Sunday, April 14, 2013

የኮሌጁ የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት ኮሌጁን እንዲለቁ ታዘዙ


  • መንሥኤው ‹‹ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም›› የሚል ነው
  • ‹‹ማስታወቂያው ለብቀላና እስር ሰበብ መፈለጊያ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት ከዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የኮሌጁን ንብረት እያስረከቡ ኮሌጁን እንዲለቁ አሳሰበ፡፡ ኮሌጁ ማሳሰቢያውን በዛሬው ዕለት በቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርቱ ላይ ያወጣው ‹‹ያቋረጣችኹትን ትምህርት አግባብነት ባለው መንገድ አልጀመራችኹም›› በሚል ነው፡፡
Holy Trinity College Academic Programs
የኮሌጁ የትምህርት መርሐ ግብር

ከድኅረ ምረቃና ከማታው ተከታታይ መርሐ ግብሮች በቀር የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ‹‹ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም›› በሚል ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን መጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ያወጣውን ማስታወቂያ የጠቀሰው የዛሬው የኮሌጁ ማሳሰቢያ÷ ኮሌጁ ‹‹ለሰላም ባለው ጽኑ ፍላጎት ያቋረጣችኹትን ትምህርት ትቀጥላላችኹ›› በሚል እሳቤ እስከ ዛሬ ድረስ ‹ በትዕግሥት ቢጠብቅም ተግባራዊ ባለመደረጉ›› የቀኑ መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ የተዘጋ መኾኑንና ደቀ መዛሙርቱ የኮሌጁን ንብረት እያስረከቡ ኮሌጁን እንዲለቁ አስታውቋል፡፡
ጥያቄ ያቀረቡባቸው ሁለት የኮሌጁ ሓላፊዎች ከያዟቸው ተደራራቢ ኮርሶች በቀር ትምህርታቸውን በዛሬው ዕለት ጭምር መቀጠላቸውን የተናገሩ ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው÷ ውዝግቡን የሚያጣራ የጋራ ኮሚቴ በተቋቋመበት ኹኔታ የወጣው የዛሬው የኮሌጁ የልቀቁ ማስታወቂያ ተማሪውን ለመበቀልና ለማሳሰር ምክንያት የሚፈለግበት የጥቂት ሓላፊዎች ፍላጎት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አንድ የውጭ መምህር እንዳያስተምር በዛሬው ዕለት መታገዱን የተናገሩ ሌላው የኮሌጁ መምህር፣ መርሐ ግብሩ ያለቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ማንም እንደፈለገ ሊዘጋው እንደማይችልና ርምጃውን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡
ኮሌጁ በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር 181 መደበኛና ስምንት ተመላላሽ ደቀ መዛሙርት አሉት፡፡

Source: http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment