Friday, July 5, 2013

በሙስና የተጠረጠሩት የመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የሓላፊነት ምደባ ታገደ

ቋሚ ሲኖዶስ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ የመደባቸው መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከሙስና ተግባር ጋራ በተያያዘ በቀረበባቸው አቤቱታ ምክንያት የፈቀደላቸው ምደባ እንዲታገድ ማድረጉ ተገለጸ፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና በሥሩ ለሚገኙ ልዩ ልዩ መምሪያዎችና ድርጅቶች ባካሄዳቸው ምደባዎች መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊነት ወደ ውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተዛውረው እንዲሠሩ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡
ይኹንና መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው በቆዩባቸው ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የቅርስ ማሸሽ ተግባራት ስለ መፈጸማቸው ልዩ ልዩ አካላት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩና ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የክሥ አቤቱታዎችን በማቅረባቸው በውጭ ግንኙነት መምሪያ የተፈቀደላቸው የዋና ሓላፊነት ምደባ ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑ ተገልጧል፡፡
Dn. DANIEL SACKED FROM HIS POSITIONበቁጥር 1/1188/2005 በቀን 14/10/2005 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ተፈርሞ የወጣውና በአድራሻ ለመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የተጻፈው ደብዳቤ፣ መ/ር ዳንኤል ላለፉት ሦስት ዓመታት ከቆዩበት የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ መነሣታቸውን ያስታወቃቸው ሲኾን በአስተዳደር መምሪያ የሠራተኞች አስተዳደር ዋና ክፍል ክፍል ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በመግለጽ ሲሠሩበት የነበረውን ቢሮ፣ ወንበር፣ ጠረጴዛና ዶኩመንቶች በቦታው ለተመደቡት መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል በሚመድበው አረካካቢ እንዲያስረክቡ አዝዟቸዋል፡፡


ሐራዊ ምንጮች ከመንበረ ፓትርያሪኩ አካላት እንደተረዱት፣ በከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና ቅርስ የማሸሽ የሙስናና ምዝበራ ተግባራት ተጠርጥረው ከሓላፊነት በተነሡት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ላይ የክሥ አቤቱታ ያቀረቡባቸው÷ በማእከላዊ ዞን ትግራይ ሀ/ስብከት የእንዳአባ ገሪማ ገዳም፣ የመንበረ ፓትርያሪክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ጠቅላላ አገልግሎት እንዲሁም ገዳሙንና የመንበረ ፓትርያሪኩን ሙዝየም በገንዘብ የረዳው የፈረንሳይ ኤምባሲ ናቸው፡፡
እንደ ዜናው ምንጮች ማብራሪያ፣ የመንበረ ፓትርያሪኩን ሙዝየም በዘመናዊ መሣርያዎች ለማደራጀት የፈረንሳይ ኤምባሲ ከሩብ ሚልዮን በላይ ብር በርዳታ ሰጥቶ ነበር፡፡ ራሳቸውን ገንዘብ ያዥ ራሳቸውን ዕቃ ግዥ በማድረግ የርዳታ ገንዘቡን አወጣጥ በብቸኝነት ተቆጣጥረዋል የተባሉት መ/ር ዳንኤል፣ ያለፕሮፎርማ በፈጸሟቸው ግዥዎች የግል ጥቅማቸውን አካብተውበታል፡፡ የመንበረ ፓትርያሪኩ ሙዝየም ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባሰሙት አቤቱታቸው፣ ‹‹በሙዝየሙ ስም የመጣው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለተባለው ዓላማ አልዋለም፤››ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ያለፕሮፎርማ በተከናወነው ዕቃ ግዥ ከተፈጸመው ሙስና በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩን ለመመዝበር በተደረጉት ስልታዊ ሙከራዎችና ደብዛቸው በጠፉት ዕቃዎች መነሻነት ጥብቅ የቅርስ ቆጠራና ቁጥጥር ሊካሄድ እንደሚገባ ምንጮቹ ያሳስባሉ፡፡ ለቀድሞው ፓትርያሪክ በስጦታ የተበረከተና በሙዝየሙ የተቀመጠ ዘመናዊ ድጅታል ካሜራ በኮምፒዩተር አካል ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን በምሳሌነት የሚጠቅሱት ምንጮቹ፣ ከመ/ር ዳንኤል ጋራ በቅርበት የሚሠሩት የሙዝየሙ ድጅታል ክፍል ሓላፊ አቶ ያዕቆብ ታደሰና የሙዝየሙ አስጎብኚ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬ እንደ መ/ር ዳንኤል ሁሉ አብረው ተጠያቂ መኾን እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡
በተለይም በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በሹፌርነት ሲሠሩ የመኪና መለዋወጫዎችን ሲሰርቁ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የተባረሩት፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በፈጸሙት ማጭበርበር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማኔጅመንት ኮሚቴ በዲስፒሊን የተቀጡትና የኮንትራት ቅጥራቸው እንዲቋረጥ የተወሰነባቸው፣ ‹‹አጥማቂ ነኝ›› በሚል በርካታ ሴቶችን በማነወር የሚታወቁት የሙዝየሙ አስጎብኚ፣ ‹‹ከጥፋታቸው አይማሩም፤ ያዳበሩት የእጅ አመልም ለቀጣይ የሙዝየሙ ደኅንነት ስጋት ያደርጋቸዋል፤›› ይላሉ ምንጮቹ፡፡
በመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ላይ አቤቱታ ያቀረበባቸው ሌላው አካል በማእከላዊ ዞን ትግራይ ሀ/ስብከት የሚገኘው የጥንታዊው እንዳባገሪማ ገዳም አስተዳደር ነው፡፡ ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ከሄዱት የገዳሙ አበምኔት ለመረዳት እንደተቻለው፣ የፈረንሳይ ኤምባሲ የማኅበራዊ ልማት ፈንዶች በለገሠው ርዳታ የተቋቋመውንና ግንቦት፣ ፳፻፬ ዓ.ም የቀድሞው ፓትርያሪክና የፈረንሳይ አምባሳደር በተገኙበት የተመረቀውን የገዳሙን ሙዝየም በዘመናዊ መሣርያዎች ለማደራጀት፣ ቅርሶቹን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግና ለካታሎግ ሥራዎች የብር 800,000 ድጋፍ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይኹንና ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ከብር 300,000 የማይበልጥ ሲኾን የቀረው ገንዘብ የት እንደገባ እንዳልታወቀ ተዘግቧል፡፡
የርዳታ ገንዘቡን በገዳሙ ስም ተቀብለው በብቸኝነት ሲቆጣጠሩ ነበር የተባሉት መ/ር ዳንኤል የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን በማስተባበል ብር 600,000 ብቻ እንደኾነ ተናግረዋል ቢባልም የገዳሙ አስተዳደር ከኤምባሲው ጋራ ባደረገው ግንኙነት የተለገሠው ገንዘብ ብር 800,000 እንደነበርና ገዳሙ ተጠቃሚ ባልኾነበት ኹኔታ መመዝበሩን በመግለጽ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማመልከቱ ታውቋል፡፡
አቤቱታውን መነሻ በማድረግ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ጋራ በጽ/ቤታቸው ከተወያዩበት በኋላ ጉዳዩ በፍትሕ አካል በሚታይበትና መ/ር ዳንኤልን ጨምሮ ተባባሪዎቻቸው በሕግ ስለሚጠየቁበት አግባብ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት ክፍል መመሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡ በድኅረ ምረቃ የውጭ ትምህርት ዕድል ሰበብ ከሀገር ለመውጣት መዘጋጀታቸው የሚነገርላቸው መ/ር ዳንኤል አምባሳደሯ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ በተነጋገሩበት ወቅት እንዲገኙ ተፈልገው የነበረ ቢኾንም ዳናቸውን አጥፍተው መቆየታቸው ተገልጧል፡፡
መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራና ቅርስ ማሸሽ ተግባራት ተጠርጥረው ከሓላፊነት በተነሡበት የቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ በነበሩበት ወቅት በእጃቸው እንዳስገቧቸው ከሚነገሩት ሀብቶች መካከል፣ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ በኾኑት ጻድቁ አቡነ ገሪማ (አባ ይሥሓቅ) በግእዝ ቋንቋ ከተጻፈው ወንጌል ላይ በድጅታል ካሜራ የተነሡ፣ እንደ ዣክ መርሴ (Jacques Mercier) ያሉ የጥቅም ተባባሪዎቻቸው ድረ ገጽ ከፍተው በውድ ዋጋ የሚቸበችቧቸው በርካታ ቅዱሳት ሥዕላትና የብራና ጽሕፈቱ ቅጠሎች ይገኙበታል፡፡Garima Gospel
በ፮ው መ.ክ.ዘ በዐፄ ገብረ መስቀል በተመሠረተውና ከዐድዋ በስተምሥራቅ 5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የእንዳገሪማ ገዳም በደጋጎቹ አበው መነኰሳት ብልሃትና መሥዋዕት ተጠብቆ የቆየን የአቡነ ገሪማ ግእዝ ወንጌል የጥንተ ክርስትናችን ምስክር ነው፡፡ ከፍየል ቆዳ በተሠሩና በሁለት ቅጾች በተጠረዙ የብራና ወንጌላት (በቅርሱ ጥገና ላይ የሠሩ ባለሞያዎችና ቅርሱን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች Garima – 1 እና Garima – 2 ይሏቸዋል) ላይ፣ የአራቱ ወንጌላውያን ሥዕለ ገጾችና ሥነ ጥበባችንን በጉልሕ የሚያሳዩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ከ1500 ዓመት በፊት በተሣሉበት አኳኋን ቁልጭ እንዳሉ ተጠብቀው መገኘታቸው የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቀልብ ስቧል፡፡
የብሪታንያ በጎ አድራጊ ከኢትዮጵያ ሄሪቴጅ ፈንድ ጋራ በመተባበር በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አርኬዎሎጂ ላብራቶሪ በብራና ወንጌላቱ ቅጠሎች በተካሄደው የካርቦን አቆጣጠር ምርመራ (Carbon 14 test)÷ Garima – 2 ከ390 – 570 ድኅረ ልደተ ክርስቶስ፣ Garima – 1 ከ550 – 660 ድኅረ ልደተ ክርስቶስ እንደተጻፉ በመረጋገጡ የጻድቁ አቡነ ገሪማ ግእዝ ወንጌል÷ ከዓለም ቀደምቱ ጽዱል ክርስቲያናዊ የእጅ ጽሑፍ (The world’s earliest surviving illuminated Christian manuscripts) ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህም የተነሣ በቅ/ሥዕላት የተደገፈውና የተዋበው የአቡነ ገሪማ ግእዝ ወንጌል አጻጻፍ÷ ለግእዝ መልክአ ፊደል (calligraphy)፣ ለግእዝ ቋንቋ ታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ አንድምታ ጥናት ከፍተኛ ሀብት እንደኾነ፣ በኅዳጉ የሰፈሩት የታሪክ መረጃዎችም ለታሪክ ጥናት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው፣ የዘመኑን የመጽሐፍ ድጒሰትና ጥረዛ ጥበብ ለማጥናት እንደሚረዳ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡
The Manuscript before and after restoration
የአቡነ ገሪማ ወንጌል
ከጥገና በፊትና በኋላ
ቅርሱ እ.አ.አ በ1960፣ በ2006 እና በ2012 ጥገና እንደተካሄደለት የተዘገበ ሲኾን በ2012 የብሪታንያ በጎ አድራጎት ከኢትዮጵያ ሄሪቴጅ ፈንድ ጋራ ባካሄደው ጥገና በ1960ው ጥገና ወቅት የተጎዳው የብራናው ጥራዝና የተዘበራረቁ ገጾች እንዲስተካከሉ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በቀድሞው ፓትርያሪክ ተወክለው በዚያው በገዳሙ የተካሄደውን የጥገና ሂደት ይረዱ የነበሩት የቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ መ/ር ዳንኤል ከበጎ አድራጊው አካል በገዳሙ ስም እስከ ብር መቶ ሺሕ መቀበላቸው ይነገርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን ከውጭ አገር እየመጡ በቅርሶች ላይ ጥናት ለማካሄድ የመምሪያቸውን የድጋፍ ደብዳቤ ከሚጠይቁ የውጭ ዜጎች ከብር 25,000 – 50,000 ጉቦ እንደሚጠይቁ የጀርመን ተመራማሪዎችን አቤቱታ ዋቢ ያደረጉ የዜናው ምንጮች አስረድተዋል፡፡
መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊነት የተፈቀደላቸውን የዋና ሓላፊነት ምደባ ያሳጣቸውና ሰሞኑን የተሰማው የእንዳባገሪማ አስተዳደርና የለጋሹ የፈረንሳይ ኤምባሲ የክሥ አቤቱታ÷ በተለይ በዘመናዊ የቅርስ አጠባበቅ መንገድ ይደራጃል ቢባልም አጥጋቢ ሥራ ባልተሠራበት የገዳሙ ሙዝየም የቅርስ ማሳያ ሣጥኖች ዝግጅትና ካታሎግ ሥራ፣ የጥንታዊውን ገዳም ታሪክና የጻድቁ አቡነ ገሪማን ወንጌል በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታቅዶ በትግርኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ከሚጻፈው መጽሐፍ ዝግጅትና ለአዘጋጆቹ የሚገባው ክፍያ በአግባቡ ካለመፈጸሙ ጋራ የተያያዘ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ከተጋበዙት በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ጋራ የመ/ር ዳንኤል የረጅም ጊዜ የጥቅም ተካፋይ ፈረንሳዊው ዣክ መርሴ አብረው በመምጣት የአቤቱታው ተባባሪ መኾናቸው የዜናውን ምንጮች በእጅጉ አስገርሟል፡፡ አጋጣሚው ከቅርስ ጥናት ጋራ በተያያዘ በሥልጠና የተደገፈ ትምህርት ይኹን ሞያ ሳይኖራቸው  Ethiopian Art” ኤክስፐርት ነኝ በሚል ብቻ ቅዱሳት ሥዕሎቻችንንና የብራና መጽሐፎቻችንን ሲነግዱባቸው የቆዩት አወዛጋቢ ግለሰብ፣ በጥቅመኛ አድራጎታቸው ለመቀጠል ያላቸውን እስስትነት የሚያሳይ በመኾኑ መንበረ ፓትርያሪኩ በቃኽ ሊላቸውና ሊያጋልጣቸው እንደሚገባ በአጽንዖት ተመልክቷል፡፡
ፈረንሳዊው ዣክ መርሴ በጥናትና ምርምር ስም ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሱባቸው ባለፉት ዐሥር ዓመታት፣ በተለይ የትግራይን ገዳማት አብዛኞቹን ቅዱሳት ሥዕላት ድጅታይዝድ በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ በማትኾንበት መልኩ ድረ ገጽ ከፍተው ለግላቸው እያተረፉበት መኾኑ በቅጡ ሊጤን እንደሚገባው ባለሞያዎች ያሳስባሉ፡፡
ቅዱሳት ሥዕሎቻችንን በድጅታይዜሽን መሰነዱና በድረ ገጽ ማስተዋወቁ ጥናትና ምርምር በዘመናዊ መንገድ የሚካሄድበትን ኹኔታ ለማመቻቸት፣ የስፍራውን የቱሪዝም መስሕብነት ለማስተዋወቅና ለማጠናከር እንዲሁም ለቅርስ አጠባባቅ ከፍተኛ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አይካድም፡፡ እኒህ ጠቀሜታዎች ግን ተገቢነት የሚኖራቸው ቤተ ክርስቲያናችን በተቋም/በማእከል ደረጃ የድጅታይዚንግ ቴክኖሎጂው ባለቤትና ተቆጣጣሪ የምትኾንበት  አሠራር ሲረጋገጥ ነው፡፡ በጥቂት ግለሰቦች አቅም የተወሰነው የቴክኖሎጂው አጠቃቀም እውነታ ግን ይህ ባለመኾኑ ቤተ ክርስቲያን በገዛ ሀብቷ የሚገባትን ጥቅም አለማግኘቷ ያሳዝናል፡፡ የቴክኖሎጂው አጠቃቀም አሁን በሚታየው ግለሰባዊ አሠራር ከቀጠለም የቅርሶቻችንን መካናዊ፣ ግዘፋዊ/አካላዊ አስፈላጊነት በሂደት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው ጥርጥር የለውም፡፡
የመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ጥቅመኛ ወዳጅ ዣክ መርሴ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሀብት የግል ጥቅምና ዝናቸውን ያካብታሉ እንጂ የአገራችን ጥንተ ሥልጣኔ መንኳሰሱ አይገዳቸውም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንጡራነት ያፈለቋቸውና ልዩ መታወቂያቸው የኾኑት ቱባ/አገራዊ ጥበቦች ከሌሎች ጋራ በሚደረግ መስተጋብር/መወራረስ ከዳበሩት ለይቶ ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ለመስጠት አይሹም፡፡
ዣክ መርሴ ስለ ቅ/ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ ባሳተሙት የፎቶ ስብስብ መጽሐፍ አብያተ መቅደሱን ያነፁት ግብፃውያን እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ ፎቶ – መጽሐፉ ከኅትመቱ በፊት የደረሰው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና የባለሥልጣኑ ባለሞያዎች ግለሰቡ እይታቸውን እንዲያጤኑት ለመጽሐፉ ግምገማ ባልሥልጣኑ በጠራው ስብሰባ ቢያሳስቧቸውም መጽሐፉን አሳትመው ከማስመረቅ አልተከለከሉም፡፡ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተመዘገበ ሀብት ዣክ መርሴ የመሰላቸውን አቋም የመውሰድ ‹ምሁራዊ› ነጻነታቸው የተጠበቀ ቢኾንም በቅንነት ምክር የለገሷቸውን ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ግን ‹‹ሐበሻ ምቀኛ ነው›› ብለው በገዛ አገራቸው ለመዝለፍ አለማፈራቸው በእውነቱ ያስቆጣል፡፡
Abba Garima Museum
የእንዳባገሪማ ገዳም የአቡነ ገሪማ ሙዝዬም
ዣክ መርሴ ከግብፃውያን ልዩ ፍቅር ያላቸው ወይም ልዩ ተልእኮ የተሰጣቸው ይመስላሉ፡፡ “Illustrated Abba Garima Museum”በሚል ርእስ ለኅትመት ባዘጋጁትና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቀርቦ ለዝርዝር እይታ ለባለሞያዎች በተመራው ባለ 27 ገጽ የጽሑፍ ረቂቅ ላይ (በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት አካባቢ ተጽዕኗቸውን ለማጠናከር ያልተቋረጠ ጥረት የሚያደርጉት ‹‹የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ›› ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃም በዚህ ዝግጅት ውስጥ አሉበት)÷ ለጻድቁ አቡነ ገሪማ ሥዕላዊ ወንጌል (the illustrated Gospel of Abba Garima) ብርቅዬነት፣ ኢትዮጵያዊ መሠረቶችና መልኮች ዕውቅና ለመስጠት ሲተናነቃቸው ይታያል፡፡ በምትኩ እንደ ዣክ መርሴ እምነት÷ በቆብጦች፣ ማሙሉክ ግብፆች፣ ፍልስጥኤማውያንና ቤዛንታይን ተጽዕኖ የተዋጡት የአቡነ ገሪማ ወንጌሎች በሌሎች ዘንድ የማናገኛቸው ከነበሩበት በመጥፋታቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ በመኾናቸው ብቻ አይደለም፡፡
ዣክ መርሴ ለ‹ጥናትና ምርምር› በሚሄዱባቸው ቅዱሳት መካናት የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዐት ያለማክበር ንቀት ይታይባቸዋል፡፡ በገዛ ሀብታችን መነገዳቸው ሳያንስ ዘለፋቸውን ያተረፍንበትን የቅ/ላሊበላ ፎቶ – መጽሐፍ ግብአት ለመሰብሰብ ወደ ቅ/ላሊበላ የቤተ ጎልጎታ እና ቤተ ማርያም አብያተ መቅደስ በሄዱበት ወቅት ያለማዕርጋቸው፣ ከነጫማቸው ወደ መቅደሶቹ ለመግባት ተደፋፍረዋል፡፡ በቤተ ጎልጎታ ከ፲፮ው መ.ክ.ዘ ጀምሮ በአገር ባህል ሸማ ተሸፍና የምትኖረውንና ምእመን የማይዳስሳትን ‹‹ዓምደ ብርሃን›› ተገልጣ ፎቶ ካላነሣኹ በሚል የደብሩን ሓላፊዎች አውከዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ በቤተ ማርያም መቅደስ ቅ/ላሊበላ ያሠራውን የቅድስት ሥላሴ መንበር ፎቶ ካላነሣኹ ያሉበትን ትምክህት የተከላከሉትን የደብሩን ሊቀ ገበዝና የወቅቱን መምህር በተደጋጋሚ እየተመላለሱ በመፈታተናቸው በሕዝቡ እንቅስቃሴ ከከተማው ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ተመልሰው የወቅቱን የቅ/ላሊበላ ደብር አለቃ በቀድሞው ፓትርያሪክ ‹‹የትእዛዜን አልፈጸምኽም›› ሰበብ ከደብሩ እልቅና በማስነሣት ቢሳካላቸውም በእጅጉ የጠላቸው የቅ/ላሊበላና አካባቢው ምእመን ግን ዛሬ ዣክ መርሴን የሚፈልጋቸው ለብርቱ ቅጣት ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ወደ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ መንግሥት ያለፈቃድ ገብተው የቅዱሳት ሥዕላቱን ደኅንነት የሚያሰጋ ጥፋት የፈጸሙት ዣክ መርሴ፣ ቅርሱን ጠብቆ ባቆየው ምእመን ቅንዓት ተመልሰው አገሩን እንዳይረግጡ ኾነው ከስፍራው ተባረዋል፡፡
ጥቅመኝነትና ባዶ ትምክህት የጋረዳቸው ዣክ መርሴ ከዚያ በኋላ የቀራቸው አቅም፣ ከላይ እንደገለጽነው ‹‹ላሊበላን ያነፁት ግብፆች ናቸው››የሚለውን መጽሐፍ አሳትሞ በምሁራዊ መሰል ቀሳጢነት (intellectual dishonesty) መበቀል ነበር፡፡ ክፉ መንፈሳቸውን የተረዱት የጀርመን ባህል ተቋም ሓላፊዎች በዣክ መርሴ የተጠየቁትን የፎቶ – መጽሐፍ ማስመረቂያ አዳራሽ የነፈጓቸው ሲኾን የጣልያን ባህል ማእከል መተባበሩ ደግሞ ያስተዛዝባል፡፡ ሰሞኑን የአቡነ ገሪማን ሙዝየምና ወንጌሎች በማስመልከት ዣክ መርሴ የሚዘጋጁበት ጽሑፍም ኋላ በገዛ ዳቦዬ. . . እንዳያሰኘን ከወዲሁ ልንጠነቀቅበት ይገባል፡፡ ዛሬ ዣክ መርሴ የመ/ር ዳንኤል ከሳሽ ኾነው (መስለው) ቢቀርቡም የአለመግባባታቸው መንሥኤ ከጥቅም ክፍፍል የራቀ አይደለምና ዣክ መርሴም ከተጠያቂነት ውጭ መኾን አይገባቸውም፡፡
31ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአቋምና ውሳኔ መግለጫ፣ የቅርሳ ቅርስ ምዝገባና ጥበቃን በተመለከተ ከየአህጉረ ስብከቱ በሪፖርት የቀረቡለትን ተግባራት አወድሷል፡፡ ቅርሳቅርስና ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳት÷ የቤተ ክርስቲያን አንጡራ ሀብቶች፣ የማንነታችን ምልክቶች፣ የአባቶቻችንና እናቶቻችን መዘክሮች ስለኾኑ ጥበቃና ክብካቤው በቅርሶች ምዝገባና በሙዝየሞች ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበረታቷል፡፡ በቅርሳ ቅርስና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የታየው ዘመናዊ አደረጃጀትም ለቅርሳቅርስ አጠባበቅ አስተማማኝነት ታላቅ ተስፋ የሚታየበት ስለኾነ እንዲቀጥል አስገንዝቧል፡፡
የሚታዩት፣ የሚጎበኙት ገዳማትና ቅርሶች የቤተ ክርስቲያን መኾናቸውን ለዜና ቤተ ክርስቲያን መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ያስታወሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው÷ የንብረቶቿን አጠባበቅና አጠቃቀም በራሷ ሰዎች መሪነት እንደምታከናውንና ቅርሶቿንና መብቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዐት እንደምትዘረጋ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ምትክ በቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ በዋና ሐላፊነት የተመደቡት መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ ከፍተኛ ሓላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቀደምት ምሩቃን አንዱ በመኾን በበርካታ አጥቢያዎች በሰባኬ ወንጌልነትና በጸሐፊነት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልዩ ልዩ መምሪያዎችም በዋና ሓላፊነት የሠሩት መ/ር ሰሎሞን÷ የቴዎሎጂና የሕግ ዲፕሎማዎች ያሏቸው ሲኾን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲሁም በቱሪዝም በርካታ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ በክርስቲያን ካውንስሊንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ካገኙ በኋላ በሊደርሽፕ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ በሀገር ውስጥና በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን በማስጎብኘት ልምድ አዳብረዋል፡፡ ለቱሪዝም ሥራው የሚረዱ ሁለት መጻሕፍትንም አሳትመዋል፡፡
ዋና ሓላፊው በዚህ የትምህርት ዝግጅታቸውና በአገልግሎት ልምዳቸው መዲናዪቱን አዲስ አበባን በሚጎበኙ ቱሪስቶች ዘንድ በተሻለ እንደሚታወቁት÷ እንደ መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም፣ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙዝዬሞች ሁሉ የመንበረ ፓትርያሪኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ይዞታ በቱር ኦፕሬተሮች ታውቆ በቱር ፓኬጅ እንዲካተት፣ የሙዝዬሙን አገልግሎት ምቹ በማድረግ÷ ለተመራማሪዎች፣ ተማሪዎችና ምእመናን ያለውን መስሕብነት የመጨመር፣ የተጠቃሚዎችንና የጎብኚዎችን ቁጥር የማሳደግና የቤተ ክርስቲያናችንን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች የማስተዋወቅ ውጤታማ ጥረት ይጠብቃቸዋል፡፡ መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ፣ በአብዛኛው የሥራ ሰዓታቸው የተመደቡበትን ተቋማዊ ሓላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለራሳቸው የሚያተርፉበትን ግላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያዘወትሩት መ/ር ዳንኤል ከገጠማቸው ተምረው የተጣለባቸውን አደራና ሓላፊነት በብቃት እንደሚፈጽሙ ተስፋ ይደረጋል፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment