Tuesday, August 7, 2012

የአቡነ ጳውሎስ የዶክትሬት ጥናት መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል



  • በጥናቱ መታተም ስለ ነገረ ማርያም  ቅ/ሲኖዶስ በአቡነ ጳውሎስ ላይ ያነሣውን ጥያቄ ለማድበስበስና ወዲያውም ደግሞ የጥቅም አሳዳጆችን ፍላጎት ለማሟላት እንደታለመ ተነግሯል።
  • ፓትርያርኩ ለእጅጋየሁ በየነ ካባ አልብሰዋል።
  • ወይዘሮዋ “ለአራት ዓመታት ያረገዝኹት ነው” ያሉትን ‹ፎቶ-መጽሐፍ› አስመርቀዋል፤ ከ‹ፎቶ-መጽሐፉ› ኅትመት ጋራ በተያያዘ እስከ ብር 700,000 ወጪ መደረጉ እየተነገረ ነው።

(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 28/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 4/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF):- አምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን “ዓለም አቀፋዊ እና ሀገር አቀፋዊ ሰውነትና ክብር” ማእከል አድርጎ በተለያዩ ሰበቦች የሚካሄደው የኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበር አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ይኸው የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለከፍተኛ ብክነትና ዘረፋ እየዳረገ በሚገኘው÷ ከነጻነት በዓል ወደ ግለሰባዊ የተክለ ሰውነት ግንባታ በተቀየረው የበዓል አከባበር ቀጣዩ መድረክ ደግሞ÷ የአቡነ ጳውሎስን የነገረ መለኰት ዶክትሬት ጥናት ጽሑፍ በመጽሐፍ መልክ ማሳተም፣ ማስመረቅና ማሻሻጥ ነው፡፡


የመጽሐፉ ምረቃ ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡00 ላይ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ፓትርያርኩና በጥንቃቄ የተመረጡ ግለሰቦች በተገኙበት እንደሚከናወን ተጠቁሟል፤ በሰሞኑ የበዓለ ሢመት ድግሶች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው እነ እጅጋየሁ በየነና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬ ለጥናት መጽሐፉ ኅትመት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡

በ1967 ዓ.ም ከሌሎች ሁለት አባቶች ጋራ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አንብሮተ እድ ኤጲስ ቆጶስነት እንደተሾሙ ለወኅኒ የተዳረጉት አቡነ ጳውሎስ÷ ከሰባት ዓመት እስር በኋላ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አማካይነት ባገኙት የነጻ ትምህርት ዕድል ከአሜሪካው የፕሪንስተን ቴዎሎጂካል ሰሚናሪ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የማስትሬት ዲግሪ ቀጥሎም በነገረ ማርያም ንጽጽራዊ ጥናት ላይ ባተኰረው የነገረ መለኰት ትምህርት ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡

አቡነ ጳውሎስ “Filsata: The Feast of the Assumption of the Virgin Mary and the Mariological Tradition of the Ethiopian Othodox Tewahedo Church” በሚል ርእስ እ.አ.አ በ1988 በነገረ ማርያም ላይ የሠሩት የነገረ መለኰት ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት ከቀድሞው ጀምሮ ውስጥ ለውስጥ ጥያቄ ሲነሣበት ቆይቶ አባ ሰረቀ “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ ባሳተሙት የዶሴ ስብሰብ ሰበብ በግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ አቡነ ጳውሎስን ማስጠየቁ ይታወሳል፡፡
“ይመረቃል” በተባለው መጽሐፍ በተለይም የእመቤታችንን ንጽሕና አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያናችንን በማይወክል መልኩ በአቡነ ጳውሎስ ንጽጽራዊ ጥናት ውስጥ የእኛ መስሎ የተገለጸው የባዕዳን ትምህርት እርምት ተደርጎበት እንደኾን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2004 ዓ.ም በመጽሐፉ ላይ ስላካሄደው ስብሰባ “የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሰባተኛ ቀን ውሎ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአቡነ ጳውሎስ ኮመጠጠ” በሚል ርእስ ያቀረብነውን ዘገባ ከፊል ይዘት የሚከተለው ነበር፡፡

. አቡነ ጳውሎስ በእመቤታችን ንጽሕና ላይ እምነታቸውን እንዲገልጡ ቢጠየቁ አንደበታቸው ተሳሰረ፤ ለጥያቄው መነሻ የኾነው ፓትርያርኩ በአባ ሰረቀ ‹መጽሐፍ› ላይ ስለተጠቀሰው የዶክትሬት ጽሑፋቸው ዝምታን በመምረጣቸውና ኮሚቴውም የእርሳቸውን ምላሽ ወይም አቋም አለመመርመሩ ነው - “አባ ሰረቀ ጽሑፍዎን ጠቅሰው መጽሐፍ ከጻፉ በኋላ ለምን ዝም አሏቸው? ኮሚቴውስ ለምን አልጠየቀም? ይሉኝታ ነው ወይስ ተመሳስሎ ለመኖር ነው?” /ብፁዕ አቡነ አብርሃም - ነደ ‹ተሐድሶ›/
ይኹንና ኮሚቴው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ላይ በየደረጃው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የተናነቃቸው ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ ያንን በመገልበጥ ሌላ የውሳኔ ሐሳብ ይዘው በመቅረብ ያነባሉ፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም አቡነ ጳውሎስ ያነበቡት ትላንት ካዳመጡት የሚለይባቸውን ነጥቦች በመጥቀስ ቀደም ሲል በቀረበው ወደ ውሳኔ መሄዱ የተሻለ መኾኑን ይናገራሉ፡፡ አቡነ ጳውሎስ ግን የኮሚቴውን አባላት ሌሎች ተናጋሪዎችን “እናንተ ባቀረባችኹት አላምንበትም፤ ኮሚቴው በትክክል እና በጥራት አልሠራም፤ ሪፖርቱ ችግር አለበት፤ አልቀበለውም” በማለት ፍርጥም ይላሉ፡፡

ይህን ጊዜ ነበር ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተነሥተው “አዎ፣ ችግር አለ፤” አሉ “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ አባ ሰረቀ ያሳተሙትን መጽሐፍ መሰል ጥራዝ በማስታወስ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፤ “አዎ ችግር አለ፤ ዝምድና ነው፣ ይሉኝታ ነው፣ ወይስ ተመሳስሎ ለመኖር ነው ኮሚቴው እርስዎን ያልጠየቀው? አባ ሰረቀ ከእርሰዎ ጽሑፍ በመጥቀስ እመቤታችን ጥንተ አለባት እንደሚሉ አውጥተዋል፤ እውነት ይህ ቃልዎ ነው? እንዲህ ብለዋል? መጽሐፉ ከወጣስ በኋላ ለምን በዝምታ አለፉት? ትክክል ነው ብዬአለኹ፤ ካላሉ ደግሞ አላልኹም ብለው ለምን አልተናገሩም? ኮሚቴውስ ለምን አልጠየቀም?” የሚል ጠንካራ ጥያቄ አንሥተዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ ሰበቡ የአባ ሰረቀ “እውነትና ንጋት” ይኹን እንጂ አቡነ ጳውሎስ በፕሪንስተን ቴዎሎጂ ኮሌጅ “Filsata: The Feast of the Assumption of the Virgin Mary and the Mariological Tradition of the Ethiopian Othodox Tewahedo Church” በሚል ርእስ እ.አ.አ በ1988 በነገረ ማርያም ላይ የሠሩት የነገረ መለኰት ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት ከቀድሞው ጀምሮ ውስጥ ለውስጥ ሲነሣ የቆየ ነው፡፡

በነገረ ማርያም ላይ የኢኩሜኒዝም አንድነት(Ecumenical Unity) ለማምጣት በሚል ዓላማ የተሠራው ይኸው ጥናት በአቀራረቡ ንጽጽራዊ ሲኾን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን (ከገጽ 45 - 306)፣ የሮም ካቶሊክን (ከገጽ 307 - 320)፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስን (ከገጽ 333 - 348) እና የፕሮቴስታንት አብያተ እምነትን (ከገጽ 321 - 332) የነገረ ማርያም አስተምህሮ እየራሱና በንጽጽር የቀረበበት ነው፡፡ ለዚህም በታሪክ የተደረገ የንግግር ጥረቶችን በማስታወስ በቀጣም በክርስትናው ዓለም አንድ የተዋሐደ የነገረ ክርስቶስ አስተምህሮ መደረስ እንደሚቻል ይመክራል፡፡

አባ ሰረቀ በመጽሐፍ መሰል የዶሴ ጥራዛቸው የጠቀሱት ከገጽ 336 - 338 ያለውን የጥናቱን ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል ግን አቡነ ጳውሎስ በተለይም የምሥራቅ ኦርቶዶክስን (መለካውያን) የነገረ ማርያም አስተምህሮ ታሪክና ምንነት የዘረዘሩበት ነው፡፡ አባ ሰረቀ እንደ እነአስተርኣየ ጽጌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነገረ ማርያም ከሌሎች ጋራ ለመቀየጥ ካልፈለጉ በቀር አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ባቀረቡበት ክፍል ከአንድ በላይ አስረጅዎችን ለመጥቀስ በቻሉ ነበር፡፡

በዚህ ክፍል (በተለይ ከገጽ 45 - 141) ፓትርያርኩ ነገረ ማርያምን በቅዱስ ያሬድ፣ በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ድርሳናት ውስጥ ደኅና አድርገው የተነተኑትን ያህል በአንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች ግን “የአስተምህሮ አንድነት አመጣበታለኹ” ለሚለው አካዳሚያዊ ፕሮጀክታቸው ይመስላል ከኢትዮጵያ ምንጮች የማያገኙትን አስተምህሮ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይትበሃል ካልታቃኑት ምንጮች ሲጠቅሱ እናገኛቸዋለን፡፡

ለአብነት ያህል በዚሁ ክፍል አቡነ ጳውሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስዋም በሥጋዋም ንጽሕት (በሁለት ወገን ድንግል) የኾነችና በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያልተለየች ብትኾንም ከውርስ ኀጢአት ግን ነጻ እንዳልነበረች የጻፉት የቅብጦችን ምንጭ ጠቅሰው ነው፡፡ አቡነ ጳውሎስ ምንጩን ጠቕሰው በጥናታቸው እንዲህ ይላሉ፡-

For the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church the Virgin Mary is the example par excellence of obedience and faithfulness to God. She is two-fold virgin; i.e, virgin both in body and soul, who, though not “immaculate” or free from original sin, yet was all-holy, pure, chose to actively participate in the saving work of God, His Incarnation. (p.306) (Amba Alexander, “The Assumption in the Liturgy of the Church of Alexanderia;” Eastern Churches Quarterly, 9 (1951)

በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና (በ1986 ዓ.ም) በቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝና ፈቃድ በተሰበሰቡ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና 11 ሊቃውንት “ወኢረኵሰት በኢምንትኒ እምዘፈጠራ፤ ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ርኵስ ነገር አልተገኘባትም፤ በነፍስም በሥጋም ሁልጊዜም ንጽሕት ናት፤” (ሃይ. አበ 53) በማለት በቅዱሳን አበው የተመዘገበውን መሠረት በማድረግ ያዘጋጁት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት” መጽሐፍ ግን ስለ እመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና የሚለው የሚከተለውን ነው፡-

“ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነውና የምታስተምረው፡- አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሐሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡”

አቡነ ጳውሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለ ተባለ “የበደል ውርስ አለባት” ብለው ከሚያምኑ ጸሐፊዎች ጋራም ተባብረዋል፡፡ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌም የሚሉት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህም ከአበው ድርሳናት ምስክርነት ቢያጡ የጠቀሱት ከቅብጦቹ ምንጭ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-

Like all daughters and sons of Adam, the holy Virgin Mary died as a result of Adam’s sin. “Mary sprung from Adam, died on consequence of original sin; Adam died in consequence of sin, and the flesh of the Lord, sprung from Mary, died to destroy sin.” (p.302) (Malaty, T.Y. St. Mary in the Orthodox Concept, 1978)

ይህን ሐሳብ በተመለከተ አባ ሰረቀን ጨምሮ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌና ሌሎችም “ስሜን (ሥራዎቼን) በመጥቀስ ማታለያ አድርገውኛል” ያሉት ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ ግለሰቦቹ እሳቸውን በእነርሱ የኑፋቄ ሐሳብ ውስጥ እንዳይጨምሯቸው፣ ለራሳቸው እንዲመለሱና እንዲታገሡ በመከሩበት “ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ” በሚል ርእስ ባዘጋጁት የመጨረሻ መጽሐፋቸው፡- “እነ ቄስ አስተርኣየ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለተባለ የበደል ውርስ እንዳለባት አድርገው ሊቈጥሩት ሞክረዋል፡፡ ክሕደቱ፣ በደሉ ካልቀረ ሰው የኾነ አምላክ ልጇም የመስቀልን ሞት ተቀብሏልና ከአይሁድ ጋራ ቆመው የጲላጦስን ምስክርነት ቢያስተባብሉ ይሻላል፡፡ ከአበዱ ወዲያ በመንገዱ መሄድ መስነፍ ነው ይባል የለ?” በማለት ተችተዋል፡፡

እንግዲህ ትናንት አቡነ ጳውሎስ በእመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና ላይ “እምነትዎን ይግለጡ፤ ይመኑ ወይም ያስተባብሉ” ሲባሉ ወዲያና ወዲህ በሚላጉ ንግግሮች አንደበታቸው መተሳሰሩ ነው የተዘገበው፡፡ ከዚህ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት 60 ገጽ ያለው የኮሚቴው ሰነድ በቁጥራቸው ልክ ተባዝቶ እንዲደርሳቸውና እያንዳንዱን የውሳኔ ሐሳብ በጥንቃቄ እየተመለከቱ ለመወሰን ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ነገ ግንቦት 11 ቀን 2004 ዓ.ም የሚከበረውን የማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ “ወደ አኵስም እሄዳለኹ” የሚለው የፓትርያርኩ ሐሳብ ያሰጋቸው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በይደር የተያዘው አጀንዳ በውሳኔ ሳይታሰር እንዳይቀር የሚያስጠነቅቅ ማሳሰቢያ ተናግረዋል - “በሐዋርያት ቃል፣ በሐዋርያት ቃል÷ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ ይህ አጀንዳ ሳምንትም ቢፈጅብን እርስ በርሳችን ሳንፈታተሽ አንድ ሰው እንዳይሄድ!”

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment