Thursday, May 30, 2013

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጀመረ፤ ‹‹ሙስና ቤተ ክህነት››ን ያጠፋሉ የተባሉ የእርምት ርምጃዎች ይፋ ተደረጉ

  • ሙሰኛ እንክርዳድ ሁሉ በፀረ – ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ ተለይቶ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድበታል!
  • የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር፣ ሕግና ደንብ በውጤት ተኮር ማሻሻያ ይዘጋጃል
  • ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ እስከ አጥቢያ የፋይናንስ ሥርዐቱ በዘመናዊ አሠራር ይደራጃል
  • የቤተ ክርስቲያንን ርእይና ተልእኮ የሚያሳይ የስትራተጂያዊ አመራር ሥርዐት ይነደፋል
  • በሁሉም የለውጥ ርምጃዎች የባለሞያ ምእመናን ተሳትፎ ይረጋገጣል
  • በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ለሚመዘነው የለውጥ ርምጃ በጋራ እንነሣ!
  • ‹‹በዚህ ትልቅ የሓላፊነት ወንበር ላይ ስታስቀምጡኝ÷ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ፣ የምእመናንን የልብ ትርታ እያዳመጥኹ ለእናንተ ለብፁዓን አባቶች ሳቀርብ ይኹንታውንና እገዛውን እየለገሣችኹኝ የጋራ ሓላፊነታችንን እንድንወጣ መኾን አለበት፡፡››/የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ንግግር/
ቢሮክራሲው በእጅጉ በተንዛዛውና ከሚያስፈልገው በላይ የሠራተኛ ቁጥር በተሸከመው÷ ለመንፈሳዊነት፣ ሞያና ልምድ ቦታ በማይሰጠው÷ የሰው ኀይል አመዳደቡም ከመሠረታዊ ተልእኮው ጋራ ባልተቀናጀው፣ ከዚህም የተነሣ ሙስናና ወገንተኝነት በሰፈነበት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሊወሰድ የሚገባውን የእርምት ርምጃ የሚያመላክቱ ሦስት የይኹንታ ሐሳቦችበዛሬው ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ይፋ ተደርገዋል፡፡
Abune Matyas Looking Forward
ወደፊት፤ በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ለሚመዘነው የለውጥ ርምጃ!
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ዛሬ ጥዋት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ባሏቸው መሠረታዊ የለውጥ ርምጃ ይኹንታቸው እንደገለጹት÷ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የሚታየው የሥነ ምግባር ብልሹ አሠራር ከቤተ ክርስቲያን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣም ነው፤ በምእመናን ላይ ባሳደረው ከፍተኛ ቅሬታ ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያላቸውን እምነት እያሳጣ ነው፤ አሳፋሪውና አሳዛኙ ብልሹ አሠራር ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሳይታረም ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚጥል በግልጽ እየታየ ነው፡፡
ብልሹ አሠራሩን ለማረምና ለማስወገድ፣ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀሙን ግልጽ በኾነና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማደራጀት የሚወሰደው የእርምት ርምጃ÷ የቤተ ክርስቲያንን ስምና ክብር በማስጠበቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚታደግ፣ ካህናትና ምእመናን የተባበሩበትና ተሳትፎቸው የተረጋገጠበት፣ አመራሩንም ከታሪክ ፍርድና ወቀሳ የሚያድን ሊኾን ይገባል፡፡
የፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ የመሠረታዊ ለውጥ ርምጃ ይኹንታዎች፡-



1)  የፀረ – ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ፡- ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጡ አባላት የሚገኙበት የፀረ – ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ኾኖ ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ኹኔታውን እየመረመረ፣ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ እንዲያቀርብ ማድረግና እንክርዳድ ኾነው በሚገኙት ላይ አስተማሪ የሚኾን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፡፡
2)  የአስተዳደር መሻሻል ዐቢይ ኮሚቴ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር መዋቅር የሚሠሩባቸውን ደንቦችና ሕጎች ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ጨምሮ የሚመረምርና የማሻሻያ ሐሳብ የሚያቀርብ የአስተዳደር መሻሻል ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋምና፤ አባላቱም አሁንም ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከካህናትና ከምእመናን የተውጣጡ እንዲኾኑ ተደርጎ አስተዳደሩ ለለውጥ የተዘጋጀ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማድረግና ውጤት ተኮር የኾነ ሥርዐት ለመዘርጋት የሚያስችል የማሻሻያ ጥናታዊ ሐሳብ እንዲያቀርብ ማድረግ፤ በተጨማሪም አስተዳደሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእይና ተልእኮ በግልጽ የሚያሳይ ስትራተጅካዊ አመራር ሥርዐት እንዲነድፍና የተሟላ የማሻሻያ ሐሳብ እንዲያቀርብ ማድረግ፡፡
3)  የገንዘብ አያያዝ ሥርዐት ማሻሻያ ዐቢይ ኮሚቴ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዐት ዘመናዊ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማደራጀት የሚያስችል ሥርዐት እንዲዘረጋ ለማድረግ ጥናት እንዲቀርብ ባለሞያዎች በአባልነት የሚገኙበት የገንዘብ አያያዝ ሥርዐት ማሻሻያ ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የሚሠራበትን ሥርዐት መርምሮ አንድ ወጥ የኾነ ሥርዐት ለመዘርጋት የሚያስችል ሐሳብ እንዲቀርብ ማድረግ፡፡
ሦስቱ የይኹንታ ሐሳቦች ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሂደት የሚወስኑ እጅግ አስፈላጊ ርምጃዎች ናቸው፤›› ያሉት ቅዱስነታቸው ለተግባራዊነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በቀዳሚ አጀንዳነት ይዞ፣ በቆራጥነት፣ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ እንዲያዳብረውና እንዲያጸድቀው ጠይቀዋል፡፡ በውሳኔው ተፈላጊውን ለውጥ በአጭር ጊዜ ማምጣት ባይቻልም የለውጡን መሠረት ማስቀመጥና የለውጡን አቅጣጫ መቀየስ እንደሚቻል የቅዱስነታቸው እምነት ነው፡፡
ፓትርያሪኩ÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እግዚአብሔር በልዩ አጠራሩ ጠርቶና መርጦ ያስቀመጣቸው መኾኑን በማስታወስ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ለሚታየው የአሠራር ክፍተት መፍትሔ ለማበጀት የሚካሄደው ጉባኤና ጉባኤው የሚያሳልፈው ውሳኔበእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ሁልጊዜ በሚዛን እየተመዘነ እንደሚኖር ሊዘነጋ እንደማይገባው አሳስበዋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ የመክፈቻ ንግግር ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከቱ፤His Holiness Good Governance Recommendation00His Holiness Good Governance Recommendation01His Holiness Good Governance Recommendation02His Holiness Good Governance Recommendation03

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment