Thursday, September 19, 2013

በሐሮ ወንጪ ቅ/ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ

  • መነኰሳቱ ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ነው
  • አስተዳደሩ ለመነኰሳቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም
  • ‹‹ከዚህ ቦታ ባትመጡ ይሻል ነበር፤ ብትውሉ አታድሩም!›› /ጥቃት ፈጻሚዎቹ/
Haro Wonchi Monasteryበደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ወንጪ ወረዳ ሐሮ ወንጪ ቀበሌ በሚገኘው የሐሮ ወንጪ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው ጳጉሜ ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ምሽት 5፡00 ላይ ወደ ገዳሙ ቅጽር በተወረወረው ቦምብ ነው፡፡
በገዳሙ የኪዳነ ምሕረት፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልና ቅድስት አርሴማ ታቦታት መኖራቸውን የገለጹት የገዳሙ አበምኔት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ኣብርሃ፣ የተወረወረው ቦምብ በገዳሙ ቅጽር ውስጥ ቢፈነዳም በመነኰሳቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ለዜና ሰዎች ተናግረዋል – ‹‹ቢፈነዳም እርሱ ሊቀ መልአኩ በተኣምሩ አንከባሎት ከልሎናልና ጉዳት አላደረሰብንም፡፡››

Friday, August 16, 2013

‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በእግዚአብሔር››


 ‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተሐዋርያት ርትዕት በእግዚአብሔር›› ብለን የምንታዘዘው በመላውዓለም ላለችው በእምነትና በጥምቀት አንድ ሆነን ፤ በቅዱስ ሥጋውናበክቡር ደሙ ተዋሕደን አንድ የክርስቶስ አካል በሚያደርገን ምሥጢርለሚሳተፉት ሁሉ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአንዱ አካላችን ብልቶችየሆኑት የግብጽ ክርስቲያኖችና በዚያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በታላቅመከራ መሆኗን እናስብ ፡፡ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ በሶርያ ያሉወንድሞቻችን መከራውን እንደተቀበሉ እናውቃለን፤ አሁንምበመቀበል ላይ ናቸው፡፡ ስለእነዚህ ሁሉ በእውነት ልንጸልይ ግዴታችንመሆኑን በቀኖናው የታዘዘ ቢሆንም በጸሎተ ቅዳሴያችንም ጊዜቢታወጅልንም ኅሊናችን እነርሱን ሁሉ እያሰበ መጸለይ ይገባል፡፡እንገፋለን እንጂ አንወድቅም! ክርስቲያን እንደ ሚስማር ሲመቱትየሚጠብቅ ነው-እግዚአብሔር አምላክ በሶሪያ ፤ በግብጽ ፤ በኢራቅ  እና በሌሎች የዓለም አካባቢዎች በፅንፈኞችአማካኝነት እየተሰየፉ እና እየተቃጠሉ በሰማዕትነት በክብር ላረፉ ክርስቲያን ወገኖቻችን መንግሥቱንያውርስልን!

Wednesday, August 14, 2013

“በ22 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ያስተዳደረ ሙስሊም የለም” የሙስሊሞች የተቃውሞ ድምጽ


(አንድ አድርገን ነሀሴ 5 2005 ዓ.ም)፡- ባሳለፍነው ዕለተ ሀሙስ በሙስሊሞች የበዓል እለት አዲስ አበባ በብዙ ቦታዎች በተቃውሞ ስትናጥ መዋሏን የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ኢቲቪን ሳይቀር ተቀባብለው መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ በተነሳው ግጭት ፖሊስ ብዙዎችን ማረፊያ ቤት ማጎሩም ይታወቃል፡፡ ባሳለፍናቸው 3 ቀናት ፖሊስ ጣቢያዎች የምሳ እና የእራት ሰሀን በያዙ ሰዎች ተከበው ውለዋል፡፡ በወቅቱ የታሰበበትና የተጠና ሰላማዊ ሰልፍ መሆኑን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ ፤ የባነሮቹ ተመሳሳይነት ፤ የመፈክሮቹ ይዘት ፤ ተቃውሞ የተነሳበት ሰአትና ቦታ ሰልፉ ታሰበበት መሆኑን ያመለክል ፡፡

አዲስ አበባ በለውጥ አመራር ያብባል ገና

  • በምደባ ቅር የተሰኙ ሓላፊዎች በየሆቴሉና ሬስቶራንቱ የዐመፅ ምክክር ይዘዋል
  • ‹‹የቋሚ ሲኖዶሱ ምደባ በአተገባበር በደላሎች ተጠልፏል›› የሚል ቅሬታ አላቸው
  • የረዳት ሊቀ ጳጳሱና ጽ/ቤታቸው ድርሻ የቋሚ ሲኖዶሱን ምደባ ማስፈጸም ብቻ ነው
  • በዘላቂው የሀ/ስብከቱ መዋቅር ስፍራ የሚኖራቸው በጊዜያዊ ምደባቸው ብቃት ያሳዩ ሓላፊዎችና ሠራተኞች መኾናቸው ተገልጧል
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት ለዘረጋው የሽግግር ጊዜ መዋቅር የሓላፊዎችና ሠራተኞች ምደባ አካሂዷል፡፡ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ፳፻፮ ዓ.ም ድረስ ለሦስት ወራት በሚቆየው የሽግግር መዋቅር 133 የሀ/ስብከቱ ሐላፊዎችና ሠራተኞች በምደባው ታቅፈዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ 57 በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት፣ 76 ያህሉ ደግሞ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ቅርበት ባላቸው ሰባት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የተመደቡ ናቸው፡፡
ምደባውን ያካሄደው በቋሚ ሲኖዶስ የተሠየመውና በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ የሚመራ መዳቢ ኀይለ ግብር ነው፡፡ ኀይለ ግብሩ ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት አባላት ያሉት ሲኾን እነርሱም የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አስተዳደር መምሪያ፣ የሒሳብና በጀት መምሪያ፣ ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊዎችንና የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተወካይን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ መረጣና ምደባው (selection and placement) የተሠራበት መነሻ በቋሚ ሲኖዶሱ የጸደቀው የሀ/ስብከቱ አስተዳደራዊ መዋቅርና ከእያንዳንዱ የሥራ መደብ ጋራ ተነጻጽሮ የቀረበው ዝርዝር የመመዘኛ መስፈርት ነው፡፡ በመስፈርቱ መሠረት የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ዋነኛ መመዘኛ መደረጉ የተገለጸ ሲኾን ‹‹የብሔር ተዋፅኦ››ም ከግንዛቤ ገብቷል ተብሏል፡፡

Thursday, July 25, 2013

በሙስና የተጠረጠሩት የደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ

  • በተጭበረበረ ውል ደብሩን ከ3 ሚልዮን ብር በላይ በማሳጣትና ሰነድ በማሸሽ ይጠየቃሉ
  • ከጥቂት የሙዳይ ምጽዋት ገቢ ምርመራ ብቻ ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ጉድለት ተገኝቷል
  • የአብዛኛዎቹ የደብሩ ሕንጻ ሱቆች የኪራይ ውል በትክክለኛ ሰነድ የተፈጸመ አይደለም
  • ለማተሚያ ቤት አገልግሎት በተከራየው ክፍል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማይታወቅ ሞዴላሞዴል እንደሚታተምበት ተጠቁሟል
  • የፕሮቴስታንት ቤተ ጸሎት እንደሚያዘወትሩ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል

Dn Mirutse Tikue in Courtበአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ምሩፅ ትኵዕ በተጭበረበረ ሰነድ ከተፈጸመ የኪራይ ውል እና ለሒሳብ ምርመራ የሚፈለጉ የሙዳይ ምጽዋት የገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችን ከማሸሽ የሙስና ወንጀል ጋራ በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡
ዋና ጸሐፊው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ረፋድ ላይ በደብሩ ጽ/ቤት ባሉበት ሲኾን ከዋና ጸሐፊው ጋራ በተጭበረበረው የኪራይ ሰነድና ውል ለደብሩ የሚገባውን ክፍያ ሳይፈጽሙ የግል ጥቅማቸውን አካብተዋል የተባሉ ሌሎች ሁለት የሕንጻው የንግድ ቤቶች ተከራዮችም በተመሳሳይ ቀን መያዛቸው ተመልክቷል፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ እና ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት መቅረባቸው ተገልጧል፡፡
ዋና ጸሐፊውና የጥቅም ተባባሪዎቻቸው ፈጽመውታል የተባለውን ማጭበርበርና ምዝበራ  የሚያረጋግጡ የሰነድ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮች እንዳሉት ለችሎቱ የገለጸው ፖሊስ፣ በዋና ጸሐፊው ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብና የሰው ምስክሮችን ለማዘጋጀት የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችባቸው ክሥ እንደሌለና ከሣሻቸው እንደማይታወቅ በመጥቀስ የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ በጠበቃቸው በኩል የተቃወሙት ዲያቆን ምሩፅ÷ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መኾናቸውን፣ የሚጠየቁትን ማስረጃ ቤተሰቦቻቸው እያቀረቡ መኾኑን፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ቢሯቸውን ለመዝጋት እንዳልተፈቀደላቸው እና ሐምሌ ፳፪ ቀን በደብሩ የቅዱስ ዑራኤል ክብረ በዓል በመኾኑ ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጭ መከታተል እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡ ዮሐንስ አይዳኝ እና ዓለም ፍሥሓየተባሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፣ እነርሱ ውል የያዙበት ሰነድ ከሌሎች ተከራዮች የተለየ እንዳልኾነ በመጥቀስ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ላይ ስጋት ገብቷቸዋል

  • የተነሡ ሓላፊዎችን የተመለከቱ የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔዎች ወጪ አልተደረጉም
  • ንቡረ እዱ÷ አቡነ ጢሞቴዎስ ‹‹በሚሰጧቸው መመሪያ›› እንደሚሠሩ ተናግረዋል
  • ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መምህራንና ሠራተኞች የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ ነው
  • ጥያቄያችን አልተመለሰም ያሉ መምህራን በተቃውሟችን እንቀጥላለን  እያሉ ነው
  • ነገ ፈተና የሚጀምሩት የዘንድሮ ምሩቃን ፈተናቸውን በጨረሱ ማግሥት ይመረቃሉ!
  • ‹‹የተያዘው ጨዋታ ነው፤ መፍትሔ እንደሚሰጡን ከተናገሩ በኋላ እንደ ልጅ ሊያታልሉን እየሞከሩ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
  • ‹‹ከዚህ በኋላ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀጥሉ አይችሉም፤ የእኛ ሥራ ነው፤ ለእኛ ተዉት›› /የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለደቀ መዛሙርቱ/      
Sourse: Hara Zetewahedo
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

አቡነ ጢሞቴዎስ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊነት ተገለሉ፤ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ኮሌጁን በጊዜያዊ ሓላፊነት እንዲመሩ ተመድበዋል

  • አቡነ ጢሞቴዎስ ጉዳያቸው ከሚታይበት ስብሰባ ላለመውጣት ሲለመኑ ውለዋል
  • ፓትርያሪኩ ስለ አቡነ ጢሞቴዎስ ብዙ ከመናገር ተጠንቅቀዋል፤ ተቆጥበዋል
  • ደቀ መዛሙርቱና መምህራኑ ደስታቸውን በቅኔ፣ ወረብና መዝሙር እየገለጹ ነው
  • የቦርድ አባላቱ በሲኖዶሱ ፊት ያሰሙት ያልተጠበቀ ምስክርነት አስተዳደሩን አጋልጧል
  • የአጣሪ ኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲተገበሩ ቅ/ሲኖዶሱ መመሪያ ሰጥቷል
  • የንቡረ እድ ኤልያስ ምደባ ከሚያስነሣው ግዙፍ ጥያቄ ጋራ የምረቃው ቅድመ ዝግጅት ይቀጥላል..
His Grace Abune Timothy
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ
ላለፉት 14 ዓመታት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በበላይ ሓላፊነት ሲመሩ የቆዩት ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ ቅዱስ ሲኖዶስ መስማማቱ ተገለጸ፡፡
ቅ/ሲኖዶሱ ዛሬ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በደረሰበት ስምምነት መሠረት÷ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት እና መምህራን ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሣባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በበላይ ሓላፊነት ከያዙት ሥልጣን ይገለላሉ፤ ለኮሌጁ አዲስ ሊቀ ጳጳስ እስከሚመድብ ድረስም የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ‹‹የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ›› ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በጊዜያዊ ሓላፊነት እየሠሩ እንዲቆዩ ተመድበዋል፡፡

Thursday, July 18, 2013

ዜና ብሥራት ዘሥላሴ! ሐኬተኛው እና መናፍቁ ዘላለም ረድኤት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲወገድ ቋሚ ሲኖዶስ ወሰነ!

  • መ/ር ፍሥሐ ጽዮን ደመወዝ በማስተማር ሥራ ብቻ ይወሰናሉ
  • የአቡነ ጢሞቴዎስ ቀጣይነት እየተጤነ ነው
  • የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ ነገ እንደሚካሄድ ይጠበቃል
ጥቅመኛው፣ ሐኬተኛው (ክፋተኛው) እና መናፍቁ ዘላለም ረድኤት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከያዘው የቀን መደበኛ መርሐ ግብር አስተባባሪነት እንዲወገድ ቋሚ ሲኖዶስ ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ ከዚህ ዐቢይ የስምምነት ውሳኔ ላይ የደረሰው በኮሌጁ አስተዳደርና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ላለፉት ስድስት ወራት እየተባባሰ የመጣውን ውዝግብ ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ከኮሌጁ መምህራንና የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራሮች ጋራ ከመከረ በኋላ ነው፡፡

Friday, July 5, 2013

ጨለማ የለውጥ ተግዳሮት

*እስክንድር ገብረ ክርስቶስ
ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ ፶፱ኛ ዓመት ቁጥር ፻፶፰ ግንቦት እና ሰኔ ፳፻፭ ዓ.ም
                 /መጠነኛ አርትዖት ተደርጎበት የቀረበ/
Ato Eskinder Gebre Kirstos, Head of EOTC General Patriarchate Planning and Development Department
አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ
በቤተ ክህነታችን አሠራርና አደረጃጀት ውስጥ የሚታየውን የሙስናና የጎጠኝነት ችግሮች በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳናት በመጠቀም ያልጠቆመው ያላመላከተውና በመረጃ በማስደገፍ ይፋ ያላደረገው ብልሹ አሠራር ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዎች እጅጉን በተቃራኒው መንገድ የሚገለጹት የብልሹ አሠራር ምንጮች እንዲወገዱም ምንጮችን እየጠቀሰና መረጃዎችን እያስደገፈ፣ ‹‹ኧረ በሕግ አምላክ! ቤተ ክርስቲያኒቱን እናድናት››በማለት መልእክቱን አስተላልፎአል፤ ሰሚ አላገኘም እንጂ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በልዩ ልዩ ወቅቱ ያስተላለፏቸው መልእክቶች ቤተ ክርስቲያናችን ከሙስና፣ ጎጠኝነት፣ መድልዎና ጥላቻ የጸዳች እንድትኾን ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም የሚያመላክቱ መኾናቸውን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ይህን አቋም በእጅጉ እንደሚጋሩት የጽሑፉ አዘጋጅ ስለሚያምን የቅዱስነታቸውን መልእክቶች መነሻ በማድረግ ስለችግሮቹ አስከፊነት ጥቂት ማለቱ አስፈላጊ ኾኖ አግኝቶታል፡፡
ወደ ዋናው የጽሑፌ መልእክት ከመግባቴ በፊት÷ ቤተ ክህነቱ ተቋማዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፤ ብልሹ አሠራር፣ ሙስናና አድልዎ ይወገድ የሚል ጠንካራ አቋም ይዘው ለውጥ ለማምጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደረጉ መሪዎችን ለአብነት ማንሣት የጽሑፌን ሐሳብ ስለሚያጠናክር ጥቂት ለማለት ወደድኹ፡፡
ለአብነት ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅተው ሲያበቁ የጥናቱ ጠቃሚነት በቅጡ ሳይጤን በግፍ ከቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲለቁ የተገደዱትን አቶ በድሉ አሰፋን እናንሣ፡፡ አቶ በድሉ አሁን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ከሚመሩት ተቋም አንጻር ያስመዘገቡት ውጤት በትክክልም የለውጥ ሰው መኾናቸውን፣ ኋላቀር አሠራር ጠላልፎ ሊጥለው የደረሰውን የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በተግባር በመለወጥ ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ሠርተው አሳይተውናል፡፡ እኒያን የተግባር ሰው ያጣው ቤተ ክህነታችን ቁጭት ውስጥ ገብቶ ለለውጥ እንዲዘጋጅ የሚያነሣሣው ጠፍቶ አባቶችን ካባቶች የሚያለያይ ነግሦበት ከረመ፡፡ በመሠረቱ አቶ በድሉ የጨለማው ቡድን ሰለባ መኾናቸውን ስንቶቻችን እናውቅ ይኾን?

በሙስና የተጠረጠሩት የመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የሓላፊነት ምደባ ታገደ

ቋሚ ሲኖዶስ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ የመደባቸው መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከሙስና ተግባር ጋራ በተያያዘ በቀረበባቸው አቤቱታ ምክንያት የፈቀደላቸው ምደባ እንዲታገድ ማድረጉ ተገለጸ፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና በሥሩ ለሚገኙ ልዩ ልዩ መምሪያዎችና ድርጅቶች ባካሄዳቸው ምደባዎች መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊነት ወደ ውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተዛውረው እንዲሠሩ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡
ይኹንና መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው በቆዩባቸው ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የቅርስ ማሸሽ ተግባራት ስለ መፈጸማቸው ልዩ ልዩ አካላት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩና ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የክሥ አቤቱታዎችን በማቅረባቸው በውጭ ግንኙነት መምሪያ የተፈቀደላቸው የዋና ሓላፊነት ምደባ ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑ ተገልጧል፡፡
Dn. DANIEL SACKED FROM HIS POSITIONበቁጥር 1/1188/2005 በቀን 14/10/2005 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ተፈርሞ የወጣውና በአድራሻ ለመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የተጻፈው ደብዳቤ፣ መ/ር ዳንኤል ላለፉት ሦስት ዓመታት ከቆዩበት የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ መነሣታቸውን ያስታወቃቸው ሲኾን በአስተዳደር መምሪያ የሠራተኞች አስተዳደር ዋና ክፍል ክፍል ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በመግለጽ ሲሠሩበት የነበረውን ቢሮ፣ ወንበር፣ ጠረጴዛና ዶኩመንቶች በቦታው ለተመደቡት መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል በሚመድበው አረካካቢ እንዲያስረክቡ አዝዟቸዋል፡፡

Thursday, June 27, 2013

አቡነ ጢሞቴዎስ ለቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ አልታዘዝ ብለዋል

  • ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ለኮሌጁ የመደባቸውን ሓላፊ አልቀበልም ብለዋል
  • ከኮሌጁ እንዲባረር የተወሰነበትን ዘላለም ረድኤትን ዋና ዲን ለማድረግ አስበዋል
  • ደቀ መዛሙርቱና መምህራኑ ለከፍተኛ ተቃውሞ እየተዘጋጁ ነው
  • ፓትርያሪኩ ለአቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ የማደር ዝንባሌ እየታየባቸው ነው
በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን መልክ መያዝና እልባት ማግኘት ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ውሳኔን በተግባር ተፈጻሚ ለማድረግ ያለመቻልልምሾነት ነው፡፡ ችግሩ ከሁሉ በፊት፣ ከፍተኛ አመራሩ በመግለጫው ያስቀመጠውን ያህል ለውሳኔው ተፈጻሚነት አለኝ የሚለውን ቆራጥ አቋም አጠያያቂ የሚያደርግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይኸው ‹‹ጥርስ አልባነት›› የሚያረጋግጥልን÷ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና ጥቅመኞችአስተዳደራዊ መዋቅራችንን በማይናቅ ደረጃ እንደተቆጣጠሩትና በአንዳንድ አብነቶች ተስፋ ሰጪ መነሣሣቶች እየታዩበት በሚገኘው የለውጥ ርምጃ ላይ በቀጣይነት የሚጋርጡትን ስጋትና ዕንቅፋት ነው፡፡ ጥቂት አስረጅዎችን እንጥቀስ፡-
የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔዎች የተፈጻሚነት ጅምር ሚዛን

ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ የጠቅ/ቤ/ክ ም/ሥራ አስኪያጅ ኾኑ፤ የመምሪያዎችና ድርጅት ሓላፊዎች ምደባም ተደርጓል

  • ለተመደቡበት ሥልጣን ፍጹም የማይመጥኑ ሓላፊዎች መካተታቸው አነጋገረ
  • ‹‹የተቋማዊ ለውጡን ሂደት ከአመስጋኝ አማሳኞች ድለላ መከላከል ይገባል፡፡››
Dr Aba Hailemariam Melese
ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ
የጠቅ/ቤ/ክ ም/ሥራ አስኪያጅ
ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ዛሬ፣ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ም/ዋ/ሥራ አስኪያጅነት በቀረቡት ዕጩ ላይ በመስማማት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ እንዲሾሙ አድርጓል፤ የልዩ ልዩ መምሪያዎችና ድርጅቶች ዋና ሓላፊዎች ምደባም ተካሂዷል፡፡

ከሓላፊነቱ የታገደው ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ከአስተዳዳሪነቱ ተነሣ

ላለፉት ስምንት ዓመታት ለመዝባሪ እና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ቡድኖች/ግለሰቦች ሽፋን በመስጠት፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከትን በአጠቃላይ የሐረር ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በተለይ ሲያውክ የቆየው መልአከ ጽዮን ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ከአስተዳዳሪነቱ መነሣቱ ተገለጸ፡፡
ርምጃው የተወሰደው በዛሬው ዕለት ሲኾን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በጉዳዩ ላይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ ከመከሩ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በተሰጠ ውሳኔ መኾኑ ተገልጧል፡፡
‹አባ› ጳውሎስ በደብሩ አስተዳዳሪነት ከተሾመበት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ጀምሮ ለለየላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦች፣ ለእነርሱ በተላላኪነት ለሚያገለግሉ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን የመድረክ አገልግሎት ዕድል በመስጠት ለብዙዎች መሰናከል ኾኖ ቆይቷል፡፡
ከግንቦት ወር መጨረሻ አንሥቶ ደግሞ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ለቁጥጥር ያሸገውን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትና ሙዳይ ምጽዋት በመከፋፈት፣ በአምሳያው ያደራጀውን የዘረፋና ኑፋቄ ቡድን በማሰማራት የደብሩን ሀብት በግላጭ ሲመዘብር ሰንብቷል፤ ከዚህም በላይ የደብሩ አስተዳደር ከሀ/ስብከቱና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማእከላዊ መዋቅር እንደተለየና ለማንም እንደማይታዘዝ በማወጅ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ መጠነ ሰፊ የዐመፅ ቅስቀሳ ለማካሄድ ሲዘጋጅ እንደነበር ታውቋል፡፡
የቤተ ክህነታችን ብስልና ጥሬ! በፈጸሙት ጥፋትና ክሕደት የሕግ ተጠያቂነት ሳይሆን ከቦታ ወደ ቦታ ማዘዋወርን እንደ መፍትሔ የሚወስደው ቤተ ክህነታችን ከሐረር ደብረ ሣህል ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እልቅና ያነሣውን ‹አባ› ጳውሎስ ከበደን፣ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አበምኔት አድርጎ ነው የሾመው!!!
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

የተሐድሶ መናፍቃንና ጥቅመኞቻቸው የሐረር ደ/ሣ/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ከሀ/ስብከቱ አስተዳደር ለመለየት እየቀሰቀሱ ነው

  • ለመናፍቃኑና ጥቅመኞቻቸው ሽፋን ሲሰጥ የቆየው የደብሩ አለቃ ከሓላፊነቱ ታግዷል!
  • በሀ/ስብከቱ የታሸገው የሰበካ ጉ/ጽ/ቤትና ሙዳይ ምጽዋት ተከፍቶ ገንዘቡ ተመዝብሯል
  • የሀ/ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ እያስጨነቁ የሚገኙት አለቃውና ግብረ በላዎቹ በሊቀ ጳጳሱ ላይ ሁከት ለመቀስቀስ እየተዘጋጁ ነው፤ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የክልሉ ፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ሰላምን የማስከበር ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል
  • ‹‹ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉ ሌቦች ናቸው፡፡›› /አለቃው ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ለተከታዮቹ ካሰማው የመድረክ ንግግር/
  • የቤተ ክህነቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ርምጃ÷ እንደ ‹አባ› ጳውሎስ ያለብቃታቸው የተሰገሰጉ፣ የቤተ ክርስቲያን አሐቲነትና ተቋማዊ ነጻነት ፀር የኾኑ የሙስናና ኑፋቄ መሸሸጊያዎችን በስፋትና በጥልቀት በማጥራት መጀመር ይኖርበታል

Wednesday, June 5, 2013

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ
የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ፣ ግንቦት ፳፷ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም የቀትር በፊት ውሎው፣ የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑትንብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ በብዙኀኑ አባላቱ ድምፅ ደግፎ መድቧቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በሀ/ስብከቱ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲኾኑ የተደረገው ምደባ የቅ/ሲኖዶሱን ይኹንታ ያገኘው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አቅራቢነት ነው፡፡ ይኸውም በ1991 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶስ ጸድቆ በወጣው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ልዩ መተዳደርያ ደንብ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመላው አህጉረ ስብከት ማእከል በመኾኑ ፓትርያሪኩ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን በቋሚ ሲኖዶስ እያስወሰነ በበላይነት እንደሚመራና እንደሚቆጣጠር በተገለጸበት አንቀጽ 7 ንኡስ ቁጥር 1 የተደገፈ እንደኾነ ተገልጧል፡፡
የልዩ መተዳደርያ ደንቡ መውጣት በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ 43 ንኡስ አንቀጽ 4 ድንጋጌ የተመለከተ ቢኾንም ሊቀ ጳጳሱን የፓትርያሪኩ ረዳትየሚያደርገው አንቀጽ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 35(2)÷ ‹‹እያንዳንዱ ሀ/ስብከት ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጀምሮ በቅ/ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ ወይም ጳጳስ ይመራል›› በሚል ከተደነገገው ጋራ የሚቃረን ነው፤ ‹‹ረዳት›› የሚል ቅጽል የለውምና፡፡

Tuesday, June 4, 2013

ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተመርጠዋል፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው ተሠይመዋል


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም አምስተኛ ቀን ጥዋት የስብሰባ ውሎው የሰቲት ሁመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው እንዲሠሩ ሠይሟል፤ የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን ደግሞ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ መርጧል፡፡
His Grace Abune Lukas
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፳፭ ንኡስ አንቀጽ ፩ እና ፬ መሠረት÷ ቅ/ሲኖዶስ በምልአተ ጉባኤውና በቋሚ ሲኖዶስ በየጊዜው በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ሁሉ የሚነጋገርባቸውን ርእሰ ጉዳዮች የማዘጋጀት፣ ውሳኔዎቹን ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን የመከታተል ሥልጣንና ተግባር የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ነው፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፴ ንኡስ አንቀጽ ፱ መሠረት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ÷ የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎችን የማስፈጸም፣ ሥልጣነ ክህነት፣ በቂ የትምህርት ደረጃና ችሎታ ያላቸውን ሦስት ሰዎች ለም/ሥራ አስኪያጅነት በዕጩነት ለቋሚ ሲኖዶስ አስቀርበው ቅ/ሲኖዶስ ሲስማማበት የማስመረጥና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የማሾም ሥልጣን አላቸው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ፲ መሠረት የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችን እያጠኑና እያስመረጡ ፓትርያሪኩን በማስፈቀድ ይሾማሉ፡፡
His Grace Abune Mathewos
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ
የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ
በሙሰኛና ጎጠኛ ቡድኖች ሤራ የምክነት ስጋት ያንዣበበት የተቋማዊ ለውጥ ዕቅዱ በሁለቱ ብፁዓን አባቶች አመራር የመስጠት ክሂልና የማስፈጸም ትጋት ከፍጻሜ ደርሶ የቤተ ክህነታችንን ትንሣኤ እንደሚያሳየን እናምናለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአደጋ ላይ! የቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ ሂደት በፅልመታዊው ጎጠኛና ሙሰኛ ቡድን ተጽዕኖ እንዳይጠለፍ ተሰግቷል


  • የጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ምርጫ ሊቃነ ጳጳሳቱን እርስ በርስ አደፋፍጧል
  • ርእሰ መንበሩ ስብሰባውን በአግባቡ ለመምራትና ለመጠቅለል ተስኗቸዋል ተብሏል
  • በሙሰኝነትና ጎጠኝነት በተዘፈቁበት ተግባራቸው ከሚመጣባቸው ተጠያቂነት ራሳቸውን ለማዳን የተባበሩ ጳጳሳትለተቋማዊ ለውጡ ስጋት ደቅነዋል፤ የፓትርያሪኩን የተቋማዊ ለውጥ ይኹንታዎች ተፈታትነዋል፤ አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ማርቆስ፣ አቡነ ፋኑኤል፣ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ አቡነ ቄርሎስ እና አቡነ ሕዝቅኤል ይገኙበታል
  • ምክትል ዋ/ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ፅልመታዊውን ቡድን በብርቱ የተቋቋሙ የተቋማዊ ለውጡ አውራዎችከሓላፊነታቸው እንዲነሡ መወሰኑ ተሰምቷል፤ራሳቸውን በሙሰኛና ጎጠኛ አሠራር ከመጠየቅ ለማዳን የሚረባረቡ ጳጳሳት ቡድናዊነትና ለዋ/ሥራ አስኪያጅነት ምርጫው የተያዘው መደፋፈጥ በሰፈነበት አጋጣሚ በአጀንዳው ዝርዝር ሳይካተት ም/ዋ/ሥራ አስኪያጁን ከሓላፊነት የማንሣት ውሳኔ የተላለፈበት ኹኔታ ተኰንኗል
  • ምክትል ዋ/ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ከሓላፊነት የተነሡበት ምክንያት ‹‹ክህነት የላቸውም››  በሚል ቢኾንም ቄስ አይሏቸው መነኵሴ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ቦታውን ለመረከብ አሰፍስፈዋል፤ የአራት መኖርያ ቤቶችና አንድ የንግድ ቤት ባለቤት መኾናቸው የተረጋገጠው ንቡረ እዱ የፀረ – ሙስናውን እንቅስቃሴ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ለማክሸፍ ተነሣስተዋል
  • ‹‹የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ስብከተ ወንጌል ነው›› በሚል የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲፈርስ ተወስኗል፤ የጠ/ቤ/ክህነቱ አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ ታግደዋል፤ ውሳኔው ‹‹በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ መሠረት ደረጃውን ጠብቆ ያልተወሰደ፣ በፅልመታዊው ቡድን ጎጠኝነት የተገፋና የፀረ – ሙስና ትግሉን የሚያደናቅፍ የቂም በቀል ርምጃ ነው፤›› በሚል ተተችቷል
  • የፀረ – ሙስና እርምት ርምጃዎችን፣ የአስተዳደራዊ መዋቅር እና ፋይናንስ ሥርዐት ለውጦችን አጥንቶ የሚያቀርብበሁለት ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የባለሞያዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል፤ ሕጉንና ቃለ ዐዋዲውን የማሻሻል ጅምርሥራዎችን የማስፈጸምና የስልታዊ ዕቅዱ ዝግጅት በኮሚቴው ይከናወናል
  • የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በአንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በአራት ሥራ አስኪያጆች እንዲመራ የቀረበው ሐሳብእያከራከረ ነው
የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሁለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. የመክፈቻ ጸሎት ያካሄደው ምልአተ ጉባኤው 18 ያህል አጀንዳዎችን በማጽደቅ ዛሬን ጨምሮ በሥራ ላይ በቆየባቸው አራት ቀናት 13 ያህል አጀንዳዎችን ተመልክቶ ውሳኔ ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡

ምንጭ: ሐራ ዘተዋህዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

Friday, May 31, 2013

ጀብራሬው ‹‹ኢህአዴግ›› በአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ላይ


የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ሲነሳ

(አንድ አድርገን ግንቦት 23 2005 ዓ.ም)፡- ‹‹ ከምሽቱ 1፤30 ላይ አንድ ሞቅ ያለው የተበሳጨ ጀብራሬ አቡነ ጴጥሮስ  ሃውልት ላይ ሽንቱን እየሸና  ‹አንተ ድንጋይ ጓደኞችህ  ተመችቷቸው በማርቼዲስ ሲንሸራሸሩ ይህው አንተ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ ድንጋይ አሸናብሃለሁ › ሲል በልጅነት ደም ፍላት  ዘልዬ  ከጀብራሬው ጋር ግብ ግብ ገጠምኩኝ ፡፡ ድንጋይ አይደለም፡  ‹ድንጋይ ነው› በሚል በቡጢም  ተቃመስን ፡፡ ከስብሰባው የተበተኑ ሰራተኞች ገላገሉንና እየተበሳጨሁ ቤቴ ገባሁ፡፡ ሌሊቱን አልተኛሁም፡፡ ጴጥሮስ ሕያው ነህ ለማለት ፤ ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም ለማለት ይመስለኛል ‹ጴጥሮስ ያችን ሰዓት› ስጭር አደርኩ ›› ጸጋዬ ገብረ መድህን

ሃሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2004 ዓ.ም  ጠዋት ሳተና የሆኑ ወጣቶችና ጎልማሶች የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት ልክ እንደ አስቸጋሪ ኮርማ በገመድ ጠልፈው አንዳች የሚያህል ክሬነር አስረው ከነበረበት ለመንቀል ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
አላፊ  አግዳሚው ወጪ ወራጁ እንደ ዘበት እያየ ያልፋል፡፡ ከፊሉም ሞባይሉን አውጥቶ ፎቶ ሊያነሳ እና ሊቀርጽ ይሞክራል፡፡ ‹‹የሰውየው›› (ሁነኛ ሰው) ሃውልት (የእኛ የእውነተኝነት) ዋቢ ከውስጥ በአቡጀዲ ተጠቅልሎ ፤ ከውጭ በጣውላ ተጠፍንጎ ፤ በብረት ዘንግ ተደግፎ ሊነቀል ትዕዛዝ ይጠብቃል፡፡
 

ቅ/ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን ስልታዊ ዕቅድ ላይ ይወያያል


  • ምልአተ ጉባኤው 18 የመነጋገሪያ አጀንዳዎችን ለይቶ ውይይቱን ቀጥሏል
ምልአተ ጉባኤው በዋናነት ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች ውስጥ፡-
  • ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ መመራት እንዳለባት የታመነበት በመኾኑ መሪ ዕቅዱ ‹‹ተዘጋጅቶ ሲቀርብ›› ተመርምሮ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
  • የሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ቃለ ዐዋዲ ማሻሻያ ረቂቆች በኮሚቴው ቀርበውና ተደምጠው ተጨማሪ ሐሳብ ይሰጥባቸዋል፤
  • በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደርና ሙስና ችግሮች ላይ ‹‹መጠነ ሰፊ›› ውይይት ተደርጎ ውሳኔ  ይተላለፋል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ድርጅቶች፣ በሁሉም አህጉረ ስብከት መዋቅሮች ሙስናን የመከላከያውና መቆጣጠርያው አግባብ ከሚያሰፍነው ጥብቅ ሥርዐት አንጻር አጀንዳው አነጋጋሪና አከራካሪ እንደሚኾን ይገመታል፡፡
  • የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥ/አስኪያጅ ምርጫ ይካሄዳል፤ በበቂ የሰው ኀይልና በበጀት ተደግፎ በሦስት ዴስኮች እንዲደራጅና የራሱ ወርኃዊ መጽሔት እንዲኖረው የተወሰነለት የውጭ ግንኙነት መምሪያ አዲስ ሓላፊና ሊቀ ጳጳስ ይሾምለታል፤ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ቢኾንም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ይጠበቃሉ፤

Thursday, May 30, 2013

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጀመረ፤ ‹‹ሙስና ቤተ ክህነት››ን ያጠፋሉ የተባሉ የእርምት ርምጃዎች ይፋ ተደረጉ

  • ሙሰኛ እንክርዳድ ሁሉ በፀረ – ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ ተለይቶ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድበታል!
  • የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር፣ ሕግና ደንብ በውጤት ተኮር ማሻሻያ ይዘጋጃል
  • ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ እስከ አጥቢያ የፋይናንስ ሥርዐቱ በዘመናዊ አሠራር ይደራጃል
  • የቤተ ክርስቲያንን ርእይና ተልእኮ የሚያሳይ የስትራተጂያዊ አመራር ሥርዐት ይነደፋል
  • በሁሉም የለውጥ ርምጃዎች የባለሞያ ምእመናን ተሳትፎ ይረጋገጣል
  • በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ለሚመዘነው የለውጥ ርምጃ በጋራ እንነሣ!
  • ‹‹በዚህ ትልቅ የሓላፊነት ወንበር ላይ ስታስቀምጡኝ÷ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ፣ የምእመናንን የልብ ትርታ እያዳመጥኹ ለእናንተ ለብፁዓን አባቶች ሳቀርብ ይኹንታውንና እገዛውን እየለገሣችኹኝ የጋራ ሓላፊነታችንን እንድንወጣ መኾን አለበት፡፡››/የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ንግግር/
ቢሮክራሲው በእጅጉ በተንዛዛውና ከሚያስፈልገው በላይ የሠራተኛ ቁጥር በተሸከመው÷ ለመንፈሳዊነት፣ ሞያና ልምድ ቦታ በማይሰጠው÷ የሰው ኀይል አመዳደቡም ከመሠረታዊ ተልእኮው ጋራ ባልተቀናጀው፣ ከዚህም የተነሣ ሙስናና ወገንተኝነት በሰፈነበት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሊወሰድ የሚገባውን የእርምት ርምጃ የሚያመላክቱ ሦስት የይኹንታ ሐሳቦችበዛሬው ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ይፋ ተደርገዋል፡፡
Abune Matyas Looking Forward
ወደፊት፤ በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ለሚመዘነው የለውጥ ርምጃ!
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ዛሬ ጥዋት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ባሏቸው መሠረታዊ የለውጥ ርምጃ ይኹንታቸው እንደገለጹት÷ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የሚታየው የሥነ ምግባር ብልሹ አሠራር ከቤተ ክርስቲያን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣም ነው፤ በምእመናን ላይ ባሳደረው ከፍተኛ ቅሬታ ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያላቸውን እምነት እያሳጣ ነው፤ አሳፋሪውና አሳዛኙ ብልሹ አሠራር ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሳይታረም ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚጥል በግልጽ እየታየ ነው፡፡
ብልሹ አሠራሩን ለማረምና ለማስወገድ፣ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀሙን ግልጽ በኾነና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማደራጀት የሚወሰደው የእርምት ርምጃ÷ የቤተ ክርስቲያንን ስምና ክብር በማስጠበቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚታደግ፣ ካህናትና ምእመናን የተባበሩበትና ተሳትፎቸው የተረጋገጠበት፣ አመራሩንም ከታሪክ ፍርድና ወቀሳ የሚያድን ሊኾን ይገባል፡፡
የፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ የመሠረታዊ ለውጥ ርምጃ ይኹንታዎች፡-