መ/ር ዓንዱአለም ዳግማዊ |
- ልኡኩ ዛሬ ምሽት ወደ አሜሪካ ያመራሉ
- በዐቃቤ መንበሩ ተጠርተው ከገቡም በኋላ የጥበቃ ሓላፊው ለማስወጣት ሞክረዋል
- በቅ/ሲኖዶሱ ፊት የተጠየቁት የጥበቃ ሓላፊ የእገዳውን ምንጭ ማስረዳት አልቻሉም
- የሰላም ልኡካኑ ለአዲሱ አደራዳሪ አካል ረዳት (facilitators) ኾነው ይሠራሉ ተብሏል
- ‹‹ሰው በማያስፈራ ነገር ሲፈራ፣ በማያሰጋ ነገር ሲሰጋ በተለይ ከሃይማኖት አባቶች አልጠብቅም፡፡›› /የቪ.ኦ.ኤው ጋዜጠኛ የቅ/ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ እንደታዘባቸው/
በዳላስ ቴክሳስ የተካሄደው ሦስተኛ ዙር ጉባኤ አበው÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት ወደ ሁለቱም አካላት ምልአተ ጉባኤ ተልከው ለቀጣዩ የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የማግባባት ሥራ እንዲሠሩ በደረሰበት ስምምነት መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ሁለት ልኡካን አንዱ መ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ÷ በዛሬው ዕለት ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጋራ ከተወያዩ በኋላ ከጽ/ቤታቸው በወጣ ደብዳቤ ወደመጡበት ተሸኝተዋል፡፡
ልኡኩ ለቤተ ክርስቲያናችን ሥራ እንደመጡ የሚገልጸው ደብዳቤው የመጡበትን ጉዳይ ፈጽመው በመመለስ ላይ መኾናቸውን የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡ የደብዳቤው አስፈላጊነት ዛሬ ምሽት ወደ አሜሪካ የሚመለሱት የሰላም ልኡኩ ምናልባትም በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ላይ የደረሰው የእገታ/ወከባ ችግር እንዳይደርስባቸው ለመርዳት ነው ተብሎ ተገምቷል፡፡ የዚህም ምልክቱ ልኡኩ ዛሬ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ በሚገቡበት ወቅት በተጨባጭ መታየቱ ነው የተዘገበው፡፡
ይኸውም መ/ር አንዱዓለም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ታግደው ወደቆዩበት ጽርሐ መንበረ ፓትርያሪክ በሚገቡበት ወቅት የግቢው ጥበቃ ሓላፊ አቶ ብርሃኔ ጨዋነት በጎደለው አነጋገር ለማስወጣት ሞክረዋል፡፡ ከመ/ር አንዷለም ጠንካራ ተቃውሞ የገጠማቸው የጥበቃ ሓላፊው ‹‹ከግቢው ውጭ ሁለት ሰዎች ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉ›› በማለትም ለማሸማቀቅ ሞክረው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ተጠርተው እየገቡ መኾናቸውን በመናገር በቀጥታ ወደ ብፁዓን አባቶች ማረፊያ ያመሩት ልኡኩ የገጠማቸውን በማሳወቃቸው የጥበቃ ሓላፊው በስብሰባ ላይ በነበረው ቅዱስ ሲኖዶሱ ፊት ተጠርተው መጠየቃቸው ተነግሯል፡፡ ይኹንና አቶ ብርሃኔ የእገዳ መመሪያው በዐቃቤ መንበሩ፣ በዋና ጸሐፊው ይኹን በዋና ሥራ አስኪያጁ ሳይታወቅ በማን እንደሰጣቸው ወይም ከማን እንደተቀበሉ በጥያቄና በተግሣጽ ቃል ላጠደፏቸው ብፁዓን አባቶች የሚመልሱት አጥተው ሲቸገሩ ታይተዋል ተብሏል፡፡
መ/ር አንዱዓለም በግማሽ ቀን ውሎ ከተቋጨው ከዛሬው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ በኋላ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ መወያየታቸው ታውቋል፡፡ ቀደም ሲል መ/ር አንዱዓለም አብረዋቸው መጥተው ከነበሩት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ጋራ በመኾን በአዲስ አበባ የደቡብና ምዕራብ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት ተገኝተው ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋራ ሁለት ጊዜ መወያየታቸው ተዘግቧል፡፡ በውይይቱ ቅ/ሲኖዶሱ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ስለሚቀጥልበት ኹኔታ ያለውን አቋም ያመለከተበት ጉዳይ እንደሚገኝበት የዜና ምንጩ ገልጧል፡፡
የቋሚ ቅ/ሲኖዶስና ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱን ለማጠናከር ከተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ የተገኙ ሌሎች ብፁዓን አባቶች ሁሉ ተሳትፈውበታል በተባለው በዛሬው የቅ/ሲኖዶሱ የግማሽ ቀን ስብሰባ÷ በዳላስ ቴክሳስ ከኅዳር 26 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የዕርቅና ሰላም ጉባኤ የተሳተፈው ልኡክ ሪፖርት ተደምጧል፡፡ ከዚህም ጋራ ተያይዞ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ቅ/ሲኖዶሱ በአወዛጋቢ ውሳኔ አስመራጭ ኮሚቴ በመሠየም የምርጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን በመቃወም ባወጣው መግለጫ ሳቢያ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አዲስ አነጋጋሪ አካል በቶሎ በሚሠየምበት ኹኔታ ላይም መክሯል፤ ነባሩ የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላትም በአዲስ መልክ ከሚቋቋመው አነጋጋሪ (አደራዳሪ) አካል ጋራ በአመቻችነትና ረዳትነት (facilitators) ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡
ዕርቀ ሰላሙን በተመለከተ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ሲመከርና ሲወሰን የቆየው በምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ነው ያሉት የዜናው ምንጮች÷ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ለአራተኛ ዙር በተቀጠረበት፣ የዕርቀ ሰላሙን ፋይዳ ከፓትርያሪክ ምርጫ አጀንዳ ለይተው በሚያዩ የውስጥና የውጭ አካላት ከባድ ተጽዕኖ ሥር በወደቀበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅትም ምልአተ ጉባኤው ለጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱ ‹‹ተገቢና ትክክለኛ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የዛሬውን ስብሰባ ዐቃቤ መንበሩ ለመሰብሰብ እንደማይፈቅዱ፣ ቢፈቅዱም በተለይም የመንበረ ፕትርክናው ዓላሚዎች ላይገኙ እንደሚችሉ ሲወራ የቆየውን ሐሰት በሚያደርግ መልኩ ቅ/ሲኖዶሱ ያሳለፈው ውሳኔ እንዳስደሰታቸው ጭምር ምንጮቹ የገለጹት፡፡
ይህም ኾኖ አሁንም ‹‹ዕርቁ ይቅደም›› የሚሉ ብፁዓን አባቶችን (የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሳይቀር) አቋም በተለያዩ መንገዶች ለማላላት የሚደረገው ጫና ተጠናክሮ መቀጠሉ እንደሚያሳስባቸው ምንጮቹ አልሸሸጉም፡፡ ጫናው ደግሞ የመንበረ ፕትርክናው ዓላሚዎች (ሕልመኞች?) በኾኑ ጳጳሳት በሚያቀናጁት ዘመቻ የሚካሄድ መኾኑ ደግሞ በእጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው አባላት ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና ከዋና ጸሐፊው ዕውቅና ውጭ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገቡ በስውር የተላለፈው መመሪያ፣ ከአገርም ተገደው እንዲወጡ የተደረገበት መንገድ እኒሁ ጳጳሳት የያዙት ዘመቻ አካል መኾኑን የሚያስረዱት ምንጮቹ÷ በተለይ በዚህ ድርጊት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል የሚሏቸውን አባት በስም በመጥቀስ ጭምር ከመንግሥት ጋራ አላቸው የሚሉትን ትስስር ያስረዳሉ፡፡
‹‹ከሦስት ቀን እስር ወይም ወደመጣኽበት ከመመለስ›› ምርጫ ቀርቦላቸው በግዳጅ ከአገር ስለ ወጡት የሰላም ልኡክ ቅ/ሲኖዶሱ ያውቅ እንደኾነ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የተጠየቁት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል አንዱ የጫናው ዒላማ ናቸው፡፡ በትላንትናው ዕለት ምሽት በተላለፈው ምላሻቸው ‹‹የአወጣጣቸውን ነገር የምናውቀው ነገር የለም፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው ከተናገሩት ይልቅ አነጋገራቸው መቸገራቸውን እንደሚጠቁም ጠያቂው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ የታዘበው በሚከተለው መልኩ ነበር – ‹‹ሰው በማያስፈራ ነገር ሲፈራ፣ በማያሰጋ ነገር ሲሰጋ በተለይ ከሃይማኖት አባቶች አልጠብቅም፡፡››
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment