Friday, April 19, 2013

ከሸፈ እንዴ?! ‹‹ዜና ቤተ ክርስቲያን›› ጋዜጣ በመጽሔት ቅጽ መታተም ጀመረ!


His Holiness Abune Matyas Zena BeteK Magazine Cover
  • መጽሔቱ የቤተ ክርስቲያንን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚያጠናክር ነው፡፡
  • በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በየሩብ ዓመቱ በላቀ የኅትመት ጥራት ይዘጋጃል፡፡
  • አዘጋጂው በአዲስ መልክ የተዋቀረው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው፡፡
  • የዝግጅቱ ውጥን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በ፳፻፭ ዓ.ም የበጀት ዓመት ለማካሄድ ካቀደው ተቋማዊ የአደረጃጀት ለውጥና የወቅታዊ እንቅስቃሴዎችን መረጃ በተሻለ አሠራር ከመቀመር አኳያ በመምሪያው የሕዝብ ግንኙነት ቁልፍ ተግባራት ውስጥ ቀደም ብሎ ዓላማና ግብ ተወስኖለት የተካተተ እንጂ ከፓትርያሪኩ ‹‹የዜና መዋዕል ዝግጅት›› ጋራ ፈጽሞ የተያያዘ አይደለም፡፡
  • መጽሔቱ ቤተ ክርስቲያናችን በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች የምታከናውናቸው ተግባራትና ውጤቶቻቸው በአገር ውስጥና በውጭ ባለድርሻ አካላት እንዲታወቁ እንዲሁም ‹‹ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት ስትራቴጂ›› ላይ አተኩሮ ይዘጋጃል፡፡
  • በመጽሔቱ ዝግጅት ሂደት የሚገኘው ልምድ ወደፊት ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ መጽሐፍ እንዲኖራት በመምሪያው ለታሰበው ዕቅድ ግብዓት እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡
  • ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የመጽሔቱ ኅትመት ወቅቱን ጠብቆ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ እናስ፣ የከሸፈው÷  የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጁ ብሎግ ወይስ የመጽሔቱ አዘጋጆች ዕቅድ?!

 His Holiness on Interview
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ከዜና ቤተ ክርስቲያን መጽሔት ጋራ ካደረጉት ቆይታ

  • ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን ለብቻዋ እንደ ደሴት ኾና መቅረት የለባትም፡፡ የኔ ምኞትና ፍላጎት ቤተ ክርስቲያኒቱ በሠለጠነና በተማረ የሰው ኀይል እንድትንቀሳቀስ ነው፡፡ ስለኾነም ሠራተኛው ሁሉ ራሱን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል ለሥራ ታጥቆ ይነሣል የሚል እምነት አለኝ፡፡››
  • ‹‹እንደ እኔ እምነት ቤተ ክርስቲያን ትልቁን በጀት መመደብ ያለባት ለስብከተ ወንጌል ሥራ ነው – ያሉንን ለማጠናከር፤ ያላመኑትን ለማስተማር፡፡ ወጣቱን ትውልድ በሚገባ ለመያዝ የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ወደ ተግባር ለመለወጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ትልቅ ሓላፊነት አለበት፡፡ ስብከተ ወንጌል መምሪያው በሠለጠነ የሰው ኀይልና በበጀት መጠናከር አለበት፡፡››
  • ‹‹ቤተ ክርስቲያናዋ ሳታውቀው የሚንቀሳቀስ አካል መኖር የለበትም፡፡ በርግጥ እዚህ ላይ የእኛም ድክመት አለበት፡፡ ለወደፊቱ ቤተ ክርስቲያናችን ቅርሶቿንና መብቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዐት መዘርጋት ይኖርባታል፡፡››
  • ‹‹ዘመናዊ ትምህርት ብቻውን ለኅብረተሰቡ አይጠቅምም፤ መንፈሳዊነት ይጎድለዋልና፡፡ መንፈሳዊነት ግብረ ገብነት የሚገኘው ደግሞ በገዳማት፣ በአብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡ ገዳሞቻችን ደግሞ የምስጢራት፣ የሥነ ምግባር፣ የዕውቀት ምንጮች ናቸው፡፡ በመኾኑም ለወደፊቱ ገዳሞቻችን የምስጢርና የምርምር ተቋማት ኾነው መቀጠል አለባቸው፤ ምክንያቱም ጸጥታና ሰላም ያለው በእነርሱ ዘንድ ስለኾነ ለምርምር የተመቸ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለን መጠን ገዳሞቻችን ወደዚህ መለወጥ አለብን፡፡››
  • ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን የእግዚአብሔር ቤት ኾና የተመሠረተች ስለኾነች በዘረኝነት መበከል የለባትም፡፡ ማንኛውንም ሠራተኛ ልንወደውም ልንጠላውም የሚገባን በግብሩ እንጂ በዘሩ መኾን የለበትም፡፡ ማንም ሰው በራሱ ፈቃድ ከእገሌ ዘር ልወለድ ብሎ የተወለደ የለም፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በመኾኑ ከሰው አቅም በላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ሊመሰገንም፣ ሊሾምም፣ ሊሻርም፣ ሊወቀስም የሚገባው በጠባዩ፣ በግብረ ገብነቱ፣ በትምህርቱ ብቻ እየተመዘነ መኾን አለበት፡፡ ጥሩ ኾኖ ከተገኘ ይሾማል፤ ይሸለማል፤ ካልኾነም ይወቀሳል፤ ይመከራል፤ ይቀጣል ማለት ነው፡፡››
  • ‹‹በኢየሩሳሌም ለ50 እና 60 ዓመታት በዐረቦችና በአክራሪ ይሁዲዎች እጅ በቁልፍ ተይዘው የነበሩ ሕንፃዎቻችንን አስመልሰናል፡፡ አሁንም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ የሚመለሱ አሉ፡፡ የሕንፃዎቻችን ይዞታ ሕጋዊነት እንዲኖረው በእስራኤል ሕግ በርስት ክፍል አስመዝግበናል፡፡››
  • ‹‹እኛ እንደፈለግነው ጉዳዩ በዕርቅ አልተቋጨም፡፡ በኛ በኩል የሰላም ጉዳይ በሩ ስላልተዘጋ ዛሬም ነገም ለሰላም የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል፡፡››
  • ‹‹በእውነቱ ፓትርያሪክ እኾናለኁ የሚል መንፈስ በውስጤ ስላልነበረ ውጤቱ ሲገለጽ፣ እንዴት ነው ይህ? የእግዚአብሔር ሥራ ምንድን ነው? ከሚል ደነገጥኹ፡፡ በዛ ቅጽበት የተሰማኝ÷ እግዚአብሔር ይህንን ታላቅ ሓላፊነት እንዴት እችለዋለኹ? በል አንተ ታውቃለኽ የሚል ነበር፡፡››
  • ‹‹ሳሆ የሚባል ሙስሊሞች የሚነጋገሩበት ቋንቋ አለ፡፡ በልጅነቴ በጣም ነበር የምችለው፤ በኋላ ግን እየቆየ ሳይጠፋኝ አይቀርም፡፡. . .በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቼ የተማርኹት እንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች በኢየሩሳሌም ቆይታዬ በልምድ ያወቅኋቸው ናቸው፡፡ በተለይ የዕብራይስጥና የዐረቢኛ ቋንቋዎች በኢየሩሳሌም የሀገሩ ቋንቋዎች ስለኾኑ ለማወቅ ቀላል ነው፡፡››
ቀጣይ ዘገባዎችን ይከታተሉ፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment