Monday, April 7, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን የደረሰበት ፈታኝ ወቅት

FACT magazine Megabit 3rd cover(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፴፱፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)
ተመስገን ደሳለኝ
  • በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነት በማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡ ወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪከማለት አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ/የግንቦት ሰባት ከበሮ መቺ/›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡
  • የማኅበሩ አመራሮች እንዲኽ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረኸት ስምዖን እስከ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሀ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሯቸው ተገኝተው ውንጀላው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
  • በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነት ጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
  • በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበት አስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ኹለት ናቸው፡፡ ‹‹ችግሮች ኹሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበትን ይህን ፈታኝ ጊዜ ተከትለው የሚመጡ ኹለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበውየስቅለት ቀን ነው፡፡ ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ነው፡፡
  • የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚውሉበት የስቅለት በዓል የትኞቹም የሕገ መንግሥቱ ሐሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ሥርዓት እጁን ከማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እንዲያነሣ ለመጠየቅ ብሎም ሕያውነታቸውን የመሠረቱበትን ሃይማኖት ለማስከበር የተመቸ ቀን ስለመኾኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንዳይኾን ተስፋ አደርጋለኹ፡፡
‹‹ማሕበረ ወያኔ››
በኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው መንግሥት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አውሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ቢደበድብም በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምራት ኾነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጭ›› ቤዝ-ዓምባው በተወሰነ መልኩም ቢኾን ለጥቃት የመጋለጥ ዕድሉ አናሳ በኾነው የሳህል በርሓ በመኾኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያ አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመኾኑ፣ በርካታ ክፉ ቀናትን ካሳለፉባቸው ቦታዎች መካከል በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ መደበቅ እንደኾነና በየስፍራው መዘዋወር ሲፈልጉም ራሳቸውን ከሚሰውሩባቸው ዘዴዎች ውስጥ በቀሳውስቱና መነኰሳቱ አልባሳት መጠቀም አንዱ እንደነበር በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊና ኣባይ ፀሃዬን ጨምሮ የአመራር አባላቱ የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡
በርግጥ እኒኽ የወያኔ መሪዎች በእንዲህ ዓይነቱ ከመርፌ ዓይን በእጅጉ በጠበበ ዕድል ‹ሕይወታችን ከሞት ተርፎ ኰሎኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዝምባቡዌ ሸኝተን በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥና ለኻያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታኽል ታላቅ አገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢኾን አዳጋች ይመስለኛል፤ የኾነው ግን ይኸው ነበር፡፡
‹‹ማሕበረ ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግሥጋሴ ሲያፋጥኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሰብሳቢነት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴ የጦር ማሠልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርስቲውም ተዘጋ፡፡
ከመላው ዘማቾች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የኾኑ ሠልጣኞች በየድንኳኑ እየተሰበሰቡ ፈጣሪ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ በጸሎት መማፀን የሕይወታቸው አካል አደረጉት፡፡ ከቀናት በኋላ በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ኹለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል እሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሰየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡…ይኹንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም. በፓዌ መተከል ዞን የተደረገውን የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ቅዱሳን ከሚዘከሩባቸው ሌሎች የጽዋ ማኅበራት ጋር በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የኾነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
ሃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይኾን ለሥልጣን እርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ በሚል ርእስ ሠርቶት ኋላ ወደ መጽሐፍ በቀየረው “The Origin of TPLF” የጥናት ጽሑፉ ላይ÷ ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሃት ነጋ የሚመራ የስለያ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኰሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ሥር የማስገዛት ሥራ ሠርቷል›› ሲል በገጽ 317 ላይ ገልጧል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሃይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሣበትን ገፊ ምክንያትም እንዲኽ በማለት አብራርቷል፡-
‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ ዕንቅፋት እንደነበረች ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ሥር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሣም የእርስዋን ተጽዕኖ ለማግለል ጥልቅ ርምጃ ወስደዋል፡፡›› /ገጽ 315 – 316/
ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ ርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያን ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ሥር ማካተት›› እንደነበረ በዚኹ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይኹንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያኽል የምንደነግጠው፣ ዶክተሩ ከዚኹ ጋራ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሣሣውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢኾን ሐሳብ የተቃኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱን በመሪነትና ሐሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖሊቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡
የኾነው ኾኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም. ድረስ ባሠለጠናቸው ካድሬ ካህናት አማካይነት ‹‹ነጻ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ ክህነት አስተዳደር (ከማእከላዊ ሲኖዶስ የተገነጠለ) መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእኒኽ አብያተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ ዓሥርቱ ትእዛዛት በፍጹም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡
እንዲኽ ዓይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምና ላይም መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የኾኑ ታጋዮችን እየመረጠና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሐሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደኾነ በመግለጽ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ በዚኽ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢኾን የአንዳንድ ዓረብ አገሮችን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦቹ በገፍ ርዳታ ያጎረፈለት ሲኾን ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡
ከመንግሥት ለውጥ በኋላም ሁለቱንም እምነቶች የተቆጣጠረው በታጋይና ምልምል ‹ካህናት› እና ‹ሼኾች› ለመኾኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አስተዳደራዊ መዋቅር የበላይ በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ከሚገኙ ዐሥራ ስምንት መምሪያዎች ውስጥ ዐሥራ ስድስት ያኽሉ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ኹኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡
በተለይ ዋነኛው ሰው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቅ/ሲኖዶሱን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው፣ ትችትና ተቃውሞ በተሰነዘረባቸው ቁጥር ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚኽ መንበር ላይ የተቀመጥኹት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለሥርዓቱ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚኽ ቀደም ለሦስት ወራት የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ኾነው የሠሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ኹልጊዜ ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው ‹መንግሥት እንዲኽ አለ›፤ ‹መንግሥት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል(በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ ነገር የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለኹ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡)
በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞው መጅሊስ የባሰ እንደኾነ በርካታ ሙስሊም ምእመናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዝዳንቶች ሲኾን፣ ይህች ዓይነቱ ጫዎታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመኾኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼኽ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ ምእመናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር እንደሚደፍሩ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታጋይ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሼኽ ኪያር መሐመድ ከእኚኹ ታጋይ ምክትላቸው ጋራ በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸውና ‹‹መንግሥት የሚያዘውን ኹሉ ለመሥራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከ ማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከሓላፊነታቸው ሊነሡ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡
ኢሕአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ ገበያው››
ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤ ከሦስት ጉዳዮች አንጻር በአዲስ መሥመር ለመተንተን እገደዳለኹ፡-
የመጀመሪያው÷ ቤተ ክህነት በነገሥታቱ ዘመን የነበራትን ፖሊቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳ ራሱ ኢሕአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ኾነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማኅበራዊ ተቀባይነት ባላቸው ሼኾች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቀሰቅስ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ እንዲኹም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናን ይኹን የደርጉን ኹሉንም ሃይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብሩ ኣስራት እንደ ሼኾች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ብዙኃኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚኽ ዘመንም በአብያተ እምነቶች ካድሬ ጳጳሳትንና ካድሬ ሼኾችን አሰርጎ የማስገባቱ ምሥጢር ይኸው ነው፡፡
እንደ ኹለተኛ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው÷ የታገለለትን ዘውግ ተኰር ፖሊቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የኹሉም ሃይማኖቶች ‹‹የሰው ልጆች ኹሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመኾናቸው አኳያ፣ ማንነታቸውን በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚኽም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹መንፈሳውያን› በየእምነቱ ተቋማቱ እንዲፈለፈሉና ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሠረተ ብቻ መኾኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡
ይህ ‹ዕውቀታቸውም› ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስና በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፣ እንዲሁም በእምነት አቋማቸው በተከታዮች ዘንድ ተኣማኒና ቅቡል ያልኾኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከ ማድረግ ያደረሳቸው፡፡ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም ጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም. ‹‹ለዋናው መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲኽ ሲል ገልጾታል፡-
‹‹ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመኾናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠለጠለ ኾኗል፡፡››
ከዚኽ ሪፖርት በኋላም እንኳ በቀጣዩ ሢመት ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገደድናል፡፡
አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ተሳክቷል ሊባል ባይቻልም፣ በሥነ ምግባር መታነፅ፣ በአገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም በወገንነትና በሓላፊነት ስሜት መቆም፣ የትኛውንም ሕገ ወጥነት ለምን ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሑ አድርጎ የሚነሣ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልንታሳቢ አድርጎ እየሠራ ያለውን ሤራ ነው ብዬ አስባለኹ፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ ሰዎች በዚኽ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደኾነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡
ከዚኽ ጋራ አንሥተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵዊ ብሔርተኝነት ጋራ የሚያያዝ ነው፡፡ የሃይማኖቱና የማእከላዊ መንግሥቱ የቅድመ – አብዮቱ ጋብቻ (በምንም ዓይነት መከራከርያ ልንሟገትለት ባንችልም) ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሃይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ኾኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሃይማኖቱ ተቋማዊ ነጻነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ኹሉ ሲያደርግ፣ ሃይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡
ገደል አፋፍ የቆመው ማኅበረ ቅዱሳን…
ሥርዓቱ የሃይማኖት ተቋማቱንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ ምክንያቶች ኾነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኋቸውን ሦስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረጉበት፣ በቀጥታ በምእመናኑ የተመሠረቱ ማኅበራት መኾናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያኽል ከኦርቶዶክስ ክርስትና – ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከእስልምና ያለፉትን ኹለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ኾኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግሥትንም ኾነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ይኹንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ኾነ መሰል ማኅበራት ጠንካራ እንደኾነ የሚነገርለትን ማኅበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ዒላማ አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማኅበሩ አባላት በዓለማዊ/ዘመናዊ ዕውቀት የተራቀቁ፣ በሀገራዊ አንድነት ፈጽሞ የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ…የመኾናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ አስባለኹ፡፡
በርግጥ በአቶ መለስ ይዘጋጅ እንደነበር ከኅልፈቱ በኋላ በይፋ በተነገረለት የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት – አዲስ ራዕይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖሊቲከኞች፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፤ አንድ ሃይማኖት አንድ ሀገር እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፣ ከዚኽም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎች በማቅረብ ለማነሣሣትና ለማተረማመስ ሲሠሩ ማየት የተለመደ ኾኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ በድፍን ፍረጃ ዘልሎ መንፈሳውን ማኅበራትን በስም ጠቅሶ ያወገዘባቸው አጋጣሚዎች ብዙም አልነበሩም፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይኹን ማኅበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ኾኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ ዐደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ሥቅየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈጸም ጉዳዩን በጠመንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡
‹‹ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?›› በሚል ከስድስት ወራት በፊት በዚኹ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኁት ኹሉ፣ ከላይ በተዘረዘሩ የፖሊቲካ አጀንዳዎችና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ዓለማዊ ይኹን መንፈሳዊ ነጻ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለው የእነ ኣባይ – በረከት መንግሥት፣ በአኹኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍጹም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያኽል አንዱን በአዲስ መሥመር ላቅርብ፡-
ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ አገልጋዩና ምእመኑ እንዲወያይበት ሲኖዶሱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከኹሉም አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ 2700 ሰዎች የተሳተፉበትና በድምሩ 14 ቀናት የፈጀ ውይይት ይጠራል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነት በተመራውና ጥናቱን በሠራው የባለሞያ ቡድን ፈጻሚነት የተከናወነው ውይይት ሲካሔድ በነበረባቸው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በአንዱ ቀን ‹ከአንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ አጋጥሟል› መባሉን ተከትሎ በሊቀ ጳጳሱና በፓትርያርኩ መካከል የሚከተለው ውዝግብ መካሔዱን ሰምቻለኹ፡-
‹‹ጥናቱን የሚሠሩት ባለሞያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሞያዎች ናቸው የሠሩት››
‹‹አይደለም! የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሞያቸውን ዓሥራት ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍጹም ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢኾንስ፣ ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግሥት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሣሉና የጸጥታ ስጋት አለ››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሡት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሐሳቡን ይግለጽ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሔ ይኾናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ ይተችበት ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››
ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን ቢሮ ድረስ መጥቶ፣ ትእዛዙን ያስተላለፈውን አካል ገልጾ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን ‹እናንተ የጸጥታ ስጋት አለ› ብላችኹ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱ ለምእመናኑ ኹኔታውን ዘርዝረን እንገልጻለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ‹ውይይቱ ይቋረጥ› የሚለው ማስፈራሪያ ለጊዜው ግልጽ ባልኾነ ምክንያት ሊነሣ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማኅበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና በአገዛዙ ለሚወሰድበት ማንኛውም ርምጃ ተባባሪ መኾናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ሌላው መንግሥትና ፓትርያርኩ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሠሩ መኾናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና ያወጡትን የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡
ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ÷ የማኅበሩና የዋነኛ መሥራቾችና አባላት የባንክ አካውንት፣ ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ጨምሮ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ ት/ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የአክስዮን ተቋማት፣ የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡና በመግባት ላይ ያሉ ዕቃዎች በሚመለከታቸው የመንግሥት መሥ/ቤቶች እንዲታገዱ በቅ/ሲኖዶስ አማካይነት ደብዳቤ እንዲጻፍ፤ ከምእመናን በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው ዓሥራት እየፈረጠመበት ስለኾነ እንዳይቀበል ይከልከል፤ የግቢ ጉባኤያት(የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው ትምህርት እንዳይወሰዱብን በደንብ መሥራት፤ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅነቱ ሥር ወጥቶ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ውስጥ አንድ ንኡስ ክፍል ይኹን የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ከዚኽ ሤራ ጀርባ ፓትርያርኩና ተቃዋሚዎቹ አግዞናል የሚሉት መንግሥት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪ መሰብሰቢያ አዳራሹን ለመጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፈቃድ እንደኾነ ከመግለጽ በዘለለ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚኽ ተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም፤ አይዟችኹ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚኽ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም እንጂ ካስወጡን መንግሥታችን ቸር ስለኾነ ከእርሱ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ርስ-በርስ ለመረዳዳት ‹‹የአዲስ አበባ አገልጋዮች ማኅበር እንመሠርታለን›› እስከ ማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተቀሰቀሱት 169 አድባራትና ገዳማት እንዲኹም ከዐሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት ያኽል አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ያኽል ተሳታፊዎች ብቻ እንደነበሩ ከምንጮች አረጋግጫለኹ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነት በማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡ ወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪ ከማለት አሻግረው‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ/የግንቦት ሰባት ከበሮ መቺ/›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእኒኽ ጥናት ተብዬዎች መደምደሚያ‹‹ማኅበሩ ከጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች ጋራ ትስስር የፈጠሩና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ ያላቸው ትምክህተኞች ምሽግ ነው፤ አመራሩና የኅትመት ውጤቶቹ የፖሊቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፤ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር/አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሠራል፤ በውጭ ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡
የማኅበሩ አመራሮች እንዲኽ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረኸት ስምዖን እስከ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሀ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነት ጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ከእነዶ/ር ሺፈራው ጋር ስብሰባውን ባካሔደበት አንድ ሰሞን ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ዶ/ር ሺፈራው አቡኑን ቃል በቃል እንደነገራቸው የተሰማው ነገር ይህን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-
‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ያሉና ማኅበሩን ለተቃውሞ ፖሊቲካ እንቅስቃሴ የሚጠቀሙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ፤››
‹‹ምንድን ነው ማስረጃኽ?››
‹‹ዝርዝራቸው አለኝ፤ በሀገር ውስጥ ካሉ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሠማሩም አሉበት፤››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማኅበሩ ከእንዲኽ ዓይነት ተግባር የራቀ ነው፤ ማስረጃ አለ ካልኽ ደግሞ አቅርብና እንየው፤ ከዚኽ ውጭ እንዲኽ ዓይነቱን ክሥ አንቀበልም፡፡››
በአናቱም የግንባሩ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት የማኅበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትንና ለምን ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለጽ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማኅበሩ ዕጣ ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡-
‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጠብጥ ለመፍጠር፣ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህት ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እኒኽ የትምክኽት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሃይማኖትን በፖሊቲካ ዓላማ ዙሪያ ብቻ መጠቀሚያ አድርገው እየሠሩ ለመኾናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ አንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ኹነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› /አዲስ ራዕይ፤ ሐምሌ – ነሐሴ 2005 ዓ.ም.)
የኾነው ኾኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማኅበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት ዕቅዶች ማኅበሩ መሠረቱን ከጣለበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት አባላት ከማለያየት፣ ንብረቶቹን ከመውረስ ጋራ የሚያያዙ ናቸው፡፡ (ከላይ የተመለከተው የተቃዋሚዎች የአቋም መግለጫም ለማኅበሩ የደም ሥር ለኾኑት እኒኽ ኹለት ጉዳዮች ትኩረት የሰጠ መኾኑን ልብ ይሏል)
ስቅለትን ለተቃውሞ
ኢሕአዴግ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን በመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ ርምጃዎች›› በሚል ርእስ ለካድሬዎች በበተነው ድርሳን (በአቶ መለስ እንደተዘጋጀ ይገመታል)፣ ይህን አኹን የተነጋገርንበትን ሃይማኖታዊ ተቋማትን ለሚያቅዳቸው ሥልጣንን የማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለሥርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደኾነ ያሠምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከኾነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳውያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሃይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መኾን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልጽ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲኽ ከመጅሊሱ እስከ ማኅበረ ቅዱሳን ያየነው መንግሥታዊ አፈና የዚኽን ኻያ ዓመት የሞላው የተጻፈ ሐሳብ መተግበርን ነው፡፡
ግና፤ ከዚኽ ቀደም በተጻፈ ነውረኛ ሐሳብ ትግበራ ፊት ከኹለት ዐሥርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኋቸው አሳማኝ መረጃዎችና ተጨባጭ ኹነቶች በተከታታይ መከሠት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበት አስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ኹለት ናቸው፡፡
‹‹ችግሮች ኹሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ኹለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበው የስቅለት ቀን ነው፡፡ ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩን የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ለማስገደጃነት መጠቀም ነው፡፡
በተለይም የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚውሉበት የስቅለት በዓል አገዛዙ እጁን ከማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እንዲያነሣ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመኾኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንዳይኾን ተስፋ አደርጋለኹ፡፡ ከዚኽ የቀረው ጉዳይ ‹‹ሃይማኖታችኹን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳት መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግሥት መታመን ብቻ እንደሚኾን እንረዳለን፡፡
************************************************************
ማስታወሻ፡- ጽሑፉ በመጽሔቱ የቀረበበት ርእስ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት›› የሚል ነው፡፡ ይኸው የጽሑፉ ዐቢይ ርእስና ጽሑፉ ማኅበረ ቅዱሳን ለደረሰበት ፈታኝ ወቅት በመፍትሔነት የጠቆማቸው ነጥቦች ከጡመራ መድረኩ አንጻር ከመጠነኛ ማስተካከያ ጋራ ተጣጥመው እንዲቀርቡ መደረጋቸውን እንገልጻለን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment