Friday, November 1, 2013

የምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት ይካሄዳል: የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ

  • ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ለሊቃውንት ጉባኤው ትእዛዝ ሰጠ
  • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
  • ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው[የአየር ሽፋኑ]ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
  • ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩእናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
Holy SynodTikmit Meeting
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ቆጠራ ለማካሄድ ከብር 29 ሚልዮን በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡን መዘገባችን የሚታወስ ሲኾን ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት የሚካሄደውን ቆጠራ ክንውን በቀጣይ የምንመለከተው ይኾናል፡፡


በተያያዘ ዜና፣ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልኾነውን፣ በማስመሰል የሚነገረውንና የሚጻፈውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመኾኑም እውነተኛውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይኾን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሊቃውንት ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት በምልአተ ጉባኤው ላይ የተነበበውንና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጀውን የመነሻ ጽሑፍ አብራርቶ፣ አስፍቶና አምልቶ ለግንቦት፣ ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስበቅርቡ በተካሄደው ፴፪ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፥ ኢትዮጵያ ከአይሁድ በፊት ጀምሮ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንታ መኖሯን፣ ክርስትናም ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስቶስ ባረገበት ዓመትና ቅዱሳን ሐዋርያት ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት በ፴፬ ዓ.ም. መኾኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት በማስረዳት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ጋራ መጠያየቃቸው ይታወሳል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት የጀመረውንና ለዐሥር ቀናት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው ባለ28 ነጥብ መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አካትቷል፡-
  • ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሞያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድየታየው የሥራ መዋቅር ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም አይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲኾን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ ፳፻፭ ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኮሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊ እንደመኾኗ ኹሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ኾነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሞያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጎም በሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት የታደለ ሲኾን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ፳፻፮ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሄድበት ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
  • በውጭ አገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋራ ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
  • ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ኹኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመኾኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለኾነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋራ ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም. ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፡-
1.  ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ – የምዕራብ ሸዋ /ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
2.  ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል – የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፣ የሕንፃዎችና   ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይሓላፊ
3.  ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ – የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመምረጥ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅተስማምቶ ወስኗል፡
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕልና ኪነ ጥበብ ቅርሶችና ሀብቶች ባለቤት መኾንዋ የታወቀ ስለኾነ፣ የእነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መጻሕፍት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሕንፃዎች፣ የቋንቋ በአጠቃላይም ብሔራዊው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቷ በሕግ ይከበር ዘንድ በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ  ተከታታይነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ፤
  • የአብነት ትምህርት ቤቶችንና የካህናት ማሠልጠኛ ማእከላትን፣ በጥንታዊነታቸውና በታሪክ መዘክርነታቸው ዕውቅና ያላቸውን ገዳማት፣ አሳዳጊ አልባ ዕጓለማውታ ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበትንና ሴቶች መነኰሳዪያት በምናኔ የሚኖሩባቸውን ገዳማት በበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ የታመነበት ስለኾነ፣ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል በጀት በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር ተጠንቶ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል መመሪያን ሰጥቷል፤ አሁንም በድጋሚ መምሪያውን አጽንቷል፡፡
  • ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ዘርፍ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴ በማእከልም ኾነ በየአህጉረ ስብከቱ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
  • የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅትን በተመለከተ በሚፈርሱ ቤቶች ምትክ ቸል ሳይባል በትጋትና በንቃት የመልሶ ማልማቱ የሕንጻ ግንባታ ለማካሔድ የሚያግዝ ገንዘብ ማግኘት እንዲቻል ለየአህጉረ ስብከት፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ላሉ ድርጅቶች የአክስዮን ሽያጭ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
  • የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሦስቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች በጀታቸው ተጠቃሎ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ እየኾነ በጀታቸውንም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየበጀተ እንዲከፍል ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ ከዚህም ጋራ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሥር የሚተዳደረው ከኮሌጁ ጋራ ተያይዞ የሚገኘው አዲሱ ትልቁ ሕንጻ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሥር ኹኖ የሕንጻዎቹ ወርኃዊ የኪራይ ገቢም በሕጋዊ መንገድ እንዲሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
  • በጥንታዊቷ፣ በታሪካዊቷ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በመሠራት ላይ ያለው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታን አስመልክቶ ከዓቢይ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ በመነጋገር በቀጣይ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ያስቀመጠ ከመኾኑም በላይ ለጊዜው ለተቋራጩ ብር 5‚000‚000 (አምስት ሚልዮን ብር) እንዲሰጠውና የቆመው የግንባታ ሥራ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡
  • የጣራ ቂርቆስ ገዳም አንጡራ ሀብት የኾነው መስቀለ ያሬድ ተሰርቆ ወደ ውጭ ተወስዶ ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ስለሚገኝ ገዳሙ መስቀሉ እንዲሰጠው በጽሑፍ በመጠየቁ እንዲሰጥ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ከጊዜ ብዛት የተነሣ ውኃ በማስገባቱ እድሳት የሚያስፈልገው ስለኾነ የእድሳቱም ጥናት በመቅረቡ የካቴድራሉ ሕንጻ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና የሀገር ቅርስ እንዲሁም የቱሪስቶች መዳረሻ በመኾኑ የውስጥና የውጭ ቁመናው እንደያዘ በጥንቃቄ እድሳቱ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • የ፴፪ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውሳኔና የጋራ መግለጫ የ፳፻፮ ዓ.ም. የሥራ መመሪያ እንዲኾን በምልአተ ጉባኤው ጸድቋል፡፡
  • ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ውስጠ ደንብ ተጠንቶ የቀረበው መመሪያ ጸድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡
  • በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጠንቶ እንዲቀርብ ስለታዘዘው የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ደንቡን እንዲያጠና የተመደበው ኮሚቴ ጥናቱ ለጊዜው ያልደረሰለት መኾኑን ስለገለጸ ለ፳፻፮ ዓ.ም. የግንቦት ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ጥናቱ ተጠናቆ እንዲቀርብ ጉባኤው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
  • በጉጂ ዞን ነገሌ ቦረናና የሲዳማ ዞን አህጉረ ስብከትን በተመለከተ በሁለት ተከፍለው ያለመግባባት ችግር ፈጥረዋል በሚል የተነሣው ሁከት ዓመታትን ካስቆጠረ በኋላ ችግሩን የፈጠሩት የሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ በዕርቅ እንዲፈጸም ጥያቄ በማቅረባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የዕርቀ ሰላሙን ሂደት የተቀበለ በመኾኑ እቦታው ላይ ተገኝተው ዕርቀ ሰላሙን የሚያወርዱ ብፁዓን አባቶችን ሠይሟል፤
1.  ብፁዕ አቡነ ማትያስ – የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
2.  ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ – በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳትና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳ
3.  ብፁዕ አቡነ ሉቃስ – የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳሳት፤
በመኾን ስምምነቱንና ዕርቀ ሰላሙን አስፈጽመው የመጨረሻ የዕርቁን ሰነድ ለጉባኤው እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment