Tuesday, March 26, 2013

የኮሌጁ መምህራን ደቀ መዛሙርቱን ትምህርት ለማስጀመር እየጣሩ ነው

Dr Aba Hailemariam Melese
ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ
(የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል ዋና ዲን)

  • መምህራኑም ከፍተኛ የአስተዳደር በደል እንደሚደርስባቸው ተናገሩ
  • ፓትርያሪኩ÷ ተጠያቂዎች በጥናት ተለይተው ርምጃ እንዲወሰድ መመሪያ ሰጥተዋል
  • የመብት ማስከበር እንቅስቃሴው የመናፍቃን መጠቀሚያ እንዳይኾን ጥንቃቄ ያስፈልጋል
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን÷ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርት በማቋረጥና ከምግብ በመከልከል የጀመሩትን አካዳሚያዊ መብትን የማስከበር የተቃውሞ እንቀስቃሴ አቁመው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የማግባባት ጥረት መጀመራቸው ተገለጸ፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞ ያነሡባቸው የኮሌጁ ሁለት ሓላፊዎችና የጠየቋቸው አካዳሚያዊ መብቶች ጉዳይ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ መታየቱንና በጥልቀት እንዲጠና በፓትርያሪኩ መመሪያ የተሰጠበት መኾኑን ዋስትና በማድረግ ነው መምህራኑ ደቀ መዛሙርቱን የማግባባት ጥረት መጀመራቸው የተመለከተው፡፡

በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ የሚመራውና ሦስት የኰሌጁ መምህራን በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ ትላንት ከቀትር በኋላ በጀመረው የማግባባት ጥረት መሠረት÷ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀውን የደቀ መዛሙርቱን ተቃውሞ እስከ ነገ፣ መጋቢት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. አስቁሞ የተቋረጠውን ትምህርት ለማስጀመር መታቀዱ ተገልጧል፡፡
ሦስት የኮሌጁ መምህራን የሚገኙበት ኮሚቴ የተቋቋመው አራት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች፣ የፖሊስና የጸጥታ አባላት ትላንት፣ መጋቢት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ከኮሌጁ አስተዳደርና መምህራን  ጋራ ለአራት ሰዓት የፈጀ ውይይት ካካሄዱ በኋላ መኾኑ ታውቋል፡፡ ‹‹ችግሩ እንዴት ይፈታ፤ ትምህርቱንስ እንዴት እናስጀምር?›› በሚል ርእሰ ጉዳይ በተካሄደው ውይይት÷ ደቀ መዛሙርቱ በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት (ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ) በግልባጭ ደግሞ ለኮሌጁ አስተዳደር፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለአዲስ አበባ ወጣቶች ቢሮ፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ባደረሱት ደብዳቤ የጠቀሷቸው ችግሮች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በቀደሙት ዘገባዎች እንደተገለጸው÷ ደብዳቤው በዋናነት አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን የሚዘረዝር ሲኾን የችግሩ መገለጫምሙስናና የአሠራር ብልሹነት ነው፡፡
ሙስና – በዕቃ ግዥዎች፣ ሙስና – በሕንጻ እድሳትና በሕንጻ ኪራይ፤ የአሠራር ብልሽት – በበጀት አጠቃቀም፣ በምግብ ቤት፣ በዶርሚተሪ፣ በመማሪያ ክፍሎች፣ በቤተ መጻሕፍት፣ በሕክምና አገልግሎት፡፡ የደቀ መዛሙርት የውጤት ምዘና ግልጽ አይደለም (በውጤት ማሳወቂያ ቦርድ ላይ B+ ኾኖ የተለጠፈ የአንድ ደቀ መዝሙር ውጤት በወረቀት F ኾኖ የተሠራበት አብነት ቀርቧል)፤ የመምህራን ምደባው ጥቂቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሚበዙትን መምህራን የሚያገል (ማስተማር ከጀመሩ በኋላ ተማሪን ለተቃውሞ ታነቃቃላችኹ፤ ታሳምፃላችኹ በሚል ኮርስ የተነጠቁ፣   የስለላ ዐይነት ተግባር የሚካሄድባቸው ምስጉን መምህራን አሉ)፣ ተደራራቢ ኮርስና አስተዳደራዊ ሓላፊነት የያዙ መምህራን በስብሰባ ሰበብ መቅረት የሚያበዙ፣ ተማሪውንና መምህሩን የሚያሸማቅቁ፣ የሚሳደቡና የሚደበድቡ፣ በቢሯቸው ተገኝተው ባለጉዳዮችን የማያስተናግዱ፣ ዝግጅታቸውም የትምህርት አሰጣጡን የሚበድል ነው፡፡
ጥቂቶችን ተጠቃሚ ከሚያደርገው የመምህራን ምደባ የተገለሉ ብዙኀን መምህራን በቂ የክፍያ/የደመወዝ ማበረታቻ አለማግኘታቸው፣ ተሻሽሏል በተባለው ሥርዐተ ትምህርት በቂ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ዕድል መነፈጋቸው፣ ለማስተማር ያላቸው ተነሣሽነትና በኮሌጁ መሻሻል ላይ ያላቸው ተስፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሟሟተ መኾኑ፣ ደቀ መዛሙርት ከምረቃ በኋላ የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛነት እንዲሁም የኮሌጁ አስተዳደራዊ መዋቅር÷ ሥልጣንና ተግባርን ከሓላፊነትና ተጠያቂነት ጋራ በግልጽ አሟልቶ የሚሰጥ አለመኾኑ ለችግሮቹ መባባስ አስተዋፅኦ ማድረጉን በውይይቱ ላይ መግባባት እንደተደረሰበት ተዘግቧል፡፡
በውይይቱ÷ የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎች፣ መምህራኑና በተዋረድ የሚገኙ ሌሎች የአስተዳደር ባልደረቦች ያነሷቸው አቤቱታዎች ትክክለኛና ተገቢ መኾናቸው እንደታመነባቸው ተገልጧል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ባለመብላት ተቃውሟቸው ማጠናከራቸው ከታወቀና ስድስት ተወካዮቻቸው በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ቀርበው እንዲያስረዱ ከተደረገ በኋላ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሰጡት መመሪያ መሠረት ችግሩን የሚያጠና ኮሚቴ በመቋቋሙ የተቋረጠው ትምህርት መቀጠል እንደሚገባው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች አሳስበዋል፤ ለዚህም መምህራኑ ደቀ መዛሙርቱን የማሳመን ሥራ በመሥራት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ከሁሉ በፊት ሁለቱ ሓላፊዎች ከቦታቸው ካልተነሡ ትምህርት አንጀምርም፤ ምግብ ባለመመገብ የቀጠልነውን ተቃውሞ አናቆምም››ከሚለው የደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞ የተነሣ መምህራኑ ተልእኮውን ለመቀበል ተቸግረው የታዩ ሲሆን ዋስትና እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡ ‹‹ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ የቤተ ክርስቲያን አመራር የለም፤›› ያሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፣ ጉዳዩ በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ታይቶ መመሪያ የተሰጠበትና የመንግሥት አካልም የሚከታተለው በመኾኑ በችግሩ መፈታት መመምህራኑ ጥርጣሬ ሊገባቸው እንደማያስፈልግ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ይህን ተከትሎ ሦስት መምህራን የሚገኙበትና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥረት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት÷ ደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር፣ በሙስናና በአሠራር ብልሽት የተዳከመው ኮሌጁ አስተዳደራዊ ችግ ሮቹ በአፋጣኝ ታርመው እንደ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ተቋምነቱ ተልእኮውን እንዲወጣ የሚያካሂዱትን እንቅስቃሴ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኀይሎች መጠቀሚያ ለማድረግ ሙከራ የሚያደርጉ ቡድኖች መታየታቸው ተመልክቷል፡፡
ሙከራው ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በተቃውሞ እንቅስቃሴው ሰበብ በኦርቶዶክሳዊ ቀናዒነታቸው የታወቁ መምህራንንና ሓላፊዎችን አስወግዶ የተቋሙንና የትምህርት አስተዳደሩን መቆጣጠር መኾኑ ተጋልጧል፡፡ ከእኒህ ኀይሎች መመሪያ እየተቀበሉና በደቀ መዛሙርት ተቃውሞ ሥር እየተጠለሉ እንቅስቃሴውን ሌላ መልክ ለመስጠት ከሚያሤሩ የውስጥ ቡድኖችና የውጭ ተባባሪዎቻቸው መጠንቀቅ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ በኮሌጁ ምክትል ዋና ዲን ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ በተመራውና የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ባልተገኙበት በትላንቱ ውይይት÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፣ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ የትምህርትና ሥልጠና መመሪያ ሓላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና የአስተዳደር መምሪያ ሓላፊው ተገኝተዋል፡፡
Source: http://haratewahido.wordpress.com/ 
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment