Tuesday, January 22, 2013

ጉባኤ ኬልቄዶን vs. የጥር 6 የሲኖዶስ ጉባኤ


ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን
ጉባኤ ኬልቄዶን ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በመልካም አርአያነት ሊወሰድ ይገባልን?

(አንድ አድርገን ፤ ጥር 10 2005 ዓ.ም)፡- ቤተክርስቲያን እስከ 451 ዓ.ም ማለትም እስከ ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በመላው ዓለም  ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ አንድ ዶግማና አንድ ቀኖና ነበራት፡፡ ይህ ጉባኤ ግን ቤተክርስቲያንን ከሁለተ ከፈላት፡፡ ነባሩን ሐዋርያዊ አስተምህሮ የያዙት ተዋህዶዎች  የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት(Oriental Churches) በመባል የሚጠሩት  ኢትዮጵያ ፤ ግብጽ ፤ አርመን ፤ ሶርያና ሕንድ  የያዙት መለካውያን በመባል የሚታወቁት ደግሞ የምዕራብ አብያተክርስቲያናቱ (Occidental Churches) ላቲኖችና ግሪኮች ናቸው፡፡ በእነኚህ ሁለት ክፍሎች ጉባኤው ቤተክርስቲያንን ለሁለት ከፈለ፡፡  አስቀድሞ በ325 ዓ.ም በኒቂያ  ፤ በ381 ዓ.ም  በቁስጥንጥኒያ ፤ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን የተደረጉት ጉባኤዎች (ሲኖዶስ) ቤተክርስቲያን የገጠማትን ፈተና በመጋፈጥና በአንድ ድምጽ በመወሰን  የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡  ጉባኤዎቹ የሚጠሩበት  ምክንያትም ሐዋርያዊ ያልሆነ አዲስ የክህደት ትምህርት ተከሰተ ሲባል ነበር፡፡


አራተኛው ጉባኤ(ሲኖዶስ) ሲጠራ ግን የተጠቀሰ ምክንያት አልነበረም፡፡ በኋላ ላይ ግን ለጉባኤው መጠራት  መንስኤ የነበረው የስልጣን ወይም የወንበር ሽሚያ  መሆኑ ታወቀ፡፡  ውጤቱም የዶግማ ልዩነት የፈጠረና ለሁለት መሰንጠቅ ግድ አለ፡፡ ለስልጣን ሽኩቻው መነሻ የነበረው የእስክንድርያን መንበር ነጥቆ ለቁስጥንጥንያ ለመስጠት እና የበላይ ነን ያሉ  የነበሩ የሮማው ጳጳስ በእስክንድርያው ፓትርያርክ  መወገዝ የፈጠረው የመበቀል ፍላጎት ነበር፡፡ ነገር ግን ያለምንም ምክንያት ይህንን ማድረግ ስለቸገራቸው እስክንድርያዎችን በጸብ ያለሽ በዳቦ  ከጉባኤ ለማስወጣት ግድ አላቸው፡፡ 25ኛው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ነገሩ ገብቶት ነበርና  ድንገት በመነሳት ሐዋርያዊውን አስተምህሮ ገልጦ ከዚያ የወጣ የተወገዘ ነው ብሎ  አወገዘና ከጉባኤው ወጣ፡፡

የተቀሩት ግን ጉባኤውን እንዲጠራ ካደረገው የቁስጥንጥንያው ንጉሥ መርቅያን ጋር  በመሆን አዲሱን የሁለት ባህርይ የክህደት ትምህርት  አጽድቀው ወጡ፡፡  የንጉሡ ሚስት ብርክርያ አውግዞ የወጣውን የእስክንድርያውን  ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን አስጠርታ ልታግባባው ሞከረች ፤ አልሆን ሲላትም ጺሙን አስነጭታ ፤ ጥርሱ እስኪረግፍ አስደበደበችው፡፡ ስለ አንዲት ሃይማኖቱ ሰማዕትነትን ለመቀበል ቆርጦ ነበርና ከአቋሙና ከእምነቱ ፍንክች አላለም፡፡ ምንም ቢያደርጉት ሃይማኖቱን የማይቀይር መሆኑን ስለተረዱ እሱን በደሴተ ጋግራ አስረውና ከቤተክርስቲያን ሥርዓት ቀኖና ውጪ ከፕትርክናው ሽረው ፕሮቲሪዮስ የሚባለውን መለኮታዊ መነኩሴ በእሱ ቦታ ፓትርያርክ አድርገው ሹመው ላኩት፡፡ በግብጽ ክርስትያኖች ግን “የእኛ አባታችን ዲዮስቆሮስ ነው ፕሮቲሪዮስን አናውቅም አንቀበለውም” አሉ፡፡ ንጉሡ መርቅርያን በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ ከሠራዊቱ 2000 ያህል ላከ ፡፡ ሕዝቡ ግን ቁጣው እጅግ አይሎ በተነሳው ረብሻም አዲሱ ፓትርያርክ ሞተ፡፡ በመሀሉ በእስር ቤት ያለው አርበኛው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ በእስር ቤት እንዳለ ዐረፈ፡፡ እሱ ካረፈ ከሶስት ዓመታት በኋላ ምዕመናን ራሳቸው መርጠው ጢሞቲዎስን ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት እሱም የእነ አትናቲዎስንና የእነ ቄርሎዎስን ፍኖት የተከተለ ምስጉን ፓትርያርክ ሆነ፡፡

ጉባኤ ኬልቄዶን የፈጠረው ችግር ግን ዛሬም ድረስ ግን ቤተክርስቲያንን እንዳመሰ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ደጋግ አባቶችና ነገሥታት የተለያዩ ወገኖች ጠፍቶ መቅረት አሳስቧቸው የጠፋውን ወገን ለመመለስና ቤተክርስቲያንን ለማዋሃድ ብዙ ጥረት አድረገዋል፡፡  ፈጽሞ  ሊሳካላቸው ግን አልቻለም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ነገሥታት ጣልቃ ገብነትና  የሥልጣን ሽኩቻ ቤተክርስቲያንን ለምን ዓይነት ችግን እንደሚዳርጋት ምሳሌ ሆኖ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡ በእርግጥ ከዚህ አስቀድሞ ቤተክርስቲያንን የነጠቀና ለእንደዚህ አይነት የከፋ አደጋ የዳረገ አይሁን እንጂ የመንግሥት መሪዎች ጣልቃ ገብነት በቤተክርስቲያን ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ለመንበረ ማርቆስ 20 ፓትርያርክ የነበረው በሊቅነቱ እና በተጋድሎ ርዕሰ-ሊቃውንት ወጻድቃን በመባል የሚጠራው ቅዱስ አትናቲዎስ የደረሰበት ችግር ምክንያት ሰባት ጊዜ መንበረ ፕትርክናውን ጥሎ እንዲሰደድ ሲያደርጉት አምስት ጊዜ ደግሞ እንደገና እየመለሱ ሹመውታል፡፡

ሌላው ደግሞ በትምህርት ጣዕምና አመስጥሮው “አፈወርቅ” የሚል ቅጽል  የተሰጠው የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስም ጨካኟ ንግሥት አውደክያስ የሰው ንብረት በመቀማቷ የተቀማው ሰው መጥቶ “አባቴ ሆይ ፍረድልኝ ንብረቴን በግፍ ወሰደችብኝ” ብሎ ሲያመለከተው እንድትመልስላት ለመናት ፤ ንግሥት አውደክያስ እምቢ ስትለው አወገዛት፡፡ በዚህ አቂማ ቤተክርስቲያን ላይ መከራ ለማምጣት ዛተች፡፡ ሕዝቡ ሁሉ “ስለ አባታችን ለመሞት ዝግጁ ነን”  ብለው ቤታቸውን ጥለው ሌት ተቀን ይጠብቁት ያዙ፡፡ እሱ ግን በእኔ ምክንያት ሕዝቡንና ቤተክርስቲያንን ለችግር አልዳርግም ብሎ ራሱን ለውጦ በለሊት ሀገረ ስብከቱን ጥሎ ተሰደደ፡፡ እነኚህና ሌሎችም አባቶች እንዲህ  በማድረጋቸው እንደ ክህደት አልተቆጠረባቸውም ፤ ይልቁንም ሰማዕታት ተባሉ እንጂ፡፡ አስቀድሞ ክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌሉ ሐዋርያትን ጠርቶ ወደ ዓለም ሲልካቸው “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ” ማቴዎስ 10፤23  ብሎ አዝዟችዋልና፡፡

እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለው ይህንን ሆኖ ሳለ ዛሬ  ግን ብጹአን አባቶች ምዕመናን ምንም አያውቁም በሚል አስተሳሰብ ይመስል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን በደረሰባቸው ችግር በመሰደደዳቸው ጥፋት እንደሰሩ ፣ ምንም ቢደርስባቸው መጋፈጥ እንደነበረባቸው በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ይስተዋላሉ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስን  ይህ ጠፍቷቸው ሳይሆን ጳጳሳትም ሳይቀሩ ሲተባበሩባቸውና በጊዜው ከአንድ አባት በስተቀር በቁርጠኝነት በጎናቸው የሚቆም ሲያጡ ግን ምንም አማራጭ አልነበራቸውምና ተሰደዱ፡፡ በሌላ በኩል ግን ብጹአን አባቶች ከላይ የጠቀስናቸውን እነ አትናቲዎስ ፤ እነ ዲዮስቆሮስን ፤ እነ ዮሐንስ አፈወርቅን እና ሌሎችንም የተዋህዶ አርበኞች በማለት በኩራት ይዘክራሉ ፤ ያወድሳሉ፡፡

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ዛሬ አባቶቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እጣ ፋንታ የሚወስን ከባድና አሳሳቢ ጉዳይ እጃቸው ላይ ወድቋል፡፡ ሊያደርጉት እየተዘጋጁበት ካለው ጉዳይ አንጻር ግን የጉዳዩን አሳሳቢነትና ክብደት እንዳልተረዱትና ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ነገሩን ያለቅጥ አቅልለው እንዳዩት ያመለክታል፡፡ ዛሬም ቆራጥና አስተዋይ መንፈሳዊ አባቶች ካሉን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከዚህ ከተጋፈጠችው አደጋ ለመታደግ አይደለምና ቀላሉን ነገር ነፍሳቸውንም አንኳ ለመስጠት ራሳቸውን ከማዘጋጀት ወደ ኋላ የሚሉ አይሆኑም፡፡ የሚገርመው ግን የተጋፈጠውን ፈተና ይህንን ያህል መስዋዕትነት እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አለመሆኑና ፍቅርን በማሳየት ፤ እልህንና ካፈርኩ አይመልሰኝ በመተው ፤ ከግል ጥቅም በመተው ቤተክርስቲያንን ጥቅም በማስቀደም ፤ ለተቀቡበት ሰማያዊ አገልግሎት ታማኝነትን በማሳየት በቀላሉ የሚፈታ መሆኑ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን ይህ የገጠመን ፈተና ያለንን ጥንካሬና ጽናት የፈተነና ያጋለጠ ሆኗል፡፡ በቀላሉ ፈተና እንዲህ የሆንን መስዋዕትነት የሚጠይቅ ከባድ ፈተና ቢያጋጥመን ኖሮ  ቤተክርስቲያንን እንዴት ልናደርጋት ኖሯል ? በትንሹ መታመን ያልቻልን በብዙ ፤ በቀላሉ መታመን ያልቻልን በከባዱ እንዴት ነው ልንታመን ልንጸና የምንችለው? የሚል ትዝብት ያዘለ ጥያቄ ለራሳችን እንድናነሳ አድርጓል፡፡ እንግዲህ የአዲስ አበባዎቹ ብጹአን አባቶች በ”ካፈርኩ አይመልሰኝ” ስሜት በመገፋፋትና በመገደድ አዲስ ፓትያርክ  ለመሾም በወሰኑበት ወቅትም ስደተኛው ሲኖዶስም እኛ ያጎደልነውም የጣስነውም ሕገ-ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ የምናፍርበት ፤ መንፈሳዊ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት የምናቆምበት አንዳች ምክንያት የለም በሚል ስሜት እየተናገሩ ነው፡፡ እንደሚባለው ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሳያርፉ በሳቸው መንበር ሌላ ፓትርያርክ መርጠው የሚስቀምጡ ከሆነ ቤተክርስቲያኗ ለሁለት መከፈሏ ገሀድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ ሥልጣንን አመካኝቶ የሚፈጠር መከፋፈል ፍጻሜው የት እንደሚያደርስ በተደጋጋሚ ታይቷልና የዚህኛው ችግር  እጣ ፈንታም ካለፉት የቤተክርስቲያን ፈተናዎች  የተለየ አይሆንም፡፡ ይህንን አደጋ ለማስቀረት  ብጹአን አባቶች ብልህ ፤ አስተዋይ ፤ ትሁት ፤ ታጋሽ ፤ እንዲሁም ይቅር ባይ  ሆነው ወንጌሉን በተግባር አልተረጎሙልንም ፤ አባቶች ቤተክርስቲያንን ከሚጎዳ ራሳቸውን በታሪክ ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ወገን  የሚያስቆጥር ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ ብዙ ተጥሯል፡፡

ማንም የቤተክርስቲያንን ታሪክ አውቃለሁ ፤ ለአምላክ ታማኝ አገልጋይ ነኝ የሚል አባት ይህንን ግልጽ ያፈጠጠ እና ያገጠጠ አደጋ ሊረዳ የማይችልበት  አንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ ቢመስለን ነው እንጂ ይህንን የተሳሳተ ውሳኔ በመወሰን ምንም የምናተርፈውና የምንጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡ የምንጎዳው ፤ የምናጣው ፤ የምናጎለው ግን በእርግጠኝነት ይኖራል፡፡ ከምንም በላይ ቤተክርስቲያንን እናጣታለን፡፡ ሊመጣ ያለው አደጋ እንዲህ ግልጽ በሆነበት ሁኔታ በቤተክርስቲያን ላይ ያንዣበበ ምንም አይነት አደጋ እንደሌለ የሚቆጥር ወይም የሚስብና የተጋፈጠውን ችግር ማየት የማይፈልግ ሰው ካለ ይህ አርቆ የማሰብ ችግር ሳይሆን የአላማ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ቤተክርስቲያን የገጠሟት ፈተናዎችና ችግሮች የበግ ለምድ ለብሰው የገቡ ተኩላዎች እንደፈጠሩት ሁሉ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም መሰል እንቅስቃሴዎች ተከስተዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡ በእግጥ ከሁለቱም ወገኖች በስም ተለይተው የሚታወቁ በሊቃውንት የተገሰጹ እንዲህ አይነት ግለሰቦች እንዳሉ ይተወቃል፡፡ የገበያ ግርግር ለምን ያመቻል እንዲሉ አሁን ቤተክርስቲያናችንን የገጠማት ችግር ለእነኚህ ግለሰቦች  የጥፋት ዓላማ ስኬት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ የማይቀርና ግልጽ ነው፡፡

እንግዲህ ያለው ነገር ይህን ያህል ግልጽ ከሆነ ካህናትና ምዕመናን ቤተክርስቲያናቸውን ለመታደግ መንቃት ግዴታችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት  ሁኔታው የሚረጋጋና መስመር የሚይዝ ከሆነ ለቀኖና እንዲበቁ ለማድረግ እንዲሁም ይህን ታሪካዊና  ቀኖናዊ ስህተት ያለበትን ውሳኔ ለመወሰን እያደቡ ያሉትን ሰዎች ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሳይገባቸው በየዋህነት እያገዙ ያሉትን አባቶች ደግሞ በተቻላቸው አጋጣሚ ሁሉ በመቅረብ ከዚህ  ቤተክርስቲያንን ለአደጋ የሚዳርግ ስህተት ውሳኔ እንዲታቀቡ  ጉዳዩን በሚገባ በማስረዳት የተጣለብንን ክርስቲያናዊ ግዴታ መወጣትና ቤተክርስቲያናችንን መታደግ ይኖርብናል፡፡ ነገሩ እንዴት ነው ወገን ? እንደ አንድ አማኝ ኃላፊነትም ይሰማን እንጂ ? እግዚአብሔርንም እንፍራ መድኃኒዓለም ክርስቶስ የቸርነቱን ስራ ይስራልን ፤ እንደ ስራችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ ይቅር ብሎ ይታረቀን ፡፡ቤተክርስቲያንን ከመፍረስ ይታደግልን… አሜን

የአንድ ሰው ሃሳብ
የልጅ ልጆቻችን በእኛ ዘመን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሁለት የሆነችውን ቤተክርስቲያን ልናወርሳቸው ግድ የሆነብን ይመስላል ፡፡ እኛ በዚህ ዘመን ሆነን ደጋጎቹ አባቶቻችን ስለ ቤተክርስቲያን ብለው ያደረጉትን መልካም ጉባኤያት በመጥቀስ በዚህ ጊዜ እንዲህ  ሆነ እንላለን ፤ ልጆቻችንስ የእኛን ዘመን ምን ብለው ያንሱት ? የምንሰራውን ብቻ ሳይሆን ሰርተን የምናልፈውንም ነገር እናስተውል ፤ ልጆቻችን ሙት ወቃሽ አናድርጋቸው ፤ በእኛ ችግር እነሱ ለምን ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ? እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ለሚያልፍ ዕድሜያችን ጥሩ መስራት ቢያቅተን እንኳን ያለውን ማስቀጠል ያቅተን ?  ሞት አንዱን ከቅዳሴ አንዱን ከህዳሴ ሲጠራ እየተለመከትን እንዴት እኛስ አንማርም ?  ከዚህ በላይ የሰላም አጋጣሚ ማግኝት እንደ ሰውኛ አዳጋች ይሆናል ብለን እናስባለን ፤ በዚህ ወቅት ያልጠበቡ ልዩነቶች ከአሁን በኋላ በሚደረጉ ድርድሮች ይጠባሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ፤ አንድም ምክንያት ይኑረን መቶ ከሁለት በላይ የሆነች ቤተክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ተዘጋጅተናል ፡፡ ሀላፊው ጠፊውና ከዘላለማዊው በአንድ መንገድ ለማስኬድ እየሞከርን እንገኛለን ፡፡ በዘመን ሰው ማጣት አለመታደል ነው ፤ አሁን አባቶች የያዙት አካሄድ ለሁላችን የመጀመሪያ ሽንፈት ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ግን መሸነፍ ያለብን አይመስለንም ፤ ከሁለት ያጣች ሆነን ያሳለፍነው 20 ዓመት ሁለት መቶ ሆኖ እንዳይመጣብን በዓላማ ለዓላማ በአንድ ልንቆም ይገባናል ፡፡ እርቀ ሰላሙን እንዲህ ዘጉት …ቀጣዩ የፓትርያርክ ምርጫስ እንዴት ይሆን ?

ጉባኤ ኬልቄዶን ቤተክርስቲያንን ሁለት ቦታ ሰነጠቃት… ይህን የእኛን ዘመን ደግሞ ጉባኤ ምን እንበለው…?

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment