Thursday, August 16, 2012

(UPDATED) የአቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት ጉዳይ ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር

  •  READ THIS UPDATED NEWS IN PDF
  • በአንድ የመንግሥታዊው ባንክ ቅርንጫፍ ሦስት አካውንቶች ውስጥ በፓትርያሪኩ የተለያዩ ዘመዶች ስም ከ22 ሚልዮን ብር በላይ መከማቸቱ ተጠቁሟል፤
  • የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስከሬናቸው ባለበት በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ተገኝተው ሥርዐተ ግንዘቱን አከናውነዋል፤ ጥቅመኛዋ እጅጋየሁ በየነ “አልሞቱም፤ አስከሬናቸው ይመርመርልኝ” እያለች በማወክ ላይ ትገኛለች፤
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ ተደርጓል፤
  • የአቡነ ጳውሎስን ቀብር የሚያስፈጽም ኮሚቴ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ተቋቁሟል፤ መኖሪያ ቤታቸውና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ታሽጓል፤ በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ሙዝየሞች ለጎብኚዎች ዝግ ተደርገው ጥበቃው እንዲጠናከር ታዝዟል፤
  • ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ በማካሄድ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ይሾማል፤ ከቋሚ ሲኖዶሱም ጋራ እየመከረ ይሠራል፤ (ሕገ ቤተ ክርስቲያን)
  • “ውሉደ ጳውሎስ” /እነ እጅጋየሁ በየነ/ በፓትርያሪኩ ስም “ጳውሎስ ፋውንዴሽን” ለማቋቋም እየተሯሯጡ ነው፤ የሀብት ቅርምቱን ለማመቻቸት ይኾን?

(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012/READ THIS UPDATED NEWS IN PDF):- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዛሬ፣ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ንጋት ላይ በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል በተወለዱ በ76 ዓመታቸው፣ በተሾሙ በኻያኛ ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡


ፓትርያሪኩ ከትናንት በስቲያ፣ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ገብተው ሕመማቸውን ለረጅም ጊዜ ሲከታተሉላቸው በቆዩት የሆስፒታሉ ዶክተሮች ሕክምና ቢደረግላቸውም በቆየባቸው በሽታ ዛሬ ንጋት 11፡00 ላይ መሞታቸውና አስከሬናቸውም ረፋድ ላይ ወደዚያው ባመሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሥርዐተ ግንዘት እየተከናወነለት እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡
አቡነ ጳውሎስ የምንገኝበትን የፍልሰታ ለማርያም ጾም በድሬዳዋ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ወቅድስት አርሴማ የሴቶች ገዳም የማሳለፍ ልማድ ቢኖራቸውም በዘንድሮው ሱባኤ ግን መሰንበቻቸውን ያደረጉት የፕትርክናው መንበር በሚገኝበት በአዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነበር፡፡
በቀደሙ ዘገባዎቻችን እንደገለጽነውና በሰሞኑ የሱባኤው ቅዳሴ ውሎዎች እንደተረጋገጠው÷ አቡነ ጳውሎስ የጀመሩትን ጸሎተ ቅዳሴ ለመጨረስ ተስኗቸው ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት /እነ ብፁዕ አቡነ ገሪማ/ እየተተኩ ጸሎተ ቅዳሴው እንዲጠናቀቅ ሲደረግ ነበር፡፡
የዐይን እማኞች እንደተናገሩት÷ ፓትርያሪኩ በጸሎተ ቅዳሴው መካከል በወንበር ላይ እንደተቀመጡ ሁለት እግራቸውን ፊት ለፊታቸው በሚገኝ ሌላ ወንበር ላይ ሰቅለው ታይተዋል፤ ወደ መኖሪያቸው ሲወጡም ይኹን ሲገቡ ዙሪያቸውን በረዳቶቻቸው ተደግፈው ነው፡፡ ከቆየባቸው የስኳር በሽታና ከፍተኛ የደም ግፊት ሕመሞቻቸው (hypertension and diabetes) መወሳሰብ ጋራ በተያያዘ ሁለቱም እግሮቻቸው ከአውራ ጣታቸው ጀምሮ እስከ ጉልበታቸው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድተዋል፡፡ እግራቸው እንዲቆረጥ ጤናቸውን በሚከታተሉላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሐኪሞች ሲነገራቸው ቢቆይም ፓትርያሪኩ ለሥልጣናቸው በመሳሳት [በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በአካል ጉዳተኝነት በፕትርክናቸው - ክህነታዊ ሥልጣን - መቀጠል አይችሉም] የሐኪሞቹን ምክርና ማሳሰቢያ ችላ ብለው በውጭ ምንዛሬ በሚገዟቸውና በመርፌ በሚወስዷቸው መድኃኒቶች ራሳቸውን ሲያስታምሙ ቆይተዋል፡፡ አባ ጳውሎስ ከትናንት በስቲያ ወደ ሆስፒታል የገቡት ታዲያ በእግራቸው ላይ በሚሰማቸው ከፍተኛ ጥዝጣዜ እየተሠቃዩ ባለበት ኹኔታ ነበር፡፡
በኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበርና ከዚያም ወዲህ ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎች ወቅት ጥልቅ የመቀዘዝ ስሜት ይታይባቸው የነበሩት አባ ጳውሎስ÷ ትምክህታቸውን በሚገልጹላቸውና እንደ አለኝታም በሚቆጥሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጽኑ መታመም ክፉኛ መደናገጣቸውና ግራ መጋባታቸው፤ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በሃይማኖት ሕጸጽ ከተጠየቁ ወዲህ [በመጽሐፍ መልክ ባሳተሙት የዶክትሬት ጥናታቸው ሕጸጹ የተገለጸባቸውን አንቀጾችና ዐረፍተ ነገሮች አውጥተዋቸዋል] በአያሌው መጨነቃቸው፤ ከቅዱስ ሲኖዶሱ በላይ አመራር ሰጪ በመኾን የቀድሞውን ዐምባገነናዊ አሠራራቸውን ለመመለስ ከወርኀ ግንቦት ጀምሮ ሕገ ወጥ ቡድኖችን በማደራጀት ያደረጓቸው ጥረቶች መክሸፋቸው፤ ከዚህም ሁሉ ጋራ በሄዱበት ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚከተሏቸው በርካታ ጳጳሳት የሸሽዋቸው መኾኑ እዚህም እዚያም ከሚሰማው የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምእመናንና ወዳጆች ሐዘንና ጸሎት ጋራ ተደማምሮ የፈጠረባቸው አካላዊና መንፈሳዊ መጎሳቆል ለተመልካች በጉልሕ የሚረዳ እንደ ነበር የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንጮች ለደጀ ሰላም ተናግረዋል፡፡
ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም የተሾሙትና ለኻያ ዓመታት በፕትርክና የቆዩትን የአቡነ ጳውሎስን የቀብር ሥነ ሥርዐት ለማስፈጸም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የአስተዳደር ጉባኤው ዛሬ ጠዋት ከመከሩበት በኋላ ‹‹የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ›› መቋቋሙ ተዘግቧል፤ የቀብር ሥነ ሥርዐት አፈጻጸሙም በተከታታይ እንደሚገለጽ ከፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ የወጣው የሐዘን መግለጫ አስታውቋል፡፡ የፓትርያሪኩ የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤትና ፕሮቶኮል ሹሞችና ሓላፊዎችም በየአህጉረ ስብከቱ ስልክ በመደወል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በርካታ አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን በመንበረ ፓትርያሪኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ሐዘናቸውን ሲገልጹ የዋሉ ሲኾን ስለ ጸሎተ ፍትሐቱ እና የቀብር አፈጻጸም መርሐ ግብሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የሚያወጣው መግለጫ እየተጠበቀ ነው፡፡
የአባ ጳውሎስ ኅልፈተ ሕይወት በመጀመሪያው የደጀ ሰላም ዜና መገለጹን ተከትሎ÷ በርካታ ወገኖች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዓለማዊው አገራዊው ኹኔታ አኳያ በወሳኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ፣ በሹመታቸው ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት የከፈሉት አባ ጳውሎስ በሞታቸውም እንደይከፋፍሉን ይልቁንም ቀጣይ ርምጃዎች ያለፉትን ስሕተቶች የሚያርሙና እንዳይደገሙ የሚያደርጉ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት መጠናከርም የሚያግዙ፣ ተቋማዊ ነጻነቷንና ብሔራዊ ክብሯን የሚመልሱ በመኾናቸው ላይ የተረጋጋና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንዲሠራ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡
በፓትርያሪኩ ሞት ሰበብ ዘመዶቻቸው፣ የጥቅም ተጋሪ ቡድኖችና ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እንዳያሸሹ ማሳሰቢያ እየተሰጠም ነው፡፡ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው፣ በቅርስና ቱሪዝም መምሪያ ሓላፊው ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ሓላፊነት የሚመራውና ከቀደሙት አራት ፓትርያሪኮች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች የተከማቹበት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት እንዲታሸግ ተደርጓል፡፡ እንደ እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም ቦታዎች ያሉት ሙዝየሞች ለጊዜው ለጎብኚዎች ዝግ ተደርገው ጥበቃቸው እንዲጠናከር ከመንግሥት የተሰጠውን ትእዛዝ የአዲስ አበባ ፖሊስ በማስፈጸም ላይ ይገኛል፡፡
ይኹንና የተፈራውን ስጋት በሚያጠናክር አኳኋን የአባ ጳውሎስ ‹‹ቁም ተዝካር›› በተባለው የኻያኛው በዓለ ሢመታቸው አከባበር ወቅት የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩት ውሉደ ጳውሎስ (እነ እጅጋየሁ በየነ) በአቡነ ጳውሎስ ስም የሚጠራ ‹‹ጳውሎስ ፋውንዴሽን›› እናቋቋማለን በሚል እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
ለ‹ፋውንዴሽኑ› መቋቋም ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብም እንደተለመደው ከስፖንሰርሽፕ፣ ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኢኮኖሚያዊ ምንጮች ለመሰብሰብ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን የገለጸው የመረጃ ምንጩ÷ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማን (ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል)፣ ሰሎሞን በቀለን (ቦሌ መድኃኔዓለም)፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬን (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልን (ጠቅላይ ቤተ ክህነት) በዋና አደራጅነት ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኀይሎች በመታገዝ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የወይዘሮዋንና ሌሎች አካላትን ችግር ፈጣሪነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም እየሠራ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
በተከታታይ ስለከናወኑት ተግባራት ለመወያየት የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚካሄድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መናገራቸው የተዘገበ ሲኾን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአባ ጳውሎስ እምቢተኝነት ሳይካሄድ በቀረውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከእምባ ጋራ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፈረድ›› በሚል ሐዘናቸውን ከገለጹበት የሐምሌው ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መስተጓጎል በኋላ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ሦስት አባላት የሚገኙበትና በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመራ ኮሚቴ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተጀመረው የሰላምና ዕርቅ ንግግር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለአስታራቂ ኮሚቴው ሰባት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ እንደነበር ተነግሯል፡፡
የሰላምና ዕርቅ ንግግሩ እንዳይቀጥል ዕንቅፋት ሲፈጥሩ የቆዩት አባ ጳውሎስ ሞታቸው በሂደቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ገና የሚታይ ይኾናል፡፡
በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያሪክ ድኅረ ዕረፍት ወይም ከሥልጣን መውረድ (አንቀጽ 16) በኋላ ስለሚሆነው ጉዳይ በአንቀጽ 17 ንኡስ አንቀጽ 1 - 3 ላይ የሚከተለውን ይላል፡፡
አንቀጽ 17 - ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ
1. ፓትርያሪኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያሪክ ምርጫም ይካሄዳል፡፡
2. የተተኪው ፓትርያሪክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደ ሥራው ኹኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይኾናል፡፡
3. የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ተግባር-
) ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ጊዜያዊ ጉዳዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ እየመከረ ያከናውናል፡፡
) በፓትርያሪኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ኾኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡

የአባቶቻችን አምላክ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment