Monday, April 7, 2014

በተጠርጣሪ የፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ኅቡእ አራማጆች ላይ ዛሬ ምስክሮች ይሰማሉ

holy trinity building
  • ከሓላፊነታቸው ውጭ የሚንቀሳቀሱ ፕሮቴስታንትና ጉዳዩን ፖሊቲካዊ ያደረጉ የደኅንነት አባላት ነን ባዮች የኮሌጁን ሓላፊዎች በመጫን ተጠርጣሪዎቹን ከተጠያቂነት ለማዳን እየሠሩ ነው፤ ተጠርጣሪዎቹ በኮሌጁ አስተዳደር የተከለከለ ስብሰባ በግቢው እንዲያካሒዱ ረድተዋቸዋል፡፡
  • በ‹ደኅንነት አባላቱ› የሚደገፉትና ‹‹የኢሕአዴግ ተወካዮች ነን›› የሚሉት ተጠርጣሪዎቹ፣ ለሃይማኖታቸው የቆሙትን ብዙኃኑን የኮሌጁን ደቀ መዛሙርት በስለትና በፌሮ ብረት የታገዘ ዛቻና ማስፈራራት እያደረሱባቸው ነው፤ ደቀ መዛሙርቱና የኮሌጁ አስተዳደር ጉዳዩን ለጸጥታ አካላት አስታውቀዋል፡፡
  • ተጠርጣሪዎቹ÷ ‹‹ጽንፈኝነትን ታስፋፋለች›› በማለት ቤተ ክርስቲያንን የከሰሱ ሲኾን ዋና ዲኑን ጨምሮ አንዳንድ የኮሌጁን ሓላፊዎች ደግሞ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ፖሊቲከኞች ናችኹ›› በሚል ውንጀላ በምርመራው ሒደት እንዳይሳተፉና ከቦታቸው ለማስነሣት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡፡
  • ኅቡእ የኑፋቄ አንቀሳቃሾችን በመመልመልና በማደራጀት የሚታወቁ ግለሰቦች (አሳምነው ዓብዩ፣ ደረጀ አጥናፌ እና ታምርኣየሁ አጥናፌ) ተጠርጣሪዎቹ ጥፋታቸውን እንዳያምኑ ከመገፋፋት ጀምሮ ደቀ መዛሙርቱን በጎጠኝነት በመከፋፈል አንድነታቸውን ለማሳጣትና ክሡን ለመቀልበስ እያሤሩ ነው፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ መጋቢት ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጠዋት፣ የፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ኅቡእ አንቀሳቃሾች ናቸው በሚል በተጠረጠሩ ዐሥር ደቀ መዛሙርት ላይ የጀመረውን ማጣራት ዛሬም ቀጥሎ ይውላል፡፡
በሦስት የኮሌጁ መምህራንና የሕግ ባለሞያ የሚታገዘው የአስተዳደር ጉባኤው በመጀመሪያ ቀን ውሎው፣ ዐሥሩ ተጠርጣሪዎች በተናጠል እንዲቀርቡ በማድረግ በኻያ ነጥቦች በተደራጁና በየስማቸው አንጻር ተለይተው በሰፈሩ ክሦች ላይ የእምነት ክሕደት ቃላቸውን ጠይቋቸዋል፤ ኹሉም ተጠርጣሪዎች ‹‹እንዲኽ አልተናርንም፤ እንዲኽም አላደረግንም›› በሚል የቀረቡባቸውን ክሦች እየተማሉና እየተገዘቱ መካዳቸው ታውቋል፡፡
የኅቡእ እንቅስቃሴው መጋለጥና የአስተዳደር ጉባኤው ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ድንጋጤም ብስጭትም እንዳሳደረባቸው በግልጽ የታየባቸው ተጠርጣሪዎቹ እንደተለመደው፣ ‹‹ክሡ ፖሊቲካዊ ነው፤ ከሣሾቻችን ማኅበረ ቅዱሳን የኾኑት እገሌና እገሌ ናቸው፤››በማለት መደናገር ለመፍጠር ሞክረው የነበረ ቢኾንም በአስተዳደር ጉባኤው አባላት እየተመከሩና እየተገሠጹ አደብ እንዲገዙ መደረጋቸው ተሰምቷል፡፡
የአስተዳደር ጉባኤው ዛሬ ከቀትር በኋላ ለኹለተኛ ጊዜ በሚሠየምበት ስብሰባ፣ የተጠርጣሪዎቹን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ኅቡእ እንቅስቃሴ የሚያስረዱ የ፵፭ የሰው ምስክሮችን ቃልማዳመጡን እንደሚቀጥል ተገልጦአል፡፡
የኮሌጁን የቀን መደበኛ የዲግሪ መርሐ ግብር የሚከታተሉት ከ፩ኛ – ፬ኛ ዓመት ያሉት ደቀ መዛሙርት አጠቃላይ ቁጥር ፻፶ ነው፤ ከእኒህም ውስጥ የድምፅ፣ የጽሑፍና የሰው አስረጅዎች የቀረቡባቸውን ተጠርጣሪዎች ጨምሮ ክትትል የሚደረግባቸው ከኻያ የማይበልጡ በመኾኑብዙኃኑ ደቀ መዛሙርት ለሃይማኖታቸው መጽናት የቆሙ ርቱዓን እንደኾኑ ግልጽ ነው – ‹‹ዐሥሩንም ተጠርጣሪዎች ከንግግራቸው እስከ ግብራቸው ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፤›› ብለዋል በማስረጃቸው ሐቀኝነት ላይ ስላላቸው ርግጠኝነት የተናገሩ ኹለት የደቀ መዛሙርት ም/ቤት አባላት፡፡
ብዙኃኑ ጽኑዓን ኦርቶዶክሳውያን ደቀ መዛሙርት በተጠርጣሪዎቹና አደራጆቻቸው ‹‹ያልበራላቸው የጌታ ጠላቶች፣ በጨለማ ጫካ የሚኖሩ፣ ደንቆሮዎችና ግንዞች›› የሚሉ ስድቦችና ዘለፋዎች የሚደርሱባቸው ሲኾን ይህም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአበው መነኰሳትና ቀሳውስት እንዲኹም በአኃው ዲያቆናት ላይ ሳይቀር የሚሰነዘር እንደኾነ በክሡ መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡
አራተኛ ዓመት ደቀ መዛሙርት ተራ ገብተው በሚያስተምሩበት ጸሎት ቤት በተለይ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ትኩረት ሰጥተው ሲያስተምሩ ‹‹ተረታ ተረትኽን ተውና ውረድ›› በሚል ግልጽ ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው ተገልጦአል፡፡ የክሡ መግለጫ ጨምሮ እንደሚያስረዳው፣ ትኩረታቸውን በአንደኛ ዓመት ደቀ መዛሙርት ላይ አድርገው የሚንቀሳቀሱት የፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ኅቡእ አንቀሳቃሾቹ፣ አዲስ ገቢ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ቴዎሎጂ መማር ከፈለግኽ የበላኸውን ትፋ!›› በማለት በኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸውም ያሸማቅቋቸዋል፡፡
ከኮሌጁ ውጭ በሚሰጣቸው አስተምህሮና ተልእኮ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ የፕሮቴስታንት አስተምህሮን ለማሰራጨት የሚሠሩት ተጠርጣሪዎቹ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን አትሰብክም፤ የምትሰብከው ፍጡራንን ነው›› ከማለት አልፈው ‹‹ጽንፈኝነትን ታስፋፋለች፤ የተወሰነ ጎሳ ናት፤›› በሚልም በትምክህተኝነት ይከሷታል፡፡
ይህን የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጠባብ ፖሊቲከኞች ክሥ የሚያስተጋቡት የስም ደቀ መዛሙርት ራሳቸውን ‹‹የኢሕአዴግ ተወካይ ነኝ››ለማለት የማያፍሩ ሲኾኑ ጉዳያቸው መታየት ከጀመረበት ካለፈው ኀሙስ ምሽት ጀምሮ የስለት መሣርያዎችና ፌሮ ብረት ይዘው በመኝታ ክፍል ኮሪዶሮች ላይ በመንቆራጠጥ ኑፋቄአቸውንና ክሕደታቸውን ያጋለጡ ደቀ መዛሙርትን ‹‹ፖሊቲከኞችና የማኅበረ ቅዱሳን አጫፋሪዎች››በማለት እየዛቱባቸውና እያስፈሯሯቸው መኾኑ ተገልጦአል፡፡
ጠብ አጫሪ አካሔዳቸው ግጭት ቀስቅሶ ወደ ደም መፋሰስ ከማምራቱ በፊት የኮሌጁ አስተዳደር እኒኽን ግለሰቦች እንዲቆጣጠር ደቀ መዛሙርቱ በዚያው ዕለት ምሽት ለኮሌጁ አስተዳደር ኹኔታውን ከግለሰቦቹ ስም ዝርዝር ጋራ አያይዘው የገለጹ ሲኾን አስተዳደሩም በበኩሉ ለሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
ከዚኹ ጋራ በተያያዘ ራሳቸውን በደኅንነት አባልነት ያስተዋወቁ ግለሰቦች፣ የቀረቡት ክሦች ሃይማኖታዊ ሳይኾን ፖሊቲካዊ ናቸው በሚል በኮሌጁ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና የአስተዳደር ሓላፊዎች ላይ ጫና በመፍጠር ክሡን ለማዳፈንና ተጠርጣሪዎቹን ከተጠያቂነት ለማዳን እየሠሩ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ ከቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ሓላፊነት ተወግዶ ከኮሌጁ የተባረረው ዘላለም ረድኤትን፣ ተጠርጣሪዎችን በመመልመልና በማደራጀት የሚታወቁ ሦስት ግለሰቦችን በአስተባባሪነት የጠቀሰው የመረጃ ምንጩ÷ ጫናው በኮሌጁ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ በኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ፣ በአካዳሚክ ዲኑና በቀን መርሐ ግብር ሓላፊ ላይ ያተኮረ መኾኑን አስረድቷል፡፡
የኮሌጁ አስተዳደር በቅጽሩ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳይካሔድ በከለከለበት ሰሞናዊ ኹኔታ ችግሩን በማባባስ የሚወቀሱና ተጠርጣሪዎችን በኅቡእ በማደራጀት የሚታወቁ ግለሰቦች የደኅንነት ነን ባዮቹን አይዞኽ ባይነት ተገን በማድረግ በአንድ በኩል ‹‹በዕርቅ እንፈታለን›› በሚል ጉዳዩን በሽምግልና ኮሚቴ ለማድበስበስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩን ከተወላጅነትና ክልላዊነት ጋራ በማገናኘትና የኾነ ወገን በማንነቱ እንደተፈረጀ በማስመሰል ደቀ መዛሙርቱን በጎሰኝነት የሚከፋፍል ዘመቻ በግቢው እያካሔዱ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የደኅንነት አባላት ነን በሚል በኮሌጁ ሓላፊዎች ላይ ጫና ለመፍጠርና ተጠርጣሪዎችን ከተጠያቂነት ለማዳን ከሚሠሩት ግለሰቦች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሚገኙበት የገለጹ የጉዳዩ ታዛቢዎች፣ የግለሰቦቹ ተልእኮ ከጸጥታ አንጻር ብቻና ስምሪታቸውም ሕጋዊ ስለመኾኑ መረጋገጥ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡ የግለሰቦቹ ስምሪት በርግጥም ሕጋዊ ከኾነ ደግሞ የተልእኳቸው አፈጻጸም የእምነታቸውን ተጽዕኖ በጣልቃ ገብነት ከማሳረፍ የጸዳና የቤተ ክርስቲያኒቷን ሉዓላዊነትና የትምህርት ተቋሞቿን ነጻነት ያከበረ ሊኾን እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment