Monday, October 21, 2013

የካህናት እና ምእመናን ምዝገባ(ቆጠራ) ሊካሄድ ነው

  • ከ29 ሚልዮን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ቀርቧል
  • የ49 አህጉረ ስብከትን 800 ወረዳዎች ይሸፍናል
  • ከ21,680 በላይ የሰው ኃይል ይሳተፍበታል
  • አጽንዖት ተሰጥቶ እንዲሠራበት አጠቃላይ ጉባኤው በጥብቅ አሳስቧል
  • የአህጉረ ስብከት የስታቲስቲካዊ መረጃዎች አያያዝ ጥራት አሳሳቢ ኾኗል
  • ‹‹የምእመናን ምዝገባ ለቤተ ክርስቲያን ያለው ጠቀሜታ ከመለካት በላይ የኾነ ወሳኝ ተግባር እንደኾነ የጉባኤው አባላት ተረድተናል፡፡ ያለንን አቅም በማቀናጀት በቀጣዩ ጊዜ በጥራት መዝግበን ለማቅረብ ቃል እንገባለን፡፡›› /የአጠቃላይ ጉባኤው የአቋም መግለጫ/


የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ያላትን አቅም በማቀናጀት አኀዛዊ መረጃዎቿን በተለይም የምእመኖቿን ቁጥር መዝግባ በጥራት ማወቅ እንደሚገባት አሳሰበ፡፡
ዓመታዊ ስብሰባው ትላንት እሑድ፣ ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ቀትር ላይ ሲጠናቀቅ በንባብ የተደመጠው የዐቢይ መንፈሳዊ ጉባኤው የአቋም መግለጫ÷ የምእመናን ምዝገባ ለቤተ ክርስቲያን ያለው ጠቀሜታ ከመለካት በላይ የኾነ ወሳኝ ተግባር እንደኾነ የጉባኤው አባላት‹‹የምእመናን ምዝገባ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ልማት ያለው ጠቀሜታ›› በሚል ርእስ ባካሄዱት የቡድን ውይይት መረዳታቸውን አስገንዝቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አኃዛዊ መረጃን በተመለከተ የካህናትና የልዩ ልዩ ዘርፍ ሠራተኞቿን ብዛት በየአምስት ዓመቱ እየመዘገበች መቆየቷን የአቋም መግለጫው አስታውሷል፡፡ እንደ መግለጫው÷ በ፳፻፭ ዓ.ም. የአብያተ ክርስቲያን ስምና የትክል ኹኔታ፣ የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት፣ ካህናት በየማዕርጋቸው፣ በሰበካ ጉባኤ ተመዝግበው አስተዋፅኦ የከፈሉና ያልከፈሉ ምእመናን ብዛት እንዲገለጽ ከሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ተላልፎ የነበረው መመሪያ ተፈጻሚ ያደረጉት 27 አህጉረ ስብከት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ቢኾን ምዝገባው በቂ ጊዜ ተሰጥቶት የተካሄደ ስላልነበር ስታቲስታካዊ ጥራቱ አሳሳቢ ኾኖ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡
በቀጣዩ ጊዜ ያለውን አቅም በማቀናጀት የቤተ ክርስቲኒቱን አኃዛዊ መረጃዎች በጥራት መዝግቦ ለማቅረብ ቃል የገባው አጠቃላይ ጉባኤው፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ማዕከላት በሠለጠነ የሰው ኃይልና ብቃት ባለው ቁሳቁስ በማደራጀት መፈጸም እንደሚገባው አስታውቋል፡፡ ለዚህም መረጃው ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ በኾነ መንገድ እንዲዳረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመገናኛ አውታሮች እንዲገለጽ፣ በድረ ገጾች ዜናው እንዲሰራጭ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጽንዖት ሰጥቶ ይሠራበት ዘንድ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በተያዘው የ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ምዝገባ ለማካሄድ በያዘው ዕቅድ ብር 29,442,043.70 ያህል የበጀት ጥያቄ ከዝርዝር ወጪዎቹና ተግባራቱ ጋራ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡ ታውቋል፤ የበጀት ጥያቄው ሰኞ ማምሻውን በመክፈቻ ጸሎት በሚጀመረው የጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ ተገምግሞ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል፡፡
የምእመናን ምዝገባው፣ ቤተ ክርስቲያን በአገር ውስጥ ባዋቀረቻቸው 49 አህጉረ ስብከት ያሏትን 800 ወረዳዎች እንደሚሸፍን የተገለጸ ሲኾን በአዲስ አበባ 6000፣ በአህጉረ ስብከት ደግሞ 15,680 በአጠቃላይ 21,680 የሰው ኃይል እንደሚሰማራበት ተዘግቧል፡፡ በቆጠራ የሚሰማራውን የሰው ኃይል ለማሠልጠን 442 ባለሞያዎች የተዘጋጁ ሲኾን በሁለት ዙሮች በሚካሄደው የአሠልጣኞች ሥልጠናና የዋና ቆጣሪዎች ሥልጠና በድምሩ ብር 7,280,000 በጀት መያዙ ታውቋል፡፡
የዓለም አቀፍ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምክር ቤት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤት፣ የተ.መ.ድ ልማት ፕሮግራም እና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኢጀንሲ ቆጠራውን በገንዘብና በባለሞያ እንደሚደግፉት ይጠበቃል፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment