እንኳ ይህ የምርጫ ሕግ እንደ አጥር ቅጥር ሆኖ የመከላከል አቅም ይሆናል።
ይህም
ብቻ ሳይኾን ከውስጥም ወደ ወጭ የሚንጠራሩ ከእግዚአብሔር ይልቅ በፍጡር የሚመኩና በተጥባበ ነገር የተነደፉበትን ክፉ ደዌ (ፍቅረ ሢመት) ለማሳካት የውጭ አካላትን ምልጃና ድጋፍ የሚፈልጉ ወይንም መመዘኛው ከመንፈሳዊ አሠራር ወጥቶ ለነሡ በሚመች መንገድ ዘርና ቋንቋን ጎሳና ነገድን እንደ ዋነኛ ወይም መሠረታዊ መመዘኛ ለማድረግ የሚፈልጉ አብድንት ቢነሡና ቢፈጠሩ እንደከዚህ በፊቱ ለኀጢአት የማይጋብዝ በቅዱሳት መጻሕፍት የዓለማውያን ነገሥታትን ወይንም መኳንንትን ምልጃና ርዳታ በመጠየቅ የተሾመ ኤጲስ ቆጶስ (ጳጳስ) ቢኖር ከሥልጣኑ ይሻር የሚለውን በማሰብና አበው የክርስቲያን በተለይም የኖላዊ ሐዋርያ ሀገረ ሙላዱ ትውልደ ነገዱ አይጠየቅም የሚሉትን ወርቃማ አባባል እየተፈታተነ የሚገኘው የቤተ ክህነት ነቀርሳ ደረቅ ወንዝን ተሻግሮ ማሰብ አለመቻል የሚያከትምበትን መንገድ ለመጥረግና ሥራው በአግባቡ ለመሠራቱ የመለኪያ እና የመከታተያ ሥርዓት ለመሥራትም ይጠቅማልና ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ከመተረቱ በፊት ቀድሞ አስቦ መሥራት እጅግ የተመረጠ አካሄድ ነው ብለን እናምናለን ።
ማጠቃለያ
የሺሕ
ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ ነውና እነዚህ ከላይ ያነሣናቸውን የእርቀ ሰላም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና የምርጫ ሕግ አስመልክተን የማጠቃለያ ነጥቦችን እንደ ቅደም ተከተላቸው እናያቸዋለን፡፡ የፓትርያርክ ምርጫ ኖረም አልኖረም እርቀ ሰላሙ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ወሣኝ እና አስፈላጊ በመሆኑ የይዋል የይደር ቀጠሮ ሊቀጠርለት የማይችል ወይም የማይገባ አጀንዳ ነው። ይልቁንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በፓትርያርክነት የሚመራ ማን ይሁን ወይም ማን ይሆን የሚል ጥያቄ በአእምሯችን በሚጉላላበት ወይም በሚመላለስበት በዚህ ልዩ አጋጣሚ ችላ ሊባል የማይችል ነውና ቅድመ ሲመተ ፓትርያርክ ሊታዩ እና እልባት
ሊሰጣቸው ከሚገባቸው መሠረታዊ ኩነታት አንዱ እና ተጠቃሹ ያደርገዋል።
እንደ
አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ብጹዓን አበው ልዩነታቸውን ፈትተው ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን በጋራ ተቀምጠው ሲመክሩ እና ፓትርያርካቸውን ሲሰይሙ ማየት እግዚአብሔር የወደደውን እነርሱም መውደዳቸውን ሲያረጋግጡ መመልከት እጅግ የሚናፍቅ መንክር የሚያስብል ምግባረ ሃይማኖት ነው። ጉጉታችን ይህ ሲሆን በዐይናችን ማየት በጆሯችን መስማት ነውና ይደረግለን እያልን እያመለከትን እንጠባበቃለን። ሲሆን ዐይተን ለማሳየት ታሪኩንም ጽፈን በምሳሌነቱ አንዲጠቀስ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።
“በቍጣዬ
ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት።” ተብሎ እንደተጻፈው
መሪ መስጠቱን እግዚአብሔር ሊሰጥ ይችላል። ሆሴ ፲፫፥፲፩። ይኽም እግዚአብሔር ደስ ሳይሰኝበት ሊሆን እንደሚችል ከነቢዩ ቃል እንረዳለን። መረጋገጥ ያለበትም ዐቢይ ቁም ነገር ይህ ነው። እግዚአብሔር በጉዳዩ ውስጥ እንዲገባ ካስፈለገ ደግሞ ፍቅር እና ሰላም ተንሰራፍቶ መገኘት አለበት። ይኽ ሳይሆን ሲቀር እግዚአብሔር መዓት አለው። መዓት እና መቅሰፍት ደግሞ ያንገሸገሸን ነንና ስሙም እንዲጠራብን አንፈቅድም።
“ደግሞ
እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” ተብሎ በጌታችን እንደተነገረ በመስማማት መሰብሰብ እርሱ በመካከል እንዲገኝ ምክንያት ነውና አባቶች ተስማምተው እግዚአብሔርን ወደ ጉባኤያቸው ሊጋብዙት ግድ ይሆናል። ማቴ ፲፰፥፲፱−፳። በእርቀ ሰላም አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ይዘው በመሰብሰብ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያን መሪ እግዚአብሔር እንዲሰይም በሩን ይከፍታሉ ተብሎ ይጠበቃል። እርቀ ሰላሙ ከተፈጸመ በኋላ ቀጥሎ የሚነሣው ጉዳይ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጉዳይ ነውና በቀጥታ ወደዚያው ማጠቃለያ እናመራለን።
የአቡነ
መርቆሬዎስ ዕጣ ፋንታ ምን ይሁን የሚለው ወቅታዊ ጥያቄ እርቀ ሰላሙ ከተከናወነ በኋላ ደረጃውን ጠብቆ ወደ አንድ በመጡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና በሌላው ሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ መታየት ያለበት አጀንዳ መሆኑ አያጠያይቅም። ጉዳዩ ቀላል ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልምና በረጋ እና በሰከነ መንፈስ በንጽሐ ልቡና ከሚቀርብ ጸሎት ጋር መያዝ ያለበት ወሣኝ አጀንዳችን ነው። ልንሸሸው የማንችል የእኛው የራሳችን፥ በሌላ በማንም ሊሠራ የማይችል አደራችን በመሆኑ ልዩ ትኩረት ከልዩ ጥንቃቄ ጭምር ልንቸረው ይጠበቅብናል።
አቡነ
መርቆሬዎስን በተመለከተ ከላይ የተዘረዘሩት አራት የተለያዩ ሐሳቦች እንዳሉ እና ሁሉም በየራሳቸው አመክንዮ የታጀቡ መሆናቸውን ዐይተናል። እነዚህን የተለያዩ ሀሳቦች መዝኖ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን ይዞ መውጣት የውዴታ ግዴታ ነው። ሁሉንም አባቶች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ባማከለ ሁኔታ መልስ ለመስጠት እጅግ ከባድ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ግን የትኛውንም ያኽል አስቸጋሪነት ቢኖረውም ሁሉም በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ሊደረጉ ካለመቻላቸው አንፃር የበለጠ ጠቃሚ እና አስፈላጊ የሆነውን በጠባብ ልዩነትም ቢሆን መምረጥ ሌላ ምትክ የማይገኝለት ከባድ ግን አስገዳጅ ጉዳይ ይሆናል።
ከቀረቡት
አማራጮች አንዱን መምረጥ ሲባል ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም እና ፍላጎት እንጂ ማንንም ለመጥቀም ማንንም ለመጉዳት መሆን የለበትም። ስለሆነም ሚዛናችን ለእናት ቤተ ክርስቲያን የተሻለ የሚጠቅመውን የሚመዝነ እንዲሆን ይጠበቃል። ከአማራጭ ተራ መገባቱ ተፈልጎ ሳይሆን በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ ያስገደደው በመሆኑ አይቀርም። ከፀሐይ ወዲያ ሌላ ፀሐይ የማየት ያኽል አስቸጋሪ መሆኑን ሳንክድ የተሻሉ አማራጮችን ለማየትና ወደ እነርሱ ለማጋደል ያሉትንና ሊኖሩ የሚችሉትን አማራጮች ኹሉ ማየቱና መዳሰሱ ተመርጧል።
ከላይ
በፊደል ተራ “መ” ላይ የቀረበው “አቡነ መርቆሬዎስ ራሳቸውን ቢያገልሉ” የሚለው አማራጭ ከራሳቸው የሚመነጭ ራስን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ የመስጠትን ያኽል ዕንቈ የሆነ በእግዚአብሔር ኃይል በመንፈሳዊ ጥብዓት ብቻ የሚቻል የክርስቶስን መስቀል መሸከምን የሚያመለክት የቅዱሳን አበውን ፍኖት የመከተል ምልክት ነው።
በአማራጭ
“ሀ” የቀረበው ሀሳብ ከእርሱ ወደታች በአማራጭ “ለ” እና “ሐ” በእርሳቸው ላይ የተነሡትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም የሚያጥረው እንደሆነ መገመት ከባድ አይሆንም። ምንም እንኳ ለተፈጠረው ክፍተት አቡነ መርቆሬዎስ ብቸኛው ተጠያቂ ናቸው ማለት ባይቻልም የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚችሉ ግን አይካድም። መሪዎች ከሌሎች የተለዩ ፍጥረታት ባይሆኑም ቅሉ እንዲወጡት የሚገባቸው ፈተናና እና በተቀመጡበት ቦታ የሚኖራቸው የሓላፊነት ድርሻ ላቅ ይላል። አንድ ኖላዊ አባት ከበጎቹ በፊት ራሱን አሳልፎ የማቅረብ መንፈሳዊ ሓላፊነት እንዳለበት ወንጌላችን ያዝዛል። ከዚህ አንፃር ምንም ከባድ ቢሆን ከእርሳቸው የሚጠበቀው ከፍ ይላል። በዚህ ምክንያት ለተፈጠረው ክፍተት ሊወስዱት የሚገባው ሓላፊነት ከሌሎቹ አበው ስህተት ከፍ ብሎ ይታያል። ስለሆነም በአማራጭ “ሀ” የቀረበውን ለመቀበል እና ለመፈጸም እጅጉን ይከብዳል። መክበድ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ከፀሐይ ወዲያ ሌላ ፀሐይ የማየት ያኽል ፍጹም ርቆ የቆመ አማራጭ በመሆኑ ከሁሉም አማራጮች የመጨረሻውን ደረጃ ይይዛል።
በመኾኑም
ከላይ በአማራጭ “ለ” እና “ሐ” በእርሳቸው ላይ የተነሡትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ከማዳገቱ አንጻር በአማራጭ “መ” ላይ የተገለጸው የበላይነቱን ይይዛል። ለቤተ ክርስቲያን ሌላ አስቸጋሪ እና ውስብስብ የውጣ ውረድ ዘመን መጋበዝ የሚቆመው ቢቻል ሁሉም ካልተቻለ ደግሞ አንደኛው ወገን በሚከፍለው መሥዋዕትነት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ የግድ ነው። ፍቅር እኔን ብቻ ይድላኝ አይልም የሚለው ሐዋርያዊ መልእከት ቦታ የሚያገኘው እንደዚህ ባሉ ፈታኝ ጉዳዮች እንደሆነ እናምናለን ። ክርስትና ነውና ለሚያምን ሁሉ ይቻላል። ማር ፱፥፳፫።
የሚጎዳ
ካለም እንኳ ተጎድቶ የቤተ ክርስቲያንን ቁስል ከማጥገግ በላይ ምን የተሻለ መንፈሳዊነት ሊኖር ይችላል? እየታመሙ ማዳን እየቀለጡ ማብራት የክርሰትና ወጉ ነው። በእርግጥ በዚህ አማራጭ ላይ የሚነሣው ጥያቄ እርሳቸው ያለምንም ተጽእኖ ፣ በራሳቸው የመወሠን አቅማቸው ምን ያኽል ነው? የሚለው ሲሆን ግን ቅዱስነታቸው
ይህንን ተሻግረው ኹሉን ትተን ተከተልንህ የሚለውን የሐዋርያት ቃል በተግባር ቢፈጽሙት ኹሉን መተዋቸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን ለኾነ ለማንም የማይጎረብጥ የማይሻክር ሐሳብ ከመኾኑም በላይ እርሳቸው ይህንን ቢወስኑ ከእግዚአብሔር በታች ታሪካቸው ያማረ ፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ሰላምና አንድነት ዐቢይ አስተወጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል። የማንንም ተጽዕኖ በመቋቋም በራሳቸው ይህንን ጠንካራ ውሳኔ ቢወስኑ ቤተ ክርስቲያንን እንደታደጓት ይቆጠራል የመጀመሪያውንም ድርሻ ይይዛል ደግሞም ሊቀ ሰማእታት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተናገረው አመዱን ሰው የሚያደርግ አምላክ ያለን ነንና ትምክህታችን ወደር አይገኝለትም።
ቤተ
ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆቿ ብቅ የሚሉት እንደዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሙ ጊዜ ነው። አበው “ዝናብ ከሌለ ሁሉ ቤት እንግዳ ከሌለ ሁሉ ሴት” እንዲሉ ፈታኝ ሲመጣ የማን ማንነት ይታወቃል። ለአቡነ መርቆሬዎስም የቀረበላቸው ወቅታዊ ፈተና ይህ ነው። ታሪክ ሠርተው ታሪክ ሆነው በወርቅ ቀለም ተጽፈው የሚኖሩት እግዚአብሔርም ፍጻሜያቸውን የሚያሰምረው በዚህ መንገድ ቢሄዱ ነው የሚል የቅንነት ሀሳብ ያለበት ነውና ሁሉን በፈታኝ ወቅት የሚያጸና ልዑለ ባሕርዪ እግዚአብሔር ከጎናቸው እንዲቆም እንጸልይ።
እርሳቸው
ይህንን አማራጭ “መ” ላይ የተቀመጠውን የሚፈጽሙ ከሆነ ተከትሎ የሚመጣው አማራጭ ያለ ጥርጥር አማራጭ “ሐ” ይሆናል። የምርጫ ሕግ ከተሠራ በኋላ ዐዲስ ፓትርያርክ ወደ መምረጥ ይገባል ማለት ይሆናል። ይህም ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አስፈላጊ ሂደት ነውና መቻኮል ሳያስፈልግ ለእግዚአብሔር ጊዜ በመስጠት መከወን ይኖርበታል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም ወገን ገለል ብላ ማንም ጣልቃ ሳይገባባት የምትፈጽመው ሊሆን ይገባልና አማራጩ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ መታሰብ ያለበት ይሆናል። የምርጫ ሕጉ በሚገባ ከሀሜት በጸዳ ሁኔታ የሚቀረጽበት ይሆናልና ልዩ ትኩረትን ይሻል።
ምድራዊ
እና የለየለት ሥጋዊ አሠራርን ለፓትርያርክነት የምርጫ መስፈርት አድርጎ አሾልኮ ለማስገባት የሚራወጡ አካላት ይጠፋሉ ተብሎ አይታሰብም። የጨዋታ ሜዳውን የመለየት ችግር ካልገጠመን በቀር ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ባለው ዓለም ተጉዛም አታውቅም እንድትጓዝም አልተፈቀደላትም። የሃይማኖት ሰው ቋንቋህ ምንድን ነው ሀገርህ የት ነው ተብሎ አይጠየቅም። የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ መሆን በቤተ ክርስቲያን የሚያስገኘው ልዩ ጥቅም ጉዳትም ኖሮም አያውቅም ሊኖርም አይገባውም። ይኽኛው አሠራር በሌላ ቦታ ሊሠራ ይችል ይሆናል፤ በቤተ ክርስቲያን ግን ቅንጣት ታክል ስፍራ የለውም። ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ሙላዱን ትውልደ ነገዱን የምትዘግበው ዜና መዋዕሉን ስትጽፍ ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ግን ለምንም ተጠቅማበት አታውቅም።
አሁንም
በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት በነበረው በአበው ትውፊት ትቀጥላለች እንጂ ማንንም ለማስደሰት ሲባል የብሔር ተዋጽኦ በሚሉት በማይመለከታት አና በማትፈልገው ጉዳይ አትዘፈቅም። የቤተክርሰቲያን ልጆች ከአንድ አብራከ መንፈስ ቅዱስ ከአንድ ማየ ዮርዳኖስ መወለዳቸውን እንጂ የሚያስቡት ሌላውን አይደለም። በዚህ አንድ ነን። የተወለድነው በቅዱሱ ልደት ከአንድ ማኅፀን ነው። በነገድ በጎሳ በዘር ያለው ልዩነት ትምህርተ ሃይማኖትን በተለያየ ቋንቋ ለማዳረስ ይረዳል። ማንነትንም ለማወቅ ያግዛል። ከዚያ አልፎ ግን በቤተ ክርስቲያን ለመሾምም ለመሻርም መስፈርት ለመሆን አቅም የለውም። ይህንን ለማስፈጸም በቅንነትም ይሁን በየዋኅነት ያለበለዚያም በተቃራኒው ካሉ ወደ ከባድ የስህተት አዘቅት ራሳቸውን ወርውረውታል እና ከገቡበት ጉድጓድ ቢወጡ ይመረጣል። አባቶችም የተለየ ጥቅም እንደማያስገኝ አውቀው ለክፉው ነገር መሣሪያ ከመሆን ይድናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ነገር ዘልቆ መግባት የራስን ታሪክ እና ስም ከማጠልሸት ያለፈ ምንም የሚያስገኘው ጥቅም እንደሌለ ሊያውቁት ይገባል። አንዱን ማጥ የምናልፈው ሌላ ማጥ ውስጥ ለመዘፈቅ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ቤተክርስቲያን የታመመችባቸው ያለፉት ዓመታት ከበቂ በላይ አስተምረውን አልፈዋልና።
አማራጭ
“መ” ሰፊ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ከሚታየው ከሚሰማው መረዳት ቢቻልም አማራጩ ይህ ብቻ ነው ማለት ደግሞ ደካማነት መኾኑንና ጥረቱም ልዩነትን አጥብቦ ወደ ተሻለ ለመድረስ ከመመኘት ባሻገር ምትረተ ፈቃድን የሚጠይቅ መኾኑ መዘንጋት የሌለበት ወሳኝ ነጥብ ነው።
ስለዚህ
ሁሉም አማራጮች ወደ ጠረጴዛ መጥተው ጉዳት እና ጥቅማቸው ተተንትኖ ምን ያኽል አመክንዮአዊ ይሆናሉ፣ ቅቡልነታቸውስ? የሚለው ታይቶ በጣም አነስተኛ ጉዳት ያለውን (the lesser
evil) መምረጥና በእርሱም ላይ መስማማት አማራጭ የሌለውና ግዴታም መኾኑን ኹሉም የግራ የቀኙ ወገን ትንሽ ትልቁ ሊቀበለው የተገባ መኾኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በመኾኑም
የመጨረሻ የመፍትሔ ሐሳብ ሊኾን የሚችለውን በሁለተኛ ደረጃም የተቀመጠውን፤ ብፁዕ ወቅዱስ
አቡነ መርቆሬዎስ የፓትርያርክነቱን ክብሩን እና ማዕርጉን ይዘው ነገር ግን ከአስተዳደራዊ ጉዳይ ርቀው በሕይወት እስካሉ
ድረስ በመረጡት ቦታ በቡራኬ እና በጸሎት ተወስነው ፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለአንድ ፓትርያርክ በሚገባ ክብር እንዲቀመጡ ማድረግ እሙን ነገሩ ወርቱዕ ይትወከፍዎ በኩሉ እንዲል ያለ ምንም ማቅማማት ማመንታት ኹሉም ሊቀበለው የተገባ ከሕልውናችን ጋር የተያያዘ ትንሣኤ ፍቅር ወሳላምን የሚያውጅ ይደልዎ ! ይደልዎ ! ይደልዎ ! ልንለው የተገባ ወርቃማ ሐሳብ ነው፡፡
እነዚህን
ዋና ዋና ጉዳዮች በእርጋታ እና በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ሲመተ ፓትርያርኩ ለተጨማሪ ክፈተት ያልተጋለጠ ፣ ከማንኛውም አካል ሊመጣ የሚችልን ጣልቃ ገብነት በመመከት እና በመቋቋም መቋጨቱ ለቤተክርስቲያናችን ትንሣኤ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል። አባቶቻችን አባቶች መሆናቸው የሚፈተንበት ዐቢይ ተጋድሎ የሚጠይቅ ተግባር ይሁን እንጂ በእነርሱ ትከሻ ላይ ብቻ ተጭኖ የሚቀር አይደለም። ገዳማውያን አበው ከአሁን ጀምሮ በተለየ ሁኔታ እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት፣ እግዚአብሔር ያመለከታቸውንም መልእክት በሚያውቁት መንገድ በማስተላለፍ ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንዳይጣስ ፣ ሌላ ስህተት እንዳይደገም በማስተማር እና በማሳወቅ ፣ ካህናት ምእመናንን በመምከር ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ያገባናል በማለት እርስ በእርስ ከመወያየት ባሻገር በተቻላቸው መጠን ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ እንዲከወን በጎ ተጽዕኖ በማሳደር በበቂ ትኩረት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በቅርበት የሚያውቋቸውን አባቶች በማነጋገር እና በተዘረጋው መዋቅራዊ አሠራር በመጠቀም ሥራ የሚሠራበት ጊዜ አሁን ነው። የሚወጣው የምርጫ ሕግም ይህንን ሱታፌ ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሚሆን ይጠበቃል።
“ለሁሉም
አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል።” ያለው የመጽሐፍ ቃል ለእኛ እንዲሆንልን እንልፋ እንጣር። ሕዝ ፴፯፥፳፬። አንድ እረኛ ካለ መንጋውም አንድ ይሆናል። ለወገን ያስደስታል ለጠላት ያስፈራል። ልጆቿ አንድ የሆኑላት ቤተ ክርስቲያን ሞገስ እና ክብሯ ይመለሳል። የውስጥ ችግሯን በራሷ ለመፍታት በመቻሏ እጅግ ያኮራል። ልጆቿ ሁሉ አንገት መድፋታቸው ይቀራል መሣለቂያ መሆናቸው ያከትማል።
የተፈጠሩትን
ክፍተቶች ለመሙላት በሚደረገው ርብርብ ከዳር ቆሞ መመልከት ምንም ዓይነት ጥቅም ለቤተክርስቲያን ይዞ አይመጣም። ብዙ ጊዜ የዳር ተመልካቾች ለመተቸት የሚፈጥኑ ናቸውና ከእነርሱ ጎራ ላለመቀላቀል ከወዲሁ እንወስን ። በቤታችን ጉዳይ ሁላችንም ባለቤቶች ነን ። ኳሱን አቀብለን እኛ ዘወር ማለት የለብንም። በጋራ እንጀምርና በጋራ እንፈጽም። ያን ጊዜ ጠላታችን የበጎ ነገር ጠላት ከይሲ ዲያብሎስ ብቻ ሆኖ ይቀራል። ለመዋጋትም ለማሸነፍም ይመቸናልና በቤታችን ጉዳይ በጋራ እንቁም እንነሣ እንሥራ ። ይህንን ለማድረግ የተለየ መዋቅር የግድ አይደለም። በያለንበት ድርሻችንን እየለየን እንቀሳቀስ ። ወደፊት በዚያ ደግ ዘመን እኛም ነበርን ብለን ለመጥቀስ የማናፍርበት ሥራ ለመሥራት እንቁረጥ። ለዚህም ሁሉን ማከናወን የሚችል ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን ።
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment