Thursday, January 24, 2013

ልናስተውል ይገባናል!

ዛሬ ቆም ብለን የምናስብበት ወቅት ነው!
አንድ አንባቢ የላኩልን መልዕክት ደርሶናል መልዕክቱ ጥሩ ስለሆነ እና አንባቢያን ቢያነቡት ይማሩበታል ወይም ይጠቀሙበታል ብለን ስላሰብን አቅርበነዋል።
መልካም ምንባብ . . .

ጽሑን በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ


ልናስተውል ይገባናል!

ይሄን ጽሑፍ ልጽፍ የተነሳሁት በደጀሰላም “ሁሉም “የማንም አሿሿሚ አልሆንም! የሥልጣን ጥመኞችንም አላገለግልም!” ቢል” በሚል የተነበውን ጽሁፍ ካነበብሉ በኃላ ነው ጸሓፊው “መልዕክተ ተዋሕዶ-ዘኪሮስ” በመባል ይታወቃሉ መልዕክቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ ትክክለኛ ሆኖ ሳለ ከታች የተሰጡ አስተያየቶችን ሳነብ በጣም አዘንኩ! እንዴት አይነት ዘመን ነው ብዬም አሰብኩ ከዛም እኔስ እስኪ በጎለድፌ ብዕሬ ለምን አልጽፍም ቤዬ ጀመርኩ፣ አንባቢ ያግኝም አያግኝም ሃሳቤን ለመግለጽ ወደድኩ ሚዛን ከደፋች አመልከቷት ካልደፋችም ደግሞ ወደ ሚመለከተው ላኳት።


በእውነት እጅግ የሚያሳዝን ጊዜ ላይ ደርሰናል እንደእውነቱ ከሆነ ሁሉም ወገን ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። በእውነቱ ጸሐፊው የተሰማቸውን ጽፈዋል የእኛ ክርስትና ጨዋነት የሚለካው አንዱ የተናገረውን አንዱ በመተቸት ሳይሆን የተሻለ ሃሳብ ነው ብሎ የሚያስበውን ቢያመጣ የተሻለ ውጤት ለቤተክርስቲያናችን ልናመጣ እንችላለን። ሲጀመር ጀምሮ ሰዎች ሰዎች ናቸው ዛሬ በውስጥም ሆነ በውጪ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ግድ የሌላቸው እንደሚኖሩ መጠበቅ ይኖርብናል እንጂ ገና ለገና እኛ የምናምነው አባት ተነካ ተብሎ ቡራ ከረዮ ማለቱም አግባብ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ሰዎችን ሳይሆን መዕከል ማድረግ ያለብን ቤተክርስቲያንን ብቻ ነው። በዚህ ዘመን ሰዎች ትላንት ብዙ መስዋዕትነት ሊከፍሉ ይችላሉ ነገ ደግሞ ማሊያ ቀይረው ቤተክርስቲያንን ሊያፈርሱ ይችላሉ፥ ስለዚህ ትላንት በጎ ሥራ ስለሰሩ ዛሬ ያፍርሱ መባል ያለባቸው አይመስለኝም እንደ ትክክለኛ የቤተክርስቲያን ልጅነታችን ከሆነ። ነገር ግን ተገፍተው ነው፣ ተገደው ነው፣ አቅም ስላጡ ነው እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ደርድሮ ከአፍራሽ ጋር መቆም እኛንም ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ስለማንለይ ድርጊታችን ወይም የምንከተለው ሰው በመጀመሪያ ለቤተክርስቲያን ብቻ የቆመ መሆን ይገባዋል። ነገር ግን ዛሬ ሆኖ ካልተገኘ እንደእውነቱ ከሆነ ልንመክረው፣ ልንነግረው፣ ወይም ልንለየው እንጂ የሚገባን ዝም ብለን በጭፍን ያደረገው ያድርግ ብለን ልንከተለው አይገባም የሚል እምነት አለኝ።
ሌሎች ወገኖች ደግሞ ስለ ማኅበር ይበልጥ ሲቆረቆሩ ይታያሉ እርግጥ ነው ማናችንም እንደምናውቀው ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ማኅበር ቢሆንም አሁንም ትልቁ ችግር ብዬ የማምነው ማዕከል ማድረግ ያለብን ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንጂ ማኅበራችንን መሆን የለበትም፥ ሲጀመር እኮ በማኅበር የተሰበሰብነው ለቅድስት ቤተክርስቲያን ዙሪያ ገባውን ከመናፍቃን ከከሃዲያን እና ከጠላት ልንጠብቃት እንጂ ማኅበራችንን ለመጠበቅ አይደለም። ቤተክርስቲያን ከሌለች እኮ ማኅበር ሊኖር አይችልም፥ ስለዚህ በቅን ልቦና እንመልከተው መታገል ያለብን መቆም ያለብን መጠበቅ ያለብን እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን የሚለቅ ቅሱስ ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን እንጂ ለማኅበር መሆን እንደሌለበት መገንዘብ ይኖርብናል ብየ አምናለሁ።
ሌላ መንግሥትን መናገር ወይ ዝም ማለት፤ በጽሁፉ ላይ ጸሐፊው እንደተናገሩት መንግሥት የዚህ ሁሉ ችግር እርሱ ነው፥ ሲጀመር አቡነ መርቆርዮስን ማባረር እና ለራሱ ለአገዛዙ የሚመች ጎጡን ወደ ቤተክርስቲያን ባያመጣብን መልካም ነበር፣ የሆነ ሆነና ላለፉት ሃያ አንድ አመታት ስናለቅስ ስናዝን እና ስንከፋፈል ኖርን። የዚህ ሁሉ ችግር ማዕከል ሰሪና ፈጣሪው መንግሥት እንደሆነ እንኳን እኛ ምራቅ የዋጥነው ዛሬ የናት ጡት የሚጠባ ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው፤ መንግሥት አሁንም እኔ አውቅላችኋለው ብሎ የራሱን ጎጠኛ ሊያስቀምጥ ሲሯሯጥ እኛም ተቀብለን አብረን መዘመር የለብንም አይሆንም ማለት ይኖርብናል። ማወቅ ያለ እስከ ዛሬ በሃገራችን እየተሰሩ ያሉት በርካታ ችግሮች በቤተክርስቲያን ላይ እየተዘመተባቸው ያሉት ክስተቶች ሁሉ መንግሥት በአንድም በሌላም እጁ አለበት ለአብነት ያህል
1/ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ሕልውና እና ተሰሚነት ለማጥፋት በመጀመሪያ ቤተክርስቲያንን ከፈለ፣ በመቀጠል የእስልምና ሃይማኖትን ቁጥራቸውን በውሸት አብዝቶ ብዙ ነን ብለው እንዲያስቡ እና የቤተክርስቲያኒቱን የበላይነት ለማሳጣት ያደረገው ታክቲክ ነው፣ ሌላው ደግሞ በዚህም በተከፋፈለች ቤተክርስቲያን ውስጥ በካድሬዎቹ አማካኝነት በዘር፣ በጎጥ፣ በወንዝ፣ በተራራ፣ ወዘተ በመሳሰሉት ለያይቶን አንዱ አንዱን እንዳያምን እና በጋራ ለዚህች ሀገር እንዳይቆም ወኔያችንን ሰለበው። በአጠቃላይ በከፋፍለህ ግዛው ስልቱ እርስ በእርስ ስንባላ መንግሥት እና የሕዋሃት አባሎች አንጡራ የሆነውን የዚህችን ሃገር ሃብት ዘርፈው በውጪ ባንኮች እና በትግራይ ላይ እያደረጁነው እኛ እርስ በእርሳችን እንባላለን፥ የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎች እነ አቶ አባይ ጸሀይ እና ስብሃት እና በርካታ የትግራይ ሕዋሃት የበላይ እና የበታች ሹማምንቶች አንጡራ የሆነውን የዚህችን ሃገር ሃብት እየዘረፉ ነው ስለዚህ ዝም ማለታችን ይቁም
2/ በርካታ አድባራት እና ገዳማት ተቃጥለዋል እየተቃጠሉም ነው ታሪክን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ዋነኛው ነው፣ እነሱም እንደተናገሩ በግልጽ “ኢትዮጵያን አፍርሰን እንገነባታለን” ብለውናል ኸረ ለመሆኑ ሃገር ፈርሳ ትገነባለች እንዴ? ሃገር እኮ ፎቅ ቤት አይደለም በርካታ የሃገራችን ብርቅዬ ልጆች የሞቱላት፣ ደማቸውን ያፈሰሱላት፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር እንዴት ነው የምናፈርሳት እና የምንገነባት? መልሱን ለእነሱ እንተው እና ወደ ቤተክርስቲያናችን ስንመለ  በርካታ ገዳማት ተቃጥለዋል፣ ክርስቲያኖች ታርደዋል፣ ገዳማት ታርሰዋል፣ ፋብሪካ ሊከፈትባቸው ነው፣ ለባለሃብት ይዞታቸው ተሰጥቷል ወዘተ . . .ለምሳሌ የአሰቦት ገዳም በተደጋጋሚ ተቃጥሏል መንግሥት እንደመንግሥትነቱ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ግዴታው ሆኖ ሳለ ለምን ለውን "ጸረ ሰላሞች" ናችሁ በማለት ስም ይሰጣል፣ በጅማ እና በኢሊባቡር ክርስቲያኖች ሲታረዱ ሲገደሉ፣ በእሳት ሲጠበሱ፣ ቤተክርስቲያናቸው ሲቃጠል እነሱም አብረው ሲጋዩ ለምን ክርስቲያኖች ለምን ይታረዳሉ ሲባል ሞታሉ፣ ይቃጠላሉ ሲባሉ "የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስነሳት የተነሱ አክራሪዎች" ችሁ ከተባልን እምኑ ጋር ነው የዜግነት መብታችን?
3/ ዝቋላ ገዳማችን ሲቃጠል መንግሥት ሆነ በቤተክህነት ያሉት የመንግሥት ጋሻ ጃግሬዎች መንግሥት ስንቱን ይስራ ይላሉ እሳት እንደማንኛውም ቦታ ተነሳ ተቃጠለ ብለው ባልተገራ ምላሳቸው ይነግሩናል። እውን ይሄ ማደናገሪያ ነው ወይስ ተቆርቋሪነት ነው? ልንመለከተው የሚገባው መንግሥት ቤተክርስቲያኒቱን ለማጥፋት በተለያየ ጊዜ የሚያደርጋቸው ጥፋቶች በሙሉ ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፥ እነ እገሌ ናቸው ወይም የውጪ ወራሪዎች ናቸው እያለ ስም በመስጠት ቀስ እያለ እየገደለን ነው ለዚህ ደግሞ ምስክሩ ዛሬ ቅዱስ ሲኖዶስን ሲወርስ ጥራሽ የራሳችን የምንላቸው ተቆርቋሪ ሆነው ሲኖዶሱ ስራውን ይስራ እያልን መከላከል ይዘናል። እውን አባቶቻችን ሥራቸውን መስራት ይችላሉ ጠብ መንጃ ተደቅኖባቸው? እውን ሃገርን እና ቤተክርስቲያንን ሊያጠፋ የመጣ ወንበዴ እኛ እንደምናስበው ዝም ብሎ ያልፈናል? እንዳይመስለን የዛሬ ዝምታችን የነገ ድንጋይ መንከስ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ።
4/ የዋልድባ ገዳም ሲታረስ እና የገዳሙ አባቶች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ በዘር እና በጎጥ ሲታመሱ ለማን ነው አቤት የሚባለው መንግሥት "ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት ሃይሎች " ናቸው ይላል ቤተክህነቱ ስለዋልድባ አያሰማን ይላል ስለዚህ የዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው መንግሥት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ይልቁንም ጸረ ልማት ሃይሎች የሚፈጥሩት ችግር ነው እየተባለ ሲነገረን እሺ ብለን ተቀብለናል፥ አባቶችን አስሮ መግረፍስ፣ ቆብን አውልቆ መደብደብስ? በችጋር እና በረሃብ መጥበስስ? በጎጥ እና በወንዝ መለያየትስ? ኸረ ስንቱ እሱስ ምን ሊባል ነው። ሃገር ስትለማ የሚቃወም ሰው አለ ለማለት ባልደፍርም የሚሰራውን ግን ይቃወማሉ ብዬ አላምንም ይሁን ተቃዋሚዎች ናቸው እንበል፥ ለምን ገለልተኛ አካል ሄዶ ቦታውን እንዲመረምር ቅዱስ ሲኖዶስ ወይም መንግሥት አያደርግም? ስለምንስ ለንግስ እና ለቡራኬ የሚሄዶ ምዕመናን ፈትሾ እና በርብሮ ማስገባት ለምን አስፈለገ? ምዕመናን እኮ ቤተመንግሥት አይደለም የሚሄዱት ቤተ እግዚአብሔር እንጂ እኮ ምዕመናኑ በታጣቂ ማስበርበር እውን እዚህ ጋር ትክክል ነው ብለን ነው የምንቀበለው? ለነገሩ የዛሬው መንግሥታችን እኮ የሚፈልገውን ተቃዋሚውን ገሎ፣ ሥጋውን ቆራርጦ በፍሪጅ ያስቀምጥ እና እንደገና አብሮ የሚያፋልግ ጭራቅ የሕዝብ ጠላት የኮሚኒስት ጥርቅም የሆነ መንግሥት ለመሆኑ ብዙ እና በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። ፖለቲካ ሳይሆን መንግሥትን መናገር፣ ቤተክርስቲያንን አትንካ ማለት ፖለቲካ አይደለም! ከሆነም ይሁን እንግዲህ። የሕዋሃት መንግሥት እጆቹን ከቤተክርስቲያን ላይ ያንሳንልን አሁንም እንጩኽ እሚሰማን እስክናገኝ ድረስ።
ይሄ ጦርነት ለማስነሳት ወይም እርስ በእርስ ለማጋጨትም አይደለም፣ ጥያቄው አንድ እና አንድ መሆን አለበት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ህልውናዋን ካጠፋ ማዕከል ሆኖ የህዝብን አንድነት የሚናገር አይኖርም ስለዚህ እናውቅልሃለን ባዮቹ አሁንም በተከበረው በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማድረግ ያለባችሁ እንዲህ ነው ካሉን እምኑ ጋር ነው መንፈስ ቅዱስ የመራው ስብሰባ የምንለው?
ወገኖቼ ዝም ብለን ጎጠኝነት ይዞን፣ ወገንተኝነት ይዞን ዛሬ እውነት መናገር ካልቻልን ቤተክርስቲያናችንን እንደዋዛ ልናጣት እንችላለን እንኳን እንዲህ ባለ ሊብራልነት በበዛበት ዘመን ቀርቶ በዘመነ ሰማዕታት እንኳን ጥቂት ሰማዕታት ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ክርስትና እኛ ጋር መድረስ ባልቻለ ነበር። ለቅድስት ቤተክርስቲያን ለዘር ባያስቀርልን ኖሮ ዛሬ ሁላችንም አረማውያን በሆንን ነበር ስለዚህ አሁንም በያለንበት ከወገንተኝነት፣ ከዘረኝነት፣ ከማኅበር ስሜት፣ ወይም ከአጥቢያ ስሜት ወጥተን ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንቁም፤ ሌላው ቢቀር እንደ ፊተኞቹ ታላላቅ ገዳማትንና አድባራትን ለማነጽ እና ለማሳነጽ ባንታደልም ሉትን እና የነበሩትን ብርቅ እና ድንቅ አድባራት እና ገዳማት መጠበቅ እንዴት ይሳነናል? ዛሬ እኮ እንደቀደሙት ሰማዕታት የደም መስዋዕትነት አልተጠየቅንም ነገር ግን እንዴት እውነት ለመናገር ተሳነን። ለቤተክርስቲያን ያልቆመ ከእኛ ሊሆን አይችልም፣ ስለመንጋው ሳይጨነቅ ስለሚያገኘው ምድራዊ ሹመት እና ክብር ለተጨነቀ ው እንዴት ብሎ ሰማያዊውን መንገድ ለኛ ያሳየና? አባትን ለመውቀስ ብቃት ባይኖረኝም፥ ዛሬም ተረፈ አሪዎሳውያን፣ ተረፈ ንስጥሮሳ በመካከላችን መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም።
በመጨረሻ ለማለት የምፈልገው በውጪ የሚኖሩ አባቶችን ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ብላችሁ የስህተት ስህተት አትፈጽሙ እስከ ዛሬ የተሰሩ ስህተቶች ታርመው ህዝብን እና ሃገርን አንድ ለማድረግ መጣጣሩ ለሁላችንም ሞገስ ነው ነገር ግን የሕዋሃት አመራሮች እንደሚያደርጉት እናንተም ከፋፍለህ ግዛው የምትሉ ከሆነ ከእነሱ በምንም ልትለዩ እንደማትችሉ ልታውቁት ይገባል። ቢያንስ እናንተ በሥጋ የወለዳችኋቸው ልጆች ባይኖራችሁም ለሚከተሏችሁ በርካታ ምዕመናን ልጆች ሕጻናት ስትሉ የሰላሙ መንገድ እስከ መጨረሻው ልትጠብቁ ይገባል፣ ዛሬ ጥቂት በሕዋሃት ከህዝብ በዘረፉት ገንዘብ የተታለሉ አባቶች ያሉትን ይዛችሁ እናንተ እንዲህ ካደረጋችሁ እኛም የባሰ እናጠፋለን የሚለውን የሞኞች በትር ስለቅድስት ቤተክርስቲያን ብላችሁ፣ ለማታበ ቃሉ ብላችሁ ታገሱ እባካችሁ ከትውልድ ወቀሳ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደማታመልጡም ልታውቁ ይገባል።
ዛሬ ከፋፍላችሁን ብታልፉ ነገ ካለፋችሁ በኃላ ሥጋችሁ እንኳን ሊሸከመው የማይችለው የታሪክ ወቀሳ እና እርግማን እንደሚደርስባችሁ እወቁት ተረዱት።
ሌላው ምዕመናን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንኖር በሙሉ ዋናው መርሳት የሌለብን ነበር ለማስታወስ ትላንት ቅድስት ቤተክርስቲያንን በብዙ ተጋድሎ ለእኛ ያስረከቡንን አባቶቻችንን እናስታውስ፥ ደሙን በቀራኒዮ አደባባይ አፍስሶ መድኅን የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ እናስታውስ፥ ሐዋርያት በሰበሰቧት አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት እናታው ትላንትናም ዛሬም ነገም ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ብለን ለልጆቻችንም እንንገር እኛ እነ እገሌ አይምጡብን የእራሳችን እንመሰርታለን፣ እኛ ትክክለኛ ነን፣ የሚሉንን ወግዱ ልንላቸው የሚገባ ጊዜ ላይ ደርሰናል አምላካችን በውስጥም ሆነ በውጪ እንደ መዥገር ተጣብቀው ቤተክርስቲያንን ለመለያየት፣ ለመከፋፈል ምክንያት የሆኗትን አባቶችም ሆነ ምዕመናን ዛሬ የንሰሐ ጊዜ ነው ዝም ብለ ጎጣችንን ሰብስበን ወይም ስለወንዝ እና ምንጭ እምናወራ ከሆነ ድህነት ልናገኝ አንችልም ዚህ መንገድ ጽድቅ የለም ስለዚህ አምላከ ጻድቃን ሰማዕታት በጅራፉ እየገረፈ ከምዕመናን ጀርባ ተደብቀው የሚከፋፍሉንን እስኪለይልን ድረስ በአንድነቷ እንጽና ለበለጠው ክብር እንዘጋጅ ሕዋሃት የሰጠንን የመገነጣጠል ጸበል የመለያት ኪኒን የተጎነጨን ከምንከፋፍል እና እራሳችንም ከምንከፋፈል፣ መጀመሪያ ቆመን በረጋ መንፈስ እናስበው ከዛም የተሰጠንን ኪኒን አሽቀንጥረን ጥለን አንድነትን እንስበክ ለዛሬም ሆነ ለነገው ትውልድ የሚያስፈልገው አንድነት ብቻ ነው በመለያየት ይሄ ጎጥ ያኛው ወንዝ ወይም ያኛተራራ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ሊያስገባን ቀርቶ ሊያሳየን ስለማይችል ሃክ እንትፍ ልንለው ይገባል።
ይቆየን
ፍኖተ አበው ነኝ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. From the beginning they are intended to gradually abolish EOTC. Let`s plan & do some thing. We need Coordinator!

    ReplyDelete