" የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።" ማቴ. ፯ ፥ ፲፭
"ድሮ ድሮ ነጣቂ አውሬ ሲመጣ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ይናገር ነበር" ይላሉ አንድ አረጋዊ አባት በሀዘኔታ በዚህ በእኛ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ፣ በደል፣ እንዲሁም ስደት እያሰቡት። አዎ ዛሬ ትላንት አይደለም፣ ትላንትም ለዛሬ ሰጥቶ ለተረኛው ሄዷል የተራውን ማስተናገድ ያለበት ተረኛው ዛሬ ነው ነገር ግን ዛሬ ዛሬነቱን ሊለውጥ ሊክደው አይችልም የመጣውን ጽዋ በትዕግስት መጎንጨት ወይም ደግሞ ጥንት የነበሩ አበው "የአንገቴን መሀተብማ አትበጥስም፣ ከነ አንገቴ ትወስዳታለህ እንጂ" ብለው ሰማዕትነትን እንደተቀበሉት።
አዎ በዚህ በዛሬ ጊዜ በእኛ ዘመን ሃጢያተኛ ከጻድቅ፣ በደለኛ ከተበዳይ፣ ሃሰተኛ ከእውነተኛ፣ መናፍቅ ከእውነተኛ አማኞች ተደባልቀው ባሉበት በዚህ ወቅት ጠላት እና ወዳጅን ለይቶ በማይታወቅበት ጊዜ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ በደል ሲፈጸም ሥርዓቷን፣ ቀኖናዋን፣ ትውፊቷን ሊያፈርሱ እኛን መስለው ለጠላት ለነጣቂ አውሬ ሊሰጡን በግራም በቀኝም፣ በፊትም በኃላም ተሰልፈው ባሰፈሰፉበት ጊዜ ሁላችንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ልንነቃ ልናውቅ የሚገቡን ነገሮችን ለማመልከት ነው።
ጊዜው እንደተባለው ወዳጅን ከጠላት መለየት ያዳገተበት ጊዜ ቢሆንም ሁልጊዜ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቷን አገልጋዮች በድምጻቸው ልንለያቸው ይገባል፣ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ "መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።" ዮሐ. ፲ ፥ ፲፬ እንደተናገረው መልካሙን እረኛ በድምጹ ልንለየው ይገባል። ድምጹም የተለየ ነው መለያ መንገዶቹም የተለዩ ናቸው እስቲ አንድ በአንድ እንመልከተው።
የእውነተኛ እረኞች መለያ ባሕሪይ:
፩/ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የራሳቸውን ስም በምንም መልኩ ከቤተ ክርስቲያን በላይ አያደርጉም፣ ሊታወቁም አይፈልጉም ውዳሴንም አይሹም፣ ከራሳቸው ክብር በላይ ለጓደኞቻቸው ክብር ይተጋሉ እንጂ የራስን ክብር ለማግኘት አይታገሉም። "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።" ሉቃስ ፪ ፥ ፲፬ እውነተኛ አገልጋዮች ክብራቸው የቤተ ክርስቲያን መስራቿ እና እራሷ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበር ብቻ ነው ለዚህም ነው እነዚህ አገልጋዮች ስማቸው መግነን ሲጀምር ይጠፋሉ፣ ክብር ለፈጣሪ ብቻ መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።
፪/ እውነተኛ አገልጋዮች ፈጽሞ በምድር ለሚገኝ ሀብት ወይም ገንዘብ አይወድቁም፣ ሀብትን ማካበት ወይንም ገንዘብን መውደድ የነሱ ባሕሪይ አይደለም ፈጽመውም ይቃወሙታል፣ ብዙ ጊዜ እነዚህ አገልጋዮች ገንዘባቸው በሰማይ፣ ሀብታቸው በአርያም መሆኑን ስለሚያውቁ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ገንዘብ እንከፍላችኃለን፣ ቤት እንሰጣችኃለን፣ መኪና እንገዛችኃለን፣ ልብስም መቀየሪያ መጎነጸፊያም በአጠቃላይ ከእነሱ ፍላጎት ጋር የማይሄድ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው ይሸሻሉ ደግመው እነዚህ ሰዎች ለማየት አይፈቅዱም አይፈልጉም ምክንያቱም የሰማያዊውን መንገድ ሊዘጉባቸው የተነሱ ተረፈ አሪዎሳውያን እንደሆኑ ስለሚያውቁ ነው። " ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።" ሉቃስ ፲፪ ፥ ፳፩ እንደተጻፈው የነሱ ባለጸጋነት ወይም ባለሀብትነት ከእግዚአብሔር መንገድ አለመውጣት ብቻ ነው። ዛሬ ዛሬ አገልጋዮች ይሄን ያህል ብር ካልተከፈለን ፥ አንመጣም አናገለግልም ያ ማለት አገልግሎታው ለእግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ ሥራቸው የጉሮሮአቸው መድፈኛ አገልግሎቱ ሆኗል "አበስኩ ገበርኩ" የሚያሰኝ ነው።
፫/ ስለ እውነተኛው የእግዚአብሔር አገልግሎት የሚተጉ ናቸው እነዚህ አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳ ጠዋት ለነግሕ ጸሎት ማታ ለሰርክ ጸሎት ሊሄዱ አገልግሎታቸው ለእግዚአብሔር መሆኑን ስለተረዱ ሰው መጣ ወይም ቀረ የነሱ ችግር አይደለም፣ እነሱ ለፈጣሪያቸው ቅን አገልጋይ ሆነው መገኘትን ብቻ ነው የሚፈልጉት። መቼም በአንዳንድ ሀገሮች በተለይ በሰሜን አሜሪካ ምዕመኑ ካልመጣ ቅዳሴውም ሰዓቱ ይሻሻላል እንደውም በአንዳንድ ቦታ ሰንበትም ተሽሮ አገልግሎቱ የሚሰጠው በሰንበት መሆኑ ቀርቶ በሌላ ቀን ነው። የሀገሩ ጸባይ ነው እንደየ ሀገሩ የተለያየ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል የሚሉ የዋሆች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን እውነተኛ አገልጋይ መስዋዕቱ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው እርሱ ወይም ምዕመኑ በሚመቸው ቀን ሳይሆን ለፈጣሪ ስለሆነ ሰንበትን ከሌሎች ቀኖች መርጦ ያከበራት እራሱ እግዚአብሔር ነው "እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።" ዘጸአት ፳ ፥ ፲፩ ስለዚህ እነዚህ አገልጋዮች ጉዳያቸው ከምዕመኑ ሳይሆን መስዋዕቱን ከሚቀበው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። " እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሃሉ አላቸው" ሉቃስ ፲፱ ፥ ፵ የተጻፈው ቃል እንደሚያስረዳን ምዕመን ባይኖር ድንጋዮችን እንኳን ያናገረ አምላክ ለእርሱ ቀዳሽ እና ሰላሽ እንደማያጣ ጠንቅቀው ያውቁታል።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የእውነተኛ አገልጋይ /እረኛ/ መለያ ባሕሪዎች ናቸው፣ እስቲ ደግሞ የነዚህ እውነተኛ እረኞች መለኪያው መመዘኛቸው ምን እንደሆነ እንመልከት።
የእውነተኛ አገልጋዮች መመዘኛ
፩ኛ/ ሕገ ቤተ ክርስቲያን
፪ኛ/ የሐዋሪያት ጉባኤያት (ኒቂያ፣ መቅዶኒያ)
፫ኛ/ የቤተ ክርስቲያን አበው አስተምህሮ
እነዚህ እንግዲህ የእውነተኛ አገልጋይ መመዘኛ መሣሪያዎች ናቸው፣ አገልጋዮች፣ እረኞች፣ ዘማሪያን በአጠቃላይ ከምንጣፍ አንጣፊው እስከ ሊቀ ጳጳሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት በሙሉ ሊመዘኑ የሚችሉት በእነዚህ መሣሪያዎች ብቻ ነው። ለምሳሌ: ሊቀ ጳጳሱ ሲያስተምሩ ወይም ሥራዎችን ሲሰሩና ሲያሰሩ ሊመዘኑ የሚችሉት በሕገ ቤተ ክርስቲያ፣ በተለያዩ የሐሪያት ጉባኤዎች ላይ የቀረቡትን ድንጋጌዎች ይጥሳል ወይ?፣ ወይም ከአበው አስተምህሮ ውጪ ነው ወይ? እነዚህን ሁሉ የሚያሟላ ከሆነ ተቀብለን እንደ ተዋሕዶ ልጆች አብረን እንሠራለን፡ ነገር ግን እኔ ያልኩት ብቻ በሚል ፈሊጥ (my way or the highway) አካሄድ አያስኬድም፣ ተቀብለን የምንሄድብት ጊዜ ያከተመ ይመስለናል።
ጊዜው እያንዳንዱን አባት ወይም አገልጋይ ተብዬ የምንመረምርበት ጊዜ ነው፣ እንደ የዋሃኑ ተቀብለን ዝም ብለን የምንሄድበት ጊዜ በአሁን ሰዓት የለም፣ አባት እንደ አባትነቱ አገልጋይም እንደ አገልጋይነቱ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል እንጂ፣ እንደ ዘመኑ ቀሚስ ብቻ ስለለበሰ አገልጋይነት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው አበው ሲያስተምሩ "መማር ይቅደም፣ ከመጠምጠም" እንዳሉት ገና ለገና የሹመት መአት ሳይገባቸው የተሰጣቸው ሀሰተኛ አገልጋዮች በበዙበት በአሁን ሰዓት እያንዳንዳችን ይህችን ርትዕይት ቤተ ክርስቲያን የመጠበቅ የማስጠበቅ ሀላፊነት አለብን። ይህንንም ካላደረግን ውጤቱ በጣም የከፋ እንደሆነ ለመጠቆም እንወዳለን፣ እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የዛሬዋ ቱርክ (ኮንስታኖፕል) እንዲሁም የዛሬዋ ሱማሊያ ልክ እንዳሁኗ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ተብለው ከሚጠቀሱት ሀገሮች መካከል ነበሩ ፥ ነገር ግን በአሁን ሰዓት በሱማሊያ አንድም የክርስትና ቅርስ ሳይቀር በእስልምና አክራሪዎች ወድሞ የእስላም ሀገር የምትባለው፣ በቱርክም በአንዳንድ የእስታንቡል ከተሞች በሚዚየምነት ከምትጠቀምባቸው የክርስትና አመልካች ቅርሶች በስተቀር በሙሉ ወድመዋል። በአሁን ሰዓት የተነሱብን ጠላቶቻችን ሰመ ክርስትናችንን ለማጥፋት፣ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ትውፊቶቻችንን በሙሉ ለማውደም እና ለመቀየር የተነሱ ኃይሎች ናቸው እነዚህን ሁሉ ልንከላከል፣ ለክብራችንም ለሀገራችንም መገለጫ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ልንቆም ይገባል እንላለን፡
ወስብሃት ለእግዚአብሔር።
No comments:
Post a Comment