Thursday, March 7, 2013

ፓትርያሪኩ ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ በራሱ መተማመን አለበት›› አሉ

Image
  • ቋሚ ሲኖዶሱን ለማገዝ የተቋቋመው ‹‹ሥራ አስፈጻሚ›› የሥራ ጊዜ አበቃ
  • አዲስ የቋሚ ሲኖዶ አባላት ተመርጠዋል
  • ፓትርያሪኩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ጋራ ትውውቅ አደረጉ
  • ‹‹ቅድስና፣ ንጽሕና፣ ታማኝነት በተለይም ደግሞ ሃይማኖትን ይዞ መገኘት ያስፈልጋል›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለሠራተኞች ከሰጡት ማሳሰቢያ/
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካልና የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት በመኾን ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የሚያወጣው ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹በራሱ መተማመን አለበት››ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አሳሰቡ፡፡ ቅዱስነታቸው ማሳሰቢያውን የሰጡት ስድስተኛ ፓትርያሪክ በመኾን ሥርዐተ ሢመታቸው በተፈጸመበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ፓትርያሪክ (ርእሰ አበው) ኾነው የተመረጡበትን ሓላፊነት የቅ/ሲኖዶሱን አባላት በመያዝ በጋራ እንደሚወጡት ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾኖ በሥምረት ከሠራ ችግር ይኖራል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደገለጹት፣  በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅ/ሲኖዶስ በራሱ መተማመንና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡

‹‹እምነትና ሐቅ ከቤተ ክርስቲያን ካልተገኙ ከየት ይገኛሉ?››
 ሲሉ የጠየቁት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሐቅ በስፋት የሚገኝባት የእምነትና ሐቅ አስተማሪ መኾን እንደሚገባት በቃለ ምዕዳናቸው መክረዋል፡፡ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጹ ታማኞች፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንደ ምሶሶ አቅፈው ደግፈው የያዙ፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሞያቸውን በልግስና የሚሰጡ ምእመናን ያሉባት ቤተ ክርስቲያን መኾኗን ፓትርያሪኩ አስታውሰው፣‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ ሕግንና ሥነ ሥርዐትን ተከትሎ መሥመሩን ሳይለቅ እንዲጓዝ ካህናትና ምእመናን የድርሻቸውን ለመወጣት ብርቱ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤››ብለዋል፡፡                                                                                                                                                             ለሀገር ዕድገትና ልማት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ያላትና ሊኖራት የሚገባው ተሳትፎ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን ውስጥ ተዳስሷል፡፡ በስብከተ ወንጌልና በትምህርተ ሃይማኖት ምእመናንን ከማብዛትና ማጠናከር ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያን ዕድገቷንና ልማቷን ለማፋጠን ከምንጊዜውም የበለጠ መነሣት አለባት፡፡ ቅዱስነታቸው ‹‹የልማት ግሥጋሴ›› ካሉት የአገሪቱ ኹኔታ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ወደ ኋላ መቅረት የለባትም፡፡ ለዚህም የሰው ኀይሏን አሠልጥና ራሷ የምትፈልጋቸውን÷ ለአብነት ያህል ከውጭ የምታስመጣቸውን ንዋያተ ቅድሳት÷ ራሷ ለማምረት መዘጋጀት አለባት፡፡ የሠለጠነ የሰው ኀይል ለመፍጠር ግን መጠነ ሰፊ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሀገር ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን፣ የሕዝብ ፍቅርና አንድነት እንዲጸና ቤተ ክርስቲያን ከኅብረተሰቡና ከመንግሥት ጋራ ተሰልፋ ቀድማ በመገኘት ምሳሌ መኾን አለባት፡፡በቅዱስነታቸው ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ምዕዳን እንደተመለከተው÷ ይህ ግዴታ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ እንደተዘረዘረው ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ መጠበቅና ማስጠበቅ ነው፤ ይህ ግዴታ ምእመናን ከአበው የተቀበሉትን ሃይማኖትና ሥርዐት ጠብቀው በትምህርተ ሃይማኖትና በመልካም ሥነ ምግባር ታንጸውና ጸንተው እንዲኖሩ፣ አእምሯቸውም እንዲሰፋ ጠንክሮ ማስተማር ነው፤ ይህ ግዴታ ቤተ ክርስቲያን ፍትሕ ርትዕ እኩልነት የሞላባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ በሕግና በሥነ ሥርዐት የምትመራ የእምነትና ሐቅ መገኛ እንድትኾን መጠነ ሰፊ ሥራ መሥራት ነው፡፡
መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወነው በእግዚአብሔር ስም በመኾኑ በመንፈሳዊነት የተደገፈ ታማኝነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተጠያቂነት የመላበት መልካም ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅብን ቅዱስነታቸው በበዓለ ሢመታቸው ቀን በሰጡት ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ምዕዳን ደጋግመው ጠቅሰዋል፡፡ ከስሕተት ባንጸዳም የምንችለውን ጥንቃቄ ካደረግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሁሉም ይቻላል፡፡ ቅድስና፣ በመንፈሳዊነት የተደገፈ ታማኝነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተጠያቂነት በተለይም ደግሞ ሃይማኖትንና እምነትን ይዞ መገኘት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በዛሬው ዕለት÷ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ጋራ ባካሄዱት የትውውቅ መርሐ ግብር ላይም አጽንዖት የሰጡበት ጉዳይ ነበር፡፡
ከሁሉም በፊት ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ፣ አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን የማድረግ ዓላማ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ÷በሥምረት እየሠራ ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት ‹‹በራሱ መተማመን›› አለበት፡፡ በቅዱስነታቸው ርእሰ መንበርነት የሚመራው ቅ/ሲኖዶስ በሥምረት መሥራቱ የጠበቀ እንዲኾን በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አነሣሽነትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው አባቶች መልካም ፈቃድ የምርጫው ሂደት ፈጥሮት ባለፈው ክፍተትና የግንኙነት መሻከር ላይ በግልጽ ተነጋግሮ በቀጣይ ለሚጠበቁት ታላላቅ ተግባራት መግባባት ለመፍጠር ችሏል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዕጩ ፓትርያሪኮች ላይ ተነጋግሮ እንዲወስን ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ ላይ ከፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንጻር የዕጩዎች አቀራረብንና የአስመራጭ ኮሚቴውን አሠራር የተቹት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልና ብፁዕ አቡነ አብርሃም አቋማቸውን አብራርተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል÷ ‹‹የወጣው የምርጫ ሕግ አልተከበረም፤ አስመራጭ ኮሚቴውም ግዴታውን አልተወጣም›› ከሚል አቋም መውሰዳቸውን፣ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ከማሰብ አንጻር እንጂ የፓትርያሪኩን (በወቅቱ ብፁዕ አቡነ ማትያስ) አባትነት አልያም በብዙኀኑ የምልአተ ጉባኤው አባላት የተደገፈውን አቋም ላለመቀበል አለመኾኑን ገልጠው ተናግረዋል፤ ‹‹ብፁዕ አባታችን ያስችልዎት ነው የምንለው›› በማለት በፓትርያሪኩ በዓለ ሢመት ዋዜማ በተፈጠረ መድረክ አለመግባባቱን ለማስወገድ ተችሏል፡፡
የይቅርታ ጥያቄው ለእርሳቸው (ለቅዱስነታቸው) ሳይኾን በአለመግባባቱ ተደፍሯል ላሉት ቅዱስ ሲኖዶስ መቅረብ እንደሚገባው ያመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ÷ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት በበዓለ ሢመቱ ላይ እንዲገኙ ጠይቀዋቸዋል፤ እነርሱም ተገኝተዋል፡፡ ሐቁ ይህ ኾኖ ሳለ የአቋም ልዩነቱን የጠብ መሣሪያ ለማድረግ የቋመጠ አንድ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ አባቶችን ያሳንስኹ መስሎት የሚደራርተው አሉባልታ÷ ሥር የሰደደ ጥላቻውንና ስጋቱን ከሚያጋልጥበት በቀር ርባና ሊኖረው አይችልም፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በትላንትናው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰበሰቡት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ ላለፉት ስድስት ወራት ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱንና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩን ለማገዝ የተመረጡት ስምንት ብፁዓን አባቶች የሥራ ጊዜ ማብቃቱ ታውቋል፡፡ ስምንቱ ብፁዓን አባቶችን በቋሚ ሲኖዶሱ ውስጥ ተካተው እንዲሠሩ የተደረገው የቀጣይ ፓትርያሪክ ምርጫ እስኪከናወን ድረስ በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱንና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩን ለመርዳት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ስምንቱ አባቶች÷ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እንደነበሩ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በኋላ ቢያንስ ቀጣዮቹ ሁለት ሦስት ወራት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የመንበረ ፓትርያሪኩን ጠቅላላ ኹኔታ በመገንዘብ ካለፉት የሚማሩበት፣ ከምርጫው በኋላ በፓትርያሪኩ ፊት ሞጎስ (ተወዳጅነት?) በማግኘት ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሙን ለማራመድ የእርስ በርስ ሽኩቻ እንደጀመረ የሚነገርለትን የፅልመት ቡድን የሚጠራርጉበት፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ሳቢያ በውዝፍ የተተዉ የመዋቅርና የአሠራር ለውጦችን ለማካሄድ ዝግጅት የሚያደርጉበት፣ በአንዳንዶቹም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገቡበት እንደሚኾን ተስፋ ተደርጓል፡፡‹‹ትብብራችኹ አይለይ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ይዤ በጋራ እወጣዋለኹ›› ብለዋልና ከነባር የሥራ ሓላፊዎችና ዕውቀቱ ክህሎቱ ካላቸው ባለሞያዎች የሐሳብና የተግባርም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በትላንቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ በአዲስ/ተለዋጭ አራት ብፁዓን አባቶች ተዋቅሯል፡፡ ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ከብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ በመኾን እየሠሩ የሚቆዩት አራቱ አባቶች÷ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው፡፡
መጋቢት ሁለት ቀን ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ) የሚጀመርበት ነው፡፡ በትላንቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ሁሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ የአህጉረ ስብከታቸው ተመልሰው ወርኀ ጾሙን በአገልግሎት እንዲያሳልፉ በማሳሰብና በመምከር መልካም የሱባኤ ወቅት በመመኘት ተሰነባብተዋል፡፡
Source: http://haratewahido.wordpress.com

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment