Monday, July 2, 2012

ቤተ ክርስቲያን “ተራሮችን አንቀጠቀጥኩ” በሚለው ወይም በ“ያ ትውልድ” ቁጥጥር ሥር፦ የዳላስ ተሞክሮ


(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 20/2010)፦ ይህ ጽሑፍ በቅርቡ በተከታታይ ስናስነብባችሁ እና በዩ-ቲዩብም ስናሳያችሁ የቆየነው “የዳላስ ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ተከታታይ” ሳይሆን ከዳላሱ ጉዳይ በመነሣት የቀረበ አጠቃላይ ምልከታ ነው። ርዕሱን የበለጠ ለመረዳት ግን ሁለት መሠረታዊ አባባሎችን መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህም “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ” እና “ያ ትውልድ” የሚሉት ሐረጎች ናቸው። እነዚህ ሁለት ወካይ ሐረጎች አሁን ኢትዮጵያን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ እና የኢህአፓ መታወቂያዎች ናቸው። ኢሕአዴግ ስለ ራሱ ገድል ያወጣቸው የነበሩት (የነተስፋዬ ገብረ አብ) መጻሕፍት የሚታወቁት “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” በሚል ሲሆን ስለ ኢሕአፓ ታሪክ በሰፊው ያተተው የፓርቲው መሥራች ክፍሉ ታደሰ የጻፋቸው መጻሕፍት ደግሞ “ያ ትውልድ” ይባላሉ። ይህ ጽሑፍ እነዚህ ሁለት ትውልዶች ከቤተ ክርስቲያን ላይ እጃቸውን እስካላነሱ ድረስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጻነት እንደሌላት ለማጠየቅ ይሞክራል።
ቤተ ክርስቲያን እኛ ልጆቿን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ያወጣች፣ በእናትነቷ ደግሞ እኛን የወለደች እና በሰማያዊ ጸጋ ያሳደገች፣ በአገርነቷ ያሉንን መንፈሳዊና ዓለማዊ ቅርሶች የለገሰች ናት። ይሁን እንጂ ይህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እርሷ ነጻ ባወጣቻቸው ልጇቿ የባርነት ቀንበር ሥር የምትገኝ “ገባር” ናት። በአገር ቤት በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር፣ በውጪው ዓለም ደግሞ በአብዛኛው በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር የምትገኝ፤ በዚህም ሆነ በዚያ የራሷ ድምጽና አንደበት የሌላት ቤተ ክርስቲያን ናት። በተለይም ኮሚኒስታዊው የአብዮት ማዕበል በአገራችን ከነፈሰበት ከ1966 ዓ.ም (1974) ወዲህ ወታደራዊው የመንግሥቱ ኃ/ማርያም አገዛዝም ሆነ ሌላኛው ኮሚኒስታዊው የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ከቤተ ክርስቲያን ጫንቃ ላይ አልወረዱም። በውጪው ዓለም ደግሞ ከኮ/ል መንግሥቱ ጋር የነበሩ፣ ወይም በአጼው ዘመን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ይገኙ ነበሩ እና ዘር ቆጣሪ ዘመዶቻቸው፣ ወይም ኢሕአፓ እና ኢሕአፓን መሰል ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ቤተ ክርስቲያንን ተቆጣጥረዋል። እንግዲህ “እናንት ልጆቿ እባካችሁ ለእናታችሁ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነጻነቷን መልሱላት፣ ከቀንበራችሁ አሳርፏት፣ የከበደ መዳፋችሁን አንሱላት” ስንል ሁሉንም ወገን ማለትም በአገር ውስጥ ያለውንም በውጪው ዓለም ያለውን የዳላስ ሚካኤሉንም ዓይነት አገዛዝ ማለታችን ነው።

በአገር ውስጥ
በአገር ውስጥ ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በኢሕአዴግ ፓርቲ ቁጥጥር ስር የወደቀ አስተዳደር ነው። ከቅ/ሲኖዶሱ ድምጽ ይልቅ የፓርቲው ድምጽ የበለጠ ተሰሚነት አለው። ሌላው ቀርቶ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ላይ አባቶች ምን ማድረግ እንደሚገባቸው መመሪያ እስከመስጠት የሚደፍር “ደፋር” ፓርቲ ያለበት አገር ነው። ቤተ ክህነቱም የመንግሥትን ድምጽ እየተከተለ “አብ ሲነካ ወልድ ይነካ” እያለ “መንግሥትን የሚነካብኝን ሥጋውን ለመከራ ነፍሱን ለሰይጣን” እስከማለት እንዲደርስ ያደረገ ፓርቲ ነው። በየትኛውም የቤተ ክህነቱ እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግሥት ሚጢጢ ካህን-መሰል ካድሬዎች ተሰግስገውበታል። እውነቱን ለመናገር ኢህአዴግ ቤተ ክህነቱን የሚንቀውን ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱን ደግሞ በእጅጉ ይፈራታል። ጥርስ እንደሌለው አንበሳ የሚመለከታትን ያህል እንዳሸለበ አንበሳም ይፈራታል። አንድ ቀን ብትነሣ ጉዴን ታፈላዋለች ብሎ ይሰጋል። ስለዚህም በዘር ላይ በተመረኮዘው ወገንተኝነቱ “ዘመኑ የነ እንትና ነው” የሚሉ ደቀ መዛሙርቱን በማሰለፍ በአባቶችና በአገልጋዮች መካከል ወደፊትም ሊያመረቅዝ የሚችል ጠባሳ በመጣል ላይ ይገኛል።

በውጪ አገር
በውጪው ዓለም ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በአብዛኛው በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠለፈ ነው ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ ኢህአዴግ የሚውልባትን ግፍ፣ በውጪው ዓለም ደግሞ ሌሎቹ ፓርቲዎች እየደገሙት ነው።  አብዛኞቹ ካህናት የእነርሱን ፖለቲካ እንዲደግፉ፣ ባይደግፉም አፋቸውን ይዘው ቁጭ እንዲሉ ያስገድዳሉ። በዐውደ ምሕረቱ የፖለቲካ ማስታወቂያቸውን ይናገራሉ፣ ውግዘታቸውን ያስተላልፋሉ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ይጥሳሉ። ለእነርሱ የማይገዙ ካህናትን አዋርደው ያባርራሉ። የሚቃወማቸውን በሙሉ “በወያኔነት” ፈርጀው ስሙን ያጠፋሉ። ከዚህም አለፍ ሲል ደግሞ ለራሳቸው እንዲመቻቸው ባደረጉት እና “ስደተኛ ሲኖዶስ” ባሉት ተቋም አማካይነት ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት የማይታዘዙትን፣ ከአገር ቤት በተለያየ የሃይማኖት ችግር የኮበለሉትን፣ ሥነ ምግባርና ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት የሌላቸውን በጉያቸው አቅፈው ይኖራሉ።

በውጪ ያለው የቤተ ክርስቲያን ስብጥር ገለልተኛ፣ ስደተኛ እና የአባ ጳውሎስ  በሚል ኢ-ክርስቲያናዊ አከፋፈል የተቧደነ ሲሆን የቤተ ክርስቲያናችን ለዛና ወዝ ምጥጥ ብሎ ጠፍቶ ሃይማኖተኛው በፖለቲከኛው እግር ስር ወድቆ የሚገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር በቅቷል። በዚህም ምክንያት ሥርዓት-አልበኝነት በመንገሱ ክህነት የሌላቸው “ክህናት”፣ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑ ቦርዶች፣ የኑፋቄ ትምህርት የሚያስተምሩ ሐሰተኞች ተቀላቅለው ሃይ የሚባልበት ቦታ ጠፍቶ ሁሉም ተተረማምሷል። አንድ ሰው በሚያጠፋው ጥፋት ተጠያቂ የማይሆንባት ባለቤት አልባ ቤተ ክርስቲያን እየተፈጠረች ነው። በዳላስ ሚካኤል እየሆነ እንዳለውና በሌሎችም ቦታዎች እንደሆነው ባለቤት ስለሌላት ጉዳያችን በሙሉ ወደ ፍርድ ቤት እየሄደ መሳቂያ እና መሳለቂያ ሆነናል። የፖለቲካና የግል ጥቅም ዓላማ እንጂ ሌላ ግብ የሌላቸው፣ በቅጡ ከሲጋራ ሱሳቸው እንኳን ያልተላቀቁ፣ በሥርዓት በቤተ ክርስቲያን ጸሎት የማይሳተፉ፣ እምነቷን የማያከብሩ ነገር ግን አስተዳደሯን የተቆጣጠሩ “ቦርዶች” ታላቂቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወደ ገደል እየመሯት ነው።


ምን ይሻላል?
የዚህ ችግር መኖር ገና ዛሬ ለእኛ የተገለጠ አዲስ “መገለጥ” አይደለም። ችግሩ የገባቸው ብዙዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ገና አንገታቸውን ቀና ሲያደርጉ “ወያኔዎች ናቸው፣ ቅንጅቶች ናቸው፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ለአባ ጳውሎስ (ለአባ መርቆርዮስ) ሊሰጡብን ነው፣ ጎበዝ ተነሥ፣ ማህበረ ቅዱሳን ናቸው፣ አድሃሪዎች ናቸው” እያሉ አንድም ሃይማኖታዊ ነጥብ በሌለው ክስ ስሙን ያጠፉታል።

መፍትሔው አጭር ነው። የቤተ ክርስቲያንን ለቤተ ክርስቲያን፣ የፖለቲካን ለፖለቲካ። በየቡድኑ ተቆርቁዳችሁ የተቀመጣችሁ እና የቤተ ክርስቲያናችሁ ጉዳይ የሚያስጨንቃችሁ አበው ካህናት፣ ምእመናን ቤተ ክርስቲያቱን ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ሸክም ልንገላግላት ይገባናል። ለዕለት ጉርስ ብላችሁ አፋችሁን የከደናችሁ፣ ዓይናችሁን የሸፈናችሁ ብትኖሩም ቢያንሰ በጸሎት ልትረዱ ይገባል። ለጊዜያዊ ጥቅም ብላችሁ የቦርድ ወይም የመንግሥት ሰባክያን የሆናችሁ ሰባክያነ-ቦርድም/ ሰባክያነ-ፖለቲካ ከታሪክ ተወቃሽነት ራሳችሁን ማዳን ይገባችኋል። በአገር ቤት ያለው የመንግሥት ከባድ እጅ ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዲመነሳ አጥብቀን የምንጮኸውን ያህል በውጪ አገርም ያለው እንዲስተካከል መጮኽ ይኖርብናል። እባካችሁ ለቤተ ክርስቲያን ነጻነቷን መልሱላት!!!


ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment