Thursday, June 27, 2013

የተሐድሶ መናፍቃንና ጥቅመኞቻቸው የሐረር ደ/ሣ/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ከሀ/ስብከቱ አስተዳደር ለመለየት እየቀሰቀሱ ነው

  • መናፍቃኑና ጥቅመኞቻቸው ሽፋን ሲሰጥ የቆየው የደብሩ አለቃ ከሓላፊነቱ ታግዷል!
  • በሀ/ስብከቱ የታሸገው የሰበካ ጉ/ጽ/ቤትና ሙዳይ ምጽዋት ተከፍቶ ገንዘቡ ተመዝብሯል
  • የሀ/ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ እያስጨነቁ የሚገኙት አለቃውና ግብረ በላዎቹ በሊቀ ጳጳሱ ላይ ሁከት ለመቀስቀስ እየተዘጋጁ ነው፤ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የክልሉ ፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ሰላምን የማስከበር ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል
  • ‹‹ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉ ሌቦች ናቸው፡፡›› /አለቃው ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ለተከታዮቹ ካሰማው የመድረክ ንግግር/
  • የቤተ ክህነቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ርምጃ÷ እንደ ‹አባ› ጳውሎስ ያለብቃታቸው የተሰገሰጉ፣ የቤተ ክርስቲያን አሐቲነትና ተቋማዊ ነጻነት ፀር የኾኑ የሙስናና ኑፋቄ መሸሸጊያዎችን በስፋትና በጥልቀት በማጥራት መጀመር ይኖርበታል


በቀደሙ ዘገባዎቻችን በተደጋጋሚ አንሥተነዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ በቃል የሚነገረውና በውሳኔ የተደረሰበት አቋም በተግባር ተተርጉሞ ችግሩ ሁነኛ መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስም በቀጣይነት መወትወታችንን እንቀጥላለን፡፡ ሙስና እና ኑፋቄ ተሳስረውና ተመጋግበው በኦርቶዶክሳዊ ማንነታችንና በተቋማዊ አንድነታችን ላይ የጋረጡብን አደጋ ከቤተ ክህነታችን አስተዳደር የወቅቱ ዋነኛ ፈተናዎች መካከል ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለናል፡፡ የውስጥ ጥቅመኞችና ሕገ ወጥ ቡድኖች ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ግንባር ቀደም መሪዎች ጋራ በተለያየ ሽፋን የተሳሰሩበት ይኸው አደጋ ሰሞኑን የክፋቱን ዳርቻ እያሳየን ነው፡፡
የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞን ሀ/ስብከት የ‹ገለልተኛ አስተዳደር› ጠያቂዎች እንደመነሻ
ከጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት አቤቱታ አቅራቢዎች ነን በሚል ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን የወነጀሉ ግለሰቦች የመፍትሔ ሐሳባቸው በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን መርሕና ሕግ የተወሰነ ሳይሆን በ‹ገለልተኛ› አስተዳደር እስከ መመራት መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ግለሰባዊ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበትንና አፅራረ ቤተ ክርስቲያን የጥፋት ተልእኳቸውን የሚፈጽሙበትን ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር መኾኑ ግልጽ ነው፡፡
እኒህ ግለሰቦች÷ በሀ/ስብከቱ ስም ተጠይቆ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተፈቅዶ ከተላከው 2000 ጥራዝ ሞዴል ፴ የገቢ መሰብሰቢያ ላይ 1000 ሞዴል ፴ ደብቀው የሀ/ስብከቱን ሥራ ሲያውኩ ከነበሩት ሓላፊዎች ጋራ አባሪ ተባባሪ የነበሩ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ፣ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ከወረዳዎች (ሀገረ ማርያም፣ ቀርጫ) ተሰብስቦ ለመንበረ ፓትርያሪኩ ገቢ መደረግ የነበረበትን ፳% የገንዘብ አስተዋፅኦ በግላቸው ሰብስበው በከፊልና ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም ባሻገር መዝብረው እስከ መሰወር የደረሱ ለመኾናቸው ከሻኪሶ ወረዳ ቤተ ክህነት እና ሻኪሶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሰነድ ተደግፈው ለመንበረ ፓትርያሪኩ የቀረቡ አቤቱታዎች የሚያረጋግጡት ሐቅ ነው፡፡
እኒህን ጥቅመኞች ለአቤቱታ በማበረታታት በሐቀኛ የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ በመፍጠር የሚታወቁት የቀድሞው የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከቦታው ተነሥተው ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሲመደቡ፣ለካህናት ማሠልጠኛ ማሠርያ በሚል ከሀገረ ማርያም ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም እና ከሞያሌ ወረዳ ቤተ ክህነት የተሰበሰበውን በድምሩ ብር 32,000 ለጽ/ቤቱ አላስረከቡም፤ ገንዘቡ በሐዋሳ ዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በስማቸው በተከፈተ አካውንት መቀመጡም ተገልጧል፡፡
ከሻኪሶ ቅድስት ማርያም እና ከሻኪሶ ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ ሹፌር አማካይነት ሕግን ባልተከተለ አሠራር ወጪ ተደርጎ በሻኪሶ ንግድ ባንክ በኩል የተላከና በኦዲተር ማጣራት የተረጋገጠ ብር 40,000 ስለመኖሩም የሀ/ስብከቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ከጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ተነሥተው ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሲመደቡ የመንበረ ጵጵስናውን ጽ/ቤት ማኅተም እንዳላስረከቡ ሁሉ፣ ማኅተምና የሚፈለግባቸውን ንብረት ሳያስረክቡ ጠፍተው የሚሄዱ የወረዳና የአጥቢያ ሓላፊዎችን በተዛወሩበት ሀ/ስብከት ያለመሸኛ ተቀብለው በመቅጠራቸውም ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል፡፡
የሊቀ ጳጳሱ አፍራሽ አካሄድ በሰሞኑ የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በ‹ገለልተኛ› ቤተ ክርስቲያን እንመራለን እስከማለት ደርሰው ከዛቱት ጥቅመኞች ጋራ ባላቸው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከዚህም ባለፈና ግሁድ በኾነ መልኩ የሚታይ ነው፡፡
ለአብነት ያህል – ሊቀ ጳጳሱ በመጥፎ አስተዳደራቸው በጉጂ ቦረናና ሊበን ዞን ሀ/ስብከት ትተውት የሄዱት ክፍተት በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ተጽዕኖ ውስጥ ለሚዋዥቁ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያንም ምቹ ኹኔታ የፈጠረ ነበር፡፡ ሀ/ስብከቱ ለ31ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ የክብረ መንግሥት ቅ/ሚካኤል እና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የታገደ ጉባኤ የተካሄደበት፣ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በተፃራሪ ሕገ ወጥ የሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር የተፈጸመበት በዚህም ደብሩ ‹‹ከሀ/ስብከቱ መመሪያ ውጭ እንዲንቀሳቀስ መንገድ የተከፈተበት›› ኾኗል፡፡ እኒህ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሀ/ስብከቱ ዕውቅና ውጭ የኾነ አጥቢያ ያቋቋሙና ያጠናከሩ መኾናቸውን ያስታውሷል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ እንደወትሮው ሁሉ የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል ያከበሩት በኢየሩሳሌም ሲኾን ይኸውም የወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን የጉዞ ወኪል አጅበው ለሊቀ ጳጳስ በማይመጥን ክብር በየመደብሩ በመዘዋወር እንደነበር ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ኾነው የመመደብ ፍላጎት እንደነበራቸው ቢነገርም፣ ከምደባው ጀርባ ግን የጉዞ ወኪሉንና ለጉዞ ወኪሉ እንደ ኦፕሬተር ይሠራሉ የሚባሉትን ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ስምሪትና ጥቅም የማደላደል ዓላማ እንደነበረ ተጠቁሟል፡፡
ደግነቱ፣ ምደባውም እንደታሰበው አለመኾኑ ነው፡፡
ደግነቱ፣ ሌሎች የጉዞ ወኪሎች ያስተባበሯቸው ተሳላሚዎች ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ዘንድ ቀርበው መመሪያ ተቀብለው በቡራኬ ሲሸኙ ከጉዞ ወኪልነት ባሻገር ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ይፈጸምበታል የሚባለው የወ/ሮ እጅጋየሁ የጉዞ ወኪል አለመቅረቡ ብቻ ሳይሆን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሚገኙባቸው መርሐ ግብሮች እንዳይገኝ ግልጽ መመሪያ መሰጠቱ ነው፡፡
ደግነቱ፣ ሕገ ወጥ ሰባክያኑና ዘማርያኑም ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ግንባር ቀደም መሪዎች ጋራ በማበር በቅጡ ሳያውቋት እናስተምራለን ብለው በሚሳለቁበትና ራሳቸውን በአገልጋይነት ሠይመው ከተደረደሩበት የቤተ ክርስቲያናችን የዴር ሡልጣን ገዳም ዐውደ ምሕረት በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ነጎድጓዳዊ ተቃውሞ መወገዳቸው ነው፡፡ ምስጋና ሕገ ወጦቹ ከመድረኩ የተወገዱበትን የምእመኑን መንፈሳዊ ወኔ በመቀስቀስ ጅምሩን ለወሰዱት እንደ ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ ላሉት አገልጋዮች ይኹንና፣ አጋጣሚው የጉዞ ማኅበራት ወደ ስፍራው ይዘዋቸው መሄድ ስለሚገባቸው ሰባክያንና ዘማርያን ንቃት የተፈጠረበት ኾኖም አልፏል፡፡
አሁን አጠያያቂውና አሳሳቢው ነገር፣ በምዝበራ ተግባራቸው በሕግ መጠየቅ ላለባቸው ጥቅመኛ ግለሰቦችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ መናፍቃን መሣርያ ለኾኑ ሕገ ወጥ ቡድኖች ሽፋን በመስጠት የታወቁት ሊቀ ጳጳስ÷ የፀረ ሙስና እርምት ርምጃዎችን ለመውሰድ፣ የአስተዳደራዊ መዋቅርና የፋይናንስ አሠራር ማሻሻያዎችን እንዲሁም የስትራተጂያዊ ዕቅድ ትልሞችን ለመቀየስ በተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት መሠየማቸው ነው፡፡
የዐቢይ ኮሚቴው አያያዝ÷ የሥነ ምግባርና ፀረ – ሙስና ኮሚሽን በሚያዘጋጃቸው ዐውደ ትምህርቶችና ዐውደ ጉባኤዎች ሙሰኛ የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ሳይገባቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በመወከል በግብዝነት (hypocrisy) እየተሳተፉ ሲያደንዙንና ሲያደነዝዙን የቆዩበት ዐይነት በድንነት እንዲኾን ፈጽሞ አንሻምና የሊቀ ጳጳሱ አስተዋፅኦ የቅርብ ክትትል ሊደረግበት ይገባል እንላለን፡፡
በተለይም የሙሰኞች፣ ጎጠኞችና መናፍቃን ትስስር የኾነው ፅልመታዊ ቡድን÷ የመዋቅርና አሠራር ማሻሻያ ዕቅዶቹን በከንቱ ከሚያራግበው የ‹‹ሃይማኖት ተሐድሶ›› ሤራው ጋራ በማውገርገር ውዥንብር መንዛት በጀመረበት ኹኔታ የዐቢይ ኮሚቴው አካሄድ እንዳይሰናከልና ያሳደረው የተቋማዊ ለውጥ ተስፋ እንዳይጨም በሂደቱ የሚሳተፍ እያንዳንዱ አካልና አባል የተሟላ ግልጽነት ሊይዝበትና ሊጠነቀቅለት ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ ጥቅመኞችና መናፍቃን በፈጠሩት ትስስር የተነሣ በየጊዜው የተመደቡ ብፁዓን አባቶች ሰላም የሚያጡባቸው ተግዳሮቶች በሰፈኑበት የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት አስተዳደራቸው እየታወከባቸው የሚገኙት ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ በዐቢይ ኮሚቴው አባልነታቸው የተጣለባቸው ሓላፊነት÷ የለውጥ ሐሳቦችን ለማመንጨትና ሠርተው ለማሠራት ያላቸውን የወትሮ ዝግጁነት በሌላ ተሞክሮ የሚፈትኑበት ታላቅ ዕድል እንደሚኾንላቸው ይጠበቃል፡፡
በምሥ/ሐረርጌ ሀ/ስብከት የደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ‹ተገንጣዮች›
ሰሞኑን በምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ሐረር ከተማ ከሚገኙት ዘጠኝ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አንዱ የኾነው የደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሀብት በውስጥ ጥቅመኞችና በውጭ የዓላማ ተባባሪዎቻቸው እየተመዘበረ ይገኛል፡፡
መሰንበቻውን ምዝበራው በጠራራ ፀሐይ ተባብሶ መቀጠሉ የተገለጸ ሲኾን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከትላንት በስቲያ መልአከ ጽዮን ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ የተባለውን ጥቅመኛ የደብሩ አስተዳዳሪ ከሓላፊነት ማገዱን ተከትሎ የደብሩ አስተዳደር ራሱን ከሀገረ ስብከቱ ይኹንከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር መለየቱንና ለማንም እንደማይታዘ በዐደባባይ እየለፈፈ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ ከአለቃው ጋራ በዋና ተባባሪነት የተሰለፉት የደብሩ ሒሳብ ሹምና የስብከተ ወንጌል ሓላፊም በትላንትናው ዕለት ሠርክ ላይ በቤተ ክርስቲያኑ ለሰበሰቧቸው መሰሎቻቸው ይህንኑ ማረጋገጣቸውንና ከእንግዲህ አጥቢያውን ከማእከላዊ አስተዳደር ገንጥለው ለመቆጣጠር የያዙትን አቋም እንደማይለውጡ በይፋ ማስታወቃቸው ተመልክቷል፡፡
የደብሩን አስተዳዳሪ ከሓላፊነት የማገዱ ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በወሰዱት የጥንቃቄ ርምጃ፣ ከደብሩ ሙዳይ ምጽዋትና ሌሎች ተቀማጮች አላግባብ ተወስዶ በግለሰቦቹ እጅ የተቀመጠ በጠቅላላ ብር 360,000 ወደ ደብሩ አካውንት እንዲመለስ መደረጉ ተነግሯል፡፡ ለምዝበራ ተጋልጦ ከነበረው ከዚህ የገንዘብ መጠን ብር ስድሳ ሺሕው ለደብሩ ሞንታርቦ ለመግዛት በሚል ወጪ ተደርጎ ግዢው ሳይፈጸም ተረሳስቶ የቆየ ሲኾን ቀሪው ብር ሦስት መቶ ሺሕ ደግሞ አስተዳዳሪው በአንዲት ምእመንት ላይ በሠሩት ስሕተት የተመሠረተባቸውን ክሥ ተከትሎ በፍርድ ከመወሰድ ለማዳን በሚል እንደዋዛ በመቃብር ቤት ተደብቆ የተገኘ እንደኾነ ተዘግቧል፡፡
ይኹንና የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የደብሩን ሓላፊዎች ምዝበራ ለመከላከል ያሸገው የቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ግንቦት ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ተከፍቶና ሙዳየ ምጽዋቱ ተሰብሮ ከብር 36,000 በላይ ተወስዷል፤ በዚህም በአለቃው ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ የሚመሩ ኻያ የግብር ተባባሪዎቹ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ተገልጧል፡፡ በሕግ ባልተፈቀደላቸው ቦታ እንሠራዋለን ያሉትን የኪራይ ገቢ የሚያስገኝ ሕንጻ ግንባታ በከተማው አስተዳደር እንደተከለከለ እያወቁ በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ፈራሚነት ብር 25,000 በማውጣት ለጉልበት ሠራተኛ እንደተከፈለ በማስመሰል እርስ በርስ እንደተከፋፈሉት ተነግሯል፡፡
የቅ/ሚካኤል ደብር በሀ/ስብከቱ መንበረ ጵጵስና የምትገኘውን የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ደርቦ ያስተዳድር የነበረ ሲኾን በወርከምእመናን አስተዋፅኦ፣ ከስእለትና ሙዳይ ምጽዋት እንደሚሰበሰብ በቅርቡ የተረጋገጠው እስከ ብር 30,000 ገቢዋ ለተዘጉ የገጠር አብያተ ክርስቲያን ማስከፈቻና ለካህናት ማሠልጠኛ መደጎሚያ እንዲውል ዕቅድ ተይዞበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጉባኤም ራሱን ችሎ እንዲቋቋምና ተጠሪነቱም በቀጥታ ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲኾን ተወስኗል፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን ገቢ ኾነ ብሎ እስከ 2000 ብር በማሳነስ ሀብቷን እንደ ጥገት ላም ሲያልብ ለቆየው የ‹አባ› ጳውሎስ የዘረፋ ቡድን የሀ/ስብከቱ ውሳኔ መርዶ በመኾኑ ‹‹አጥቢያው ተገነጠለ›› በሚል ቅስቀሳ ሁከት ለማስነሣት እየተጠቀመበት እንደኾነ ተገልጧል፡፡
የ‹አባ› ጳውሎስ ጥቅመኛ ቡድን በሚፈጽመው የዘረፋ ተግባር ከደብሩ የአስተዳደር አባላት በተጨማሪ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ጋራ ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን (እነበጋሻው ደሳለኝን ጨምሮ) እና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ (በኢየሩሳሌም ጉዞዋ ወቅት ወድቃ በእግሯ ላይ በደረሰባት የመሠበር አደጋ ለአልጋ ከመዳረጓ በፊት) እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፤ ከእኒህም መካከል የእምነትም የምግባርም ደዌ የተጠናወተው ‹አባ› ጳውሎስና የምዝበራ ቡድኑ ‹‹ለአምልኮና ጸሎት›› በሚል የአዳር ፕሮግራምየሚያካሂድበት ኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት የኾነች አንዲት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ግለሰብ እንደምትገኝበት ተረጋግጧል፡፡ በስደት ከሚገኘው ‹‹ሲኖዶስ›› ጋራም የመጻጻፍ ግንኙነት እንዳለው የሚያመላክቱ ፍንጮች መታየታቸውንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
የ‹አባ› ጳውሎስ ቡድን ሊቀ ጳጳሱን የሚከሰው ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባልና የወንጌል ፀር ናቸው›› በሚል ነው፡፡ ይኸው ክሥ የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች የ‹ገለልተኛ አስተዳደር› ናፋቂዎች በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ ከሰነዘሩት ውንጀላ ጋራ ያለውን ፍጹም ተመሳስሎ በማነጻጸር ከመሰል ተቃውሞዎች ጀርባ ያለውን የተልእኮ አንድነት መረዳት ይቻላል፡፡
የሐረሩ የ‹አባ› ጳውሎስ የዘረፋና ኑፋቄ ቡድን ክሥ በሊቀ ጳጳሱ አቡነ አብርሃም ላይ የተጠናከረው፣ ብፁዕነታቸው ቅ/ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም በስምንት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለመላው የሀ/ስብከታቸው ሠራተኞች፣ ለአድባራት ሓላፊዎችና አገልጋዮች ለማሳወቅና ለማስገንዘብ የዐውደ ትምህርት መርሐ ግብር በመዘርጋት ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘርጋታቸውን ተከትሎ እንደኾነ የዜናው ምንጮች ያብራራሉ፡፡ በዐውደ ትምህርቱ ሠራተኞችና አገልጋዮች ስለውሳኔው በጨበጡት ግንዛቤ ከመነቃቃታቸውም በላይ ለውሳኔው ተፈጻሚነት ያመች ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለየአድባራቱ እንዲሰራጭ በከፍተኛ አጽንዖት እስከ ማሳሰብ ደርሰውም ነበር፡፡
በወቅቱ ‹‹አሞኛል›› በሚል ሰበብ በዐውደ ትምህርቱ ያልተገኘ ብቸኛ የደብር አለቃ ቢኖር ‹አባ›  ጳውሎስ ብቻ ነበር፡፡ ‹አባ› ጳውሎስ አዘውትሮ የሚገናኛቸውንና ለተወገዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያለውን ቅርበት ለሚያውቁ ወገኖች የቅ/ሲኖዶሱን አቋም ለመደገፍ የታየበት ዳተኝነት እንግዳ አይደለም፡፡ ሊቀ ጳጳሱን ‹‹የወንጌል ፀር›› እያለ የሚዘልፈው ‹አባ› ጳውሎስ በዐውደ ምሕረት በተቀመጠበት ለመስማት የሚታገሠው ‹‹ወንጌል›› ቢኖር÷ ‹‹ስለሌሎች ስንሰብክ ኢየሱስን ይጋርድብናል››፤ ‹‹ወደ ቤተ ክርስቲያን ባትመጡም ቤታችኹ ኾናችኁ ማምለክ ትችላላችኹ›› የሚሉትን የእነ ያሬድ ዮሐንስ እና ኢዮብ ይመር ኑፋቄና ክሕደት ነው፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት በእኒህ አካላት አማካሪነት እየተገፋ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ላይ ተጽዕኖውን ያጠናከረው የ‹አባ› ጳውሎስ የዘረፋና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ቡድን ዋና ሥራ አስኪያጁን በማስጨነቅ ላይ ይገኛል፤ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ላይም ዐመፅ ለማጧጧፍ በመዘጋጀት ላይ እንደኾነ የስፍራው ምንጮች እየገለጹ ናቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ፣ ለርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ የፀረ ሙስና እርምት ርምጃዎችንና የተቋማዊ ማሻሻያ ሐሳቦችን አጥንቶ እንዲያቀርብ ለተሠየመው ዐቢይ ኮሚቴና ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት ለሚሠራው ቋሚ ሲኖዶስ አባልነት በመመረጣቸው እስከ አሁን በዚያው በአዲስ አበባ እንዳሉ ምንጮቹ አመልክተዋል፡፡
እንደሚሰማው ከኾነ የሀ/ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ በዛቻና ማስፈራሪያ እያስጨነቀ የሚገኘው የ‹አባ› ጳውሎስ የዘረፋና የኑፋቄ ቡድን ሊቀ ጳጳሱ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው በሚመለሱበት ወቅት ለማጧጧፍ ያቀደውን ዐመፅ እየተዘጋጀበት ያለው፣ ከቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በፊት ባሰባሰበው ‹‹የፊርማ አቤቱታ›› ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን ከሀ/ስብከታቸው ለማስነሣት ለመንበረ ፓትርያሪኩ ያቀረበው ያልተገባ ጥያቄ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ውድቅ በተደረገበት ኹኔታ ነው፡፡ በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የተመከረበትና ወቅት ጠብቆ በተንኰል የቀረበው የክፋት ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ግብዙ ‹አባ› ጳውሎስ በዐደባባይ እንደተሳደበው፣ ‹‹ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሙሉ ሌቦች ናቸው፡፡››
በደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ‹‹ከእንግዲህ ማንም አያዝዘንም፤ ምንም አያግደንም›› በሚል ከሀ/ስብከቱና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር መውጣቱን በዐደባባይ ያወጀው የ‹አባ› ጳውሎስ የዘረፋና የኑፋቄ ቡድን በሀ/ስብከቱ የፈጠረውን ሁከትና ለመፈጸም የሚሰናዳበትን የዐመፅ ድርጊት ለመግታት ሀ/ስብከቱ የክልሉን የፍትሕና ጸጥታ ቢሮ እገዛ መጠየቁ ተሰምቷል፤ ክልላዊ ቢሮው ጸጥታን ለማስከበር የበኩሉን ርምጃ እንደሚወስድ መግለጹ ቢመለከትም ዜናው እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በተጨባጭ የታየ ነገር እንደሌለ የዜናው ምንጮች አስረድተዋል፡፡
የወቅቱ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከመመደባቸው በፊት ሀ/ስብከቱን በመሩት ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ዐመፅ በመቀስቀስ የሚታወቀው ‹አባ› ጳውሎስ አጥጋቢ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳይኖረው ነው ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በደብር አስተዳዳሪነት የተመደበው፡፡ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆች፣ እነርሱን በመሣርያነት/ተላላኪነት ለሚያገለግሉ አንዳንድ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን እንዲሁም ለጥቅመኛ ግለሰቦች ምሽግ መኾንን በመረጠው ‹አባ› ጳውሎስ የዐመፅ ተግባራት ጠንሳሽነት ተማርረው የተነሡ ብፁዓን አባቶችን የሚያስታውሱ የሐረር ከተማ  ምእመናን÷ ‹‹የደጉ ብፁዕ አባት አቡነ ሳሙኤል እንባ አለብን፤ ከተማችን በተኣምረኛው ብፁዕ አባት ላይ ምራቅ የተፉ፣ ብዙኀኑን ደጋግ  ምእመናን የማይወክሉ የ‹አባ› ጳውሎስ ቀደምት የግብር አምሳያዎች (predecessors) ያሉባት ነች፤››በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ወቅቱ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በትክክል እንዳስቀመጡት÷ በሃይማኖቷ እንከን የማይገኝባት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር - ቤተ ክህነት – የተቋማዊ ለውጥና ማሻሻያ ርምጃ፡-
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ዋነኛው ዓላማ ቤተ ክርስቲያናቱን ባለችበት ኦርቶዶክሳዊ ማንነቷን መበረዝ አልያም ተቋማዊ አንድነቷን ከፍሎ መረከብ ነውና እንደ ‹አባ› ጳውሎስ ያለብቃታቸው ተሰግስገው የአሐቲነቷና ማንነቷ ፀር የኾኑ የሙስናና ኑፋቄ መሸሸጊያዎችን በስፋትና በጥልቀት በማጥራት የሚጀምርበት፣
  • ሕጎቻችንን፣ ደንቦቻችንንና መመሪያዎቻችንን አጣጥሞ በማዘጋጀት የሚለጥቅበት
  • ተቋማዊ ርእያችንና ስትራተጂያዊ ጉዳዮቻችንን ግልጽ በማድረግ የአገልግሎት ዝግጁነታችንና የአገልግሎት አቅጣጫችንን የምንተልምበትን ስልታዊ ዕቅድ በመቀየስ የሚጠናከርበት
  • በሌለ ሥራ ቅጥር ብቻ እየተፈጸመ ደመወዝተኝነትና ጥቅመኝነት የሰፈነበት የተንዛዛ አስተዳደራዊ መዋቅራችን ልኩና መልኩ ታውቆ የተቋማዊ ለውጥና ማሻሻያ ርምጃዎችን ለማስፈጸምና ለመደገፍ ያለው ዝግጁነት የሚረጋገጥበት፣
  • መንፈሳዊነትና ቀናዒነት የዘለቃቸው ብቁ ሞያተኞችና አገልጋዮች ሐዋርያዊ ተግባራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማከናወን የሚነቃቁበት ነው፡፡
ይህ እውን ሲኾን የሐረር ምእመናን ግፉን የሚቆጥሩለት የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እንባ ታብሶ ቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ አንድነቷንና የውስጥ ሰላሟን እንደምታጸና ርግጠኛ መኾን ይቻላል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment