· መናፍቃኑ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያናችን የክህነት፣ የክብርና የማዕርግ ስም አይጠሩም።
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
· የቤተ ክርስቲያኒቱን የከበረ ስሟን በማጉደፍ ታሪኳንና ክብሯን በመዳፈራቸው በሕግ ይጠየቃሉ።
· መናፍቃኑ እና ድርጅቶቹ ላሰራጯቸው ኅትመቶች የማስተባበያ ጽሑፎች ይዘጋጃሉ።
· ሊቃውንት ጉባኤ ከማንኛውም አካል ለሚሰነዘረው ሃይማኖት የሚያጎድፍ ክብረ ነክ ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት በሚችልበት አኳኋን በጥራትና በስፋት ይጠናከራል።
· ከተወገዙት ድርጅቶች መካከል የ”አንቀጸ ብርሃን” ድርጅት መሥራች በኾነውና በእጅጋየሁ በየነ አቅራቢነት የፓትርያርኩ መልእክቶች ጸሐፊ እስከመኾን ደርሶ በነበረው አሸናፊ መኰንን ላይ የተላለፈውን የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ለመቀሠጥ የተደረገው የሸፋጮች ሙከራ ከሽፏል (ሙከራውን የሰነዱን ገጽ 38 እና 39፣ ተ.ቁ 16ን በማነጻጸር ይመልከቱ)
· “አሁን የተሐድሶ መናፍቃኑ ዝናራቸውን ጨርሰው የአገልጋዮችን ስም ማጥፋቱን ተያይዘውታል፤ ያወገዝናቸው ስለጠላናቸው ሳይሆን ስለካዱ ነው፤ ሰውን ማስታመም የሚቻለው በምግባር ድክመቱ እንጂ በሃይማኖት ክሕደት አይደለምና፡፡” /ብፁዕ አቡነ አብርሃም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለሀ/ስብከታቸው ሰባክያነ ወንጌል እና ምእመናን ይፋ ሲያደርጉ ከተናገሩት/
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 9/2004 ዓ.ም፤ ጁን 16/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሃይማኖት ጉዳይ በተለይም ለምእመናን አንድነት ቅድሚያ በመስጠት፣ በጉዳዩ ላይ በስፋት በመነጋገር፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም፣ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና መጽሐፎቻቸው ላይ በአንድ ድምፅ ያስተላለፈውን የውግዘት ውሳኔ የያዘው ቃለ ጉባኤ ለመላው አህጉረ ስብከት ተሰራጨ፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሰኔ 7 ቀን 2004 ዓ.ምሰ ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ 48 አህጉረ ስብከት ባሰራጨው ቃለ ውግዘት የተካተቱት መናፍቃን ድርጅቶች ሰባት ሲኾኑ የግለሰቦቹ ብዛት ደግሞ 16 ነው፡፡
ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ የተወገዙት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተለየ የኑፋቄ ትምህርት በመጽሐፋቸው፣ በመጽሔታቸው፣ በመጣጥፎቻቸውና በኤሌክትሮኒክስ የኅትመት ውጤቶቻቸው ሲያሰራጩ በመገኘታቸውና ይህም በማስረጃ በመረጋገጡ መኾኑን የገለጸው ቃለ ውግዘቱ÷ውሳኔው በይፋ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ መርሐ ግብር በማንኛውም መድረክ እንዳይሳተፉ፤ እስከ አሁን ሲጠሩበት በነበረው የክህነት እና የክብር የማዕርግ ስም እንዳይጠሩበት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ ለውሳኔው መሠረት የኾነው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የሊቃውንት ጉባኤ ጥምር ኮሚቴ ሰነድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ዐዋቂዎች እና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከተመረመረ በኋላ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ የቤተ ክርስቲያኒቷን የከበረ ስሟን በማጉደፍ፣ ታሪኳን፣ ክብሯን በመዳፈር ላደረሱት በደል በሕግ እንደሚጠይቁ የውሳኔ ቃለ ጉባኤው አስታውቋል፡፡
መናፍቃን ድርጅቶቹና ግለሰቦቹ ላሰራጯቸው ጽሑፎች የማስተባባያ ምላሽ እንደሚዘጋጅና ዝግጅቱም በመጽሔት ጥራዝ መልክ ተዘጋጅቶ እንደሚወጣ የውሳኔው ማጠቃለያ አመልክቷል፡፡ በይቀጥላልም ጽሑፉን የማዘጋጀት ሓላፊነት የተጣለበት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ ከማንኛውም አካል የሚሰነዘረውን ሃይማኖትን የሚያጎድፍ ክብረ ነክ ጽሑፍ ተከታትሎ በጊዜው በቂ የኾነ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችለው ስፋት እና ጥራት እንደሚጠናከር አብሥሯል፡፡
በቃለ ውግዘቱ የተካተቱት ድርጅቶችና ግለሰቦች በበደላቸው ተጸጽተው የይቅርታ ደብዳቤ ጽፈው ይቅርታ ከጠየቁ የይቅርታ ጥያቄውን ለመመርመር እና ይቅርታ ጠያቂዎችን ለመቀበል ዝግጁ መኾኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጧል፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኒቂያና በቁስጥንጥንያ፣ እንዲሁም በአምስተኛው መቶ ዓመት በኤፌሶን በተደረጉ ጉባኤያት የተወሰኑትን ተቀብላ፣ አጽንታ በመያዝ የምታስተምር መኾኗን የገለጸው የውሳኔው መግቢያ÷ በዓለማችን በትምህርተ ሃይማኖት ሂደት ብዙ አስደንጋጭ፣ አስፈሪና አሳፋሪ ብዙ ክሥተቶች በየጊዜው በተለያየ ስምና ጠባይ መፈጠራቸውን አስታውሷል፡፡ ነቢያት በትንቢት፣ ሐዋርያት በስብከት፣ ሊቃውንት በትምህርት የተባበሩበት ትምህርተ ሃይማኖት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያው ያልተለወጠው፣ የማይለወጠው የጸና፣ የቀና እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚኖር በመኾኑ መናፍቃን ድርጅቶቹንና ግለሰቦቹን ማውገዙን አስታውቋል፡፡
ቃለ ውግዘትን ፈርቶ በተወገዙበት ጉዳይ ከልብ ተጸጽቶና ቃለ ካህንን አክብሮ ይቅርታ መጠየቅ፣ ራስን ከተሳሳተ ትምህርትና ከምግባረ ብልሹነት መጠበቅ አብዝቶ ይጠቅማል፡፡ እንደ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ክህነትንና ግዝትን ንቆና ተደፋፍሮ ሌላውን ማደፋፈር ደግሞ ድርብ ጥፋት ነው፡፡ በሰማይ እና በምድር ሁሉን በተገባ ለማሰርና ለመፍታት ሥልጣን የተሰጣቸው ቅዱሳን ሐዋርያት መንበር ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በክህነታዊ ሥልጣኑ ያስተላለፈውን ውግዘት መናቅ በምንም መንገድ መንፈሳዊነት ሊኾን አይችልምና፡፡
ከተወገዙት ድርጅቶች መካከል “አንቀጸ ብርሃን” በሚል ስያሜ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚያጭበረበረው ድርጅት መሥራች አሸናፊ መኰንን ይባላል፡፡ በእጅጋየሁ በየነ አስተዋዋቂነት በመንበረ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት “የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት” የተሰኙ ጽሑፎችን እስከማዘጋጀት መድረሱ ይነገርለታል፡፡ ወደ ልዩ ጽ/ቤቱ ከመቅረቡ በፊትም ይኹን በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የቅዱስ ሲኖዶስን ቃለ ጉባኤ ከሚይዝ አንድ ግለሰብና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና መዝገብ ቤት ሓላፊ ከኾነችው ወ/ሮ ዐጸደ ግርማይ ጋራ ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ተገልጧል፡፡
ኑፋቄን፣ ስድብንና ሽንገላን፣ ሽሙጥንና ትችትን፣ ክሕደትን የተመሉ ስድስት መጻሕፍቱ፣ 10 መጽሔቶቹ እና ሌሎችም መጣጥፎቹ ተመርምረው ዳንኤል ተሾመ ከተባለ ሌላ ግብረ አበሩ ጋራ እነርሱም፣ ድርጅታቸውም ጽሑፎቻቸውም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘው አሸናፊ÷ ገና ጉዳዩ ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ በመታየት ላይ ሳለ በወይዘሮዋና በፓትርያርኩ ተጽዕኖ ውሳኔውን ለማስቀየር ያደረገው ብልጠት ሳይሠራለት ቀርቷል፡፡
አሸናፊ ግን ቁርጡን ዐውቆ በህልውና ሥላሴ፣ በጌታችን አምላካዊ ክብር፣ በሃይማኖታችንና በኢትዮጵያዊ ወኔያችን ላይ ሲዳክርበት የኖረውን ጥፋቱን አላመነም፡፡ የመጨረሻ ነገር ግን አሳፋሪ ሙከራ አደረገ፡፡ ለዚህም የቅዱስ ሲኖዶስን ቃለ ጉባኤ ከሚይዙት የጽ/ቤት ሠራተኞች የአንዱን÷ በአንዳንድ ምንጮች ጥቆማ ግለሰቡ የ”አንቀጸ ብርሃን” የቆየ አባል እንደ ኾነም ተጠቁሟል÷ (ስሙን ብናውቅም ከመጥቀስ ተቆጥበናል) ሸፍጥ ይጠቀማል፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንደሚያስረዱት ይኸው የአሸናፊ ሸፍጠኛ የቅዱስ ሲኖዶሱ የውሳኔ ቃለ ጉባኤ ተተይቦና ተባዝቶ በሚጠረዝበት ወቅት÷ በገጽ 38 ላይ በስም ተራ ቁጥር ከሚዘረዝራቸው 16 ውጉዝ ግለሰቦች መካከል÷ በተራ ቁጥር 16 ላይ የተጠቀሰው የአሸናፊ መኰንን ስም አብሮት ከተወገዘውና በተራ ቁጥር 4 ላይ ከተጠቀሰው ዳንኤል ተሾመ በመነጠል በመጨረሻ ላይ እንዲሰፍርና እንዲገደፍ በማድረግ የ15 ሰዎችን ስም ዝርዝር ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቅርቧል፡፡ ሰነዱን በጥንቃቄ የመረመሩት ብፁዕ ዋና ጸሐፊውም ግለሰቦቹ 16 መኾናቸውንና የአሸናፊ መኰንን ስም አለመካተቱን በመጥቀስ ቀልቡን ይገፉታል፡፡
በቤተ ክህነቱ የቆየ ሠራተኛ ለዚያውም የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባልደረባ በመኾኑ ጓደኛው አሸናፊ ከክፉ ግብሩ ተመልሶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊመክረው ሲገባ ቅሠጣው የተጋለጠበት ቀሣጢው ግለሰብም በድንጋጤ ነው ቢሉ፣ ለሌላ ተንኰል እንዲያመቸውም ነው ቢሉ የተቀሠጠው (የጎደለው፣ የጎመደው) የአሸናፊ መኰንን ስም በተራ ቁጥር 16 ላይ በእጅ ጽሑፍ እንዲገባ ያደርጋል (ገጽ 38 ይመልከቱ)፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው አቡነ ሕዝቅኤል ግን ውሳኔው ከተላለፈ ወዲህ እንኳ ስሕተቱን አምኖ በተከፈተለት የይቅርታ በር ከመጠቀም ይልቅ በጓሮ በር በሽምግልና ጭምር ሲያስቸግር የሰነበተው የአሸናፊ መኰንን ስም እጅ ጽሑፉ ብቻ ሳይኾን በታይፕም ተጽፎ (ገጽ 39 ይመልከቱ) በሁሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዳግመኛ እንዲፈረምበት በማድረግ ያከሸፉትን ቅሠጣ ለታሪክ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡ በተ.ቁ (7) ላይ ስብሐት ለአብ በሚል በአባቱ ስም ብቻ የተገለጸውቀንደኛው መናፍቅና የ”ማኅበረ በኵር” መሥራች መሠረት ስብሐት ለአብ ስምስ በምን ተንኰል በዚህ መልኩ እንደታለፈ አያጠያይቅም ለማለት አይቻልም፡፡
ይህ የከሸፈ የእነአሸናፊ ሸፋጮች ሙከራ ግን የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄው ትግል ቀጣይ የተጋድሎ ዐውድማ በሚኾነው በቤተ ክህነቱ ቢሮክራሲ ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በግልጽ የሚያመለክት እንደኾነ የጉዳዩ ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክህነቱን ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቅጥረኞች እና የእነርሱ መተላለፊያ ወደብ (harbor) ከኾኑት ሙሰኞችና ዘረኞች ለማጽዳት በይቀጥላል የሚደረገው ቢሮክራሲያዊ ትግል እስከአሁን ከተካሄደው የበለጠ ውስብስብ እንደሚኾን ከታሪካዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደማቅ ውሳኔዎች ማግስት አባ ጳውሎስ እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉ አጋፋሪዎቻቸው ጋራ በእልክና በበቀል ጥማት የሚያሳዩት መወራጨት ምስክር ነው - የመጨረሻው ምሽግ መላላጥ (the last ditch effort) ይኾን?
ግሪኮች “ከዐቢዩ የወገን ድል በፊት ጠላት የሚያውጃቸው ትንንሽ ድሎች አሉ” ይላሉ፡፡ አባ ጳውሎስና እነኀይለ ጊዮርጊስ መንግሥትን ጭምር ሊያጨበረብሩበት የተዘጋጁበትና ከፈተናው በፊት ቀረርቶ የሚያሰሙበት ሰሞናዊው “ጉባኤያቸው” የት ያደርሳቸው ይኾን? ብዙ እየተናገሩ ነው፤ እርስበስ ለማናተፍ ይረዳናል፤ ያሸማቅቅልናል ያሏቸውንና ከምናባቸው በቀር በዕውን የሌለ የጭቃ ጅራፋቸውንም በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎቻቸው እያጮኹ ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ግልጽ ሊኾንላቸው የሚገባው ግን ብፁዕ አቡነ አብርሃም ትናንት፣ ሰኔ 8 ቀን 2004 ዓ.ም እንደተናገሩት “በሽተኛ እና ጤነኛ በአንድ ቤት ማደር እንደማይችል” ነው፡፡
የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰባቱ መናፍቅ ድርጅቶች እና 16 ግለሰቦች ላይ ስላሳለፈው የውግዘት ውሳኔ÷ ትናንት፣ ሰኔ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በሐረር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በተጠራው የሀ/ስብከቱና የስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት በተገኙበት ጉባኤ ላይ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ልበሱ” (ኤፌ.6÷11) በሚል ርእስ ትምህርት ሰጥተዋል፤ በውሳኔው አተገባበር ላይም አባታዊ መመሪያና ምክር አስተላልፈዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተሐድሶ ጭፍሮች ዝናራቸውን ጨርሰው የቅዱሳኑንና የትጉሃን አገልጋዮቹን ስም ወደ ማጥፋት መዝቀጣቸውን ተናግረዋል፡፡ “ድርጅቶቹንና ግለሰቦቹን ያወገዝናቸው በሰውነታቸው ስለጠላናቸው ሳይኾን በሃይማኖት ስለ ካዱ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ሰውን ለማስታመም የሚቻለው በምግባር ድክመቱ እንጂ በሃይማኖታዊ ክሕደቱ እንዳልኾነ አስረድተዋል፡፡
በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው “የኑፋቄ ትምህርት አስተላላፊዎች እና ፀረ - ኦርቶዶክስ አቋም ያላቸው መናፍቃን” ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በተወገዙበት ማግስት ለውሳኔው መሠረት የኾኑ ማስረጃዎችን አጠናቅሮ በማቅረብ እልክ አስጨራሽ ተጋድሎ ያደረጉትን በሙሉ÷ በተለይ ማኅበረ ቅዱሳንን÷ ለማዳከም ከተሳካላቸውም ለማፈራረስ፣ ውሳኔው በተገቢው መንገድ ተጠንቶና ተመርምሮ ታላቅ ፍጻሜ ላይ የደረሰበትን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የአባ ጳውሎስን ሥልጣን በሚያጠናክር አኳኋን ለመለወጥና የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን ለመፃረር፣ ከመወሰን እስከ ማስፈጸም ድረስ በየደረጃው ሓላፊነት የተጣለባቸውን ብፁዓን አባቶች፣ የሥራ ሓላፊዎች፣ ካህናት፣ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል ለመድፈቅ እየተራወጠ የሚገኘውን ስብስብ (የዐመፅ ቡድን) ተግዳሮቱ በሚጠይቀው መጠን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ገጥሞ ለማስወገድ አንድነታችንን እንድናጠነክር ደጀ ሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
የክህነትና የክብር ማዕርጋቸው ተሽሮ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ
በሰማይና በምድር የተወገዙት ድርጅቶች እና ግለሰቦች ዝርዝር
የሚከተለው ነው፤
ሰባቱ ድርጅቶች፡-
1. ከሣቴ ብርሃን
2. ማኅበረ ሰላማ
3. የምሥራች አገልግሎት
4. የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር
5. አንቀጸ ብርሃን (ከድርጅቱ ጋራ አሸናፊ መኰንንና ዳንኤል ተሾመ)*
6. የእውነት ቃል አገልግሎት
7. ማኅበር በኵር
8. የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት/ኢመተኅ/ - (ተጨማሪ ማጣራት የሚደረግበት)
16ቱ ግለሰቦች፡-
1. ‹አባ› ወልደ ትንሣኤ አስገዶም
2. አቶ መስፍን
3. አጥናፉ መኰንን
4. ዳንኤል ተሾመ
5. ግርማ በቀለ
6. ሥዩም ያሚ
7. መሠረት ስብሐት ለአብ
8. ሰሎሞን መኰንን
9. ጽጌ ስጦታው
10. ደረጀ ገዙ
11. በዛ ሰፈርህ
12. አግዛቸው ተፈራ (አሁን የጮራ መጽሔት አዘጋጅ)*
13. ተስፋ ተገኝ
14. ብሥራት ጌታቸው
15. መ/ር ተስፋ ዓለም
16. አሸናፊ መኰንን
ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ “ትምህርተ ውግዘት” በሚል ርእስ ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ ከጻፉት የተወሰደ ነው፡፡ ስለ ውግዘት አጠቃላይ ግንዛቤ በሚሰጥ መልኩ እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!!!!! አሜን
ውግዘት ምንድን ነው?
ማውገዝ በዘይቤ፣ በአገባብ ይኹን በምስጢር ብዙ ፍችዎች አሉት፡፡ ማውገዝ መለየት፣ መካድ፣ መርገም፣ መፍረድ፣ ማሰር፣ መወሰንና ሥርዐት መሥራት ማለት ነው፡፡ ኢአማንያንን፣ መናፍቃንንና ክፉዎችን ከምእመናን፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከጉባኤ እግዚአብሔር እና ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማለትም ከቅዱስ ቍርባንና ከመሳሰለው ሁሉ የሚለይ መንፈሳዊ መቍረጫ ውግዘት ነው፤ “የሚያውኳችኹ ይቆረጡ” እንዲል(ገላ.5÷11)፡፡
ውግዘት መንፈሳዊ ሰይፍ ነውና ኢአማንያንን ከአማንያን ይለያቸዋል፡፡ ማውገዝ ሰይጣንን በሃይማኖትና በሥራ መካድ ነው፡፡ “ዘይፈቅድ ይጠመቅ ይምሀርዎ ያውግዝ ሰይጣነ ወይእመን በክርስቶስ - ሊጠመቅ የፈቀደውን ሰው ሰይጣንን እንዲክድና በክርስቶስ እንዲያምን ያስተምሩት፤” እንዲል (ዲድስቅልያ 34) ፡፡ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ልዩ ልዩ የክሕደት ትምህርት አንቅተው ያስተማሩ መናፍቃን ላይ የቤተ ክርስቲያን ርምጃ “ታወግዞሙ፤ ወትረግሞሙ፤ ትፈልጦሙ፤ ወትመትሮሙ” በሚሉ ኀይለ ቃላት በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ ተገልጾ እናገኛዋለን፤ ፍቺውም ቤተ ክርስቲያን ታወግዛቸዋለች፤ ትረግማቸዋለች፤ ቆርጣ ትለያቸዋለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማውገዝ መርገም ነው፤ መወገዝ መረገም ነው፡፡
ማውገዝ መፍረድ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የሚሠራ እንጂ በእነርሱ ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም፡፡ “እውነት እላችኋለኹ፤ እናንተስ የተከተላችኹኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችኹ፤” ብሏቸዋል፡፡ (ማቴ.19÷28) ስለዚህ ሐዋርያት በምድር የፈረዱት ፍርድ በሰማይ አይገሠሥባቸውም፤ ማለትም በሥልጣነ ክህነታቸው በምድር ላይ የሠሩት ማንኛውም ዐይነት ሥራ፣ ውሳኔና ፍርድ በዳግም ምጽአት ይጸናል ማለት ነው፡፡ ይህም “በምድር ያሰራችኹት በሰማይ የታሰረ ይኾናል፤ በምድር የፈታችኹት በሰማይ የተፈታ ይኾናል፤” (ማቴ. 16÷19) በማለት ፈጣሪ ከሰጣቸው የማሰርና የመፍታት (የማውገዝ) ቃል ኪዳን ጋራ የሚዛመድ ነው፡፡
ማውገዝ መወሰን፣ ማሰር፣ ሥርዐት መሥራት ነው፡፡ የተሳሳተ እምነትንና ትምህርትን ይህ ሐሰት ነው ብሎ“ማሰር”፣ ይህ ደግሞ እውነት ብሎ “መፍታት” የማውገዝ ሥልጣንን የሚያሳይ ነው፡፡ ሰይጣንንና ሠራዊቱን ኀይል ማሳጣትና ማሰርም የማውገዝን ሥልጣን ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ማውገዝ አጥፊውን ሰው በሥጋውና በነፍሱ ማሰር፣ መንፈሱን መግታት፣ ትምህርቱንና መጻሕፍቱን መከልከል ነው፡፡ እንዲህ ባለ ክፉ ሰው ላይ አድሮ የሚሠራውንም ርኵስ መንፈስ መቃወምና ማድከም፣ ሐሳቡና ዕቅዱ፣ የሰውዬውም ጠማማ እምነት ፍሬ ቢስ እንዲኾን ማድረግ ነው፡፡ ሰውዬው ቢሞት እንኳ ያደረበት መንፈስ የሚሞት አይደለምና የዘራው ክፉ ዘር እንዳያፈራ ማገድ የውግዘት ዓላማ ነው፡፡ ሰው ይኹን ተቋም እምነቱ፣ ድርጊቱ ተመርምሮ ሲደረስበት ክፉ ኾኖ ከተገኘ÷ ከሞተ በኋላም እንደ ግለሰብ ይኹን እንደ ሥርዐት (ተቋም) ሊወገዝ ይችላል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አርጌንስ ከሞተ ከ294 ዓመታት በኋላ ከነመጻሕፍቱ ባልተወገዘ ነበር፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ ገጽ 86)
ውግዘትን የሚያስከትለው እምነትና ተግባር
አንድ ሰው በውግዘት የሚለየው በህልውና እግዚአብሔር ያላመነ ሲኾን ብቻ አይደለም፡፡ በገዛ ፈቃዱ ሥርዐትን ያፈረሰ ሰው በውግዘት ሊለይ ይችላል፡፡ አለመታዘዝ ያስወግዛል፤ “ወእመ ኢተአዘዘ ይትወገዝ መኑሂ በሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ የማይታዘዝ ማንም ቢኾን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ይወገዛል” (ተግሣጽ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ቁጥር 4)፡፡ ሥርዐት የማያከብር ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ ሐዋርያት በመልእክታቸው ጽፈዋል፡፡ ቃሉም “ወንድሞች ሆይ÷ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይኾን ያለሥርዐት ከሚሄድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፤” የሚል ነው፡፡
ሰው በምግባር ሕጸጽ ይኹን በሃይማኖት ክሕደት ሊወገዝ ይችላል፡፡ አባ አብርሃም ሶርያዊ መማለጃ የሚቀበሉትንና ዕቍባት ያሏቸውን ሰዎች ዕቍባቶቻቸውን እንዲተዉ፣ ክፉ ልምዳቸውን ያርቅ ዘንድ ገዝቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ንግሥት አውዶክስያን ደኃን ስለበደለች ስለ ክፉ ምግባሯ ገዝቷታል፡፡ (ስንክ ዘታኅ 6፤ ድርሳነ ዮሐንስ የታሪክ ዓምድ)፡፡ ይኹን እንጂ ቶሎ ርምጃ የሚወሰደው ጥፋቱ የሃይማኖት ኾኖ ሲገኝ ነው፡፡ ስለዚህም ጌታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት ካስተማሩን ውጭ “ልዩ ትምህርት” የሚያመጣ ሁሉ የተወገዘ ነው፡፡ ከቀድሞው ሌላ መሠረት መሥርቷልና፤ በአበው ትምህርት፣ ወግና ምሳሌነት የማይሄድ ሥርዐት አፍራሽ ነውና፡፡ (2ተሰ.3÷6)፡፡
“ጌታችንን የማይወደው” ሁሉ የተወገዘ ነው፡፡ “ጌታችንን የማይወደው” ማለት ምግባር ያጎደለ ማለት ነው፡፡“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ.19÷15) ስለተባለ ያልወደደ አይታዘዝምና ምግባር ሊኖረው አይችልም፡፡ የሰው አስተሳሰቡም ኾነ ሥራው ውስብስብና እንደጊዜው የሚለዋወጥ ረቂቅ ነው፡፡ ስለሆነም የሚያስወግዙ ክፉ ተግባራትን ሁሉ በተናጠል በመዘርዘር ወስኖ ማስቀመጥ አይቻልም፤ ነገር ግን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ከተዘረዘሩት
የማውገዝ ሥልጣን
ማውገዝ ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትኹን” (ዘፍጥ.3÷17)፤“ብንክደው እርሱ ደግሞ ይክደናል” (2ጢሞ.2÷13)፤ “በሰው ፊት የሚክደኝን እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለኹ” (ማቴ.10÷33)፡፡ ስለኾነም ሥርዐተ ውግዘትን የሠራ፣ የወሰነ፣ ያሰረ፣ የታሰረውንም የሚፈታ፣ የሚዘጋ፣ የሚከፍት እግዚአብሔር ነው፡፡ (ራእ.3÷7፤ 5÷9)፡፡
ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ የኾነው እግዚአብሔር በገንዘቡ የወደደውን ለማድረግ ሥልጣን አለውና በቸርነቱ ይህን ሥልጣን ለአባቶቻችን ካህናት በጸጋ ሰጥቷቸዋል፡፡ (ማቴ.20÷15) “በዘአእመረ መንፈስ ቅዱስ”እንዲሉ “እርሱ መንፈስ ቅዱስ ባወቀው” ይህን ታላቅ ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው ሕገ ወጥ የኾኑ ሰዎችን ሕገ ወጥ የኾኑ ሰዎች ምእመናንን እንዳያናውጧቸው ለምእመናን ድኅነትና ዕረፍት አስቦ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የሚያስሩበትንና የሚፈቱበትን ሥልጣነ ክህነት የተቀበሉት ጌታችን እፍ ብሎባቸው “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቀርላቸዋል፤ የያዝችኹባቸው ተይዞባቸዋል፤” (ዮሐ.20÷22) ባላቸው ጊዜ ነው፡፡
ይህ የክህነት ሥልጣን በሐዋርያት ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በእግረ ሐዋርያት እየተተኩ፣ የእነርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለው እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ለሚነሡና ብቁ ኾነው ለሚገኙ ሁሉ ይህ የሥልጣነ ክህነት ቃል ኪዳን ተነግሯል፡፡ ይህም “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” (ማቴ.28÷20) በማለት በተናገረው ቃል ታውቋል፡፡ ሌላውም ምንጭ “ከመለኰትህ ገናንነት ምስጢር ለደቀ መዛሙርትህ እንዳልሰወርኽ እነርሱም ከእኛ የሰወሩት የለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ሊቀ ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት አድርገው ሾሙን እንጂ” በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት የተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ለሐዋርያውያን አበውና ለሊቃውንት መተላለፉን ያስረዳል፡፡ (ቅዳሴ አትናቴዎስ ቁ.1)፡፡
ከአሕዛብ ይልቅ መናፍቃንን፣ ከመናፍቃን ይልቅ ደግሞ የተወገዙ ሰዎችን መጠንቀቅ ይገባል
በአግባቡ ለተወገዙ ሰዎች ያለአግባብ መቆርቆር የአጋንንት ወዳጅ ከመኾን አይዘልም፤ በእግዚአብሔር ሥራ የማይደሰቱ፣ ሰይጣንና ግብረ አበሮቹን የማያወግዙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁ ናቸውና፡፡ በሃይማኖትና በምግባር ከተወገዙ ሰዎች መራቅ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፣ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይኾን ያለሥርዐት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን” በማለት በግልጽ ተናግሯል፡፡ (2ተሰ.3÷6)፡፡ ይህ ቃል ቁርጥ ትእዛዝ እንጂ ምክር አይደለም፤ “እናዛችኋለን” ይላልና፡፡ ከትእዛዝም ጥብቅ ትእዛዝ መኾኑን ደግሞ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” የሚለው ሐረግ ምስክር ነው፡፡ ይህ የሐዋርያው የብቻው ትእዛዝ ሳይኾን በዘመኑና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ቅዱሳን አበው ሁሉ ትእዛዝ ነው፡፡ “እናዛችኋለን” ይላል እንጂ “አዛችኋለኹ” አይልምና፡፡
ምግባር እና ሃይማኖታቸው ከከፋ ከኀጥአን፣ ከቀራጮችና ከአረመኔዎች ጋራ እንዳንተባበር መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቅቆናል፡፡ 1ቆሮ.5÷9፤ 15÷33፤ 2ኛዮሐ. ቁ.10 እና 11፤ 2ቆሮ.6÷14-16፡፡ ከክፉ ሥራችን አንመለስም ብለው በውግዘት የተለዩ ሰዎች ደግሞ ምድባቸው ከአሕዛብ፣ ከአረማውያን፣ ከኀጢአተኞች፣ ከዐመፀኞችና ከመናፍቃን ጋራ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን “ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔ እንደ ቀራጭ ይኹንልህ”የሚለው እንደእነዚህ ያሉትን ነውና፡፡ (ማቴ.8÷17) ፡፡ ሥራቸውና ክፋታቸው በግልጽ ከሚታወቅ ከአሕዛብና መመለክያነ ጣዖታት ይልቅ መጠንቀቅና አለመተባበር የሚገባው መናፍቃንን ነው፡፡ ከመናፍቃን በላይ ደግሞ ከተወገዙ ሰዎች መጠንቀቅ ይገባል፤ ምክንያቱም ከአሕዛብ ይልቅ መናፍቃን፣ ከመናፍቃን ይልቅ ደግሞ የተወገዙ ሰዎች ተመሳስሎ የመኖር ሰፊ ዕድል ስላላቸው ነው፡፡ ተመሳስለው ከኖሩ ደግሞ ሌሎችን በቀላሉ ወደራሳቸው የጥፋት ጎዳና ይስባሉ፡፡
ምንጭ፡- ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ፤ ትምህርተ ውግዘት፤ 1999 ዓ.ም
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment