Saturday, September 12, 2026

የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሃገረ ስበከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል አደገኛ የቁልቁለት መንገድ

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል
በቅድሚያ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገረዎ በማለት ፤ እንኳን ለአዲስ ዓመት 2019 በሰላም
በፍቅር ጠብቆ አደረሰን በማለት የመልካም ምኞታችንን ከዚህ ከዝግጅት ክፍላችን ለማስተላለፍ እንወዳለን።

መጪውም ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የፍሠሀ፣ እንዲሁም የንሥሃ ዘመን እንዲሆንልን ልባዊ ምኞታችንን ለመግለጽ እንወዳለን፤ በዚህ ሣምንት መጀመሪያ አካባቢ የደረሰንን ዜና ይዘን በዚህ በዓዲስ አመት ለመምጣት ያስገደደን ነገሩ ትንሽ አስደንጋጭ እና አሳሳቢም በመሆኑ ይሄንኑ ከወዲሁ ለማስታወስ እንወዳለን።  

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ፋኑኤል ለአንድ አጥቢያ ምሥራቀ ጸሐይ አቡነ ተክለሃማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ፍቅረ ማርያም አስተራይ ለተባሉ መነኩስ እጅግ አደገኛ የሆነ ፤ እና የምዕመናንና የሰበካ ጉባኤ አባላትን ሃላፊነት እና ቦታ ያላገናዘበ እጅግ በጣም ከፋፋይ እና መሰሪ የሆነ ደበዳቤ በድብቅ ጽፈው ለአስተዳዳሪው በመስጠት፤ አስተዳዳሪውም ባለፍው ሣምንት ውስጥ ለአካባቢው ፖሊስ ጠርተው የማይፈልጓቸውን ሰዎች ከቤተክርስቲያን ቅጽር እንዲባረሩ እና በድጋሚ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይመለሱ በማድረግ እጅግ በጣም ከባድ እና አደገኛ አካሄድ መጀመራቸውን የሰማንው በዚህ ሣምንት መጀመሪያ አካባቢ ነበር፤  

 

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በምን እና እንዴት ይሄንን ደብዳቤ እንደጻፉት ባይታወቅም፤ ይህ ደብዳቤ ከአካባቢው ምዕመናን እደተነገረን ከሆነ ምናልባትም በርከት ላሉ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ተመሣሣይ ደብዳቤ ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል፤ በተለይ እጅግ ስግብግብ እና የራስ ጥቅም ብቻ የሚታያቸው አስተዳዳሪዎች በምዕመናን ሃብት እና ላብ የተገዛውን እጅግ ትላልቅ የቤተክርስቲያን ሃብት ለግል ጥቅማቸው እና እራሳቸውን ለማበልጸግ የጠቀሙበታል የሚል ከባድ ስጋት ከብዙ ምዕመናን እተሰማ እንደሆነ እየሰማን ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን አሜሪካ የሚገዙ በርካታ ቤተክርስቲያናት ሙሉ ለሙሉ በምዕመናን ሃብት እና ጉልበት ይገዙ እንጂ እነዚህ የግል ጥቅማቸውን የሚመለከቱ የደብር አስተዳዳሪዎች ከሊቀ ጳጳሱ ጋር በመመሳጠር መሰል ደብዳቤዎች በማስጻፍ ንብረቱን መሸጥ ወይም መለወጥ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው መሆኑን ልብ ይሏል፤ 

አሁንም በአቡነ ተክለሃማኖት ቤተክርስቲያን የተከሰተው አቡነ ፋኑኤል ያለ ደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጥያቄ እና ያለምንም መረጃ ለአስተዳዳሪው እንዲህ አይነት መሰል ደብዳቤ መስጠት ከጀርባው ምን አይነት ሃሳብ እና ውል እንዳለው የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፤ በቀጥታ ሊቀ ጳጳሱ የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያሳየው አስተዳዳሪው ያለምንም ከልከያ እና ተጠያቂነት የግል ንብረታቸው እንደሆነ የሚያሳይ በመሆኑ፤ የአካባቢውን ፖሊስ በመጥራት ጥቂት የደብሩን ምዕመናን ድጋሚ እንደማይመለሱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማባረራቸውን ስንሰማ በእጅጉ አስተደንግጦናል፤ እውነትም ይሄ አካሄድ የት እና እንዴት የሚሉ በርከት ያሉ ምእመናን ሁኔታውን እየጠየቁ እና ለማጣራት ሁኔታዎችን ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ግንኙነት እያደረጉ እንደሆን ሰምተናል፤ 

የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሃላፊ የሆኑት ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና እጅግ በርካታ የሆኑ ደብዳቤዎችን ሊቀ ጳጳሱ በሌሉበት የሊቀ ጳጳሱን ቲተር እና ማኅተም በመጠቀም ደብዳቤዎችን እንደሚያበሩ ከአካባቢው ምዕመናን ለመረዳት ችለናል፤ እኚህ ቄስ እጅግ መልካም ሰው እንደነበሩ በድሮ ዝናቸውም የምናውቃቸው እንደሆኑ ብንረዳም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ብዙ ምዕመናን የሚያሳዝኑ እና የሚያስከፉ ሥራዎችን በምዕመናን ላይ እየሰሩ እንዳለ ሰምተናል፤ ከዚህም አንዱ በቅርብ ጊዜ በጣም ጥልቅ የገበያ አዳራሽ የነበረ ቦታ ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና የሚያስተዳድሩት ቤተክርስቲያን በግዢ ለቤተክርስቲያን ይዞታ መገዛቱን ተሰምቷል፤ በግዢውም ወቅት ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና ያለ ሰበካ ጉባኤ ወይንም ያለ አንዳች የቤተክርስቲያኒቱ አባላት እውቅና ብቻቸውን የባለቤትነቱን የሚያሳየውን ውል ላይ መፈረማቸው ይታወሳል፤ ታዲያ የብዙ ምዕመናን ጥያቄ በወቅቱ የሰበካ ጉባኤው ወይንም የደብሩ ካህናት ለምን አብረዋቸው አልፈረሙም? ለምን ለብቻቸው መፈረም አስፈለጋቸው? የሚሉት ብዙዎችን ያወዛገበ እና ያወያየ ነገር እንደነበር የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፤ ምናልባት ልከ አቡነ ፋኑኤል የጻፉት አይነት ደብዳቤ የሃገረ ስብከቱ የሥራ ሃላፊ በመሆናቸው ምክንያት ይዘው ይሆን? ምናልባት እሳቸው ያሉበት አጥቢያ ያሉ ምዕመናን አጥብቀው ሊጠይቁ እና ሊረዱ የሚገባው እውነታ እንደሆነ ልብ ይሏል ነው፤ «ችግሩ ደርሶ ወደ ፍርድ ቤት ወይም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ከመሄድ፤ ቀድሞ ሁኔታዎችን ማጥራት የሚመከር ሃሳብ በመሆኑ» የደብሩ ምዕመናን ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል በማለት ለማስታወስ እንወዳለን፤ ይሄ እውነታ ደግሞ ወደፊት ሊመጡ ከሚችሉ አሰልቺ የሕግ እና የእሰጣ ገባ ሁኔታዎች ሊያድን ይችላል የሚል ምልከታ አለን፤ በተለይ በውጭ ዓለም ያሉ ምዕመናን እንደሚረዱት ብዙዎችም የሚያነሱት ጉዳይ «ምናልባት ቄሱ በሆነ አጋጣሚ ባይኖሩ ቤተሰቦቻቸው ቀጥተኛ ወራሽ እና የንብረቱ ባለቤት ይሆናሉ» የሚለው አስተሳሰብ በእጅጉ የሚያስደነግጥ እና ብዙዎችን ዓይን የገለጠ አካሄድ ሊሆን ስለሚችል፤እነዚህ ሁኔታዎች በእጅጉ አደገኛ እና መሰሪ የሆነ አካሄድ በመሆኑ የአጥቢያው ምዕመናን ነቅተው ሊጠብቁ ይገባል በለን ሃሳቡን እንሰጣለን፤ እኚህ ሰው ናቸው እንግዲህ ይሄንን ደብዳቤ ጽፈውታል እየተባለ በሰፊው እየተወራ እና ብዙዎች የሚገምቱት፤ ታዲያ ምን አስበው ይሆን? 

በመጨረሻ የአካባቢው ምዕመን በሙሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያን ያሉበት አካባቢ እንደመሆኑ መጠን የየደብሩ የሰበካ ጉባኤ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ ሰርቶ ከመሰል እሰጣ እገባ ሁሉ እራሳቸውን ከወዲሁ እንዲከላከሉ እየመከርን፤ አሁን ያለውን አቡነ ፋኑኤል እና የሃገረ ስብከቱ የሥራ ሃላፊ ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና የሰሩትን ሥራ በአስቸኳይ መርምሮ፤ ምዕመኑ አስፈላጊውን እርምጃ ከወዲሁ ካልወሰደ፤ ስግብግብ እና እራስ ወዳድ መከኖሳት እና እራሳቸውን ማበልጸግ የሚፈልጉ የደብር አስተዳዳሪዎች የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ምዕመናን ለዘመናት ለትውልድ ያፈሩትን ሃብት እና ንብረት በሥግብግብ መነኮሳት እና አስተዳዳሪዎች እንዳይወሰድ ከወዲሁ በቅርበት እየተከተታተሉ በሕግም በሰበካ ጉባኤውም ክትትል እንዲያደርግ እንመክራለን። ይቆየን በቅርብ ክትትል አድርገን ተጨማሪ ይዘን እንመለሳለን።

 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment