Monday, March 4, 2013

ፓትርያሪኩ የዕርቀ ሰላም ጥረቱ እንደሚቀጥል አሳሰቡ

The 6th Patriarch Enthronmentየብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥርዐተ ሢመት ዛሬ፣ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ለበዓለ ሢመቱ አፈጻጸም በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በካቴድራሉ ተገኝተው የቅዱስነታቸውን ሥርዐተ ሢመትና ሥርዐተ ጸሎት ያከናወኑት በሹመት ቀደምት የኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ዐቃቤ መንበሩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ ናቸው፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩም ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፤ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ ጸሎተ ቅዳሴውን (ቅዳሴ ሐዋርያት) መርተዋል፡፡

‹‹ተኣዝዞ ከመሥዋዕትነት ይበልጣል›› ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ሢመተ ፕትርክናውን እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል ፡፡ ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹አቅሜ በፈቀደው ለቤተ ክርስቲያኔ እታዘዛለኹ፤ አልችልም ማለት እችል ነበር፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ አልቀበልም ማለት መሥዋዕትነትን መሸሽ ነው፤ ሢመቱ ለክብርና ለልዕልና እንዳልኾነ ለእኔም በሚገባ ይገባኛል፤ ሁላችኹም እንደምትረዱልኝም ተስፋ አደርጋለኹ፤›› ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው የዕርቀ ሰላም ሂደቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልአክት÷ ‹‹ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የቆየው የዕርቅና ሰላም ሂደት ለጊዜው ባይሳካም በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ጥረቱ ይቀጥላል፤›› በማለት አመልክተዋል፡፡
ለበዓለ ሢመቱ በተሰራጨው የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ማትያስ አጭር የሕይወት ታሪክ መጽሔት፤ ዕርቀ ሰላምን መመሥረት በሚል ርእስ በቀረበው ጸሑፍ የሚከተለው ቃል ሰፍሯል፡፡
ብፁዕነታቸው በውጭ ዓለም የሚኖረውንና በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድነት የራቀውን ሕዝበ ክርስቲያን ወደ አንድነት ለማምጣት ያደረጉት አስተዋፅኦ ሌላ ተጠቃሽ ተግባቸው ነበር፡፡ ዕርቀ ሰላምን ለማድረግ የትኛውም አካል ባላበበት ዘመን ብፁዕነታቸው ስለ ዕርቀ ሰላም ያስቡም ይደክሙም ነበር፡፡
ለዚህም ተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አትላንታ ጆርጂያ በማምራት የውጭው ሲኖዶስ አባላት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንእንዲሁም ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን አነጋግረዋል፡፡ ከዚህም ንግግር በኋላ ለኢትዮጵያ ሲኖዶስ መልእክት በመላክ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር መሠረት ጥለዋል፡፡ ይ በጵጵስና ዘመናቸው የጀመሩ ሁለቱን ሲኖዶስ አንድ የማድረግ እንቅስቃሴ የሚቀጥል ይኾናል፡፡
የበዓለ ሢመቱ ሙሉ ዘገባው በተከታይ ይቀርባል
 Source:http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. good news this what we expect from both side at least lets unite with all the difference then other things will be solved through time..God Bless the EOC..Amen

    ReplyDelete