Tuesday, September 18, 2012

‹‹… ሙሴ በድንጋይ ዘመን የገነነ አንድ እረኛ በመሆኑ ቢሳሳት አይገርምም…›› የበዕውቀቱ ስዩም የዕውርነት ፍሬ


                                                                                                                               ቀሲስ  ወንድምስሻ   አየለ
የበእውቀቱ ዘለፋ
በዕውቀቱ ስዩም ደፋርና የራሱን የስነጽሑፍ ዘይቤ ለመፍጠር የሚሞክር ገጣሚና ደራሲ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፤ ብዙ የሚባሉ የወረቀትና የኤሌክትሮኒክስ ኅትመቶችን አዘጋጅቶ ያበረከተ የታወቀ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ የጻፋቸውን ግጥሞች ዋጋ ለክቶ በብልጫው መርጬዋለሁ ያለው ዓለምአቀፍ ድርጅትም በኦሎምፒክ ዋዜማ እንግሊዝ ሀገር ለንደን ወስዶት ግጥሙን አቅርቦና ሌሎችም መርሐግብሮችን አሳትፎ በቴምዝ ወንዝ አካባቢም አዝናንቶትሸኝቶታል፡፡ የሀገራችን የስነጥበብ ባለሙያዎችም ሲሄድ ተሰብስበው ሸኝተውት፣ ሲመጣም ከአቀባበል ጋር ልምዱን ተካፍለውታል፡፡ እንዲህ ነው የሀገር ልጅነት፡፡
የዛሬው መጣጥፌ የወጣቱን ታሪክ ለመተረክ ሳይሆን ከሌሎች በተለየ ደጉን ኢትዮጵያዊነት ደጋግሞ ከመተቸቱ አልፎ በፈጣሪ የተመረጡ በምእመናን የተከበሩ ቅዱሳንን በመዝለፍ እየታወቀ ሲሄድ ዝምታው ተገቢ ስላልሆነ፣ በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ላይ የከፈተውን አፍ ያዘጋውን ትችትና ምላሽ አላስተውል ብሎ ዛሬ ደግሞ ሊቀነቢያት ሙሴን መተቸት ውስጥ ስለገባ ለወደፊትም ትምህርት ቢሆነው፣ ሊከተሉት ለሚፈልጉ /እንዳሉ ስለማውቅ/ መንገዳቸውን እንዲያቀኑ ለመጠቆም፣ ምናልባት ከመከራ በፊት ከተመከረ ለራሱና ለሀገር የሚጠቅሙ መጣጥፎችን ያበረክት ይሆናል በሚል ተስፋ ነው፡፡


የማየት ፍሬ

እንግሊዝ ደርሶ ሲመጣ ያጋጠመውን ነገር ‹‹ የማየት ፍሬ›› በማለት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጳጉሜን ሁለተኛ ክፍል ጽሑፍ ሲያቀርብ ‹‹ድህነት ጠፍንጎ ይዞን ነው እንጂ አበላሉንስ እናውቅበት ነበር›› በማለት እንግሊዞች ስለሚመገቡት ጥንቸል ያገኘውን ‹‹ዕውቀት›› ሊያካፍለን ይተጋል፡፡ ይህ ባልከፋ፤ ጥንቸልን እንድንበላ በጎ ስጦታዎን አብዝቶ ቢጽፍ ለማሳመን እንደሚበቃው ስለማያምን ነባሩን ባህላችንን ሊተች ሲሞክር የባህሉን ተገቢነት የሚያየው ከመብላት ፍላጎትና ካለው የገንዘብ ድህነታችን አንጻር ብቻ ሆነ እንጂ፤ ሳይተች ለማሳመን ያልሞከረው በሀሳብ ጥራት ማሸነፍ ሳይሆን በማሸማቀቅ ተቀባይነትን ማግኘት የዘመኑ ‹‹ምሁራዊ›› ‹‹ፖለቲካዊ›› አማራጭ ተደርጎ በመወሰዱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከወታደር ቤተሰብ የተወለደ መሐንዲስ ጓደኛዬ አንድ ወቅት ስለዚህ አመጋገብ ሲያስረዳኝ እኔ ተጸይፌ እንዳልጨነቅ ያደርገው የነበረውን ጥንቃቄ ሳይለውጥ በውትድርና ሕይወት አባቱ ያጋጠማቸውንና ሌላውም ቢመገብ ይጠቅማል ብሎ የሚመክረውን ከራሱ ተሞክሮ ጋር እያጣቀሰ እንዴት ሲነግረኝ እንደነበረ ሳስታውስ ከበዕውቀቱ ይልቅ ምን ያህል ጨዋ መሆኑን አደነቅሁኝ፡፡

 መቼም ምንም የሚስተካከል ነገር የለንም ባልልም ‹‹ባህል›› ተብሎ ግን የተያዘን ነገር መተቸት ስሕተት ስለሆነ መንግሥታዊና መያድ ተቋማት እን£ ‹‹ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች›› ይሏቸዋል እንጂ ‹‹ጎጂ ባህል›› ማለትን ትተዋል፤ መሠረታዊ የነገረ ስያሜ /ተርሚኖሎጂ/ ስህተት ስላለበት ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሃይማኖታዊ ቀኖናዎችን ለመተቸት መድፈር ‹‹የወረቀት ላይ ጀግና›› ከመሆን ካለፈ ‹‹የእርጎ ዝንብ››ነት ነው፡፡

 የዚህ መጣጥፍ ዓላማ ‹‹ድንጋይ ዘመኑ›› ሙሴና ‹‹ICT›› ዘመኑ በዕውቀቱ ማን እንዳየ ወይም ማን እንደታወረ መዳሰስ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አዲስ አድማሶች ከወራት በፊት በብዕር ስም የላክሁላቸውን ከበዕውቀቱ የተሸለ ወቅታዊ ጽሑፍ ስላላወጡልኝ ይህንንም ያወጡልኛል ብዬ ስለማልጠብቅ ነው በዚች ማኅበራዊ ማዕድ ያቀረብኩት፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ በመጨረሻ አካባቢ እትሟ እንዳለችው፣ ጋዜጠኛው ወንድሜም በሙያዊ ትንታኔው እንዳረጋገጠልኝ ‹‹የራሱ ዓላማ/ዝንባሌ የሌለው መገናኛ ብዙኃን ስለሌለ›› ለምን ነጻ ሆና የበዕውቀቱን ዝርክርክ ጽሑፍ እያስተናገደች የእኔን የተለፋበት ጽሑፍ አስቀረች አልልም፤ ስህተቱ የእኔ ሳይሆን አይቀርምና፤ ወደ ሐተታዬ፡፡

ሕገ ሙሴ

ከሙሴ ሕግ በፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ የሥጋ አመጋገብ አማራጮች እንደነበሩ በዕውቀቱ ማስረጃ ያደረጋቸው ‹‹የሙሴ ድምጽ በማይደርስበት ቦታ ተሸሽገው የኖሩ እንደ ነገደ ወይጦ ያሉ ጥንታዊ ሕዝቦች…››  በማለት ነው፡፡ የ፫ኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ተማሪ እያለ ፈጣሪውን የካደው በዕውቀቱ ቅዱሳንን ቢሳደብ፣ ሕገ ሙሴን ቢነቅፍ ላይገርም ይችላል፡፡ ነገር ግን ያመነበትን ሳይንሳዊ ሕግ ተከትሎ ታሪክን መተንተን ግን ግዴታ መሆኑን መዘንጋት ‹‹የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ፤ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ›› እንደሚባለው የሆነበት ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የኦሪቱን ባህል ይዘው የቀሩ እንዳሉ ማስረጃ ያለ ሲሆን ከኦሪት በፊት ሌላ የአመጋገብ ባህል የነበራቸውና በዚያው አመጋገብ የሚገኙ እርሱ እንዳለው  ዓይነት ብሔር የለም፤ ለዚህን ያህል ዘመን የሙሴ ሕግ የአደባባይ፣ የእነሱ ኑሮ ደግሞ የሽሽግ መሆን አያስፈልገውም፡፡ ጥቂቶች በልዩ ልዩ ችግር ጊዜ የተገኘውን በመብላት ራሳቸውን ካዳኑ በኃላ ለምደው የቀሩ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ በጥንቃቄ ተማምለውና ወስነው በጦርነት ጊዜ የተዉትን የምግብ ምርጫ ሥርዓት ከጦርነት በኃላ ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ለምሳሌ እጅግ ቅባት የሚበዛባት ጃርት የምትወደድ ምግባቸው የሆነችላቸው በሸካና ካፋ ውስጥ አባል ጎሳ የሆኑት መንጃዎች በዚህ ሥርዓት አፍራሽነታቸው ከሕዝቡ ተገልለው እራሳቸው እንደ ርኩስ ይቆጠራሉ፡፡ በደቡብ ክልል እንደ ብሔር ሳይሆን የብሔር አባል የሆኑ ጎሳዎች ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡ የሸካ ብሔር ግራኝ አሕመድን ለመዋጋት ሲወጣ በጦርነት ውስጥ ያገኘውን ለመብላት መገደዱ ስለማይቀር ‹‹ቁርፌ ቁጶ›› በተባለ ሥርዓት ‹‹ቁርባኔን አላረክስም›› በማለት   ላለመርከስ ቁርባኑን በምራቁ ምሳሌ ለወንዝ አደራ ሰጥቶ ተዋግቶአል፡፡ የቆረበ በመሆኑ ክርስቲያን፣ ስለርኩሰት በማሰቡ ኦሪት ዐዋቂ ያደርገዋል፡፡ ጦርነቱ ሲፈጸም ደግሞ ሌላው ጎሳ ሁሉ ወደ ቀደመ ሥርዓቱ ሲመለስ የመንጃ ጎሳ ግን የበላው ተስማምቶት በዚያው አመጋገብ ቀርቶአል፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ይህንን መሰል ታሪክ አለማወቅ ጥሩ ጸሐፊ ለመምሰል ከመቀባጠር ያድናልና ጸሐፊ ብቻ ሳይሆን አንባቢም መሆን ግድ ነው፡፡

በነገራችን ላይ እኔም እንደ በዕውቀቱ በምህንድስና ሙያዬ ዲዛይን ላይ ድፍረት አበዛ እንደነበረ የገባኝ ፪ኛ ዲግሪዬን ስማር ነው፡፡ እያንዳንዱ ምሁራዊ ውሳኔ ከብዙ ንባብ፣ ምርመራና ንጽጽር በኃላ የሚመረጥና የሚተች እንጂ እንዳገኙ የሚሳለቁበት ነገር አለመኖሩን፤ በተለይ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮች ላይ ለመጻፍ ደግሞ ‹‹ታሪክን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ፣ ጥንታዊ ቋንቋና ስነቃልን /ፊሎሎጂና ፎክሎር/ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ መውሰድ ብዙ እንደሚያበስልህ እርግጠኛ ስለሆንኩ ከነዚህ አንድ ሁለቱን ተማር እባክህ›› ብዬ ልለምንህ፡፡ ከሠፈርህ የበቀሉትን ሐዲስ ዓለማየሁንና ዮፍታሔ ንጉሤን ካወቅሀቸው ደግሞ ጥንታዊ የሃይማኖት ትምህርት ምን ያህል በዕውቀት እንደሚያበለጽግ አለመረዳትህ አለማየት ወይም ማየት መሳን/ዕውርነት ያጋጠመህ ይመስላል፡፡

ሳይንስና ሳይንሳዊነት

ሳይንሳዊነት ብዙውን ነገር ‹‹ሳላይ አላምንም/ ማየት ማመን ነው›› ወደሚል ተጠራጣሪነት የሚወስድ የእምነት ተቃራኒ ሲሆን ሃይማኖት ግን ‹‹ሁሉን ዐዋቂ›› መሆን ያለበት ተመላኪ/አምላክ/ የሰጠውን መመሪያና ዕውቀት ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው›› በሚለው ሕግ ተቀብሎ በከለሩ እንደማይታወቀው ብርቱካን / በዕውቀቱ እንደነገረን ፖርቹጋላዊው ብርቱጋል-ብርቱካን/ ‹‹እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱና ዕወቁት›› በመባሉ በምግባርና ትሩፋት፣ በአምልኮና ተጋድሎ አፈጻጸም እርሱን ወደማወቅ የሚወስድ መንገድ ነው፤ ሃይማኖት፡፡ በዕውቀቱ ስለምግብ ምርጫ የነገረን ቅድም እንዳልኩት ሆዳችንን መሙላት እንደቸገረን ‹‹ረሀብተኞች፣ ድሆች፣…›› የተባልንበት ታሪክ እንዲቀየር ካለው ጽኑ ፍላጎት ይመስላል፡፡ ሳይንሱ በላብራቶሪ ወይም ሳይንሳዊ አመክንዮ /ሎጂክ/ እስኪያስረዳ ድረስ ማንኛውንም ክስተት ወይም ኅላዌ በጥያቄነት የሚይዘው ሲሆን በሃይማኖት ግን ሁሉም ጥያቄዎች በመጀመሪያ የማመን ቅጽበት ተመልሰው በዕድሜ ውስጥና ኋላም በመንግሥተ ሰማያት እስኪገለጡ ልብ የሚያርፍባቸው ናቸው፡፡ ‹አሁን በድንግዝግዝ እናያለን…› እንዲል፡፡

ሳይንሳዊውን ምስክርነት ከማቅረቤ በፊት እንደ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ያሉትን የሚያተጋቸው የዕውቀቶች ሁሉ ምንጭ የሆነው ግእዝና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ምንጭ የሆነው ኢትዮጵያዊው የቁጥር ስሌት ዘዴ መሆኑን ሳስታውስህ ቀድሞ ያስመሰከረውን ሥልጣኔ ዛሬም እንዲደገም ‹‹ ሕዳሴ›› መባሉን በማስረጃነት በመጥቀስ ነው፡፡ እንዳንተ ያሉት ተናጋሪዎች ኢትዮጵያን የ፻ ዓመት ታሪክ ‹‹ባለክብር››፣ ቤተክርስቲያንን የቅኝ መግዣ መሣሪያ ከመሆን ጋር የኋላቀርነትና የሥልጣኔ አድኃሪነት ማዕከል አድርገው ከብሔረሰቦች ልብ ውስጥ ለማውጣት ሤራ የጎነጎኑት ኢሕአዴጎች ሳይቀር ‹‹ንስሐ ገብተዋል እንዴ;›› በሚያስብል ደረጃ ነባር ሥልጣኔ የነበረንና በታሪክ አጋጣሚ ያጣነውን ማንነት ዳግም የምንፈልግ የሕዳሴ ሠራዊት እንድንሆን ሲሰብኩን፣ ለፕሮፓጋንዳውም ማካሄጃ ‹‹የሕዳሴ ድልድይ፣ የሕዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናበስራለን›› ወዘተ ሲሉ ምንያህል ገብቶአቸው እንደሆነ አላውቅም፡፡ ማጣቱም ማግኘቱም ከማያረካው ምዕራባዊ ከምትቀላውጥ በአንድያ ምርጫው ብቻ ልቡ ያረፈውን ኢትዮጵያዊ ጠባይ አክብር፤ በፈጣሪ ማመን፣ መታመን፡፡

ለነገሩ ‹‹ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ነው›› ይባል የለ፤ አለቃ ገብረሐና የነገሥታቱ አማካሪ ለመሆን ያበቃቸውን መጽሐፋዊ ዕውቀት ከያዙ በኃላ ለራሳቸው አድናቆትን፣ ለሕዝቡም ፈገግታን የሚያጎናጽፉ ቀልዶችን ሲያዘወትሩ ከርመው በሞታቸው መቃረቢያ ሐዲሳቱንና ብሉያቱን /መጻሕፍቱን/ሰብስበው ‹‹ተሳልቄባችኃለሁና ይቅር በሉኝ›› እያሉ ሲያለቅሱ እንደነበረ ታሪካቸው ይናገራል፡፡

መንፈሳዊውን ኢትዮጵያዊ ባህል መተቸት ትቶ ሳይንሳዊውን እውነታ ቢቃኝ የሚከተለውን እውነት ያረጋግጥ ነበረ፡፡ በሊ/ነ/ ሙሴ የተከለከሉትና የተፈቀዱት እንስሶች ያላቸውን የጥቅም ልዩነት በሚቀጥለው ምንባብ ያስተውሉ፡፡ በዚያ ላይ አሁንም ሳይንሳዊ ሆኖ ለተጠራጠረ የተጠቀሱትን ምንጮቼን እንዲቃኝ ልጋብዝ፡፡

‹‹መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ›› በተባለ መጽሐፉ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ሠፊ ትንታኔ ምንጮችን ጠቅሶ ያቀረበ ሲሆን በአጭሩ ለመጥቀስ ያህል፡-

እንዳይበሉ የተከለከሉት እንስሳት፣ አዕዋፋትና ዓሣት ለጤና ችግር በማጋለጥ፣ ራሳቸው ለበሽታ በመዳረግ፣ ለሌሎች ፍጥረታት ዕድገት መገታት ምክንያት የሆኑ ፈሳሾችን ከሥጋቸው በማፍሰስ ጎጂነታቸው በሳይንስ ምሁራን የተረጋገጠ መሆኑን በስፋት ገልጾል፡፡ /‹‹መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ›› መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ፳፻፬ ገጽ 27-31፣ ሩሴል 1994 ገጽ 76-77 What does the bible teach about clean and unclean meats?፣ What does Jesus eat? ገጽ 49-50 ibid], www.Gnmagazine.org/booklets/cu/matterofhealth.htm)
ከብዙ ጥናቶች ግንዛቤ በኃላ ዶ/ር ዊሊያም ‹‹… በመሆኑም ሰው አስቀድሞ ይኸንን ሕያው የኾነ የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድሞ ቢያውቅና ቢረዳ ኖሮ ብዙ ችግርና ጉዳት ሳይደርስ በፊት አስቀድሞ መቆጣጠር በተቻለ ነበር›› ብለዋል፡፡ /Coder p.49, Modern Science & Christian Faith, 1948 p.191/
ለምርምሩ ቀረቤታ ያላቸው እንዲያጤኑት ዴቪድ አይ ማችት የተባለ ምሁር ከተለያዩ እንስሳት የትኩስ ጡንቻዎችና የሥጋ ጭማቂና በሰውነት ውስጥ የያዙትን የሚገኘውን የጨው መጠን በመጨመር ‹‹የሉፒነስ አልበስ›› የበቆልት የሥር ዕድገትን በመቶኛ ማወዳደር የሞከሩትንና ከግኝታቸው ጥቂቱን ለአብነት የሚከተለውን ሠንጠረዥ አቅርቤዋለሁ፡፡ የምርምር ዘዴያቸው በዘርፉ ‹‹ከዕፅዋት መድኃኒት የማውጣት ዘዴ›› በእንግሊዝኛው Phyto-pharmacology የሚባለው ነው፡፡

በዕውቀቱ ምራቁን የዋጠባት ጥንቸልን በተመለከተ ለአብነት ብናነሳ ሥጋቸውን መብላት ብቻ ሳይሆን ሲሞቱ መንካት እን£ ‹‹ቱላሬምያ›› በተባለ ገዳይ በሽታ ለመጠቃት አምስት በመቶ ያጋልጣል፡፡ የበሽታው መተላለፊያ ተሐዋስያን ልብስንም ለመውረር ጊዜ ስለማይወስድባቸው ከነኩዋቸው በኃላ ፈጥኖ ሰውነትንም ልብስንም መተጣጠብ ግድ ይሆናል፡፡
ታዲያ ማን ዐየ ወይስ ማን ታወረ ትላላችሁ? ሙሴማ ይህን ካወቀ እነሆ በዕውቀቱ ፻$ኛ ትውልድ ነው፡፡ ‹‹ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሶች የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።›› ብሏልና ዘሌ 01:-፴9-$ የርኩስና ቅዱስ ነገር ደግሞ በትጉሀኑ ይነበብና ፍረጃውን ይከተል፡፡


ማስታወሻ

መቼስ ሥርዓት አልባነት የሚያመጣው ስህተት ብዙ ነውና እ/የተ/ሜ/ አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን የጎነጠበትን፣ ሳይንቲስቶቹን ያመሰገነበትን፣ ኢትዮጵያዊነትን ያፈረበትን ሁሉ ብነካካ ደስ ባለኝ፤ አይመለከትህም ከሚለኝ በላይ ለማንበብ የሚደክመው ያሳዝነኛልና ልተወው፡፡ ‹‹አልፎ ሂያጁን ሁላ እንዲህ ለጋስ ያደረገው ምን ነበረ? እንደ ኤሊ በድንጋይዋ ሥር ተሸሽጋ የምትኖር ኢትዮጵያዊ Superiority Complex አለች›› ያልከው ተራ ሳንቲም ለቃቃሚ እንጂ ለጋዜጣው አንባቢ የማትጨነቅ መሆንህን ያረጋግጣል፡፡ እንዳንተ ያሉት ናቸው በፖለቲካቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያልደገፏቸውን ሁሉ ሞታቸውን እንዲመኙ የሚጠብቁና ሕዝቡ ከልቡ አዝኖ ሲወጣ ቅኑን ኢትዮጵያዊ አንዴ ፖለቲከኛ፣ ሌላ ጊዜ አላዋቂ፣ ካድሬዎች ደግሞ በእነሱ ጥረት ያዘነ ይመስል በሆቴል ቤት እን£ ከዓላዋቂ ሳሚው ሬድዮና ቲቪ በቀር እንዳይሰማ ሲከለክሉና በለቅሶ ፕሮግራሞች ሰዓት ሥራቸውንና ድርጅታቸውን እንዲዘጉ ሲያስገድዱ የነበሩት፡፡ ከጽንፈኛና ሁለት ብቻ ከምትሉት አማራጮቻችሁ ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳለ የሚያስብ ልብ እንድታገኙ ብዙ እንድታነቡ/እንድትማሩ እያሳሰብኩ እጸልይላችኃለሁ /ከቻልኩ/፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴማ በሙስሊሙም ሙሳ ተብሎ በዓለም ደረጃ ትምህርቱ ለ፴፭፻ ዓመታት የዘለቀ መከበር ያለው፡-
‹‹ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ነው፤ ላጥፋውና በሌላ ታላቅ ሕዝብ ላይ እሾምሀለሁ›› ሲባል ‹‹ ሕዝብህን ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ›› ያለ የመሪዎች ምሳሌ መሥዋዕት /ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስቴራችን አደረጉት እንደሚባለው/፣
አስቦና ዐቅዶ ከሚሠራው ጀምሮ በቸልተኝነት እስከሚፈጸመው፣ ከወንጀል ነክ እስከ ፍትሐ ብሔር፣ ከፍትሕ መንፈሳዊ እስከ ፍትሕ ሥጋዊ ድረስ የሚያካልሉ ሕግጋትን ያዘጋጀ የሕግ ላይብረሪ፣

ምድራዊ ሁሉ መርምሮ ያልደረሰበትን ዕውቀት ፈጽሞ ‹‹ወነበቦ፣ ወነበቦ›› እያለ ከ570 በላይ የእግዚአብሔርን እስትንፋስ ጽፎ ያኖረና ኋላም ስለሰው ፍቅር ሰው የሆነውን ክርስቶስ በባሕርይ ክብሩ ለማነጋገር የተመረጠ የደብረታቦር የባሕርዩ ምስክር፣
‹‹የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን ሳይሆን ከወገኖቹ ጋር መከራን መቀበልን መረጠ›› የተባለለት ሀገርና ሕዝብ ወዳድ ምሁር፣
‹‹አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል›› ያለውን ኢትዮጵያዊ ካህን ዮቶር ሳይንቅ መሪ ሳለ ምክር የተቀበለና የፍትሕ ሥርዓቱን ያሻሻለ ትሑት ባለሟል ነው፡፡
 በናባው ተራራ ባረፈበት የካቲት 17 ቀን በየዓመቱ ስንዘክረው
‹‹ርሑቅ ሕይወት እምኃጥአን …›› እያልን በሌሊቱ ምስባክ
መድኃኒት ከኅጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፤ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፤ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ።
‹‹አርአየ ፍናዊሁ ለሙሴ…›› እያልን በጉን ክርስቶስን በምንሰዋበት የቅዳሴ ምስባክ
ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን። እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ።ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።
 … እያልን ትምህርቱንና ሕይወቱን እናስባለን፡፡ የማልዋሽህ ግን ታላቁን መምህር እንዲህ ስትዳፈር ነፍሴ እንዴት እንደተቆጣች ብታይ ምንያህል ታግሼ ጽሑፍ ለማዘጋጀት እንደተጋሁ ትረዳኝ ነበረ፡፡ አያያዝህ ግን ነውረኛ ነውና ከዚህ በኋላ በሌሎች ቅዱሳን ላይ እንዲህ ያለ ድፍረት እንዳትሞክር ማስጠንቀቅ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ፈጽሞ በአደባባይ ስሟን እንዳትጥራ፤ አደራ ታስቀይመኝና አስቀይምሃለሁ፡፡ በዐለትነቱ ሥር በተሸሸገችው ኢትዮጵያ እየኖርክ ‹‹በባህርዩ ክቡር ክርስቶስን ብትንቀው ‹‹በዐለቱም ላይ ለሚወድቅ፣ ዓለቱም ለሚወድቅበት›› ይቀጠቅጠዋልና ለድንጋይ አስተሳሰብህ የመዳን ውሀ ከምንጩ እንዲያጠጣህ የድንጋይ ያይደለ የሥጋ ልብ ግዛ፡፡

 ምክር

ለአቅመ መናቅ ‹‹ደርሰህ›› የናቅሀቸው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እንዳሉት ‹‹በኢትዮጵያ ላይ ክፉ አትናገር፤ ክፉ አትስማ፤ ክፉ አታስብ››  ለኢትዮጵያ ገና ምንም ሳታደርግላት ባለውለታዎን አታዋርድባት፤ ከዓለም ወደኃላ የቀረች ቢመስልህም አንተን ጨምሮ ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነች ሀገር ነችና ዕድሜህን ሳትፈጅ በወጣትነትህ ዕወቃት፤ ኋላ በማይጠቅም ሰዓት ባንነህ እንዳትጸጸት፤ አደራ፡፡
ከሔኖክ ጀምሮ በሙሴና በሌሎችም ነቢያት በተተነተነው የቁጥር ስሌት መሠረት ፳፻፭ ዓም ብዙ የሚበላበት የጥጋብ ዓመት ስለሆነ በምታውቅበት አበላል በደንብ ተዘጋጅ፡፡ በእኔና በአንተ ጥፋት በታሪክ እጅግ የከፋው ረሀብ የሚከሰትበት ዓመትም ይኼ ዓመት ሊሆን እንደሚችል ሳረዳህ ከ-Superiority Complex-ህ ታግሰህም ቢሆን ገንዘብ ለማጠራቀም የምትሽቀዳደም ስለሚመስለኝ ራስ ወዳዶች በዚህ ዓይነት ዘመን የበለጠ ትከፋላችሁና ታስፈራላችሁ፡፡
እስኪ ቸሩ ፈጣሪ እንደምሕረቱ ብዛት ይቅር ብሎ አዲሱን ዓመት ወደልባችን የምንመለስበት፣ ሀገራችንም ቤተክርስቲያናችንም መሪዎቻቸውን በሰላም የሚሾሙበት ያድርግልን፡፡


የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. A wonderful piece...Bravo!

    Reasonable and Convincing!

    ReplyDelete