ከላይፍ መጽሄት የተወሰደ
(ቅጽ 7 ቁጥር 99 … ጥር 2005 እትም)
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የጠቅላይ ቤ/ክህነት ዋና ጸሐፊ |
- “ቤተክርስቲያናችን ከግብጽ ባርነት ወጥታ ራሷን ችላ እየተራመደች በመሆኗ ከእነሱ የምትዋሰው ነገር የላትም፡፡” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
- “አቡነ መርቆሪዎስ ሳይወዳደሩ በቀድሞ የፕትርክና ስልጣናቸው ይቀጥሉ ማለትም መንፈሳዊው ህግ አይደግፈውም” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
- የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ ....... Haratewahedo
- “ራሴን ከቅዱስ ሲኖዶስ አግልዬ ብሆን ኖሮ እዚህ አታገኙኝም ነበር፡፡” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለቀናት ያደረገው ስብሰባ በመጠናቀቅ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አሜሪካን ሀገር የሚገኝው ሲኖዶስ ያቀረበውን ጥያቄ ለመቀበል ሕገ ቤተክርስቲያን እንደማይፈቅድለት በመግለጽ ስድስተኛውን የቤተርክርስቲያን ፓትርያርክ ለመምረጥ መወሰኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የላይፍ መጽሄት አዘጋጆች ከመግለጫው በኋላ ወደ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ አቡነ ሕዝቅኤል ቢሮ በማምራት አቡኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ አቡነ ሕዝቅኤል የስራ ጫና ውስጥ የነበሩ ቢሆንም መጠነኛ ጊዜ መስዕዋት በማድረግ ጥያቄዎቻችንን በመቀበል ተገቢ ነው ያሉንን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ነገር ግን አቡኑን በምናነጋግርበተ ሰዓት ማንነቱ ያልለየነው አንድ ሰው ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ጥያቅና መልሱን ይከታተል ነበር፡፡ ለብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል የምናቀርብላቸው ጥያቄ እኛን እየተመለከቱ ምላሽ መስጠት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም በእያንዳንዱ አረፍተ ነገር ግለሰቡን እየተመለከቱ ማረጋገጫ እንደሚጠይቅ ሰው አይናቸውን ገጽታው ላይ ያንከራትቱ ነበር፡፡ ጥያቄያችን ጨርሰን ከቢሮ ልንወጣ ስንልም“አቡኑን ለማስለፍለፍ ሞክራችሁ ነበር እሳቸው ግን ብልጥ በመሆናቸው አንዳች ነገር አልተናገሩም”ብሎናል፡፡ ለማንኛውን ቃለ ምልልሱን እነሆ፡፡
ላይፍ፡- የአገር ውስጥ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በቀጥታ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ወደ መምረጥ እንደሚገባ አስታውቋል ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትወስዱት ትምህርት ምንድነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ ከግብጽ ኦርቶዶክስ እንለያያለን ፤ ምናልባት ልዩነታችን በቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ በሐይማኖት በኩል አንድ ነን፡፡ በፓትርያርክ ምርጫ በኩል የራሳችን መንገድ አለን፡፡ ቤተክርስቲያናችን ከግብጽ ባርነት ወጥታ ራሷን ችላ እየተራመደች በመሆኗ ከእነሱ የምትዋሰው ነገር የላትም፡፡
ላይፍ፡- “ሲኖዶስ የሚያደርገው ስብሰባም ሆነ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የእምነቱ ተከታይ የሆኑትን ከ40 ሚሊየን በላይ ምዕመናንን አያሳትፍም፡፡ የእነሱ ድምጽ በሲኖዶስ ውሳኔ ላይ ተጽህኖ የለውም” የሚሉ ወገኖች በስፋት ይደመጣሉ፡፡ ለመሆኑ ሲኖዶስ የምዕመናንን ድምጽ የሚያዳጥበት አሰራር አለው?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ምን መሰለህ እኛ የምንመራበት የስርዓት መጽሐፍ አለን፡፡ መጽሐፉ ይህንን በግልጽያስቀምጠዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ነገሮችን በግልጽ የምታስኬድበት መመሪያ አላት፡፡ ሲኖዶሱ የሚመራው በእነዚህ መመሪያ ነው፡፡ ነገር ግን የምዕመናንን ድምጽ ሲኖዶስ አያዳምጥም ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ ድምጻቸው የሚደመጥበት የራሱ የሆነ መንገድ አለው፡፡
ላይፍ ፡- ለምሳሌ የትኛው መንገድ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- የፓትርያርክ ምርጫውን ውሰድ ፡፡ በዚህ ወቅት ምዕመኑ እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥም ምዕመናኑ ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ንፍገት የለባትም፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኒቱ የተፈጠረላት መልካምና ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም በስደት አሜሪካን ከተመሰረተው ሲኖዶስ ጋር እርቅ ትፈጽማለች በማለት የሚጠብቅ አማንያን ብዙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን መግለጫው በአጋጣሚው እንዳልተጠቀማችሁበት ምልክት ሰጥቷል፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- አልተጠቀማችሁበትም አትበል ተጠቅመንበታል ፡፡ ምንድነው ሳንጠቀም ያመለጠን ?
ላይፍ ፡- ለምሳሌ አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ እንደማይሾም የቤተክርስቲያኒቱ ህግ ይደነግጋል ፤ ይህ በአንድ ወቅት ተጥሷል ፤ አሁን በድጋሚ ጥፋቱን ለማረም የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እናንተ ግን በአቡነ መርቆሪዎስ መንበራቸው መመለስ ፈቃደኛ አልሆናችሁም፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- አቡነ መርቆሪዎስ ክብራቸው እንዳለ እዚህ መኪና ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ገዳም መቀመጥ ከፈለጉም በገዳም እዚህ ከተማ ውስጥ ከሆነም እዚህው ከተማ ውስጥ እንዲቀመጡ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ሲኖዶሱ ይህንን ወስኗል ፡፡ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳትም ወደ ሀገራቸው መግባት ከፈለጉ ሀገረ ስብከት እንሰጣቸዋለን በማለት ሲኖዶሱ አስተላልፏል፡፡ ከዚህ ውጪ ሲኖዶስ ምን ማድረግ ይችላል? ይምጡና አብረው ባለቤት ይሁኑ ፤ ከውጭ ሆነው ሌላ ነገር ሳይሉ በሂደቱ በመሳተፍ ይምረጡ ይመረጡ ይጠቀሙ ነው የተባለው፡፡ ከዚያ ወዲያ ቤተክርስቲያን ምን ልታደርግ ኖሯል ?
ላይፍ ፡- አቡነ መርቆሪዎስ አራተኛ ፓትርያርክ በመሆናቸው እንዴት ይጠቁሙ ይጠቆሙ በድጋሚ ምርጫ ውስጥ ይግቡ ይባላሉ የሚሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ የመሞገቻ ጥያቄ የምትሰጡት ምላሽ ምንድነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ይህንን ቀኖና ይከለክላል ፤ አንተ የምትለው የገባህበት በር እያለ ግድግዳውን አፍርሼ ካልወጣው ነው፡፡ በበሩ በመንገዱ እንጂ በግድግዳው እወጣለሁ ካልክ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ መመሪያችን የቤተክርስቲያኒቱ በመሆኑ ነው ሲኖዶስ ያዘዘው፡፡ ይህንን ፍትሐ ነገሥቱም አያዝም፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ሳይወዳደሩ በቀድሞ የፕትርክና ስልጣናቸው ይቀጥሉ ማለትም መንፈሳዊው ህግ አይደግፈውም፡፡
ላይፍ፡- በውጭ ሲኖዶስ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ከአሁን በኋላ በምን ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ እንታረቅ ብለናል ፤ መስመራችንም መንገዳችንም ክፍት ነው፡፡ ይምጡ ብለናል ሌላ ነገር የለም፡፡
ላይፍ ፡- ከዋና ጸሀፊነትና ከፓትያርክ ምርጫው ራስዎን ማግለልዎ እና የመልቀቂያ ደብዳቤ ስለ ማስገባትዎ ሰምተናል፡፡ ይህ የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ እየሄደበት የሚገኝው መንገድ ደስተኛ ላለመሆንዎ ማሳያ አይሆንም ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ማነው እንደዚህ ያለው ? እንግዲህ እናንተ ብዙ ታወራላችሁና እኔ የምጨምረው ነገር የለኝም ፡፡ ትንሽ ፍንጭ ይዛችሁ ያችን ማስፋት ትፈልጋላችሁ ፡፡ እኔ እኔ ነኝ፡፡ ከየትስ ነው ራሴን የማገለው ? እኔ ከቤተክርስቲያን ውጪ ነኝን?
ላይፍ ፡- እኛ የሰማነውን በመያዝ ማረጋገጫ ጠይቀንዎታል፡፡ የተባለውን ውሸት ወይም እውነት ነው የማለት ፋንታ ግን የእርስዎ ነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ራሴን ከቅዱስ ሲኖዶስ አግልዬ ብሆን ኖሮ እዚህ አታገኙኝም ነበር፡፡
ላይፍ ፡- ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቅ መቅደም አለበት ከሚሉ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የመጀመሪያ ስለመሆንዎ ይነገራል፡፡ ምናልባት እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምክንያት የሆንዎት እርቁ ባለመሳካቱ ይሆን ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እርቁ መቼ በሲኖዶስ ሳይፈለግ ቀረና ነው እኔ እንዲህ ማለት የምችለው፡፡ ሲኖዶሱ እንታረቅ አንድ እንሁን ብሏል፡፡ ስለዚህ እኔ ከሲኖዶስ ውጪ መሆን አልችልም፡፡
ላይፍ፡- የአገር ውስጡ ሲኖዶስ ያሳለፈው ወይም የደረሰበት መደምደሚያ ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የተከናወነ ነው ብለው በግልዎ ያምናሉ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- የምን ጣልቃ ገብነት ?
ላይፍ ፡-ለምሳሌ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እርቁ ያልተሳካው መንግሥት በአሜሪካው ሲኖዶስ ደስተኛ ባለመሆኑ ነው ይባላል ፡፡ ስድስተኛው ፓትርያርክ ለመምረጥ የምታደርጉት እቅስቃሴ የመንግሥት ረዥም እጅ እንዳለበት ይነገራል፡፡ ይህንን ያስተባብላሉ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ምንድነው ይህ ?
ላይፍ፡- የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ የአቡነ መርቆሪዎስን መሰደድ የመንግሥት እጅ እንደነበረበት በመግለፅ በይፋ ይቅርታ እንደጠየቁ ተናግረዋል፡፡ ይህ መንግሥት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እጁን ለማስገባቱ አይነተኛ ማስረጃ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እንዲህ ለማለቱ መረጃ አቅርቡልኝ፡፡ ይህንን መናገሩን እኔ አላውቅም፡፡ እኔ በዚህ አልነበርኩም፡፡ አንተም በዚያን ወቅት ጋዜጠኛ አልነበርክ፡፡ ስለዚህ ተወኝ፡፡
ላይፍ ፡- የቀድሞ ይቅር እሺ አሁን ነጻ ነን ብለው ያምናሉ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- መንግሥት እኔ እስከማውቀው ድረስ እዚህ ውስጥ አልገባም ፡፡ ሕገ - መንግሥቱም አይፈቅድለትም ፡፡ እነርሱ በእኛ እኛም በእነርሱ ጣልቃ አንገባም፡፡ መንግሥት ገብቶ ምን አደረገ ተባለ? አልገባንም፡፡ እኔ ለራሴ እስከ አሁን ድረስ ነጻ ነኝ ፡፡ የሌላውን አላውቅም፡፡
ላይፍ፡- የእርቁ ጥያቄ ተቀባይነት ያጣው በየትኛው በኩል ነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ ከዚያን ወገን ጋር እየተቀራረብ ነው እርቁ እንደሚፈጸም ተስፈኞች ነን፡፡
ላይፍ፡- ከኢህአዲግ አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ አባይ ጸሀዬ ሲኖዶሱ የሚያደርገው ስብሰባዎች በመገኝት የመንግሥትን አቋም ግልጽ ስለማድረጋቸው መረጃዎቻችን ይገልጻሉ፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- በፍጹም እኔ በተገኝሁበት ስብሰባ የምትለውን ሰው ተመልክቼው አላውቅም፡፡ ከሲኖዶስ ስብሰባ ተለይቼ አላውቅም፡፡ ዝም ብለን የመንግሥትን ስም ባናጠፋ መልካም ነው፡፡
ላይፍ፡- አሜሪካን ሀገር ለመሚገኝው ሲኖዶስ ሆነ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ ለቆዩት የቤተክርስቲያን አባላት የሚስተላፉት ምልእክት ምንድነው?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- መልዕክት ሳስተላልፍ አይደል እንዴ የኖርኩትኝ ? ስንት መጽሐፍ ጽፌአለሁኝ ፤ የሚሰማኝ የለም እንጂ፡፡ አሁንም እየተናገርኩ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምን እንድል ትፈልጋለህ ? መናገር የማልፈልገው ብዙ ነገር ያለኝ በመሆኑ ከዚህ በላይ ምንም መናገር አልፈልግም፡፡ ይህው ነው፡፡
ላይፍ፡- ለጥያቄዎቻችን ተገቢ ያሏቸውን ምላሾች በመስጠትዎ በአንበቢያችን ስም እናመሰግናለን
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment