(መልዕክተ ተዋሕዶ - ዘሮኪ በተለይ ለደጀ ሰላም እንደጻፉት/ PDF)፦ ደጀ ሰላማውያን እንደምን ሰነበታችሁ? ብዬ መጠየቅ፥ ዛሬ አልፈለኩም። እንዴት እንደሰነበትን፥ ሁላችንም እናውቀዋለንና። ለመላው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እያሳለፍነው ያለው ሳምንት የሐዘንና፥ ተስፋችንን አጨላሚ፥ ሆኖ ነው የሰነበተው። ይህ ሳምንት፥ ለሃያ አንድ ዓመታት ፥ መከፋፈል በተባለ በሽታ ፥ ታማ የነበረችው እናት ቤተ ክርስቲያን ፥ ስትሰቃይ ኖራ ፥ ያረፈችበት ሳምንት ነው። ነገር ግን አጥብቀን ከቀድሞው አብዝተን ከጮህን፥ ልክ በወንጌሉ እንደተጻፈው የሞተውን የሚያስነሳው ትንሣኤና ሕይወት የሆነ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ እስትንፋሷን ሊመልሰው ይቻለዋል። በእምነታችንም ጸንተን እያንዳንዳችን ማድረግ ያለብንን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንበል፤ በማለት ሰሞኑን አእምሮዬን ሲሞግቱኝ ወደ ከረሙት ጉዳዮች ተራ በተራ ልግባ።
መጀመሪያ በአሁኑ ወቅት ከበሽታቸው ጋር እየታገሉ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና ሌሎችም በአጠቃላይ፥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰጣችሁን፥ ከባድ አደራ በመወጣት ላይ ለሚገኙ አባቶቻችን፥ ለእናንተ ያለን ፍቅርና አክብሮት እጅግ የላቀ መሆኑን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ያሳያችሁት ጽኑዕ አቋም ብዙዎቻችን ጨርሰን ተስፋ እንዳንቆርጥ ረድቶናል። እያደረጋችሁት ያለውን ጥረትና ተጋድሎም፥ በእኛ በልጆቻችሁ ልቡና ለዘላለሙ ተቀርጾ በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር ይረዳናል። ዋጋችሁም በማይጠፋው መዝገብ ተመዝግቦ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ እንደምትቀበሉም ሙሉ እምነታችን ነው። ይህ ስሜት የብቻዬ ስላልሆነ ጉዳይ በሚመለከተን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ስምም፥ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።
ከሁሉ ያስደነቀኝ ደግሞ የብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ቆራጥ አቋም ነው። “የማንም አሿሿሚ አልሆንም! የሥልጣን ጥመኞችንም አላገለግልም!” ማለታቸው። ለዚህ የማመስገኛ ቃላት ያጥረኛል። ቤተ ክርስቲያን ውለታዎንና ተጋድሎዎን መቼም አትረሳውም። ምናለበት፥ እንደርስዎ ሌሎቹም አባቶች ተከትለዎት ቢወጡ ኖሮ ፥ አሰኝቶኛል። አንዳንዴ እንዲህ ያለ አቋም ቁጭ ብሎ ትርጉም የሌለው ንትርክ ከመነታረክ፥ አስር እጥፍ ይሻላል። ብፁዓን አባቶቼ፥ መቼም መሣሪያ ደቅነው ከያዙ ጨካኞች ጋር እንደምትጋፈጡ ይገባኛል፥ ነገርግን ቢያንስ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ፥ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሲወጡ፥ ሌሎቻችሁም ብትከተሉና ፤በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አባቶቻችን በዕርቁ ጉዳይ ሳይስማሙ ተለያዩ ፤ ተብሎ ቢነገረን፥ ይሻል ነበር ብዬ አስባለሁ።
ለነገሩ አሁንም ቢሆን፥ ያለቀ የደቀቀ ነገር ስላልሆነ፥ ከዚህም በኋላ እነሱ በሚያደርጉት ማንኛውም የመሿሿሚያ ስብሰባዎች ራሳችሁን ብትለዩ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ። አባቶቼ ዝምታም እኮ ተቃውሞ ነው፤ እነ አባ አብርሃምና አባ ሳሙኤል እርስስ በርሳቸው ይሿሿሙ፥ ይሰብሰቡ፥ ነገ እግዚአብሔር ፍርዱን ይሰጣል። ብፁዓን አባቶቻችን ፥ ከቻላችሁ በአቋማችሁ የምትስማሙት አንድ ላይ በመሆን ተቃውሞአችሁን ቀጥሉ፥ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማወቅ ባለበት መጠን አሳውቁ። በመንግሥት አይዞአችሁ ባይነት እየተንቀሳቀሱ ያሉት አባቶች፥ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኝ እረኞች ስለሆኑ እና በሥልጣን ጥመኝነትና በጥላቻ ስለሰከሩ፤ ከዚህ በፊት ለመጠቆም እንደሞከርኩት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከማስፈጸም፥ ወደ ኋላ አይመለሱም። ብፁዓን አባቶች፤ ውሃ ሽቅብ እንደማይፈስ አውቃለሁ። ነገር ግን ሁላችሁም ከእግዚአብሔር ያገኛችሁት ትልቅ መንፈሳዊ ሀብት በእጃችሁ አለ። አስፈላጊውን ማሳሰቢያ ከሰጣችሁ በኋላ፥ በእንቢታቸው ጸንተው፥ የእነ ዓባይ ጸሐዬን ጠመንጃ ተመክተው፥ እንመርጣለን ብለው ከተነሱም፥ በመጨረሻውን ውሳኔ ስጡ! ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ በእጃችሁ ትገኛለችና!
ሁለተኛ፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እባካችሁን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ህልውናና ስለ እኛ ስለ ተበተንነው ልጆቻችሁ ስትሉ በተደጋጋሚ ያሳያችሁትን ትዕግስት አሁንም ቀጥሉ። ቢያንስ ቢያንስ እነ አባ እንትና በስልጣን ጥመኝነት አእዕምሮአቸውን አጥተው እስኪለይላቸው ድረስ ሕዝቡን የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋና አንድነቱን የሚያጠናክርበትን መንገድ በማሳየት በጎቻችሁን በመልካምና በለምለም ሣር ላይ አሰማሩ። እንዲህ ከሆነ ይህን፥ ወይም ያንን፥ እናደርጋለን ከማለት ከእልኸኝነት የሚመነጭ ውሳኔ ተቆጠቡ።
ሦስተኛ፦ የሰላምና አንድነት ኮሚቴም እስከ አሁን ድረስ የደከማችሁትን ድካም ልጆቻችሁ የሆንን ሁሉ እንረዳለን። እግዚአብሔር በሰማያት ዋጋችሁን እንዲከፍላችሁ ጸሎቴ ነው። ከዚህ በኋላ ፥ ያጋጠማችሁን ፈተናና ሰላም እና አንድነቱን ለማምጣት ስትሉ ከመናገር የተቆጠባችሁትን ሁሉ የመግለጽ ኃላፊነት ይጠበቅባችኋል። በአንድነት ምዕመናኑን በመምራት ፥ ለሰላም ይበጃል የምትሉትን ሁሉ ሃሳብ ከመስጠት አትቆጠቡ። አቅማችሁ በቻለ መጠን ከሁለቱም ወገን ይህ መከፋፈል ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ሞክሩ።
አራተኛ፦ለማኅበረ ቅዱሳን አንድ ግልጽ መልዕክት አለኝ። ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጀምሮ ትኩረቱን በቤተ ክርስቲያን ብቻ ላይ በማድረግ፤ ከፖለቲካ ነጻ በሆነ መንገድ፥ ስብከተ ወንጌል በማስፋፋት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃንና ከተሐድሶያዊያን በመታደግ፣ አዲሱን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን የሚገደውና የሚቆረቆር አድርጎ በመቅረጽ ጊዜ የማይሽረው ትልቅ አሻራ ጥሏል። ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን በምትፈልገው ቦታ ሁሉ ስድብን፣ መታሰርን፣ መጉላላትንና ሌሎች በዚህች ጹሑፍ ዘርዝሬ ልገልጻቸው የማልችላቸውን ፈተናዎች ታግሶ፥ በአዲሱ ትውልድ ላይ፥ በእግዚአብሔር ቸርነት፥ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆንም በቅቷል። ይህን ሁሉ መከራና ዋጋ የተከፈለላት ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿ ያለ መሪ ሲቅበዘበዙ፥ ብፁዓን አባቶቻችን በህቡዕ ሣይሆን በግልጽ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው፥ ምንም እንዳልተፈጸመ ዝምታችሁ ሊገባኝ አልቻለም።
ቤተ ክርስቲያን ስትከፈል ደጆቿ ሲዘጉ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እንዳይዘጋ የምታደርጓቸው ጥንቃቄዎችም አሳዝኖኛል!! ለቤተ ክርስቲያን የመከራ ቀን ድምጹን አሰምቶ እኛ አለንልሽ ቤተ ክርስቲያን ካላለ፥ የዚህ ማኅበር ፋይዳው ምንድን ነው? እኔ በበኩሌ ይህ ማኅበር፥ በሰላሙ ሰዓት ብቻ ለስብከተ ወንጌል የሚሯሯጡ ሰባኪያንን ብቻ ሳይሆን፥ በዓላውያን መንግሥታት ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ የሰጡትን ሰማዕታትን እነ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚተካ ትውድም የሚያፈራ አድርጌ እቆጥረው ነበረ። ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? አፍቃሬ ማኅበርነት የሚፈለግ ቢሆንም ከሁሉም በላይ አፍቃሬ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን የሚያሳይበት ወቅት አሁን መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ። ለዚህ ወቅታዊ ጥያቄ ምላሽ በአስቸኳይ ያስፈልገዋል!
በመጨረሻም፦ በውጭው ዓለም የምትገኙ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በየቤተ ክርስቲያናችሁ በዚህ ጉዳይ ተሰባስባችሁ አቋማችሁን ዛሬም ለመግለጽ ዛሬም ጊዜ አላችሁ። ከሕሊና ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት ይሻላል። ብዙ አደር ባዮች በበዙበት ዘመን እውነትን ለመናገር ዳተኛ መሆን ከክርስቲያን አይጠበቅም። የፈለገው ይሾም ስም ለመጥራት ዝግጁ ነን፥ ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም ፤ወለም ዘለም አንልም የሚባል ዜማ እያዜሙ የመንግሥትን ሹመኞች እንድንቀበል መድረኩን የሚያዘጋጁ ካህናትና ምዕመናን እየተስተዋሉ ነው። በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ነው የሚባለው ሲኖዶስ ይኼ ነው ወይ? ብፁዕዓን አባቶቻችንን በገዛ ጽሕፈት ቤታችው እያስፈራራቸው ያለው ግለሰብ፥ አባይ ጸሐዬ፥ መቼ ነው የሲኖዶሱ አባል የሆነው? የሚገርመው እነአባ አብርሃም ፓትርያርኩ ያለ መንግሥት ተጽዕኖ ነው መንበር ጥለው የተሰደዱት ይበሉን? እንደው በእመ አምላክ የመንግሥትን ተጽዕኖ መኖር የሚጠራጠር ሰው ይኖር ይሆንን? እንኳን የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ሲያሳድዱ ይቅርና ፤ዛሬ ሰላም ነው ተብሎ በሚለፈፍበት ጊዜ እንኳን አዳር ውሎአቸው ቤተክህነት አይደለምን? እኛ እኮ ከሞትን ቆይተናል። የሚቀብረን ነው ያጣነው።
ይቅርታ ይደረግልኝና በታሪክ የምናውቃቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የድሮዎቹ፤ ወኔ የነበራቸው፥ እንኳን ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀርቶ ለሃገራችው ለእናት ኢትዮጵያ ሥጋቸውን ለአሞራ የሚሰጡ ነበሩ። ለዚህ መቼም ጥቅስ ፍለጋ አልደክምም። በአጭሩ ግን፥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በር ተዘግቶ የካቶሊክ እምነት በር አይከፈትም በማለት፤ በአጼ ሱስንዮስ ዘመን፥ በአንድ ቀን ብቻ፥ ከመላው ኢትዮጵያ ሰማዕትነት አያምልጥህ እየተባባሉ፤ አስር ሺህ ምዕመናን ጎንደር ላይ ሰማዕትነትን የተቀበሉበትንና የቅዱሱን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ሰማዕትነት ለአንባቢ ማስታወስ ግድ ይለኛል።
እንደው ለመሆኑ ሳናውቀው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ላይ ብቻ የሚሳተፍ፥ ሀገር ጎብኚ፥ መረር ያለ ነገር ሲመጣ እነእገሌ ይህን ያድርጉ፤ እኔ የለሁበትም የሚል ትውልድ ሆነን እንቅር? እንዲህ እንዲህ ይሸቱ የነበሩት እንኳን መናፍቃኑ ነበሩ። እረ ጎበዝ ምን ነካን? እዚህ ላይ ይብቃኝ።
አምላከ ቤተ ክርስቲያን እባክህ ተመልከተን! እኛ ደክመናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
መልዕክተ ተዋሕዶ - ዘሮኪ
----------------------------------------------------------------------------------------------
በመቀጠል ግን በጽሑፍዎ ላይ ቁጨት፣ ንዴት፣ ብስጭት ይስተዋላል። እውነት ነው ነገሩ ያስቆጫል። ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ ስንሆን። ሰላምን እንሰብካለን እያልን በመካከላችን ሰላም ማድረግ ሲያቅተን። ነገር ግን ክርስቲያን በንዴት በቁጨት በብስጭት እንዲያው አዕምሮ ያፈለቀውን ሁሉ መጻፍ አለበት ብየ አላስብም። እናም እስኪ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዳንዶች ላይ እኔም ሐሳቤን ልስጥ።
እውነት ነው ሁሉም አባቶች አንድ ሀሳብ አንድ ልብ ሆነው ምዕመኑ የሚፈልገውን ሰላም እና እርቅ ቢያስቀድሙ መልካም ነበር። ግን አልሆነም። አንዳንዶች አባቶች ተቃዎሟቸውን በግልጽ ያሳዩም እንደአሉ፤ እንዲሁም ወደ ምርጫው ነው መግባት ያለብን ብለው የሚሯሯጡ እንዳሉም ሰምተናል። ሁሉም ወደ እርቁና ሰላሙ ነው መሯሯጥ ያለብን ቢሉ ምንኛ መልካም ነበር።
ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ። ቅዱስ ሲኖዶስ ግን አይሳሳትም። ቅዱስ ሲኖዶስ ይሳሳታል ካልንማ መንፈስ ቅዱስም ይሳሳታል ልንል ነው። ይህ ደግም ፍጹም ውሸት ነው። ታዲያ እርስዎ በጽሑፍዎ "በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ነው የሚባለው ሲኖዶስ ይኼ ነው ወይ?" ያሉት ትክክል አይደለም። እንዳሉት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሳሳት ከሆነማ እስከ አሁን ድረስ የሚያውጣቸው ዶግማዎች፣ ቀኖናዎች፣ ስርዓቶችም ሁሉ የተሳሳቱ ናቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።
ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በቤተክርስቲያን ሥር ያለ እንጂ፣ ቤተክርስቲያንን መሪ አይደለም። ማኀበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያውጣው ስርዓት እና መመሪያ ይመራል እንጂ እንዲሁ እርሱ እንደወደደ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ሲወድ የሲኖዶስን ወሳኔ የሚቀበል፣ ሲፈልግ ደግሞ አይ አይሆንም አልቀበልም የሚልም ሊሆን አይችልም። ይህን ካለማ ምኑን ኦርቶዶክሳዊ ማኅበር ሆነውና። ስለዚህ ማኅበሩ ምን ያድርግ። ምናልባት ለእርቁ መሳካት የእራሱን አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችል ይሆናል። ያደረጋልም ብየ አስባላሁ። ከዚህ ውጭ ግን እርቁ ካልተፈጸመ እኔ በሲኖዶስ ህግ አለመራም ይበል? እኔ ባልኳችሁ ተመሩ ይበል ቅዱስ ሲኖዶስን? ይህን ካለማ ኦርቶክሳዊነቱ የት ላይ ነው? ይላላም ብየ አላስብም። ታዲያ እርስዎ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ያለ፣ በሲኖዶስ ህግ የሚመራ መሆኑን ረስተው ይሁን አውቀው፤ ሥራውን ብቻ ተመልክተው ይህን ማድረግ ነበረበት ሲሉ የሲኖዶስን ህግ የሚሽር አካል አደረጉት። በፍጽም ሊሆን አይችልም። ይህን የሚያደርግ ማኅበር ከሆነም ኦርቶዶክሳዊ አይደለም።
መጨረሻ ላይ ያሉት ሁለት አንቀጾች መልክት አልታየኝም።
---------------------------------------------------------------------------------------------------------
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
No comments:
Post a Comment