Monday, October 7, 2013

‹‹የበደልናትን ቤተክርስቲያንን እንክሳለን ፤ ይዘን የወጣነውን ህዝብ መልሰን እናመጣለን ፤ ላጠፋነው ጥፋትም ቤተክርስቲያኒቱ ይቅርታ ታድርግልን›› ተሀድሶያውያን

ከእንቁ መጽሄት እንዳገኝነው
(አንድ አድርገን መስከረም 20 2006 ዓ.ም)፡- ጉዳያቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ተይዞ በመታየት ላይ የሚገኝው የበጋሻው ደሳለኝ እና የያሬድ አደመን ጉዳይ በእርቅ መንገድ መፍትሄ እንዲፈለግለት በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኝው ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ መሆኗን ከቤተክህነት አካባቢ ያገኝነው መረጃ ያመለክታል፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው በጋሻውና ያሬድ አደመ‹‹የበደልናትን ቤተክርስቲያንን እንክሳለን ፤ ይዘን የወጣነውን ህዝብ መልሰን እናመጣለን ፤ ላጠፋነው ጥፋትም ቤተክርስቲያኒቱ ይቅርታ ታድርግልን›› ማለታቸውና እርቁን መፈለጋቸው ታውቋል፡፡

ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ የማስታረቁን ተግባር እንደጀመረች እና እነ በጋሻው ደሳለኝን ወደ ብጹእ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ ፤ ጌዲኦ ፤ አማሮ፤ ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዘንድ በማቅረብ እግራቸው ላይ ወድቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርጋለች ተብሏል፡፡ ብፁእነታቸውም ‹‹እኔን የሰደባችሁኝ ቢሆንም የተሰደበችው ግን ቤተክርስቲያን ናት ቢሆንም በግሌ ይቅርታችሁን እቀበላለሁ ፤ ጉዳዩ በሲኖዶስ የተያዘ ስለሆነ ግን ውሳኔውን ከወደላይ ጠብቁ›› በማለት መልስ የሰጡ መሆኑም ታውቋል፡፡
ዘማሪት ፋንቱ የማስታረቅ ጥረቷን  በመቀጠል እነ በጋሻው ወደ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ  ያቀረበች ሲሆን ፤ አቡነ ሉቃስም ‹‹ሰው ይቅርታ ሲጠይቅ እምቢ አይባልም ፤ ይቅርታን መግፋት ተገቢ አይደለም ፤ ሆኖም ወደ መድረኩ ስትመጡ ጉዳያችሁ አስቀድሞ በሲኖዶስ የተያዘ በመሆኑ ትክክለኛውን ምላሽ ከዚያ ያገኛል፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡
በጋሻው በብጹዕ አቡነ ገብርኤል ደብዳቤ ፊርማ ‹‹ሕገ-ወጥ ሰባኪያን ናቸው›› በሚል በእርሳቸው አሕጉረ ስብከት የወንጌል ማስተማር ስራ እንዳይሰሩ ካገዷቸው በኋላ በሀዋሳ ግጭት መከሰቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንኑ ጉዳይ የሚያውቁና በቅርቡ የማስታረቅ ሂደት መጀመሩን የሰሙ ወገኖች ‹‹ችግሩ በሊቃውንት ጉባኤ ታይቶ ወደ ሲኖዶስ የተመራ በመሆኑ በእርቅ ሊፈታ የሚችል አይደለም›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአዋሳ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት የተደበደቡና ፤ የታሰሩ ስላሉ ጉዳዩ በቀላል መታየት እንደሌለበት የሚያስጠነቅቁ የቤተክርስቲያን ሰዎች አልጠፉም፡፡ በዘማሪት ፋንቱ አማካኝነት እየተመራ ያለው እርቅ የማፈላለግ ተግባር እነ በጋሻውን ከሚቃረኗቸው ሰባኪያንና ዘማሪያን ጋር አቅርቦ ከማነጋገር ደረጃ አልፎ ‹‹ሕዝቡንም ይሁን ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነን›› እስከማለት ድረስ የተራመደ ነው፡፡
በሰሞንኛ የእርቅ ማፈላለግ ሂደት ከአዋሳ ከተማ የተገኙ ምዕመናን ጭምር ተሳትፎ ያደረጉበት ሲሆን ፤ ሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2006 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቢሮ ተይዞ የነበረው ቀጠሮ  በጋሻው ደሳለኝ አለመገኝቱ ምክንያት ለመስከረም 21 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
የ‹‹አንድ አድርገን›› ሃሳብ

ተሀድሶያውያን ባገኙት አጋጣሚ የነበራቸውን ቦታ ለማግኝት የማይፈነቅሉት ድንጋይ ፤ የማይወጡት ተራራ ፤ የማይገቡበት ቢሮ ፤የማይከፍሉት ዋጋ አለመኖሩን አስረግጠን መናገር እንችላለን፡፡ ይህ ጉዳይ እርቀ ሰላም የማውረድ እና ያለማውረድ ጉዳይ አይደለም ፤ ቤተክርስቲያን አንድም ሰው እንዲጠፋባት አትፈልግም ፤ ሰዎቹ ቀድሞም ከእኛ ዘንድ አልነበሩም ፤ አይን ባወጣ በክህደት ጎዳና ነጎዱ በአንድም በሌላም  መንገድ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በማጣመም እና በመበረዝ በርካታ ደጋፊዎችን በማፍራት በርካታ ጉዳቶችን ምዕመኑ ላይ እና ቤተክርስቲያኒቱ ላይ አደረሱ ፤ የምንፍቅና እና የክህደት ትምህርታቸውን በመጽሀፍቶታተቸው ፤ በሲዲዎቻቸው እና በተለያዩ መናፍቅ መናፍቅ ከሚሸቱ ብሎጎቻቸው ማር የተለወሰ መርዛቸውን ሲረጩ ከርመው ካበቁ በኋላ ያሉበት ጎዳና የት እንደሚያደርሳቸው ፤ የቆሙበት ቦታ የት እንደሚወስዳቸው ሲገነዘቡ ፤ ‹‹እርቅ›› ብሎ መምጣት አግባብ መስሎ አይታየንም ፡፡ ቤተክርስቲያን ለመናፍቅ ፤  ለከሃዲ እና ለእናት ጡት ነካሽ ይቅርታ አታደርግም አይደለም ፤ ነገር ግን አካሄዱ ጉዳያቸው በሊቃውንት ጉባኤ ታይቶ ፤ ስራቸው ተመዝኖና በቅዱስ ሲኖዶስ መክሮበት ከሚሰጠው ውሳኔ በኋላ እንጂ ጉዳያቸው እየታየ ባለበት ሰዓት ‹‹እርቅ›› ብሎ መነሳት በአምስተኛው ፓትርያርክ ሞት የተነሳ የተስተጓጎለውን መዝገብ ዳግም እንዳይነሳ የማድረግ ሃሳብ የማስቀየስ ሥራ መስሎ ይታየናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግራና ቀኛቸውን ያልተመለከቱ በርካታ ምዕመናን በመያዝ እሁድ ጠዋት ጠዋት ቤተክርስቲያን በማስቀደስ ከሰዓት ከሰዓት አዳራሻቸው እንደ መናፍቃን እያዘለሏቸው በሚገኙበት ሰዓት መሆኑም መዘንጋት የለበትም ፡፡ ‹‹ምንፍቅናን ይቅርታ ይመልሰው ይሆን!››


የአንድ ሰው ሃሳብ

ምናልባትም ሌላኛው አማራጫቸውና ቤተ ክርስቲያኒቱን ዳግም ለማመስ የተዘጋጁበት መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ጥንተ ምንፍቅናን ያስተዋልን እንደሆነ መልኩንና ስልቱን መሰል በሆኑና በተለያዩ መንገዶች በመቀያየር ቅድስት  ቤተክርስቲያንንና ልጆቿን ሲፈታተትንና ሲነጥል ኖሯል፡፡ እነዚህን ወገኖች በሰብአዊነታቸው መቼም አንጠላቸውም፡፡ ድርጊታቸውንና የልብ ክፋታቸውን ግን አጥብቀን እናቃወማለን፡፡ ለይቅርታ መዘጋጀታቸውም እውነት ከልብ ከሆነ ከዚሁ አንጻር መታየት ያለበት ሲሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ግን ይጠብቀናል፡፡ ያም አስቀድሞ ያጠፉትን ጥፋት መመልከት፣ መመዘን፣ መመርመር፣ መወሰን፡፡ ያስተማሩትን ትምህርት፣ የዘመሩትን መዝሙር፣ የጻፉትን መጽሐፍ …. እያንዳንዱን ነጥብ ተመልክቶ ማንነታቸውን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማሳወቅ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን የሚኖራቸው ምላሽና አሁንም ድረስ እየተጓዙበት ያለውን መንገድ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለማድረግ ያላቸውን ቀና መልስ በማጤን ለአሁኑ ይቅርታቸው ሌላ ውሳኔ ይዘን መጠበቅ ይኖርብናል እንጂ በምንወዳትና በምናከብራት ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ በኩል ስለመጡ የሚታለፉበት ሞኝነት ሊኖር አይገባም፡፡ የተሰደቡት አቡነ ገብርኤል እኮ አይደሉም፡፡ የተሰደቡት እኮ ጧት ማታ ለቤተ ክርስቲያን ደፋ ቀና ያሉ አባቶችና እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች በስብከታቸው እግዚአብሔርን ክብሩን አቃለዋል፡፡ በመጽሐፋቸው በዝማሬያቸው ድንግል ማርያምና ቅዱሳንን ተሳድበዋል ፤ ቤተ ክርስቲያን አዋርደዋል፡፡ ይሄ ጉዳይ ሰብአዊነት ላይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶት በይቅርታ እንደዘበት የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይቅርታም እኮ ቢሆን ዋጋ ሊከፈልበት ይገባል፡፡ ለአዳም ለጥፋቱ ፍርድ ተሰጥቶበታል፤ ለንስሐውም ካሳ ተከፍሎበታልና፡፡ ስለዚህም ስለመጀመሪያው ምንፍቅናቸውና የተሐድሶ ሀሳባቸው የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አጥብቀን እንሻለን፡፡ የልብ ንስሐቸው በተግባር ሲገለጥ ደግሞ ለይቅርታ እንቀመጣለን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment