Tuesday, February 3, 2015

የቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ የግለሰቦች መጠቀሚያ መኾናቸው ተጠቆመ

  • ሬት በካሬ በሺሕዎች ዋጋ እያወጣ የቤተ ክርስቲያን በ1.50/2.00 ሒሳብ ተከራይቷል
  • ሀብቷን እና ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የኪራይ ተመን ፖሊሲ ጥናት ተጀምሯል
  • የጥቂት አድባራት ሓላፊዎች እንቅስቃሴ ጥናቱን እንዳያኮላሸው ተሰግቷል
  • የአለቆች የመኪና ሽልማት የአማሳኞች ከለላና ለብልሹነት በር የሚከፍት ነው
*       *       *
  • የኪራይ ውሎችንና ሌሎች ሰነዶችን በመደበቅ በአግባቡ ያለማቅረብ፣ የጥናቱን ዓላማ በማጣመም ተቃውሞ ለማነሣሣት መሞከር፣ የልኡካንን ስም ማጥፋትና ሥራውን ማጥላላት ከቀንደኛ አማሳኞችና የምዝበራ ሰንሰለታቸው የሚጠበቁ ተግዳሮቶች ቢኾኑም የጥናቱ ውጤት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅምና ሀብቷን የሚያስጠብቅ ነውና እንቅስቃሴውን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ግልጽ ከማድረግ ጀምሮ ችግሮችን በሓላፊነት ስሜት እየተቋቋሙ ለመሥራት አቋም ተይዟል፡፡
  • ለጥናቱ መነሻ እንደ ሞዴል ያገለግላሉ በሚል የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እና የደብረ ምሕረት ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምአብያተ ክርስቲያን ተመርጠዋል፤ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል፣ የደ/ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም፣ የደ/ገነት ቅዱስ ሚካኤል፣ ቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም፣ የጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት፣ የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅ/ገብርኤል…ለጥናቱ ከተለዩት 61 ያኽል አድባራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

*        *       *
  • በቤተ ክርስቲያን ስም የሚፈጸሙ ጥቂት የማይባሉ የኪራይ ውሎች÷ በሰበካው ቤተ ክርስቲያን ስም በቋሚ ንብረቶችና ግምታቸው ከፍተኛ በኾኑ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ውል ለመዋዋልና የገቢ ምንጭ የሚገኝበትን የልማት ሥራ ለማቋቋም በቃለ ዐዋዲው ሥልጣንና ተግባር የተሰጠው ሰበካ ጉባኤ በአግባቡ ሳያውቃቸውና ሳይወስንባቸው የጽ/ቤት ሓላፊዎች ባላቸው የጥቅም ትስስር የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
  • የቤተ ክርስቲያንን መብት አሳልፎ በመስጠትና ጥቅሟን በማስቀረት በአቋራጭ መክበርያ የኾነው የመሬትና የሱቆች ኪራይ፣ የመካነ መቃብር ጨረታና የልማት ሥራዎች ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያከማቹና ያለአቅማቸው የሚኖሩ የአስተዳደር ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን የፈጠረውን ያኽል ካህናትና ምእመናን በቃለ ዐዋዲው የታወቀላቸው መብት (የመቃብር ቦታ የማግኘት እንኳ) የሚጣስበት ኾኗል፡፡
*         *        *
(ሰንደቅ፤፲ኛ ዓመት ቁጥር ፬፻፹፯፤ ረቡዕ፣ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
Head of EOTC Patriarchate
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ገዳማትና አድባራት÷ የገቢ ማስገኛ ምንጮችና የልማት ተቋማት የኪራይ አገልግሎት ከሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤያት የወሳኝነት ሥልጣንና ከሚመለከታቸው የአጥቢያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና የሀገረ ስብከቱ አካላት ዕውቅና ውጭ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ጥቅም ለአማሳኝ የአድባራት ሓላፊዎችና ጥቅመኛ ግለሰቦች ተላልፎ የተሰጠበት መኾኑ ተጠቆመ፡፡
ጥቆማው የተሰጠው፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና አንዳንድ ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማስገኘት የተቋቋመው አጥኚ ኮሚቴ ለፓትርያርኩ አቅርቦታል በተባለ የማስታወሻ ጽሑፍ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ለሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ለማምለኪያ፣ ለመካነ መቃብርና ለልማት መገልገያነት የሰጣቸው መሬቶች፣ ‹‹ለገቢ ማስገኛ›› በሚል ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርግ የዋጋ ተመንና ሀብቷን ለጥቅመኞች አሳልፎ በሚሰጥ የውል ዘመን ለግለሰቦች እየተከራዩ ስለመኾኑ በጽሑፉ ተመልክቷል፡፡
ተከራይ ግለሰቦች መልሰው በውድ ገንዘብ እያከራዩ ከፍተኛ ጥቅም በማጋበስ ላይ እንዳሉ ጨምሮ የገለጸው ጽሑፉ፣ በአድባራትና ገዳማት ከመሬት፣ ከሕንፃና ከሌሎች ኪራዮች ጋራ ተያይዘው የሚገኙ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስቧል፡፡ በይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አጥኚ ኮሚቴው የቀረበው የማስታወሻ ጽሑፍ ባለፈው መስከረም ወር በቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል ችግሮቹ በዝርዝር እንዲጠኑ በፓትርያርኩ አማካይነት ትእዛዝ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
ችግሩን በአስተዳደር ጉባኤው የተወያየበት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት፣ ጉዳዩ ‹‹አሳሳቢና በሀገረ ስብከቱ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት ዘንድ ሰፍኖ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ›› መኾኑን በመገምገም በጥልቀት አጥንቶ የሚያቀርብ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማቋቋሙ ተጠቅሷል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ እና የዕቅድና ልማት መምሪያዎች ዋና ሓላፊዎችን እንዲኹም የሀገረ ስብከቱንና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችን ያካተተው ኮሚቴው ከታኅሣሥ መባቻ አንሥቶ፣ የጥናቱን ዕቅድና በጥናቱ መካተት የሚገባቸውን ከስድሳ በላይ አብያተ ክርስቲያናት በመለየት በጥናት ማስፈጸሚያ ስልቱ መሠረት ወደ ሥራ መግባቱ ተዘግቧል፡፡
የገዳማትና አድባራት መሬቶች፣ ሕንፃዎች፣ የቀብር ማስፈጸምና የመካነ መቃብር ሥራ እንዲኹም ሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትጠቀምበት አገባብ አገልግሎት ላይ የሚውሉበትን ኹኔታ ማመላከት የኮሚቴው ዋነኛ ዓላማ ሲኾን የሚከራዩበትን ዋጋ፣ የተከራዩበትን ጊዜና የውል ዘመን የመሳሰሉ ዝርዝር ጉዳዮችን በመፈተሽ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዘላቂ ጥቅም የሚሰጡባቸውን መንገዶች ማመቻቸት ጥናቱ የሚያተኩርበት ግብ እንደኾነ በማስፈጸሚያ ስልቱ ተዘርዝሯል፡፡
ጥናቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነትና በሓላፊነት ስሜት እንደሚሠራ ኮሚቴው አስታውቆ÷ የጥናቱ አፈጻጸም ከግኝቶች፣ ተመክሮዎችና ተግዳሮቶች በመነሣት ወቅቱንና የአሠራር ሒደቱን ያማከለ ማሻሻያ እንደሚደረግና ለዚኽም የማስፈጸሚያ መርሐ ድርጊቱን ለሚመለከታቸው አካላት አስቀድሞ በመላክ ግብረ መልስ የመቀበያ ጊዜ ማስቀመጡን ገልጧል፡፡
የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ጸሐፊዎችና ሒሳብ ሹሞች ኮሚቴው በየአጥቢያው በመገኘት የሚያነጋግራቸው ዋነኛ አካላት ሲኾኑ ልኡካኑ የማጣራት ሥራውን በሚያከናውኑበት ወቅት ለጥናቱ የሚረዱ ሰነዶችን በማቅረብ ለተልኳቸው መቃናትና መሳካት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ፤ የጥናቱ ውጤት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤና ለቅዱስ ሲኖዶስ በየደረጃው ቀርቦ ተገቢው ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስም አጥቢያዎች አዲስ የኪራይ ይኹን የግንባታ ውሎች ከመፈጸም እንዲታቀቡ ከሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በየሰበካዎቹ አድራሻ በተጻፈ ደብዳቤ ትእዛዝና መመሪያ መተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ብሥራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት
ከጥናቱ ሞዴል አድባራት አንዱ የኾነውና በቀንደኛው አማሳኝ የጥቅም ትስስርና ምዝበራ ሳቢያ ቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ንብረትነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባውና ደብሩም ባለዕዳ የኾነበት የደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል ት/ቤት
ጥናቱ በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች ደረጃና በግል ንግድ ላይ የተሠማሩ ጥቅመኞችን የሚያስቆጣ ስለመኾኑ እንደ ስጋት የለየው ኮሚቴው÷ ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የልኡካኑን ስም የማጥፋት፣ በተለይም ከመሬትና መሬት ነክ ከኾኑ ጉዳዮች ጋራ ተያያዥነት ያላቸው ግለሰቦች የጥናቱን ዓላማ በአግባቡ ባለመረዳትና በማጣመም ሥራውን የማጥላላት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማነሣሣት የመሞከር፣ የኪራይ ውልና ሌሎች ሰነዶች በአግባቡ ያለማቅረብ፣ ጠፍተዋል በሚል ሰበብ የመደበቅ፣ የተፈላጊ አካላት ተሟልተው ያለመገኘትና መሰል ተግዳሮቶች ሊገጥመው እንደሚችል ታሳቢ አድርጓል፡፡
ይኹንና የጥናቱ ውጤት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚጠቅምና ሀብቷን የሚያስጠብቅ መኾኑን በመገንዘብ የተጣለበትን ሓላፊነት በብቃት ለመወጣት መወሰኑን ያስታወቀው ኮሚቴው፣ እንቅስቃሴውን በምዕራፎች በመገምገም ሒደቱን በብዙኃን መገናኛ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ግልጽ ከማድረግ ጀምሮ ታሳቢ ተግዳሮቶቹን የሚቋቋምባቸውን ስልቶችና አሠራሮች በዝርዝር መንደፉን አመልክቷል፡፡ አኹን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተወሰኑ ገዳማትና አድባራት መነሻነት የሚካሔደውና ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚቀርብ የሚጠበቀው ጥናት ውጤት፣ ለአማሳኝ ሓላፊዎችና ግለሰቦች የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያን የመሬት አጠቃቀምና የኪራይ ተመን የተመለከተ ወጥ ፖሊሲ ለማውጣት በግብአት የሚያገለግልም ነው ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ለአለቆች እየተበረከተ የሚገኘው የመኪና ሽልማት፣ ለአማሳኞች ከለላ የሚሰጥና ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት ነው በሚል በአስቸኳይ እንዲቆም በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መታዘዙ ተሰምቷል፡፡ መረጃው እንደሚጠቁመው፣ልማታዊ ናቸው በሚል መኪና ለአለቆች የሚሰጥበት የሽልማት ሥነ ሥርዓት÷ የሥራ አፈጻጸማቸው ያልተገመገመበትና በሽልማቱ ጉዳይ ግልጽ መመሪያ በሌለበት ኹኔታ የተፈጸመ ነው፡፡
‹ልማታዊ አባት› ስም ሕዝበ ክርስቲያኑ ገንዘብ አዋጥቷል እየተባለ የቤተ ክርስቲያን ጥሪት ለሽልማት የሚውልበት አሠራር እንዲቆምናየአጥቢያዎች የራስ አገዝ ‹ልማት› የምዝበራ ሽፋን ከመኾን እንዲገታ በፓትርያርኩ ተሰጥቷል የተባለው ትእዛዝ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሀገረ ስብከቱ በጻፉት ደብዳቤ ተፈጻሚ እንዲኾን መመሪያ የተላለፈበት ሲኾን አፈጻጸሙ የሚገኝበትን ኹኔታ በማጣራት ዝርዝር ውጤቱን ማቅረብ የዚኹ አጥኚ ኮሚቴ ተልእኮ አካል እንደኾነ ታውቋል፡፡
source: Hara Zetewahedo

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment