Sunday, September 16, 2012

ገለልተኞች ሆይ የት ናችሁ?


በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመን ታሪክ ከተፈጠሩት ገጽታዎች አንዱ ‹‹የገለልተኛነት›› አቅጣጫ ነው፡፡ ገለልተኛነት በተግባር የታየው 1970ዎቹ አጋማሽ በአሜሪካን ሀገር ከቅዱስ ሲኖዶስ ተለይተው የቀሩትን ሁለት ጳጳሳት ተከትሎ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጳጳሳት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ራሳቸውን በማግለል በቅዱስ ሲኖዶስ የማይመሩ አብያተ ክርስቲያናትን መመሥረት ጀመሩ፡፡
በወቅቱ ይህንን ተግባር የተቃወሙት በምዕራብ ንፍቀ ክበብ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ነበሩ፡፡ አቡነ ይስሐቅ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አድርሰው እስከ ማስወሰን በመድረሳቸው ሁለቱ ጳጳሳት ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› የሚለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በመተው ‹‹የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን›› በማለት እስከ ማቋቋም ተደርሶ ነበር፡፡ በርግጥ ታሪክ ራሱን ስለ ሚደግም አቡነ ይስሐቅም በተራቸው ሌሎችን ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት አቋቁመው ነበር፡፡


ገለልተኛነት በስምና በግብር ይበልጥ የገዘፈው 1986 ዓም በኋላ ነው፡፡ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ከሀገር ቤቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የተለዩ አባቶች በአሜሪካን ሀገር በሜሪላንድ ሕግ መሠረት የተመሠረተ ሌላ ሲኖዶስ 1986 ዓም ማቋቋማቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ቤት በቤተ ክህነቱ አካባቢ የሚሠሩ አንዳንድ ሥራዎች የምእመኑን ልብ እያሻከሩት መምጣታቸው ነው፡፡

በአሜሪካን ሀገር ‹‹ሲኖዶስ›› መቋቋም ነገር ሲመጣ ከሁለቱም ወገን አይደለንም የሚሉ አካላት ይበልጥ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ እነዚህ ወገኖች ‹‹የሁለቱንም አባቶች ስም አንጠራም፡፡ ነገር ግን ሁሉንም አባቶች በአባትነታቸው ብቻ እንቀበላለን›› የሚል አቋም ወስደው ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በመጀመርያ አካባቢ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ይሠሩ የነበሩት ከተሰደዱት አባቶች ጋር ነበር፡፡ ከሀገር ቤት የሚመጡትን አባቶች ላለመቀበልና በቤተ ክርስቲያናቸውም ላለማስተናገድ አቋም ይዘው ነበር፡፡
እየቆየ በሀገር ቤት በሰንበት ትምህርት ቤት ያደገው ወጣት ወደ አሜሪካ መምጣት ሲጀምር፤ ጥያቄዎችም መበርከት ሲጀምሩ፤ በአሜሪካ የሚገኙት አባቶችም ገለልተኛነትን በግልጽ ሲቃወሙ ‹‹በሀገር ቤት ያለውን ሲኖዶስ እንቀበላለን፣ ነገር ግን አቡነ ጳውሎስን አንቀበልም›› የሚለው አቋም አካል እየነሣ መጣ፡፡ በኋላ ደሞ በሁለቱ አባቶች መካከል ውግዘቶች ሲተላለፉ ገለልተኞች ከስደተኛ አባቶች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋረጠ፡፡

‹‹ገለልተኛ›› የሚለው ቃል የሃይማኖት ቃል አይደለም፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም በርግጥም በሁለት ጎራ መከፈሏ እውን ሲሆን የመጣ ፖለቲካዊ ቃል ነው፡፡ አሜሪካ ከምትመራው የምዕራቡ ጎራና ሶቪየት ኅብረት ከምትመራው የምሥራቁ ጎራ ገለልተኛ ነን ያሉ (እንደ እውነቱ ግን ገለልተኛ ያልነበሩ) ሀገራት የገለልተኛ ሀገሮች ንቅናቄ የሚባል ወገን መሥርተው ነበር፡፡ የገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ስያሜ የተወሰደው ከእነዚህ ሀገሮች ሳይሆን አይቀርም፡፡
እነዚህ በገለልተኛነት የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት ምንም እንኳን ከቤተ ክርስቲያን ቀኖናና አሠራር አንጻር ከቅዱስ ሲኖዶስና ከሀገረ ስብከት ተነጥለው እንዲኖሩ የሚፈቅድላቸው ሕግ ባይኖርም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል አገልግሎት ግን ሰጥተዋል፡፡

በአንድ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ የልዩነቱን መነሻና ምክንያት ከማብራራት ይልቅ ዝምታን በፈጠረበትና ሕዝቡ ግራ በተጋባበት ጊዜ በውጭው ዓለም ለነበረው ሕዝብ መጠጊያ በመሆን የማይናቅ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ሕዝቡ በዚህና በዚያ በዘርና በፖለቲካ ሲናጥና አማራጭ ሲያጣ ለሁሉም ክፍት የሆነ የአገልግሎት በር በማሳየት ምእመኑን ከመኮብለል ታድገውታል፡፡ ከዚህም ሌላ በአብዛኛው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በእነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብለው ከተነሡ አካላት ሕዝቡን በመጠበቅም ታላቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ላለፉት ዓመታትም ለገዳማትና አድባራት ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ሲሰጥ የነበረው ርዳታ በአብዛኛው ከገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጥ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ጉዞ ከባድ የሚሆኑ ፈተናዎችንም አስቀምጠዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈተና ሲፈጠር መሥዋዕትነት ከፍሎና ችግሩን ተጋፍጦ ከመፍታት ይልቅ ራስን ገለል የማድረግ አማራጭን አስተምረዋል፡፡ ክርስትና የመሥዋዕትነት እምነት እንጂ ሌሎች መሥዋዕት እስኪሆኑ ድረስ ገለል ተብሎ የሚቆይበት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በኦርቶዶክሳውያን ቀኖናና ትውፊት ከተገለጠውና ከሚፈጸመው ውጭ ከሀገረ ስብከትና ከሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ውጭ መኖርንና ችግሮችን በመገንጠል መፍታትን አሳይተዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የውጭ አብያተ ክርስቲያናት የተጓዙበትን መንገድ የሀገር ውስጥ አጥቢያዎች ቢከተሉት ኖሮ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ክፍልፋይ ሆና በቀረች ነበር፡፡ በሦስተኛ ደረጃም በነገሥታቱ ዘመን የነበረውን የቶፍነት ሥርዓትም መልሰው አምጥተውታል፡፡ ጥቂት የገጠር ካህናት ገባሮች ሆነው በታላላቅ መኳንንት የሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናትም ይሄው ቶፍነት በዘመናዊ መልኩ መጥቶ ካህናት በምእመናን ሥር እንዲውሉና ተቀጣሪዎች ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በርግጥ በሌላው አቅጣጫ የካህናት አምባገነንነት የሚታይበት አሠራር ስለነበር በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት በተቃራኒው ሊከናወን መቻሉ ይገመታል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ግን ሁለቱም አይጠቅማትም፡፡
በሀገር ቤት የተሾሙ ካህናት አስተዳደሩንም፣ ገንዘቡንም፣ አገልግሎቱንም ያለ ምእመናን ፈቃድና ግንዛቤ በፈለጉት መጠን ይወስናሉ፡፡ ‹‹ምእመን ደግሞ ገንዘብ አምጣ ሲሉት መስጠት እንጂ ሌላው ነገር ውስጥ ምን አገባው›› የሚል አመለካከትም አዳብረዋል፡፡ በአጥቢያዎች ዘንድ አስተዳዳሪውና ጸሐፊው ከበላይ አካላት ጋር ብቻ በመነጋገር ሰበካ ጉባኤውን ጥለው ይወስናሉ፡፡ የሚገዳደሩ የሰበካ ጉባኤ አባል ምእመናንን ካገኙ ያባርራሉ፡፡

ሁለቱም አሠራሮች ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅሟትም፡፡ በቤተ ክርስቲያን የካህናትም ሆነ የምእመናን ጠቅላይነት (totalitarianism) አልጠቀማትም፡፡ ምእመናኑ ሲገንኑ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፤ ካህናቱ ሲገንኑም ሙስና ይስፋፋልና፡፡ እናም በቀጣዩ ቃለ ዐዋዲ ልናስብበት ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ይህ ነጥብ ይመስለኛል፡፡

አንዳንድ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ንብረታቸውን በሕዝብ ስም በማድረግና የመጨረሻ ወራሽ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን በማድረግ ወደ መሥመሩ ለመቅረብ ቢሞክሩም የብዙዎቹ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ሀብትና ንብረት (ንዋያተ ቅድሳቱን ጨምሮ) በግለሰቦች የተያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶችም በአሜሪካ ሕግ መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱ ብትዘጋ የንብረቱ ወራሽ ( ታቦቱን ጨምሮ) የአሜሪካ መንግሥት እንደሚሆን ደንግገዋል፡፡ ሌሎቹም መሥራች አባላቱ እንደሚከፋፈሉት ገልጠዋል፡፡
በርግጥ እንዲህ ያሉት ነገሮች በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ነን በሚሉ አብያተ ክርስቲያናትም ዘንድ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ለስሙ የፓትርያርኩን ስም በመጥራታቸው በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር የሆኑ የሚመስላቸው አጥቢያዎች ንብረታቸው ወይ በጳጳሳት፣ ወይ በምእመናን ወይም  በግለሰቦች የተያዘ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በአንዳንድ ቡድኖች የተያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ (ለምሳሌ በአሜሪካን ሀገር እናት ቤተ ክርስቲያን የማታዝባቸው ሦስት አጥቢያዎችን በንብረትነት የያዙ አራት ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ይገኛሉ)
በአጠቃላይ ግን ገለልጠኛነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሌላ የቤት ሥራ ያቆየላት አካሄድ ሆኗል፡፡ ለመመሥረቱ ምክንያቶች ናቸው የተባሉት ሁለት ነጥቦችን እስኪ እንመርምራቸው፡፡

የአቡነ ጳውሎስ ጉዳይ

ሁሉም ገለልተኞች ለገለልተኛነታቸው ምክንያት የሚያደርጓቸው አቡነ ጳውሎስንና ፈጸሙት የሚሉትኝ ጥፋት ነው፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ በራሱ አከራካሪ ቢሆንም፤ ችግር በተፈጠረ ቁጥር መገንጠል መፍትሔ ነው ወይ? ከቤተ ክርስቲያን ልጆች የሚጠበቀው ችግር መፍታት ነው ወይስ እንዲፈታ መፈለግ ነው? የሚሉት መመለስ ያለባቸው ቢሆንም እግዚአብሔር ባወቀ ግን ተወቃሹ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አሁን ወደ ፈጣሪያቸው ሄደዋል፡፡ ታድያ ገለልተኞች ምን ይጠብቃሉ?
ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶስን እንቀበላለን፤ ፓትርያርኩን ግን አንቀበልም ይሉ ነበር፡፡ አሁን ፓትርያርኩ ዐርፈው የምትቀበሉት ሲኖዶስ ቀርቷል፤ ታድያ ምን እየጠበቃችሁ ነው?

የቤተ ክህነት አሠራር

ብዙዎቹ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክህነቱ ውሳኔዎችና አሠራሮች ምክንያት ገለል ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡ እነዚህን ውሳኔዎች ሲወስኑ ነበር የሚባሉት አቡነ ጳውሎስ ዐርፈዋል፤ ታድያ አሁን ምኑን ነው የምትቃወሙት?
ይህ ወቅት በዘመናዊቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አሁን በምንጸልየው ጸሎት፣ በምናደርገው ተሳትፎ፣ በምንሰጠው ሃሳብና በምንከፍለው መሥዋዕትነት ቀጣዩ ጉዟችን የሰላም ወይንም የመለያየት ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ፤ ችግሮቿን ለመፍታትና ቀጣዩን ጉዞዋን ሰላማዊ ለማድረግ የሁላችንንም ተሳትፎ ጊዜው ይጠይቃል፡፡ ትናንት የተፈጸሙ ነገሮችን በማንሳትና በመተቸት ራስን ገለል ማድረግ ችግር ይፈጥራል እንጂ ችግር አይፈታም፡፡ ክርስቲያን የትናንቱን ታሪክ መማርያ ያደርገዋል እንጂ መቆዘሚያ አያደርገውም፡፡ የብዙዎቹን ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄ እግዚአብሔር መልሶላቸዋል፤ ከእንግዲህ የማንን መልስ ይጠብቃሉ፡፡ የአቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በአንድ በኩል ብዙዎቻችንን ያለ ጥያቄ ለማስቀረት እግዚአብሔር ያደረገው ሥራ ነው፡፡ (ጳጳሳቱም ላለመወሰናቸውና ላለመፈጸማቸው የሚወቅሱት፤ የውጮችም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ላለመምጣታቸው  የሚወቅሱት አቡነ ጳውሎስን ነበር፡፡ ከእንግዲህ ሜዳውም ፈረሱም ይሄው)
ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ትናንትን ሲወቅሱ እንጂ ነገ የተሻለ እንዲሆን ሲሠሩ አይታይም፡፡ በዚህ ረገድ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ቢኖሩ ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ግን ለወትሮው ከወደ ላይ ችግር ሲሰሙ መግለጫ ለማውጣት ይፈጥኑ እንዳልነበር፤ አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ወቅት ተረድተው የሂደቱ አካል ለመሆን ሲያዳግታቸው ይታያል፡፡
ገለልተኞች ሆይ? የትናንቱን ተውት፤ ለነገው ሥሩ፡፡ አሁን መውቀሱንና መተቸቱን ተውና የማንወቅሰው አባት፤ የማንተቸውም አሠራር እንዲኖረን እንሥራ፡፡ መሰባሰብ ካለባችሁ አሁን ነው፡፡ መመካከርም ካለባችሁ አሁን ነው፡፡ ነገር ግን በኢንተርኔት መግለጫ ለማውጣት አይደለም፡፡ ቆርጣችሁ የሂደቱ አካል ሁኑ፡፡ እንቀበለዋለን ለምትሉት ቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድጋፋችሁን ግለጡ፡፡ መሆን አለበት የምትሉትን በድረ ገጽ ሳይሆን በአካል ቀርባችሁ አስረዱ፡፡ አሁን ደግሞ ምን ምክንያት አላችሁ? ወደ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት የምትሄዱ ጳጳሳትም ማረፊያ ብቻ አታድርጓቸው፡፡

አቡነ ገብርኤል የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ምዕመናን የቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን አካላት አድርጓቸው
አቡነ ፋኑኤል የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ምዕመናን የቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን አካላት ያድርጓቸው
አቡነ ዳንኤል የደብረ ሰላም መድኅኒዓለም ሜኖሶታ ምዕመናን የቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን አካላት ያድርጓቸው
አቡነ ማትያስ የመካነ ሕይወት መድኅኒዓለም ዲሲ ምዕመናን የቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን አካላት ያድርጓቸው 

እስቲ እናንተ የመጀመሪያውን አንድነት አምጥታችሁ አሳዩን፣ ቤተክርስቲያን እኮ ለእናንተ እናታችሁ፣ ዘመዳችሁ፣ ትምክህታችሁ፣ ክብራችሁ፣ ነች እኮ እናንተ ያልደከማችሁላት በግንባር ቀደምትነት ሌላ ማን ይምጣ አሁንም እባካችሁ አወያዩዋቸው፤ ጥሪ አቅርቡላቸው፤ ጥያቄያቸውን መልሱላቸው፡፡ የማያዛልቃቸውን መንገድም አታጽድቁላቸው፡፡

ገለልተኞች ሆይ፤ በዕርቁ፤ በምርጫው፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻል ሥራው፤ ያለፉትን ግድፈቶች በማረሙ ተግባር ባለቤት ሆናችሁ ተሳተፉ እንጂ እስከ መቼ ገለል ትላላችሁ? የሀገሬ ሰው ሲፎክር ‹‹ ደግሞ ገለሌ›› ይላል፡፡ ይሄ ለጊዜያዊነት ችግርን ለምፍታት የጀመራችሁት ገለልተኛነት ዘላቂ እንዳይሆን? ደርግም ‹‹ጊዜያዊ›› ብሎ አሥራ አምስት ዓመት ቆይቷል፡፡
ገለልተኞች ሆይ የት ናችሁ? ምንስ ትጠብቃላችሁ? ወይስ ሌላ የምትቃወሙት አባት እስኪቀመጥ ድረስ እየጠበቃችሁ ነው? ሌላ የምትተቹት አሠራር እስኪፈጠር እያያችሁ ነው?
ገለልተኞች ሆይ የት ናችሁ?

ምንጭ: http://www.danielkibret.com/
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment