“በቀልን ለተጠማ አባት ራሴን አሳልፌ አልሰጥም” - ብፁዕ አቡነ አብርሃም
- ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት በፓስፖርት እና በመኖሪያ ፈቃድ እድሳት እጦት እየተንገላቱ ነው
- በ’ተሐድሶ’ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረው ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል
- “የማያቋርጥ አቤቱታ መብዛት ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን የመዋቅርና የሥራ ሂደት መሻሻል እንደሚያስፈልገው አመላካች ነው” - የጠ/ቤ/ክ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥናት
(አዲስ አድማስ ጥቅምት 11/2004)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ካሏት ሦስት አህጉረ ስብከት መካከል የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና የሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፤ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ያለቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና በሊቃነ ጳጳሳቱ ላይ የበላይ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት በዋሽንግተን ዲሲ እንዲቋቋም ያስተላለፉትን ትእዛዝ ተቃወሙ፡፡ አቡነ ፋኑኤል ያለቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድና ያለሀገረ ስብከቶቹ ዕውቅና በሚፈጥሩት ችግር ላይ ርምጃ ባለመውሰዳቸውም ፓትርያርኩን በጣልቃ ገብነት ወቅሰዋቸዋል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች ለመረዳት እንደተቻለው፤ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ላይ በማድረግ “በሦስቱ አህጉረ ስብከት እና በመንበረ ፓትርያሪኩ መካከል አገናኝ ድልድይ እንዲሆን” በሚል በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም እንዲቋቋም በፓትርያሪኩ ለታዘዘው የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት የተሰጡት ተግባራት በአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች ሊፈጸሙ የሚገባቸው፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቅዱስ ሲኖዶስ ለሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት የሚጋፋ ሆኖ እንዳገኙት ተገልጧል፡፡ “የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሊቃነጳጳሳትን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር የሚያገናኝ ሌላ አካል የማቋቋም አስፈላጊነት ግልጽ አይደለም” ያሉት ሊቃነ ጳጳሳቱ፤ የፅ/ቤቱ መቋቋም ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰና ለአህጉረ ስብከቶቻቸው ህልውና የሚያሰጋ በመሆኑ ለጉዳዩ ቅዱስ ሲኖዶስ የማያዳግም እርምት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ ተቋቋመ የተባለው ጽ/ቤት አብዛኛውን ውይይት የሚያደርገው ራሳቸውን “ገለልተኛ” ብለው ከሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት እና መደበኛ ውክልና ከሌላቸው ካህናት ጋር መሆኑን እስከ አሁን ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ መረዳታቸውን፣ ይህም በሰሜን አሜሪካ “ራሱን የቻለ መዋቅር እየመሰለ የመጣውን ገለልተኝነት” በማስፋፋትና በማጠናከር ሀገረ ስብከቱ ለአብያተ ክርስቲያናት (ካህናት እና ምእመናን) አንድነት በሚያደርገው ጥረት ላይ ዕንቅፋት እንደሚፈጥር በመጥቀስ የፓትርያርኩን ትእዛዝ ተቃውመውታል፡፡
ቀደም ሲል የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ሩፋኤል፤ ከሀገረ ስብከታቸው ውጭ ወደ ሰሜን አሜሪካ በልዩ ልዩ ምክንያት በመመላለስ ያለሀገረ ስብከቱ ዕውቅና በአትላንታ፣ በኖርዝ ካሮላይና ሻርለት፣ በቨርጂኒያ አሌክሳንደርያ እና በናሽቪል ቴኒስ አብያተ ክርስቲያናትን ባርከው በመክፈት፣ ክህነት በመስጠት “ገለልተኛ ነን” በሚሉ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቀኖናው ውጭ እየፈጸሟቸው ባሉ ሥራዎች ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የበለጠ የሚያናጋና ቤተ ክርስቲያን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንድታመራ የሚያደርግ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን አቡነ አብርሃም ለሲኖዶሱ ጽ/ቤት የላኩት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
አቡነ ፋኑኤል እኒህን ኢ-ቀኖናዊ ተግባራት ለመፈጸም በደብዳቤ መመደባቸውን እንደማያውቁ የገለጹት አቡነ አብርሃም፤ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አቡነ ሩኑኤልንና ተባባሪ አስተባባሪዎችን ወደ ሰሜን አሜሪካ በመላክ እና የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤቱን ከፍተው፣ ባለሙሉ ሥልጣን ተጠሪ በመመደብ፣ በሀገረ ስብከታቸው ላይ ያላቸውን መብት እንደገፈፏቸው ገልጸዋል፤ በጉዳዩ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ብቻ እንደሚጠባበቁም አመልክተዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በውጭ ከሚገኙት ጳጳሳት የተወሰኑት “በነፍስ ድረሱ ዐይነት” ጥሪ ሲደረግላቸው እርሳቸው ግን በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ ተዘዋዋሪ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸው እንደነበር አቡነ አብርሃም አስታውሰዋል፡፡ የሚደርስባቸውን ሁሉ በጸጋ ለመቀበል ወስነው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡም በኋላ በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን እንዳያስቀድሱና እንዳያስተምሩ ስውር ትእዛዝ ለአድባራት አስተዳዳሪዎች በመስጠት፣ የመጡበት የሲኖዶስ ስብሰባ ከተጠናቀቀም በኋላ “ወደ ሀገረ ስብከትህ መመለስ አትችልም፤ ተከሰሃል፤ ስምህ ይጠፋል፤ እኔ የምመክርህን ማድረግ ብቻ ነው” በሚል በፓትርያርኩ በመታገዳቸው ጉዟቸው ተስተጓጉሎ ለአላስፈላጊ ወጭ እና ለበሽታ መዳረጋቸውን፣ የነበራቸው የዲፕሎማት ፓስፖርትም ጊዜው ስላለፈ ተለዋጩን ፓስፖርት እና በሚኖሩበት አገር መውጣት መግባት የሚያስችል መኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ያቀረቡላቸውን ደብዳቤ ከፊታቸው ቀዳደው መጣላቸውንና ዛሬም ለአራተኛ ጊዜ አመልክተው ተቀባይነት አለማግኘታቸውን ዘርዝረዋል፡፡
በወቅቱ ከፓትርያርኩ ጋራ ውዝግብና ክርክር ከመፍጠር “ወደ አንድ ገዳም ሄጄ ለመቀመጥ እስከ መምረጥ ደርሼ ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፤ ከጥቅምት ሰባት ቀን ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና ከጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተላለፈላቸው ጥሪ “በቀልን ለተጠማ አባት ራስን አሳልፎ መስጠት” በመሆኑ በስብሰባዎቹ እንደማይገኙ አስታውቀዋል፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተፈቀደላቸውን መብት ሲኖዶሱ እንዲያስከብርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን ምዕራብ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከታቸውን በማጠናከር ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ኤዎስጣቴዎስም፤ የተሰጣቸውን ሐላፊነት በተሻለ መልኩ ለመወጣት የማስተርስ ዲግሪ የሚያገኙበትን ትምህርት በመከታተል ላይ በመሆናቸው የመኖሪያ ፈቃድ እና ፓስፖርታቸው እንዲታደስላቸው የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በሚነካ እና አገልግሎቱን በሚጎዳ ሁኔታ እየተንገላቱ መሆናቸውን በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ከሳምንቱ መጀመሪያ አንሥቶ እየተካሄደ የሚገኘውንና ነገ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀውን 30ኛውን ሀገር አቀፍ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤንና መጪውን የሲኖዶስ ስብሰባ ምክንያት በማድረግ “የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት ለማደስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንቃወማለን” የሚሉ አካላት ከ22,000 በላይ የሆኑ ምእመናን ድጋፍ ያሰባሰቡትንና ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያሰፈሩበትን ሰነድ፤ ለሲኖዶስ ጽ/ቤትና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማቅረባቸውን የእንቅስቃሴው መሪዎች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ከአቋም መግለጫቸው ውስጥም በአንድ የውጭ ድርጅት፣ በተለያዩ ገዳማት ውስጥ እንዲሰራ በአቡነ ገሪማ ፊርማ የተፈቀደው የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም ይገኝበታል፡፡
በሌላ በኩል “በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረቶች ላይ እንዳናገለግል አላግባብ ታግደናል” የሚሉ ሌሎች አካላት ከተለያዩ ክልሎች ተጓጉዘው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ግቢ በመሰብሰብ በነገው ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡ መቋጠሪያ ውሉ የጠፋ የሚመስለው ይኸው የተለያዩ ቡድኖች ውዝግብ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ችግሮችን የሚፈታበትን ድርጅታዊ መዋቅር መፈተሽና ዲዛይኑን ማሻሻል እንደሚያስፈልገው ጠቋሚ ምልክት እንደሆነ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ መግለፃቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ “የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ፅ/ቤት አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግሮች” በሚል ርእስ ለ30ኛው ሀገር አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዲቀርብ ባዘጋጁት ባለ 14 ገጽ የዳሰሳ ምልከታ ላይ እንዳብራሩት፣ ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየጊዜው ሊነሡ የሚችሉ ውዝግቦችን አስቀድመው የሚገምቱበትና የሚከላከሉበትን መንገድ አላበጁም፡፡ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ውዝግቦች መቋጠሪያ ውላቸው በፍጥነት ካለመገኘቱም ባሻገር አባቶችን የሚፈታተን ነገር እየተስፋፋ ይገኛል፤ ጉዳዩም ወደፊት በሚከለሱ ደንቦችና መመሪያዎች ውስጥ በስፋት ሊታሰብበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማኔጅመነት ኮሚቴ አማካይነት ለፓትርያሪኩ መድረሱ በተረጋገጠውና በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ እንደሚቀርብ በተነገረው በዚሁ ሰነድ፤ የሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፅ/ቤትና መምሪያዎች እንዲሁም አህጉረ ስብከቶች የአደረጃጀት እና አሠራር ድክመት ተገምግሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የምትመራባቸው ሕጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መጣጣም ወይም አለመጣጣም አለመፈተሹና በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ፤ በሠራተኛ ምደባ፣ ዝውውርና ቅጥር ላይ የተምታታ አሠራር መፍጠሩ፣ በሕግ አውጭው በቅዱስ ሲኖዶስ እና በሕግ አስፈፃሚው በጠቅላይ ቤተ ክህነት መካከል የግንኙነት፣ የተጠያቂነትና የግልፅነት አሠራር የዳበረ አለመሆኑ፣ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዐቱን፣ የበጀት እና የፋይናንስ ሪፖርቶችን የሚተነትንና አስተያየት የሚሰጥ አካል አለመኖር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለኋላ ቀር የሒሳብ አሠራር ስርዐት መዳረጉ፣ የአስተዳደር ጉባኤው ሥራዎቹን የሚያቀላጥፍበት የአሠራር መመሪያ (ማንዋል) የሌለው በመሆኑ አቅምን የማጐልበት ተግባሩ ተቀይዶ መያዙ በጠቋሚ ችግርነት ተመልክተዋል፡፡
“በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ውጤታማ የሆነ ድርጅታዊ ዲዛይን ባለመኖሩ በውጤቱም ለሥራ የመትጋት ባህል ሊፈጠር አለመቻሉን፣ ሠራተኞች የተጠያቂነታቸውን ደረጃ ስለማያውቁት የድርጅታቸው ዓላማ እንዲሳካ ጥረት እንደማያደርጉና ለተገልጋዩ ምእመን የሚፈለገውን አገልግሎት ባለመስጠታቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ሆነ ሀገረ ስብከቶች ቅሬታ እንደሚያድርባቸውና የትየለሌ ሀብት እንደሚባክን” አቶ ልዑል ሰገድ በጥናታቸው ውስጥ አስረድተዋል፡፡ስለሆነም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ መመሪያ ደንብና የሠራተኛ አስተዳደር ደንብ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከሀገሪቱና ዓለም አቀፍ ሕጐችና ስምምነቶች አንፃር ተቃኝተው እንደገና መቀረጽ እንዳለባቸው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር ማሻሻያ እንዲደረግለት፣ ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከ5-10 ዓመት የሚደርስ ስትራቴጂክ ፕላን እንዲኖራቸው የቤተ ክርስቲያናችንን የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማረጋጥ የባለሞያዎች ፊስካል ኮሚቴ እንዲቋቋም እና አዲስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲቀረፅ በጠቋሚ የመፍትሄ ሃሳብነት መቅረቡን የምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ የዳሰሳ ምልከታ ጨምሮ ያስገነዝባል፡፡
“በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ውጤታማ የሆነ ድርጅታዊ ዲዛይን ባለመኖሩ በውጤቱም ለሥራ የመትጋት ባህል ሊፈጠር አለመቻሉን፣ ሠራተኞች የተጠያቂነታቸውን ደረጃ ስለማያውቁት የድርጅታቸው ዓላማ እንዲሳካ ጥረት እንደማያደርጉና ለተገልጋዩ ምእመን የሚፈለገውን አገልግሎት ባለመስጠታቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ሆነ ሀገረ ስብከቶች ቅሬታ እንደሚያድርባቸውና የትየለሌ ሀብት እንደሚባክን” አቶ ልዑል ሰገድ በጥናታቸው ውስጥ አስረድተዋል፡፡ስለሆነም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ መመሪያ ደንብና የሠራተኛ አስተዳደር ደንብ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከሀገሪቱና ዓለም አቀፍ ሕጐችና ስምምነቶች አንፃር ተቃኝተው እንደገና መቀረጽ እንዳለባቸው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር ማሻሻያ እንዲደረግለት፣ ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከ5-10 ዓመት የሚደርስ ስትራቴጂክ ፕላን እንዲኖራቸው የቤተ ክርስቲያናችንን የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማረጋጥ የባለሞያዎች ፊስካል ኮሚቴ እንዲቋቋም እና አዲስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲቀረፅ በጠቋሚ የመፍትሄ ሃሳብነት መቅረቡን የምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ የዳሰሳ ምልከታ ጨምሮ ያስገነዝባል፡፡
No comments:
Post a Comment