Tuesday, March 26, 2013

የቅ/ሥላሴ መ/ኮሌጅ አስተዳደርና ደቀ መዛሙርት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

His Grace Abune Timothy
ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

  • ተማሪዎች÷ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ እና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ካልተነሡ ያቋረጡትን ትምህርት እንደማይቀጥሉ አስታውቀዋል
  • አስተዳደሩ÷ ተማሪዎች ትምህርት ካልጀመሩ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፤ ለውዝግቡ መባባስ የተማሪዎች መማክርትን ተጠያቂ አድርጓል
  • የቀኑ የመደበኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ትምህርት ከተቋረጠ ዐሥረኛ ቀኑን አስቆጥሯል
  • ደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ሓላፊነቶችን ደራርበው የያዙ መምህራን በሚታይባቸው የማስተማር ዝግጅት ማነስ ተማርረዋል
  • የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው÷ መ/ር ዘላለም ረድኤት÷ በሸውከኛነት (ነገረ ሠሪነት) ኰሌጁን ሰላም በመንሳት ተከሠዋል
  • ለ14 ዓመታት ያህል በኮሌጁ የበላይ ሓላፊነት የቆዩት ሊቀ ጳጳስ ‹‹በቃዎት›› ተብለዋል
  • ውዝግቡ ከመ/ፓ/ጠ/ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሓላፊዎች አቅም በላይ ኾኗል
  • ‹‹ትምህርት የምንጀምረው የዛሬም የሁልጊዜም ጥያቄዎቻችን የነበሩት ችግሮች ተፈተው ተገቢ ምላሽ ስናገኝ ብቻ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
  • ‹‹ችግራችሁን እናስተካክላለን፤ ጥያቄዎቻችሁን እንመልሳለን፤ ነገር ግን ወደ ክፍል ገብታችኹ ትምህርታችሁ ቀጥሉ›› /የኮሌጁ አስተዳደር/
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር እና በመደበኛው የዲግሪ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት መካከል ዳግመኛ ያገረሸው ውዝግብ ዛሬ፣ መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ዐሥረኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ለውዝግቡ መቀስቀስ መነሻ የኾነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የመጣው የካፊቴሪያው የምግብ አቅርቦት መበላሸት ነው፡፡ ‹‹ጥርስ ላይ ከሚንቀጫቀጨው እንጀራ ጀምሮ ጠቅላላ ብልሽት የሚታየበት የካፊቴሪያው የምግብ አቅርቦት÷ በኮሌጁ ጥቂት የአስተዳደርና የአካዳሚ ሓላፊዎች መካከል ለገነገነው ሙስናና የጥቅም ትስስር ጉልሕ ማሳያ ነው፤›› ይላሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡
ጥያቄያቸው ከምግብ አቅርቦት በላይ የኰሌጁን መሠረታዊ አስተዳደራዊ ችግሮች በተለይም በትምህርት አመራሩ ረገድ የሚታየውን ውስንነት እንደሚያካትት ደቀ መዛሙርቱ ይናገራሉ፡፡ እንደ ደቀ መዛሙርቱ ገለጻ÷ በአሁኑ ወቅት በሓላፊነት ላይ የሚገኘው የኮሌጁ አስተዳደር፣ አንጋፋውን የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመምራት ብቃቱም ዝግጁቱም የለውም፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዋን በትውፊታዊ መንገድ ለትውልድ ጠብቃ ካቆየችባቸው የአብነት ት/ቤቶች በተጨማሪ በዘመናዊ አቀራረብ የነገረ መለኰት ትምህርት የሚሰጥባቸው ሦስት መንፈሳዊ ኮሌጆችን አቋቁማለች፡፡ ከሦስቱ ኮሌጆች ቀደምት የኾነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተ 55 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የተቋሙ ርእይ÷ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ትውፊት ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ፤ የክርስቶስን ወንጌል ያልሰሙ እንዲሰሙ፣ የሰሙ በእምነታቸው ጸንተው የሃይማኖት ፍሬ እንዲያፍሩ በመሥራት እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ወንድሙን የሚወድ፣ ለሀገርና ለወገን ዕድገት የሚያስብ ለዚህም የቆመ ትውልድ ተፈጥሮ ማየት›› መኾኑን የኮሌጁ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡


ኮሌጁ ይህን ርእዩን ለማሳካት÷ የመምህራኑን የማስተማር ችሎታ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የትምህርቱን ጥራት እንደሚጠብቅ፤ የሚያስመርቃቸው ደቀ መዛሙርት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ በትምህርታቸው በቂ ግንዛቤና ዕውቀት ያዳበሩ፣ በሃይማኖታቸው የጸኑ እንዲኾኑ እንደሚሠራ ገልጧል፡፡ በቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት ለ17 ዓመታት ተዘግቶ በ1986 ዓ.ም ዳግም ከተከፈተ በኋላ በቀን፣ በተከታታይ እና በርቀት መርሐ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪና በዲፕሎማ አሠልጥኖ የሚያስመርቀው ኮሌጁ÷ በያዝነው ዓመትበሲስተማቲክ ቴዎሎጂ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ጀምሯል፡፡ በቀንና በማታ በዲግሪ፣ በማታ በዲፕሎማ፣ እንዲሁም በድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ ከሚሰጠው የቴዎሎጂ ትምህርት ውጭ ያለው የኮሌጁ መርሐ ግብር በማታው ክፍለ ጊዜ ለሁለት ዓመት በዲፕሎማ ደረጃ የሚሰጠው የግእዝ ቋንቋ ሥልጠና ብቻ ነው፡፡
ይኹንና ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በአስተዳደሩ ላይ ባነሡት ተቃውሞ ጸንተው የሚገኙት የመደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርቱ እንደሚገልጹት÷ በሥራ ላይ የሚገኘው የኮሌጁ የቦርድ አመራርና አስተዳደር ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የኮሌጁን ርእይ ለማሳካት የሚያስችል አደረጃጀት ይኹን አቅም የለውም፡፡ ሰኞ፣ መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ.ም፣ ራሳቸውን የፓትርያሪኩ አማካሪ አድርገው በሠየሙት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ መሪነት ከኮሌጁ አካዳሚክና የአስተዳደር ሓላፊዎች ጋራ ለአምስት ሰዓታት የተወያዩት ደቀ መዛሙርቱ÷የኮሌጁን አስተዳደርና የትምህርት አመራር መዳከም የተመለከቱ ጥያቄዎቻቸውንና ተቃውሞዎቻቸውን በከፍተኛ አጽንዖትና ምሬት አንሥተዋል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የኮሌጁ ሓላፊዎች ባላቸው ሥልጣንና ተግባራት አንጻር ያነሷቸው ጉዳዮች በዋናነት÷ ምክትል ዋና ዲኑን ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰን፣ አካዳሚክ ምክትል ዲኑን መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝንና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪውን መ/ር ዘላለም ረድኤትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በርግጥ÷ የደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞ ላለፉት 14 ዓመታት ያህል የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ለኾኑት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ምሕረት ያደረገ አልነበረም፡፡ የኮሌጁ የበላይ ሐላፊና አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዐይን ሕክምና ሲያደርጉ የቆዩ ቢኾኑም በአሁኑ ወቅት ማየት የተሳናቸው ናቸው፡፡ ወደ ቢሯቸው የሚወጡትም ይኹን የሚገቡት በረዳቶቻቸው ድጋፍ ነው፡፡ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ እንደመኾናቸው በርካታ ጉዳዮች ዐይተውና ተመልክተው መወሰን፣ መፈረምና መምራት የሚገባቸው ቢኾንም ዕርግናውና ሕመሙ እንደማያስችላቸው ግልጽ ነው፡፡ ውዝግቡ ከመባባሱ በፊት የደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች በሊቀ ጳጳሱ ቢሮ ተገኝተው ለመወያየት በተደጋጋሚ እንደሞከሩ የተገለጸ ሲኾን በአግባቡ ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸው እንዳልነበረ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኮሌጁን እየመሩት አይደሉም፤›› የተባሉት የበላይ ሓላፊው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ÷ ከዚህ በኋላ ለተቋሙ የሚመጥንና ተፈላጊውን አመራር የሚሰጥ ሓላፊ መቀመጥ ስላለበት ‹‹ቢበቃዎ›› ተብለዋል – በደቀ መዛሙርቱ፡፡
የኮሌጁ ዋና ምክትል ዲን ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ፣ ምክትል አካዳሚክ ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ እና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤት ከሌላ አንድ የውጭ መምህር ጋራ በአንድ የትምህርት ዘመን በአማካይ አራትና አምስት ኮርሶችን ደራርቦ በመያዝ በደቀ መዛሙርቱ ተገምግመዋል፡፡ በአጠቃላይ 16 መምህራን እንደሚገኙበት በተገለጸው መንፈሳዊ ኮሌጅ÷ አራት መምህራን ብቻ ደራርበው ይዘው በቀኑ፣ በማታውና በድኅረ ምረቃው መርሐ ግብሮች የሚሰጧቸው ኮርሶች ከፍተኛ የዝግጅት ማነስ ይታይባቸዋል፤ የመማር ማስተማር መርሐ ግብሩ ተበድሏል፤ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸውን ዕውቀት እየገበዩ አይደለም፡፡ ተማሪዎቹ እንደሚገልጹት እኒህ ጥቂት መምህራን በየመርሐ ግብሩ የሚሰጡ ኮርሶችን አግበስብሰው በመያዝ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚበድሉት የሚያገኙትን ጠቀም ያለ ክፍያ በማሰብ ነው፡፡
መምህራኑ አስተዳደራዊ ሓላፊነትም ያለባቸው ቢኾንም ሁሉም በቢሯቸው ተገኝተው ባለጉዳዮችን በአግባቡ አያስተናግዱም፡፡ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ በኦርቶዶክሳዊ ቀናዒነታቸውና በኮሌጁ ውስጥ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሕዋሱን ለማብዛት የማያባራ ጥረት የሚያደርገውን የኑፋቄ ኀይል በመቋቋም በደቀ መዛሙርቱ ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፤ በቁጡነትና ብስጩነት ግን ተገምግመዋል፡፡ የኮሌጁ ዋና ምክትል ዲን አባ ኀይለ ማርያም መለሰ ቁርጥ ውሳኔ ለመስጠት ባለመቻልና በወላዋይነት ተተችተዋል፡፡
የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤት ወቀሳቸው የበዛ ነው፤ በመምህራን ምደባ ረገድ ቀደም ሲል በተጠቀሰው በክፍያ ጥቅም በመተሳሰር አድላዊነት እንደሚታይባቸው ተነግሯቸዋል፤ ከዚህ ጋራ በተያያዘ ነገር እያሻወኩ መምህራንን እርስ በርስና ከአስተዳደሩ ጋራ በማጣላት ኮሌጁን ሰላም እንደነሱት ተገልጧል፤ በማስተማር ችሎታቸው የተመሰገኑ መምህራን ሰበብ እየተፈለገ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፤ በኮሌጁ ሕንጻ ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ በመክፈል የሚኖሩበት ቤትና መኪና የገዙበት የሀብት ምንጭ ከፍተኛ ጥያቄ አሥነስቶባቸዋል፡፡
በሰኞው ስብሰባ አካዳሚክ ምክትል ዲኑና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በማስተማር እንዲወሰኑ ካልተደረገ ያቋረጡትን ትምህርት እንደማይቀጥሉ ደቀ መዛሙርቱ አስታውቀዋል፡፡ አወያዩ ንቡረ እድ ኤልያስ የተጠቀሱትን ሓላፊዎች ከሥልጣን የማውረድ ጉዳይ እንደማይመለከታቸውና ከአቅማቸው በላይ መኾኑን በመግለጻቸው ስብሰባው ያለውጤት ተበትኗል፡፡ ከዚህ በኋላ የኮሌጁ አስተዳደር ውዝግቡን ለቀሰቀሰው የካፊቴሪያ ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የምግብ ቤት ሓላፊ ከቦታቸው በማንሣት ወደ ቤተ መጻሕፍት አዘዋውረዋል፡፡
አስተዳደሩ በምግብ ቤት ሓላፊው ላይ የወሰደው ርምጃ ከጥያቄያቸው ጋራ እንደማይገናኝ የገለጹት ተማሪዎቹ ግን ተቃውሟቸውን በመቀጠላቸው÷ በቀጣዩ ዕለት ማክሰኞ የመ/ፓ/ጠ/ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ባሉበት ከዋና ምክትል ዲኑና ከአካዳሚክ ዲኑ ጋራ ተወያይተዋል፤ በዕለቱ በተማሪዎቹ ጥያቄና ፍላጎት ላይ ከቀድሞው የተለወጠ ነገር ባይኖርም የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤት በሌሉበት የተሰነዘረባቸው ትችት ግን ጠንካራ ነበር፤ ለውዝግቡ መባባስም ደቀ መዛሙርቱ ዋነኛ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የአስተዳደር ሓላፊነቱን ትተው በአስተማሪነት እንዲወሰኑ በቀጥታ የተነገራቸው መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ሲያለቅሱ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡
አቶ ተስፋዬ ውብሸት የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚያገኝ፣ ተገቢውን አሠራር በማይከተሉ ሓላፊዎች ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ ነገር ግን ከዚያ በፊት ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ በመግለጽ ለማግባባት ጥረት ቢያደርጉም ደቀ መዛሙርቱ‹‹ጥያቄዎቻችን ነባር በመኾናቸው ምላሽ ሳያገኙ ወደ ትምህርት አንመለስም፤›› ከሚለው አቋማቸው ፍንክች አላሉም፡፡ የሁለተኛው ቀን ስብሰባም እንዲሁ ያለውጤት ተበትኗል፡፡
በዚህ ዕለት ምሽት ዐሥር አባላት ያሉት የኮሌጁ ቦርድ አመራር መሰብሰቡ የተዘገበ ሲኾን ከቦርዱ አመራር እንደተሰጠ በተገመተ አቅጣጫ መሠረት የኮሌጁ አስተዳደር በተከታዩ ረቡዕ ዕለት ጠዋት ተነጋግሮ አራት ገጾች ያሉት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የያዘ ማሳሰቢያ እንዲለጠፍ አድርጓል፡፡ ውዝግቡን ለመፍታት በአስተዳደሩ የተደረጉ ጥረቶችን የሚያትተው ማሳሰቢያው ደቀ መዛሙርቱን ማረጋጋትና ችግሩን ለመፍታት አስተዳደሩን ማገዝ ይገባው ነበር ያለውን የተማሪዎች መማክርት ጉባኤ በዋና ተዋናይነት በተጠያቂነት ወንጅሏል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት የአስተዳደሩ ማሳሰቢያ÷ ወደ ትምህርት ገበታቸው የማይመለሱ ተማሪዎች የንብረት ማስረከቢያ ቅጽ እየሞሉ፣ መታወቂያቸውን ለሬጅስትራር እየመለሱ ከኮሌጁ እንዲወጡ ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ የአስተዳደሩ ማሳቢያ መውጣቱን ተከትሎ ቀትር ላይ የመከሩት ደቀ መዛሙርቱ÷ ጥያቄያቸው የአካዳሚያዊ መብት ብቻ መኾኑንና ተገቢ ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ በአቋማቸው እንደሚጸኑ መማማላቸው ተዘግቧል፡፡
የማታውና የድኅረ ምረዋ መርሐ ግብሩ እንደቀጠለ ሲኾን ትምህርታቸው አቋርጠው ተቃውሟቸው የቀጠሉት የመደበኛው ዲግሪ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ናቸው፤ በቁጥራቸው 189 ያህል ናቸው፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ተስፋ ከቆረጡበት የኮሌጁ አስተዳደር ጋራ ከመነጋገራቸው በፊት በተወካዮቻቸው አማካይነት ቀጠሮ በማስያዝ ከአዲሱ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ጋራ ለመወያየት ያደረጉት ሙከራ በሱባኤው ምክንያት አልተሳካም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለሚያስፈልጋት ተቋማዊ ለውጥና መሻሻል የሠለጠነ የሰው ኀይል ማእከል መኾን የሚገባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደርና አቅም ግንባታ የቅዱስ ሲኖዶሱንና የፓትርያሪኩን ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
Source:http://haratewahido.wordpress.com/ 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment