Monday, January 14, 2013

ሰበር ዜና – ዐቃቤ መንበሩ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ተሰማ

  • ዕርቀ ሰላሙንና የፓትርያሪክ ምርጫውን በተጓዳኝ እንዲካሄድ ለማስወሰን ታስቧል
  • ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉት አባቶች አቋምና ብዛት እየተጠናከረና እየጨመረ ነው
  • የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ደብዳቤ ጽፏል
  • ከ4ው ፓትርያሪክ ጋራ ፊት ለፊት መወያየት ቀጣይ የመነጋገሪያ ነጥብ ነው ተብሏል
ቅ/ሲኖዶስ በነገው ዕለት አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ለመቀመጥ በሚዘጋጅበት ዋዜማ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ መጠየቃቸው ተሰማ፡፡ ዐቃቤ መንበሩ ጥያቄውን ያቀረቡት ለመንግሥት አካል በጻፉት ደብዳቤ ነው ተብሏል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት (አቶ ኣባይ ፀሃዬ እና ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም) በሳምንቱ መጨረሻ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ቢሮ ተገኝተው ከተወያዩ በኋላ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ጥያቄው ስለቀረበበት ምክንያት የዜናው ምንጮች ሲያስረዱ÷ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› በሚል ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚደረገውን ዝግጅት በሚቃወሙ ብዙኀን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋራ ግንኙነት የለውም፤ ሁለቱም በተጓዳኝ/በትይዩ ሊከናወኑ ይችላሉ›› በሚሉ ጥቂት ነገር ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው በሚባሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በተያዘውና ከዕለት ወደ ዕለት እየተካረረ በመጣው ፍጥጫ ሳቢያ ነው ብለዋል፡፡
ከቅ/ሲኖዶስ አባላት አልፎ የአገልጋዩና ምእመኑ አጀንዳ የኾነው የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንዲሁም ቀጣይ አመራር ጉዳይ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አቋም በማራመድ የሚታወቁትን ብፁዓን አባቶች (ለመጥቀስ ያህል÷ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልንና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን) ሳይቀር በተለያየ ጎራ ያሰላለፈ መኾኑ ለጉዳዩ ክብደት በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡
የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ነገ፣ ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ ሲጀመር የምልአተ ጉባኤው ቀዳሚ አጀንዳ የዕርቀ ሰላሙ ቀጣይነት እንደኾነ ተነግሯል፡፡ በነገው አስቸኳይ ስብሰባ ከኅዳር 26 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ በተደረገው ሦስተኛው ዙር ጉባኤ አበው ላይ የተሳተፈው የዕርቀ ሰላም ልኡክ የደረሰበትን ‹‹የውሳኔ ሐሳብና ተያያዥ ጉዳዮች በሪፖርት መልክ አቅርቦ›› /የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንደገለጹት/ መወያየትና ከጥር 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም በሎሳንጀለስ ካሊፎርኒያ ለሚካሄደው አራተኛውና ወሳኙ ዙር ጉባኤ አበው ቀጣይ የመነጋገሪያ አቋሞችን ማስቀመጥ ዋነኛው ቁም ነገር ነው፡፡
የዜናው ምንጮች ባደረሱት ጥቆማ÷ በአንዳንድ የምልአተ ጉባኤው አባላት ሊነሡ ከሚችሉ የመነጋገሪያ አቋሞች መካከል÷ ‹‹ከአራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ገጽ ለገጽ ተገናኝቶ መወያየት›› እንደ ነጥብ ሊያዝ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ‹‹በመንግሥት ጫና ከመንበረ ፕትርክና ተባረርኹ፣ ተበደልኹ ያሉ እርሳቸው ብቻ ናቸው፤ ድርድሩም መካሄድ የሚገባው ከእርሳቸው ጋራ ነው፤›› የሚሉ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት÷ በውጭ የሚገኙ ሌሎች አባቶች በደል ደርሶብናል ባለማለታቸው ዋናው ድርድር ከአራተኛው ፓትርያሪክ ጋራ ብቻ መኾን እንደሚገባው ይከራከራሉ፡፡
በሹመት ቀደምትነት ያላቸውና በአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተሾሙት አባቶች በተደራዳሪነት የማይሳተፉበት የዕርቀና ሰላም ውይይት በዳላስ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ ለማካሄድ ዝግጅት በሚደረግበት ሰሞን÷ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ እንዲገናኙ ቀርቦ የነበረው ሐሳብ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው በሚባሉ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት ተቃውሞ የተነሣ ሳይሳካ መቅረቱ ታውቋል፡፡ ዐቃቤ መንበሩ ከአራተኛው ፓትርያሪክ ጋራ አድርገውታል የተባለው የስልክ ውይይት በይፋ መታወቁም ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹን ደስ እንዳላሰኛቸው ነው የተነገረው፡፡
የዕርቀ ሰላም ልኡኩ ወደ አሜሪካ ከተጓዘም በኋላ የልኡካኑን አባላት በአካል ወይም በስልክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ለማገናኘት በአቡነ መልከጼዴቅ ተደርጓል የተባለው ሙከራ ‹‹ከተልእኳችን ውጭ ነው›› በሚል ሳይሳካ መቅረቱ ተዘግቧል፡፡ በአንጻሩ አሁን ‹‹ጠባችን ይኹን ድርድራችን ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ብቻ ነው›› የሚለው የመነጋገሪያ አቋም ሐሳብ መነሻ የጉዳዩን ተከታታዮች አጠያይቋል፡፡ ጥቂቶቹም የሐሳቡ መነሻ የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫና እነርሱ ‹‹ወገንተኝነት ይታይበታል›› የሚሉት አካሄዱ እንደኾነ በመግለጽ ‹‹በዚህ አደራዳሪ አንቀጥልም፤ ከቀጠልንም ድርድሩ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ብቻ ይኾናል›› መባሉን ይጠቅሳሉ፡፡
አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ጳጳሳት የተደገፈውና በመንግሥትም ዘንድ ተይዟል የተባለው አቋም÷ ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው በተጓዳኝ እንዲካሄድ ሲኾን ይኸው አቋም የነገው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ውሳኔ ኾኖ እንዲወጣ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገ መኾኑ ታውቋል፡፡ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ተፈጽሞ በአንድነት ወደ ስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እንሂድ›› አልያም ‹‹አራተኛው ፓትርያሪክ በሕይወት እያሉ መንበሩ በእንደራሴ ይጠበቅ›› የሚሉትን ‹‹የዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› ደጋፊዎች አማራጮች መንግሥት እንደማይቀበለው የገለጹት ምንጮቹ÷ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ሠምሮ ዕርቅ ከተፈጸመ በኋላ መንግሥት ዋስትና ወደ አገር ለሚገቡት አባቶች ደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ በውጭ ባሉት አባቶች ዘንድ በቀጣይ መደራደሪያነት ተይዟል የተባለውንም ሐሳብ እንደማይቀበለው ተናግረዋል፡፡ በምንጮቹ ግንዛቤ ይህ የመነጋገሪያ ሐሳብ‹‹አጀንዳውን ከጳጳሳቱ ወደ መንግሥት ለማዞርና ውዝግቡን ለመቀጠል የታቀደበት ነው፡፡››
የሰላምና አንድነት ጉባኤውን ተሰሚነት ባላቸው ሽምግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች አጠናክሮ የዕርቅና ሰላም ሂደቱን መቀጠል ሌላው የአስቸኳይ ስብሰባው አጀንዳ ነው፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ደብዳቤ መላኩ የተገለጸ ሲኾን ስለ ደብዳቤው ዝርዝር ይዘት የተገለጸ ነገር ባይኖርም በምልአተ ጉባኤው ሊታዩ የሚገባቸውና ቀጣዩን የሰላም ጉባኤ የተመለከቱ ሐሳቦች ሊይዝ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የሰላምና አንድነት ጉባኤው የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በመቃወም ላወጣው የቅ/ሲኖዶሱ የዕርቀ ሰላም ልኡካን ‹‹ይቅርታ እንዲጠይቅ›› መጠየቃቸውና ይቅርታ ካልጠየቀና አካሄዱን ካላስተካከለ በአደራዳሪነቱ አብረው እንደማይሠሩ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አሁን የሰላምና አንድነት ጉባኤው በላከው ደብዳቤ ስላወጣው መግለጫ ማብራሪያ የሰጠበት፣ ለዕርቅና ሰላሙ መልካም ፍጻሜ ሲባልም ቅ/ሲኖዶሱን ይቅርታ የጠየቀበት ሊኾን ይችላል ተብሏል፡፡ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገቡ የታገዱትንና ከአገር በግዳጅ እንዲወጡ የተደረጉትን ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁንና ሌላውን ልኡክ የተመለከተ ጉዳይም ሊነሣበት እንደሚችል ተጠብቋል፡፡
ታኅሣሥ 8 ቀን መጽደቁ ተዘግቦ የነበረው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አከራካሪ አንቀጾችም በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ ዳግመኛ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጧል፡፡ ‹‹ሕጉ መጽደቅ ያለበት ምልአተ ጉባኤው በአግባቡ በተጠበቀበት ኹኔታ ነው›› በሚል ለዳግመኛ እይታ ተጋልጦ ሳለ÷ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ከመስጠት አኳያ በአወዛጋቢ ውሳኔ እንደተሠየመ የተነገረለት የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ቅቡልነት አከራካሪ ሊኾን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው አባላት ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተገኝተው ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማሳሰቢያ የተሰጠበትን ደብዳቤ አግባብነት መፈተሽና የደብዳቤውን መሻር የሚያስከትል ውሳኔ እንዲወሰን መሟገት በጥብቅ የሚያስቡበት ብፁዓን አባቶች ቁጥር ጥቂት አለመኾኑም የስብሰባውን ሂደት ከባድ እንደሚያደርገው ተገምቷል፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment