Monday, July 2, 2012

ለዓውደ ምሕረት የተሰጠ መልስ


ይህንን ጽሁፍ አንድ የዘወትር አንባቢያችን በመልዕክት ያደረሰሱን መልዕክት ነው፣ በአንድ ወቅት እራሱን "ዓውደ ምሕረት" ብሎ የሚጠራው ብሎግ ባወጣው ጽሁፍ ላይ የሰጡት መልስ ይመስለናል። በጽሁፉ 
በርካታ መልዕክቶች ሰፍረውበታል በተለይ እነዚህ አጽራረ ቤተክርስቲያን የሆኑ ብሎጎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት በተቻላቸው መጠን ጥሩ ነጥቦችን ለመጠቋቆም መክረዋል እኛም አንባቢያን ቢያነቡት መልካም ነው ብለን ስላመንን አቅርበነዋል መልካም ምንባብ::


ለዓውደ ምሕረት የተሰጠ መልስ
በጣም ይገርማል እንደው በዚህ ዘመን ስንት ዓይነት ሰዎች ወይም ክፍሎች ተነስተዋል? በእውነት ሁሉስ ለቤተክርስቲያን ቆምኩ ይላል እንዴ ለቤተክርስቲያኗ የቆመ ከሆነ፣ ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ግድ የሚለን ከሆነ እስቲ ምን አደረክ? እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነትህ? ካንተ ብዙ ባይጠበቅም ግን እንደ አንድ ሰው ለነገሩ ግብራችን ይመሰክራል የምናደርገውን የምንሠራውን የምናስበውን ጨምሮ። ዛሬ እኮ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተለይ በቤተክህነት ውስጥ ካሉት ሠራተኞች ውስጥ ወደ 30% የሚጠጋው ኦርቶዶክሳዊ አይደለም ለምን? አንተም ኦርቶዶክሳዊ አትሸትም (ማኅበረ ቅዱሳንን) ስለምትሰድብ አይደለም በአጠቃላይ የምታደርገው የምትጽፈው ጽሁፍ በሙሉ ስለቤተክርስቲያን ታስቦ ቢሆን  ጥሩ ነው ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳንን ከመስደብ ብዙ የማይገቡ ነገሮችን ከመናገር ይልቅ ይሁን አንተ እንዳልከው ማኅበረ ቅዱሳን ይጥፋ እንበል ከጠፋስ በኃላ ክፍተቶቹን ማን ይሞላል ገዳማቱን ማን ይረዳል፣ ምንዱባንን ማን  ይጦራል፣ የተቸገሩትን አብያተ ክርስቲያናት ማን ጧፍ ይገዛል፣ ዘቢቡን፣ ንዋየ ቅዱሳትን ማን ይሸፍናል። እርግጠኛ ነኝ እኔ ወይም እና "ዓውደ ምሕረቶች" እንደማትለኝ ነው። ምክንያቱም ጸሎቱም ይቁም ያልክ ሰው እንዴት ነው ጧፍና ዘቢብ ገዝተሕ ታጸልያለህ ብለን እምናስበው። ያለግብሩ ማቼም ማንንም መጠበቅ እና መገመት እኮ በደል ነው አንበሳ ሁልጊዜ አንበሳ ነው አህያ ልናደርገው አንችልም የርሱ ግብር በዱር በጫካው ተሰማርቶ ደካማ የሆኑትን ነፍሳት እነ ሚዳቆን፣ ተኩላን፣ የሜዳ አህያን የመሳሰሉትን አድብቶ ሰብሮ ቆራርጦ ይበላል እንጂ ዛሬ አህያ ነህ እና እንጫንህ ብንለው እኛንም ሰብሮ የዕለቱ ጉርሱ እንደሚያደርገን ሳይታለም የተፈታ ይመስለኛል። 


ታዲያ እናንተ እስከዛሬ ጸሎቱ ይቀጥል፣ የቤተክርስቲያኒቱ የቀድሞ ክብሯ በምን ይመለስ ብላችሁ የማታውቁ ዛሬ ኑና ተጫኑ ብንላችሁ እኮ ልክ እንደ አንበሳው የቤት አህያ መሆን እንደማይችለው የዚያን አይነት መሆናችሁን ጠንቅቀን የምናውቅ ይመስለናል። ጅብ በማያውቅበት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ አሉ . . . ምን ይሆን ግባችሁ? ምን ይሆን ለቤተክርስቲያን የምትመኙት? ምን ይሆን ራዕያችሁ? ለነገሩ ግማሹን ነግራችሁናል አስባችሁትም ይሁን ሳታስቡት የሆነ ሆኖ ግን ልብ ይስጣችሁ እና ይቅር ይበላችሁ፣ እዚህ ያደረሳችሁን ሕዝበ ክርስቲያኑን ተዋሕዶአዊውን አስቡት ገና ለገና ማኅበረ ቅዱሳን መናፍቃንን ስለሚቃወም ሥርዓታችን ይከበር ባለ፣ በተለየ በየአሜሪካን ቤተክርስቲያኖች የቀረውን የእመቤታችንን ታዕምራት በየሰንበቱ ይሰማ ማለቱ ሊያስከሰው አይችልም ብዬ አምናለው፣ ያማለት ግን ስህተት ሰርቶ አያውቅም ብዬ አላምንም የማላውቃቸው ብዙ ስህተቶች ተሰርተው ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የሚሰራ ሁልጊዜ ስህተት ሊጠፋበት ስለማይችል እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊያን ከሆናችሁ ወልድ ዋሕድ ብላ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንድትቀጥል ከፈለጋችሁ positive engagment የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ችግሩ ምንድነው፣ ስብራቱ የትነው ያለው ከዛም በመተባበር ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን አንድ አላማ ካላችሁ አብሮ መሥራት የማይቻልበት ጊዜ የለም ተባብሮ ያሉትን ችግሮች አንድ ሁለት ብሎ ጠቅሶ መመከት ሲቻል እዳር ቆሞ ይፍረስ እዳር ቆሞ የፖለቲካ ፓርቲ ነው እና ምርጫ ይወዳደር እያሉ መተቸቱ መልስ ይሆናል ብየ አላምንም። መጀመሪያ ግልጽ የሆነ አቋም ይኑራችሁ ተስፋችን ምንድነው? በምን መልኩ መሄድ አለብን ብሎ በግልጽ መወያየት ከወንዝ ወዲያና ከወንዝ ወዲህ ሆኖ መታኮሱ በራሱ ብዙ ንጹሐን የሆኑትን  ኦርቶዶክሳዊያን እያስበላናቸው ነው። በመሰረቱ መታደስ መታደስ አለበት የምትሉት የትም ሊያደርስ አይችልም ቤተክርስቲያን ልትታደስ ፈጽሞ የማይሆን ሙከራ ስለሆነ ወደዚያ መግባቱም ምንም የሚቀይረው ስለማይኖር በዙ መነጋገርም የሚቻል አይመስለኝ ነገር ግን የቤተክርስቲያን ውስጥ አስተዳደሮች መታደስ ሊኖርባቸው ላል ለምሳሴ በቤተክህነት ውስጥ በፊት የቤተክርስቲያን ፈርጥ የሚባሉት ግን አይናቸው ፈዞ፣ ክንዳቸው ደክሞ፣ ጆሮአቸው እንኳ በቅጡ የማይሰሙ ብዙ ሰዎች አሉ እነሱን ወጣት በሆኑ ምሁራን፣ ሊቃውንት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሰለጠኑትን ከዘር፣ ከፖለቲካ፣ ዝምድና ነጻ የሆኑትን አወዳድሮ ቦታቸውን ተካ ተረካቢ ዜጋ ተነኘ ማለት ነው እቺ ቤተክርስቲያን እኮ የወላድ መካን መሆን የለባትም፣ ሐዋሪያት እኮ በእግራቸው ሊቃውንትን ባይተኩ፣ እኛ ብቻ ነን ቢሉ ይህች ቤተክርስቲያን እኮ እኛ ጋር ባልደረሰች ነበር ነገር ግን ስለተተኩ አሁንም ያሉት የቤተክህነቱ ሰራተኞች መተካት መታደስ አለባቸው፣ ሲተኩ ግን ስለትምህርታቸው የተመሰከረላቸው ትምህርተ ሃይማኖትን ከምግባር እንዲሁም ከዘመናዊ ትምህርት ጋር የያዙ መሆናቸው Independent በሆነ ክፍል ተረጋግጦ የአባ እከሌ ዘመድ ነው ወንዝ ልጅ ነው ሳይባል ግልጽነት ባለው መልኩ የሚቀጠሩ ነገ ለማንም ሊያዳሉ፣ ለማንም ሊቆሙ አይችሉም የሚቆሙት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ነው ብየ አምናለሁ። በዚህ መሠረት ካልተሰራ ግን የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ምናልባት ዓላማቸው የዚህችን ቤተክርስቲያን very existance የማይፈልጉ ሰዎች ሕልማቸው የሚሰራ ይመስለኛል ምክንያቱም ሁላችን ለቤተክርስቲያን ነው  እያለን እርስ በእርሳችን በሳንጃ ስንሞሻለቅ ጠላት ተደብቆ ሁላችን ሞታችንን ነው የሚጠብቀው በመጨረሻ አንድ እንኳም የሚቆም ሲጠፋ ለጥፋቷ ምኞት የነበራቸው እኛ ነን  ብለው መቆጣጠራቸው የማይቀር መሆኑን ለማስመር እወዳለው።

እስቲ ልቦና ይስጠን፣ እውነት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ችግር የለባትም እንዴ ዛሬ ለምን እንካካዳለን ዛሬ ገዳማቱ አልተደፈሩም እንዴ፣ ገዳማቱ አልተፈቱም እንዴ ዛሬ እንደው ለአብነት እስቲ እንጥቀስ በጅማው የሻሾ አቡየ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን እኮ የተዋሕዶ ካህናት ናቸው አንገታቸው ከነክራቸው የታረዱት ለምን የኛም አናት እንደሚሆኑ እናስብ በጅማ የተቃጠሉት የእኔም ያንተም እህት ወንድም አባት ሊሆኑ ይችሉ እኮ ነበር፣ በጉራጌ ቅድስት አርሴማ ጽላቷ ጨምሮ ሲቃጠል እኮ ቅድስት ቤተክርስቲያን ነች እኮ የተቃጠለው፣ እኔም አንተም የምናገለግልባት ቤተክርስቲያን ልትሆን እኮ ትችላለች፣ በጎንደር እድሜ ጠገብ የሆኑት የዝማሜ እና የቋቋም /ቤቶች ሲቃጠሉ ታሪካቸው፣ በውስጣቸው ይዘውት ለዘመናት የኖሩት የሃይማኖታችን አሻራዎች እኮ አብረው ነው የወደሙት እኔንም አንተንም የሃይማኖታችን ምስክሮች ነበር፣ በደብረ ውጋግ አሰቦት ገዳም በዓመት ውስጥ እንዴት አምስት ጊዜ እሳት ተነሥቶ ሊቃጠል ቻለ? ይህ እኮ ለምን ማለት የማንም ወገን መሆን አያስፈልገንም የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጅ ወይም አማኝ መሆኑ በራሱ በቂ ነው ለመጠየቅ የኔም ያንተም እኮ አባቶች ነቸው ስለኛ ሌት ተቀን የሚጸልዩት ከእግዚአብሔር ጋር የምልጃ የሚያገናኙን እነዚህ አባቶች እንዴት ባዕታቸው ይደፈር ነው፣ በዝቋላ አቦ ለምን እንዲህ ዓይነት እሳት ተነሳ ስለምንስ እንደማንኛውም የታሪክ ቅርስ መጥፋት ተደርጎ ሊወሰዱ አልተቻለም ለምን እዳር ቁጭ ብለን እከሌ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው በዝቋላ ንግድ ነው ብለን ከምንል እስቲ መንግስትም ዝም ካለ፣ በተክህነቱም ዝም ካለ፣ እናንተም ዝም ካላችሁ፣ በሁሉም ወገን ዝምታው ከቀጠለ ዛሬ ዝቋላ ታሪክ ብቻ ሆኖ ነበር የሚቀረው ምስጋና ለተዋሕዶ ወጣቶች ይግባቸው እና ለህይወታቸው ሳይሳሱ፣ ስራቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ትምህርታቸውን ጥለው በየጫካው ተሯሩጠው የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለእኔ ላንተ በድጋሚ ዝቋላን አትርፈውልናል፣ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ለግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያገለገሉ የሃዲሳት እና የብሉይ /ቤቶች ለምን ተዘጉ? በጀት እውነት ጠፍቶ ነው ወይል ሌላ አላማ ነው የተዘጉበት ምክንያት ብዙ ሊቃውንትን ያፈለቁ እንደሆኑ ለማናችንም ድብቅ ሚስጢር አይደለም የእኔም ያንተም እኮ ቀድሰው የሚያቆርቡን እንደዚህ አይነት ማዕከላት የሚወጡ አባቶች ካህናት ናቸው ለምን ቆመ? ሌላው በዋልድባ ገዳም ላይ እየደረሰ ያለውን ፍዳ እና መከራ የማስቆም አይደለም የተዋሕዶ አማኝ ሳይሆን የማናቸውም ኢትዮጵያዊ ለቅርስ፣ ለታሪክ፣ ለሃገር ሃብት ተቆርቋሪ የሆነ ሁሉ የሚሰማው መሆን ነበረበት ስለምን አንዱ ተቆርቋሪ ሌላው ከሳሽ ሆንን መንግስት እንደተናገረው እኛ ቅዱሱን ቦታ አልነካንም፣ ነገር ግን በውጡ ያሉትን አራት ቤተክርስቲያናት ስለሚነካቸው ወደፊት ይነሳሉ፥ ከዚህ ወጪ ከገዳሙ ውጪ የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች 150 አባወራዎች ይነሳሉ፣ እነሱ ሲነሱ አብሯቸው የተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማት አሉ /ቤቶች እስከ ሃይ ስኩል ያለ፣ ገበያ ቦታዎች፣ ቤተክርስቲያኖች፣ በአጠቃላይ አብረዋቸው ያሉት ሁሉ ይነሳሉ ተብሏል አያይዘውም ለጊዜው ሁለት የገጠር ቤተክርስቲያናትን አንስተናል ብለውናል ታዲያ እኔም አንተም ለቤተክርስቲያን ከቆምን የገጠር የከተማ የሃብታም የደሃ የሚባል ቤተክርስቲያን የለም ብለን ካመንን ምን ዓይነት መረጃ ነው የሚያስፈልገን አንዱን ተቆሩቋሪ ሌላውን ጸረ ሰላም፣ ጸረ ልማት፣ ፖለቲከኛ የሚያስብለው። በመጠረሻ ላይ ልጠቁም የምወደው ቢኖር ግን እያንዳንዳችን የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ነን ካልን ምን ሰራን ትልቁ ጥያቄ ነው፣ በአዲስ አበባ ላይ እኮ አቶ አሊ አብዶ ከንቲባ ሲሆኑ 136 መስጊዶችን አሰርተዋል በዘመናቸው፣ አቶ አርከበ እቁባይስ እሳቸው ኦርቶዶክስ ነኝ ይላሉ ነገር ግን ምን አሰሩ ምን አቀኑ ነገር ግን ስንት ግዜ በግሬደር ስንት የቤተክርስቲያኒቱ ቦታዎችን እንዳስፈረሱ ሁላችንም እናውቃለን፣ ስንት የጥምቀት ቦታዎችን እንዳሶሰዱብን እናውቃለን ታዲያ ማነው ለዚህ ሁሉ በደል ተጠያቂው ወይም ተሟጋቹ እኔ እና አንተ እርስ በእርሳችን እኔ የዓውደ ምህረት ነኝ አንተ የማኅበረ ቅዱሳን ነኝ እየተባባልን ስንበላላ ለዘር እንኳን እንዳይተር ሆነን እንደምንጠፋ ግንዛቤያችን ውስጥ ሊኖር ይገባል፣ በምን መልኩ ነው እኛ ከአባቶቻችን የወረስናትን ወልድ ዋሕድ ብላ የምታምን ቤተክርስቲያን የእምነት ተቃቋም እንዴት ለመጪው ትውልድ ልናስተላልፍ እንችላለን እኛ እንደሆንን እርስ በራሳችን ለመጠፋፋት ተማምለናል ኧረ ጎበዝ እናስተውል። እንደኛ እኮ ደግሞ የአንድነትን ጥቅም ያየ በመለያየትም በመበላላትም ያየት ትውልድ እኮ የለም ሁሉንም ተመልክተነዋል ተምረንበታል ነገር ግን መጠፋፋቱን የመረጥነው ይመስላል እንደው ለትውልድ እንኳን የሚስብ አንድ ሰው እንዴት ጠፋ እውነት እግዚአብሔር ከእኛ ርቋል ያልኩበት ጊዜ ቢኖር ይህ ነው እስቲለማንኛውም መልካሙን ያምጣልን እናንተንም ስለአንድነት ስለቤተክርስቲያን ስለሃገር ተሟጋቾች እንዲያረጋችሁ ምኞቴ ነው መልካም ጊዜ
የቤተክርስቲያናችንን ትንሣኤዋን ያቅርብልን አሜን
ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment