Wednesday, April 24, 2013

ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ ከግብጽ ቅ/ሲኖዶስ ጋራ ይወያያል


    His Holiness on Interview
  • ፓትርያሪኩ የቅድስት ሀገር የታሪክና ቅድስና ይዞታችንን ለማስከበር ሕዝባዊ ዲፕሎማሲው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል
  • ፓትርያሪኩ የ፳፻፭ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤ የኢየሩሳሌም ተሳላሚ ምእመናንን አሰናብተዋል፤ እጅጋየሁ በየነ ሕገ ወጥ ጥቅም የምትሰበስብበት ‹አስጎብኚና የጉዞ ወኪል› በስንብት መርሐ ግብሩ አልተካተተም
  • ‹‹የዴር ሡልጣን ችግር ከመካከለኛው ምሥራቅ ጠቅላላ ገጽታዎች ተለይቶ መታየት የለበትም፡፡›› /በግብጽ መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘው የእስላም ወንድማማቾች አቋም/
  • ‹‹ጉዳዩ ብሔራዊ ስለኾነ ከዐረብ ወንድሞቻችንና ከእስላሞች ጋራ ካልኾነ በቀር ወደ ኢየሩሳሌም አንገባም፡፡ ይህን በተመለከተ ሁላችንም በአንድነት ቆመናል፡፡›› /ፖፕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ዴር ሡልጣንን በተመለከተ በእስራኤል ላይ የቱሪዝም ጫና ለመፍጠር የሞከሩበት ጋዜጣዊ መግለጫ/
  • ‹‹ኢትዮጵያውያን ምእመናን በታሪክ ይዞታችንና በወገኖቻችን መካከል በብዛት መገኘት ለቅድስና ይዞታችንና ለወገኖቻችን ክብር በቀላሉ የማይገመት ዋስትና ያለው ነው፡፡ ጉዟችን ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ እያገኘ በበለጠ ከቀጠለ በታሪክ ይዞታችን ላይ ያለው ችግር መፍትሔ አግኝቶ የመንፈስ ዕረፍትና ርካታ እንደሚገኝ ተስፋ አለን፡፡›› /በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ለተሳላሚዎች ከተናገሩት/

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ጥንታዊ የኾነውን የታሪክና ቅድስና ይዞታችንን ለማስከበር በአሁኑ ወቅት ያለን አማራጭ መፍትሔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከግብጽ – ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋራ ቀጥተኛ ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መሞከር መኾኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ይህን ያስታወቁት፣ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ አማካይነት በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች እየተዘጋጀ በየሦስት ወሩ ከሚታተመው ‹‹ዜና ቤተ ክርስቲያን›› መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡
በዴር ሡልጣን ገዳም ይዞታ ጉዳይ እ.አ.አ በ1770 ከግብጾች ጋራ የተጀመረው 243 ዓመታትን ማስቆጠሩን ያስታወሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ፣ ከ1600 ዓመታት በላይ የገዙን ግብጾች አጋጣሚውን በሚገባ እንደተጠቀሙበት በቃለ ምልልሱ ላይ ገልጸዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ስለዚህ ሲያስረዱ፣ ‹‹በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢየሩሳሌም በሡልጣኖች እጅ በነበረችበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን የይገባናል ጥያቄ ሲያነሡ እንኳን ‹አገሪቱን የምንመራት እኛ ነን› በማለት ንብረቶቻችንን ወረሱ፤››ብለዋል፡፡
አሁን በእጃችን ያለውን ዴር ሡልጣን የተረከብነው እ.አ.አ በ1976 ዓ.ም እንደነበር ያወሱት ፓትርያሪኩ፣ በወቅቱም ቁልፉን የተረከቡት መጋቢ ገብረ ማርያም በኋላ ብፁዕ አቡነ አብሳዲ  እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡ ከፕትርክናው ጋራ ገዳማቱን በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩት ቅዱስነታቸው፣ የገዳሙን ወቅታዊ ኹኔታ አስመልክቶ ለመጽሔቱ እንዳስረዱት÷ ጥንታዊው የዴር ሡልጣን ገዳም ከማርጀቱ የተነሣ አደጋ ላይ እንዳለ በመጥቀስ የእስራኤል መንግሥት ለመጠገን እንዲፈቅድላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ የተሰጣቸው ምላሽ ግን፣ ‹‹ከግብጾች ጋራ ካልተስማማችኹ አይኾንም፤›› የሚል በመኾኑ እስከ አሁን ምንም ለማድረግ አለመቻሉን የወቅቱ ፓትርያሪክና የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ያለው አማራጭ መፍትሔ ሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያን በቅ/ሲኖዶስ ደረጃ ተገናኝተው የሚያደርጉት ቀጥተኛ ውይይት እንደኾነ ፓትርያሪኩ በቃለ ምልልሳቸው ላይ አመልክተዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለው አማራጭ መፍትሔ የኛ ሲኖዶስ ከግብጽ ሲኖዶስ ጋራ ተወያይቶ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ነው፤›› ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ጉዳዩ በእስራኤል መንግሥት መያዙንና በመጨረሻም ውጤታማ እንኾናለን የሚል ተስፋ እንዳላቸው ከ‹‹ዜና ቤተ ክርስቲያን›› መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል፡፡
በ1971 ዓ.ም ለኤጲስ ቆጶስነት እንደመረጡ በተሾሙባት ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን ለሦስት ዓመት በበላይነት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በ1974 ዓ.ም በስደት ወደ አሜሪካ ተሻግረዋል፡፡ በዚያ ለ10 ዓመታት በስደት፣ ለ15 ዓመታት በሊቀ ጳጳስነት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም ወደቀድሞው ሀ/ስብከታቸው ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላ÷ አብያተ ክርስቲያን እንዲታነጹና እንዲጠገኑ፣ ቅርሶችና ንብረቶች እንዲመዘገቡና በአግባቡ እንዲያዙ፣ በዐረቦች ይዞታ የነበሩትን ቦታዎችና ቤቶች ይልቁንም ለ40 ዓመታት ያህል የጦር ሜዳ ኾኖ የኖረውን ቤተ ክርስቲያን አስመልሰው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ማድረጋቸው በፓትርያሪክነት በተሾሙበት ዕለት የወጣው ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ቅዱስነታቸው፣ አሁን ባለው ኹኔታ በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያን በቅ/ሲኖዶስ ደረጃ እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን ውይይት በቀዳሚ አማራጭነት ያስቀምጡ እንጂ፣ የታሪክና የቅድስና ይዞታችንን ለማስከበር ሕዝባዊ ዲፕሎማሲው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡ ይኸው ሕዝባዊ ዲፕሎማሲ በወቅቱ እየተፈጸመ ያለው በአስጎብኚ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች እንዲሁም ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በሚያጓጉዟቸው ተሳላሚ ምእመናን አማካይነት ነው፡፡Ethiopian Piligrims in Jerusalem Holy Friday
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የዘንድሮውን በዓለ ትንሣኤ ለማክበር በሦስት አስጎብኚ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች አማካይነት ወደ ኢየሩሳሌም ለሚጓዙ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ተሳላሚ ምእመናን በሰጡት ቃለ ምዕዳን፣ ‹‹ዝም ብሎ ተሳልሞ መምጣት ብቻ ሳይኾን በርካታ አባቶች ዋጋ ለከፈሉበት ርስታችን ሕዝቡን በሰፊው በማስተባበርና በማንቀሳቀስ የጎላ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡›› የተሳላሚ ምእመናኑ ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንዳለ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተመለከተ ሲኾን፣ ይህም በአስከፊ ኹኔታ ውስጥ ይዞታችንን ለሚጠብቁት ገዳማውያን (ማኅበረ መነኰሳት) ታላቅ መንፈሳዊ ማበረታቻ፣ በቂ የወገን ድጋፍ እንደሌላቸው አድርገው ለሚቆጥሩ ግብጻውያን ደግሞ ጠንካራ መልእክት እንደሚያስተላልፍ አጽንዖት ተሰጥቶታል፡፡
ይዞታችንን ከማስከበሩ ጥረት ጋራ በተያያዘ በቀጣይ በውጭና በሀገር ውስጥ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድና ሌሎች የሕዝብ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ይህም ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስ ወደፊት መክሮ በሚወስነው መሠረት ከመንግሥት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአስጎብኚ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች እንዲሁም ከምእመናን ተውጣጥቶ በማእከል በሚቋቋም አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ሊመራ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ትላንት፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2005 ዓ.ም ቀትር ላይ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪክ በተካሄደው ተሳላሚዎቹን የማሰናበት መርሐ ግብር÷በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም፣ በዮድ አቢሲኒያ እና በጎልጎታ አስጎብኚና የጉዞ ወኪልአማካይነት የሚጓዙ ተሳላሚ ምእመናንና የድርጅቶቹ ሓላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የሚመራው ‹‹ቀራንዮ በኢየሩሳሌም አስጎብኚ ድርጅት›› በመርሐ ግብሩ ላይ አልተገኘም፤ እንዲገኝም አለመጋበዙ ተዘግቧል፡፡
ወይዘሮዋ በቀድሞው ዘመነ ፕትርክና በራሳቸውና በልጃቸው ስም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅትአላግባብ ከወሰዷቸው ሦስት ቤቶች አንዱን ቢሮ በማድረግ በከፈቱት ‹‹አስጎብኚ ድርጅትና የጉዞ ወኪል››፣ ተሳላሚዎችን ወደ ኢየሩሳሌምና ግሪክ አመላልሳለኹ በሚል ሕገ ወጥ ጥቅም እንደሚሰበሰቡ ይነገርባቸዋል፡፡ ለሐራዊ ምንጮች በደረሰው ጥቆማ፣ የወ/ሮ እጅጋየሁ ድርጅት በተሳላሚነት ሽፋን ወደ ቅድስት ሀገር ከሚያጓጉዟቸው ምእመናን መካከል ወደ አገራቸው ተመልሰው የማይመጡት ጥቂት አይደሉም፡፡
ሌሎች ድርጅቶች ተሳላሚዎችን የሚመዘግቧቸውን መስፈርቶች በማጥበቅ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከተሳላሚነት ውጭ ፍላጎት ያላቸውን ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ለ‹አገልግሎቱም› ከብር መቶ ሺሕ እስከ መቶ ኀምሳ ሺሕ ክፍያ እንደሚቀበሉ ተገልጧል፡፡ ምንጮቹ እንደሚሉት በዚህ ጥንቃቄ በጎደለው የወይዘሮዋ አሠራር በትንሹ 13 ያህል ግለሰቦች በተሳላሚነት ተመዝግበው ከሄዱ በኋላ ሳይመለሱ መቅረታቸው ተነግሯል፡፡ ወይዘሮዋ በአስጎብኚ ድርጅት ስም ከሚነግዱበት ተግባራቸው በቶሎ እንዲታረሙ ካልተደረገ ሕገ ወጥ ተግባራቸው በዓመታዊው የተሳላሚ ምእመናን ጉዞና በተለይም ለሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ሥራ ፋይዳ ይኖረዋል የተባለውን ተሳላሚ ምእመናኑን በቁጥር የማብዛት ጥረት ላይ ዕንቅፋት ሊኾን እንደሚችል ምንጮቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ለተገኘው የቅድስት ሀገር ተሳላሚዎች መበርከት÷ እንደ ብፁዕ አቡነ አብሳዲ ረኀቡን፣ ጥሙን፣ የሽፍቶችንና የአራዊትን አደጋ ታግሠው በእግራቸው በርሓውን እያቆራረጡ ከሰውነት ተራ ወጥተው እስከ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ገዳማችን በባዕዳን ተውጦ እንዳይቀር ያደረጉት ኢትዮጵያውያን መነኰሳትና ምእመናን ቅድሚያውን ይወስዳሉ፡፡ ከእነርሱም በኋላ ደግሞ ግማሽ ምእት ዓመት ያስቆጠረውና በእነወ/ሮ እጅጋየሁ ጥቅመኝነት ውስጣዊ ፈተና የደረሰበት የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት የተጫወተው ትውልዳዊ ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡
በምድረ እስራኤል በሚኖሩ ምእመናን መተባበር የተመሠረተው ድርጅቱ፣ ኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን ተሳልመው በዓለ ትንሣኤውን እንዲያከብሩ ከማስቻል ባሻገር፣  ‹‹ኢየሩሳሌምን በልባችኹ አስቡ›› በሚለው ቃለ እግዚአብሔር በሚመራው የሥነ ጽሑፍ ክፍሉ አማካይነት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በሚያሳትማቸው÷ ዓመታዊ መጽሔት፣ ታሪካዊ መጽሐፍ፣ የመዝሙርና የቅድስት ሀገር ካሴቶች እንዲሁም በየወሩ በራሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚያዘጋጀው መንፈሳዊ መርሐ ግብር አባላትና ደጋፊዎቹ፣ ስለ ታሪክ ይዞታዎቻችን ሰፊ ግንዛቤ ጨብጠውና ትምህርተ ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲጓዙ ያደረገው ጥረት ይጠቀሳል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክና የቅድስና ይዞታ የኾነው ዴር ሡልጣን /ደብረ ሥልጣን/ ገዳማችን፣ አባታችን አብርሃም ልጁን ይሥሓቅን ሊሠዋበት በነበረበት ስፍራ የሚገኝ ሲሆን፣ ጌታችንም መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ ለሦስተኛ ጊዜ የወደቀበት ዘጠነኛው የፍኖተ መስቀልምዕራፍ ነው፡፡ ግብጻውያን በዚህ ስፍራ የተሠሩትን የአርባዕቱ እንስሳና የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደሶቻችንን መልሰው ለመያዝ በየአጋጣሚው በተለያየ መልኩ አቤቱታና ሮሮ ከማሰማት አልፈው የኀይል ጥቃትም ሰንዝረው እንደነበር የድርጅቱ ኅትመቶች ያስረዳሉ፡፡
በ1959 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤ በዴር ሡልጣን ሲከበር ግብጻውያን ኮፕቶች የድንጋይ በረዶ በማዝነም በዓሉ በጸጥታ እንዳይከበር ከማድረጋቸውም በላይ ጥቃቱን ለመቋቋም በተደረገ ጥረት የብዙ ተሳላሚዎች ደም ፈሶ እንደነበር በኅትመቶቹ ተዘግቧል፡፡ ኢየሩሳሌም በእስራኤል ቁጥጥርና አስተዳደር ሥር በኾነች በሁለተኛው ዓመት የእስራኤል ባለሥልጣናት በተገኙበት በዓለ ትንሣኤው ሲከበር ግብጻውያን ድንጋይ በመወርወር ጸጥታውን ለማደፍረስ ሞክረው ነበር፡፡
በዚህ መነሻ በድርጅቱ የተጓዙ ተሳላሚ ምእመናን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጠየቁ፡፡ ጥያቄያቸው ቀደም ብሎ ባለመቅረቡ ሰላማዊ ሰልፉ ባይፈቀድላቸውም እስከ ኻያ ሰው በመኾን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና ለሃይማኖት ጉዳዮች ሓላፊው አቤቱታ ቀርቧል፡፡ በቀረበው ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩሩበት የተናገሩት ባለሥልጣናቱ፣ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገውን ጉዞ በበለጠ እንዲያጠናክሩ እንደመከሯቸው ኅትመቶቹ አስፍረዋል፡፡
አያይዘውም፣ ‹‹ባለሥልጣናቱ ቃላቸውን ጠብቀው በ1962 ዓ.ም ዶክተር ሜሮን የተባሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪያቸውን ወደ አዲስ አበባ ልከው ኹኔታውን አስጠኑ፡፡ ከጥናቱ በኋላ የአርባዕቱ እንስሳና የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደሶችን ሚያዝያ 18 ቀን 1962 ዓ.ም ከሠላሳ አምስት ዓመት በኋላ፣ በኾነው መንገድ ገዳሙ ተረክቦ እነኾ አሁን መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥበታል፡፡ በዚያ ጊዜ ዝም ብንል እንደተዳፈነ ቆይቶ ነበር፤›› በማለት ነው በድርጅቱና በማኅበረ መነኰሳቱ የተቀናጀ ጥረት የተገኘውን ከፍተኛ ውጤት የሚያብራሩት፡፡
በዴር ሡልጣን ውኃና መብራት እንዳይገባ ተከልክሎ በወገኖቻችን ላይ ይታይ የነበረው የኑሮ ሥቃይ ‹‹የትላንት ትዝታ ነው›› የሚለው የድርጅቱ የቆየ ሪፖርት፣ በ1958 – 59 ዓ.ም ውኃና መብራት ገብቶ የወገኖቻችንን የኑሮ ሥቃይ ለመቀነስ የተቻለው ‹‹ሮሮ የተመላበት አቤቱታ ባለመቋረጥ በመቅረቡ፤›› እንደኾነ አውስቷል፡፡ በ1978 ዓ.ም ግብጽና እስራኤል ወዳጅነት መሥርተው ስለታባ (በሲናይ ጫፍ የምትገኝ የመዝናኛ ስፍራ) በሚነጋገሩበት ወቅት፣ ኮፕቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው የዴር ሡልጣን ጉዳይ በንግግሩ እንዲካተት በብርቱ ተጣጥረው ነበር፡፡ ከኅትመቶቹ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በወቅቱ ከአራት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ የተቃጣው የግብጻውያን ሙከራ እንዲከሸፍ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
church-with-monks_newይኹንና፣ በፍኖተ መስቀል ዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ በሚገኘው ዴር ሡልጣን መነኰሳት የሚኖሩበት አካባቢ ሰው ቀርቶ ሌላ ፍጡር እንዲኖርባቸው የሚመኝ አይኖርም፡፡ ውሾችና እንስሳት የሚኖሩበት በተለወጠበት ዘመን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በእኒህ ጉድጓዶች መኖራቸው ያየ ሁሉ ምን ይላል? በበጋ ሙቀቱ፣ በክረምት ብርዱ እያሠቃያቸው በእነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ እስከ መቼ ይቀመጣሉ? ሰው ኾነው እንደ ሰው የማይኖሩት እስከ መቼ ነው? ጉዳዩን በከፍተኛ ደረጃ ይዞ ዕለት በዕለት ተከታትሎ የሚያስፈጽመው ማን ይኾን?‹‹ጥረት አልተደረገም ማለት ሳይሆን የተደረገው ብቃት የለውም እንላለን፡፡››
ይኹንና፣ በእኛ በኩል ግብጻውያንን በተቃዋሚነት ለመቋቋም ከመታገል በቀር መብታችንን ለማስከበር ያደረግናውና የምናደርገው እንቅስቃሴ ‹‹የደከመ ነው ብንል ሐቅ ነውና ከድፍረት አይቆጠርም፤›› ይላል ድርጅቱ ‹‹ዜና ኢየሩሳሌም›› በሚል ርእስ በየካቲት ወር 1982 ዓ.ም ያወጣው መጽሔት፡፡ ግብጻውያን በደል የተፈጸመባቸው እያስመሰሉ በብዙኀን መገናኛ ባለማቋረጥ የሚያሰሙት አቤቱታ፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ጽኑ ትኩረት የሚያመለክት ነውና የሚደነቅ ነው›› ያለው መጽሔቱ፣ እኛ ድምፃችንን በግልጽ ያሰማንበት ጊዜ ከእነርሱ ጋራ ሲመዛዘን ለወሬ እንደማይበቃ ተችቷል፡፡
በግብጽና እስራኤል መንግሥታት የልዩነት አጀንዳዎች ውስጥ ከሰፈሩት አነጋጋሪ ዝርዝሮች የዴር ሡልጣን ጉዳይ አንዱ መኾኑን የተለያዩ የብዙኀን መገናኛ ምንጮችን በመጥቀስ የሚያትቱት የድርጅቱ መዛግብት፣ ዴር ሡልጣን በግብጽ – እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ መድረክከሚነሡት ዋነኛ ጉዳዮች ያነሰ ዋጋ እንደሌለው ያረጋግጣሉ፡፡ ግብጾች ዴር ሡልጣንን የመንግሥታቸው የውጭ ጉዳይ አጀንዳ ከማድረግ አልፈው (በተለይ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑ ዶ/ር ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት ወቅት) በዓለም አቀፍ መድረክ ስለ ጉዳዩ የክትትልና አፈጻጸም ድክመት የታየባቸውን ባለሥልጣኖቻቸውን ፍርድ ቤት ገትረው እስከ ማስቀጣት ደርሰዋል፡፡
በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የግብጽ ጳጳስ (አቡነ ሞንሲኞር ባስልዮስ) በዴር ሡልጣን የአርባዕቱ እንስሳና የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደሶች ካልተመለሱ የግብጽ ምእመናን ኢየሩሳሌምን እንዳይሳለሙ ከልክለዋል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ እ.አ.አ በ1988 በኢየሩሳሌም ይታተም የነበረውን ኤን – ናበር ጋዜጣ ጠቅሶ ‹‹ዜና ኢየሩሳሌም›› እንደጻፈው፣ ፖፕ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ÷ እስራኤል የአረብ ግዛቶችን ከያዘች በኋላ የክርስቲያን ቅዱሳን ስፍራዎችን መብት ጥሳለች፤ ከግብጽ የቆጵጥ ቤተ ክርስቲያን ንብረት የኾነውን ዴር ሡልጣንን በኤፕሪል፣ 1970 ነጥቃ ለኢትዮጵያ ማስረከቧን ተናግረዋል፡፡
‹‹ጉዳዩ ፖሊቲካዊ ነው›› በሚል ገዳሙን ለእኛ ለመመለስ አለመፍቀድዋን ፖፕ አቡነ ሲኖዳ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ፖፑ፣ ግብጻውያን ቆጵጦች በተያዙት የዐረብ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙትን ቅዱሳን ስፍራዎች እንዳይጎበኙ የቆጵጥ ቤተ ክርስቲያን የምትከላከል መኾኑን አረጋግጠዋል – ‹‹ጉዳዩ ብሔራዊ ስለኾነ ከዐረብ ወንድሞቻችንና ከእስላሞች ጋራ ካልኾነ በቀር ወደ ኢየሩሳሌም አንገባም፡፡ ይህን በተመለከተ ሁላችንም በአንድነት ቆመናል፡፡›
በብዙ ሺሕ ቁጥር ወደ ኢየሩሳሌም ይተሙ በነበሩት ግብጻውያን ተሳላሚዎች ላይ የተደረገው የጉዞ መከልከል፣ የንግድና ቱሪዝም መቀዛቀዝን አስመልክቶ እስራኤል ለምታነሣው ችግር የቆጵጥ – ኢትዮጵያ ውዝግብን በመሰናክልነት እየጠቀሱ ለይገባኛል ጥያቄው ጫና ለመፍጠር መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም በኢየሩሳሌም የቆጵጥ ማኅበረሰብ መሪ የነበሩት ዶ/ር ባስልዮስ ሲያረጋግጡ÷ ‹‹የጉዞ መከልከሉ ቅጣት ሳይሆን የእስራኤል ባለሥልጣኖች ገዳሙን እንዲመልሱላቸው ለማበረታታት የሚደረግ ተቃውሞ ነው፡፡››The stone huts of Deir al Sultan monastery
በሌላ በኩል ‹‹ዜና ኢየሩሳሌም›› መጽሔት፣ ዛሬ በድኅረ ሆስኒ ሙባረክ ግብጽ ለሥልጣን የበቃው የእስላም ወንድማማቾች እና ሌሎች እስላማዊ የፖሊቲካ ኀይሎች ሳይቀሩ እ.አ.አ በ1980 በካይሮ ዴር ሡልጣንን አስመልክቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ÷ የዴር ሡልጣን ችግር‹‹ከመካከለኛው ምሥራቅ ጠቅላላ ገጽታዎች ተለይቶ መታየት የለበትም›› በማለት እንደተናገሩ በወቅቱ አል – ቅዱስ በተሰኘ ጋዜጣ የወጣውን ዘገባ ጠቅሷል – ‹‹በዚህ ጉዳይ በሕጋዊ ክርክሮች ላይ መተማመን ሳይኾን የፍልስጤም ችግር በሁሉም የእስልምናና የክርስትና ቅዱሳት ስፍራዎች አኳያ መቅረብ አለበት፡፡ መብትን ለማስከበር ኅብረት እንዲጠናከር ግብጽ ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ አለባት፡፡ ሕግ በኀይል መደገፍ አለበት፡፡››
‹‹መቶኝ አለቀሰ፤ ቀድሞኝ ከሰሰ›› የሚለውን የዐረቦች ብሂል በማጠቃለያነት የጠቀሰው ‹‹ዜና ኢየሩሳሌም›› መጽሔት፣ ግብጻውያን ከኢትዮጵያ ወስደው ሲያበቁ ኢትዮጵያ ነጥቃቸው ለማስመለስ የሚደክሙ መስለው መታየታቸው የሚያሳስብ ከመኾኑም በላይ ‹‹ከክርስትና መንፈስ ውጭ ነው፤›› ብሏል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዳስታወቁት፣ መቼና የት እንደኾነ ባይገለጽም በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያን መካከል በቅ/ሲኖዶስ ደረጃ ይካሄዳል የተባለው ውይይት የሚጠበቅ ኾኖ በመንግሥት ለመንግሥት ደረጃ ባለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ጉዳዩ ተገቢው ትኩረት ሊቸረውና ብሔራዊ ንቅናቄም ሊፈጠርበት የሚገባ ነው፡፡
በታሪክ ይዞታችን የሐቀኛ ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች በየጊዜው በብዛት መገኘት በአንድ በኩል÷ ከንግሥት ሳባ ጀምሮ (1000 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) ለሚቆጠረው ባለርስትነታችን፣ ጥንተ ክርስትናችንን ለሚመሰክረው ገዳማችንና ለገዳማውያኑ በቀላሉ የማይገመት ትውልዳዊ ዋስትና የሚሰጥ መኾኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬም ድረስ በትንሣኤው ሰሞን ‹‹መብራት ይዘን ካላለፍን›› በሚል ታሪክ ለመሻማትና ቀጣይ ታሪክ ለማስመዝገብ በፖሊስ ጭምር ለሚያስወተውቱት ግብጻውያን ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፍ (በቅዱስነታቸው አነጋገር ዐይናቸውን የሚያቀላ) ነው፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment