Monday, March 11, 2013

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ የዐቢይ ጾም መልእክት

His Holiness Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በየጠረፉ የቆማችኹ፤
በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ2005 ዓ.ም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግብሩ››
‹‹በመንፈስ ተመላለሱ እንጂ የሥጋችኹን ምኞት ከቶ አትፈጽሙ እላችኋለኹ››
የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን በፊታችን ሰኞ፣ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓቢይ ጾም ወራት ጎጂ ከኾኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የኾነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተገኘ ፍጡር እንደመኾኑ በሥጋዊ ፍላጎቱ ሳይሸነፍ ራሱን ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ማስገዛት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ከዚህም አንጻር ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ፤ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡
ከዚህ አንጻር ለሥጋዊ አካላችን ጥንካሬ ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡
ከጥንት ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ቅርበት የነበራቸው ቅዱሳን በተሞክሯቸው እንዳስተማሩንና ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዳስረዱን÷ መንፈሳዊ አካላችን የሚጠነክረው የሥጋዊ አካላችን ፍላጎት በጾም ኃይል እንዲደክም ስናደርገው ነው፡፡
ሰይጣንና ክፉ ተግባሩ በሰው ላይ ኀይል የሚያገኙበት ምክንያት እኛ ወደ ምግበ ሥጋ ስናዘነብል እንደኾነ በአዳምና በሔዋን ላይ የኾነውና በጌታችን ላይ የተቃጣው በምግበ ሥጋ የመፈተን ሙከራ ማስረጃዎቻችን ናቸው፡፡ የጾም መንፈሳዊ ጥቅም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በማያሻማ ኹኔታ ተረጋግጧል፡፡
ጾም ማለት የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም መተው፣ ወይም እግዚአብሔር ከማይወደው ነገር ሁሉ መራቅ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከኾነከእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶችን ጨምሮ ከሌሎች ፍላጎቶች ሁሉ በመራቅ ራሳችንን ተቆጣጥረን በፍጹም አእምሯችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ኀይላችን እግዚአብሔር አምላካችንን ልናመልክና ለእርሱ ፍጹም ታዛዦች መኾን ይጠበቅብናል፡፡
የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሁልጊዜ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም መልካም ሥራን ከመሥራት በቀር ጉዳት የሚያደርሱ ተግባራትን ማራመድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
በየአቅጣጫው የተዘረጋው የሀገሪቱ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲኾን እየተደረገ ያለውን ጥረት የምንመለከተው በታላቅ አድናቆት ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥረቱ አካል በመኾን ጥሪውን ተቀብላ የሚጠበቅባትን ድርሻ ስታበረክት የቆየች ቢኾንም የልማት ፕሮጀክቱ እውን ኾኖ ውጤታማነቱን እስኪያረጋግጥ ድረስ ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገው የተግባር ተሳትፎ ዘወትር ይቀጥላል፡፡
ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊኾን የሚችለው ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ምጽዋትን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ስምምነትን፣ ትሕትናን፣ መረዳዳትን፣ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደኾን ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡ የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢኾኑም በተለይ መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም፤ ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፣ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው የሚቻለንን በመለገሥ፣ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል፡፡
በመኾኑም የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኀይላችን ለመታዘዝ መዘጋጀት ነውና እግዚአብሔር በቃሉ የነገረንን ሁሉ ከመፈጸም ጋራ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታችንን በመወጣት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መርሐ ግብራችንን በማፋጠን፣ መልካም የኾኑትን የልማት ሥራዎቻችንን ሁሉ በማከናወን ወርኃ ጾሙን ልናሳልፍ ይገባል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ወርኃ ጾሙን በሰላም እንዳስጀመረን ሱባዔውን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.
አዲስ አበባ


ምንጭ: http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment