Thursday, January 31, 2013

እናት ቤተ ክርስቲያናችን አልተከፈለችም


አንድ አንባቢያችን ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተጻፈውን ይህችን ወቅታዊ የሆነች ጽሁፍ ልከውልናል፣ እኛም እጅግ ጠቃሚ ነችና አንባቢያን ሊጠቀሙባት ይችላሉ ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። አንባቢያችንን ከልብ እናመሰግናለን፥ መልካም ምንባብ ይሁንልዎ።
ሙሉውን በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 
ጌታቸው ኃይሌ
መግቢያ፤
"ቤተ ክርስቲያናችን ከሁለት ተከፈለች" የሚል ሥጋትና ሐዘን ከብዙ አቅጣጫ ይሰማል። እውነት ተከፍላ ከሆነ ሥጋቱንና ሐዘኑ የሁላችንም ነው። ግን ለመሥራቿ ክብርና ምስጋና ይግባውና፥ እናት ቤተ ክርስቲያናችን አልተከፈለችም። ከፈሏት የምንላቸው ካህናትም፥ አለመከፈሏን ደጋግመው ተናግረውታል። ሳትከፈል ተከፈለች ማለት ያሳዝናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ዛሬ፥ መከፋፈልን የሚያመጡ የነገረ መልኮት ብጥብጦች በተነሡባቸው
የተለያዩ ዘመናት እንኳን፥ ጥቂት ተሞክሮ እንደሆነ ነው እንጂ፥ አልተከፈለችም። ስለዚህ ፥ መዓቱ እስኪያልፍ ድረስ፥ ቅዱስ ገብርኤል "ንቁም፡ በበህላዌነ፡" እንዳለው፥ ባለንበት ነቅተን እንጽና፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ነፃነት ተባብረን በአንድነት እንሥራ።


ቤተ ክርስቲያን መከፈል የሚደርስባት በነገረ መለኮት ላይ የተለያዩ ትርጒሞች ሲነሡና ስምምነት ሲጠፋ ነው። በእንደዚህ ያለ ጊዜ፥ ጉዳዩን በጉባኤ ለማየት የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናትና ሊቃውንት ስብሰባ ያደርጋሉ። ስብሰባ "ጉባኤ" ወይም "ሲኖዶስ" ይባል ነበር። "ሲኖዶስ"ማለት፥ "የሃይማኖትን ጉዳይ ለማየትና ለመወሰን የተሰበሰበ መንፈሳዊ ጉባኤ" ማለት ነው።  

ሲኖዶሱ የቀረቡለት አስተያየቶች በሰፊው መርምሮ አንዱን ሲመርጥ ሁሉም ከተስማሙበት፥ አለዚያም በዲሞክራሲ ሥርዓት በድምፅ ብልጫ ያለፈውን ሁሉም ከተቀበሉት፥ በቤተ ክርስቲያን መከፋፈል አይፈጠርም። ግን በዓለም-አቀፍ ደረጃ በተደረጉት ሲኖዶሶች ጊዜ የተፈጸመውን ስናይ፥ ሁል ጊዜ ከሙሉ ስምምነት ላይ አልተደረሰም። በዚህም ምክንያት፥ ኒቅያ ላይ አርዮሳውያን፥ ኤፌሶን ላይ ንስጥሮሳውያን፥ ኬልቄዶን ላይ መለካውያን (እነሱ "ተዋሕዶዎች" ወይም "ያዕቆባውያን" ይላሉ) ተለይተው የየራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን አቋቁመዋል። "እንተ፡ ላዕለ፡ ኲሉ፡ ጉባኤ፡ ዘሐዋርያት፡ (ከሁሉ በላይ የሆነች ሐዋርያት ያቋቋሟት ቤተ ክርስቲያን) ተከፈለች፤ ተከፋፈለች። ከዚያ ወዲህ፥ ለጉዳይ ካልሆነ፥ አንዱ ከሌላው አይደርስም፤ የአንዱ ቤተ ክርስቲያን ምእመን ለማስቀደስ ከሌላው ቤተ ክርስቲያን አይሄድም።

በአንድ አካል ሁለት ራስ፤
የዛሬው ችግራችን ይኸ ዓይነት አይደለም። ማንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመን ከማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስ ይችላል። በስደት ላይ ያለነው ምእመናን ኢትዮጵያ ስንሄድ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ሄደን ማስቀደስ እንችላለን። ከኢትዮጵያ የመጡም ከእኛ ጋር ያስቀድሳሉ። እዚያም እዚህም ያለነው አንድ የሃይማኖት ባህል ያለን አንድ ሕዝበ ክርስቲያን ነን። ችግራችን በአንድ ዘመን ሁለት ፓትርያርኮች መኖር ነው-- በአንድ አካል ላይ ሁለት እራስ።

ፓትርያርኮቹ አንዱ ኢትዮጵያ አንዱ አሜሪካ ሆነው፥ "ያንኛውን ትታችሁ እኔን ተከተሉ" ስላሉን ግራ ተጋባን። ግማሾቻችን አንዱን፥ ግማሾቻሻችን ሌላውን ተከተልን፤ ሌሎቻችን ማንንም አልተከተልንም። ሆኖም፥ የአንዱ ፓትርያርክ ተከታይና የሌላው ፓትርያርክ ተከታይ ወይም ገለልተኛው የሃይማኖት ወንድማማቾችና እትማማቾች ናቸው። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን "ቤተ ክርስቲያን" የምትባለው ሕዝበ ክርስቲያኑን (ኤክሌሲያን) ለማመልከት ነው። "ጉባኤ፡ ዘሐዋርያት፡" (የሐዋርያት ስብስብ) የተባለችውም ስለዚህ ነው።

ካህናቱ ከላይ እስከ ታች ልኡካን (ጸሎት በመምራትና ሃይማኖት በማስተማር ሕዝበ ክርስቲያኑን እንዲላላኩ የተላኩ) ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ፥ "ሁላችሁም የክርስቶስ ምእመናን ስለሆናችሁ፥ እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ ማለታችሁን ትታችሁ በክርስቶስ አንድነታችሁን ጠብቁ ስላለን ከውዝግቡ ውስጥ በወገንተኝነት መግባትና ለውዝግቡ ሕይወት መስጠት የለብንም። ይህ ብቻ ሳይሆን፥ በመብታችን ተጠቅመን መፍትሔ መፈለግና ውዝግቡን ማብረድ ግዴታችን ነው። መፍትሔ ከተወዳዳሪዎቹ አይጠበቅም። ሆኖም፥ ያልተከፈለች አንድ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ፓትርያርክ ሊኖራት ስለማይገባ፥ አንዱን ብቻ እንከተላለን። ያንን ማድረግ የምንችለው፥ በስሜትና በምኞት ሳይሆን፥ የችግሩ መንሥኤ ግልጽ ሲሆንልን ነው።
የችግራችን መንሥኤ፤
ከዚህ አጣብቂኝ ያደረሰንን ምክንያት ሁሉም ቢያውቀውም፥ በአጋጣሚው እንደገና በአጭሩም ቢሆን ማንሣት ይገባል። ወያኔዎች የፖለቲካውን ሥልጣን እንደያዙ፥ ቤተ ክርስቲያኗንም ተቆጣጠሯት። መንበረ ፓትርያርኩን የያዘውን ርእሰ ቤተ ክርስቲያን (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን) ገፍተው የራሳቸውን ሰው (ዶክተር አባ ገብረ መድኅን ይባሉ የነበሩትን አስከድተው) አስቀመጡበት። በዚህም ሁለት ታላላቅ ብሔራዊና ታሪካዊ ወንጀል ፈጸሙ። (1)
"ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም የሚለውን የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ጣሱት፤ (2) በሀገሪቷ ላይ የዘሩትን ጎሰኝነት ዘረኝነት ከማታውቀው ቤተ ክርስቲያን አስገቡት። ኅብረተ ሰባችንን በዚህም በዚያም አፈረሱት፤ አፈራረሱት። ያልታመመውን ሁሉ በሽተኛ አደረጉት።

ወያኔዎች አሁንም ኢትዮጵያ ያሉትን ጳጳሳት በጥብቅ እንደሚቆጣጠሯቸው ለማንም ግልጽ ነው። እዚህ ሀገር የተቋቋመው ሲኖዶስ ጥር 9 ቀን፥ 2005 . . ባወጣው መግለጫ ላይ "ቀደም ሲል ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መፋለስ ምክንያት የሆነውና ቅዱስ ፓትርያርኩን በግፍ ከመንበራቸው ያሳደዳቸው ኃይል አሁንም የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ክብር አለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ትውልድንም በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማዳከም ቆርጦ
የተነሣ ኃይል . . . ነው" ብሎታል። በወያኔ አለንጋ የሚነዱትን ጳጳሳት እናዝንላቸዋለን እንጂ፥ አንፈርድባቸውም፤ ሁሉም ወዶ ገባ አይደሉም።

እንዲህ ከሆነ፥ ምእመናን ይኸንን ግፍና ጭቆና አንቀበልም። ቅዱስ ያዕቆብ ጋኔንን እምቢ በሉት እንዳለው፥ ለሃይማኖታችን፥ ለታሪካችን፥ ለማንነታችን ስንል፥ ያለማወላወል የጋኔንን ጭፍሮች እምቢ አሻፈርኝ እንላቸዋለን። አባቶች መነኮሳት፥ ከጸሎታቸው አንዱ "ለስምህ ሰማዕት የምንሆንበት አጋጣሚ ፍጠርልን" የሚል እንደነበረ፥ መነኲሴው ፓትርያርክም ወያኔ
ሲገፋቸው፥ ሰማዕትነቱን ባይሸሹት ክብሩ ለቤተ ክርስቲያኗ፥ ለመንጋቸው፥ ከሁሉም ይልቅ፥ ለራሳቸው ይሆን ነበር። ሆኖም፥ መንግሥት እጁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲያነሣና ግፉዓን እንዲካሱ፥ ስዱዳን እንዲመለሱ፥ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሳችን እንታገላለን።

ሊሆን የሚገባው መፍትሔው፤

የተቃውሞ ዘዴያችን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማለት፥ በእኛ በምእመናኑ ላይ፥ የፈራነውን መከፋፈል የማያመጣብን መሆን አለበት። የአዲስ አበባው ፓትርያርክ ሲሞቱ ብዙዎች (የስደተኛው ፓትርያርክ ደጋፊዎች ሳይቀሩ) ችግሩ የፓትርያርክ ጉዳይ ወይም ወያኔዎች የሞቱ መስሏቸው፥ ቀና መፍትሔ ተጠባብቀው ነበር። እዚያም ሆነ እዚህ፥ ፓትርያርክ ሲሞት
ፓትርያርክ ሊተካ እንደሚችል ልብ አላሉትም። ችግር የፈጠረብን የወያኔ ኀይል መሆኑን ሁላችንም ካመንበት፥ መፍትሔው ያንን ኀይል ማስወገድ ብቻ ነው። የፓትርያርኩ ከመንበራቸው መመለስ የመፍትሔ ውጤት እንጂ መፍትሔ አይደለም። ዋናው መዘዝ የወያኔ እርኩስ እጅ ነው። ወያኔ ከሥልጣን ካልተወገደ፥ ወይም ፖሊሲውን ካልለወጠ፥ የተገፉትን
ፓርትያርክ ከመንበራቸው መመለስ ብቻውን የችግሩ መፍትሔ አይሆንም።

ሕዝቡ "መንግሥት እጁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ያንሣ" እያለ ሲጮኽ፥ የውጪው ሲኖዶስ ጥረቱንና ትኲረቱን የተገፉትን ፓትርያርክ ከመንበራቸው እመመለስ ላይ ካደረገ፥ ዓላማውን ጠባብ የሥልጣን ሽኩቻ ያስመስልበታል። እስቲ እናስበው፤ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በመቆጣጠር ላይ እያለ፥ ፓትርያርኩ ቢመለሱ፥ ጉዳቱ ለፓትርያርኩም ለታጋዩም የከፋ
አይሆንምን? "እኔም እንደሌሎቹ ጳጳሳት የወያኔ ካድሬ ልሁን" ማለት እኮ ነው። ከገቡ፥ ወያኔ ሳይውል ሳያድር ካድሬው ያደርጋቸዋል። የኛም ትግል ይዳከማል። የሚዳከመው ፓትርያርክ ስለምናጣ ሳይሆን፥ ወያኔ ከመንበራቸው ላይ አስቀምጦ በስማቸው መግለጫ እያወጣ አፋችንን በዓለም ፊት ስለሚዘጋው ነው። መንበራቸውን ለማስለቀቅ የቻሉ የጋኔን ጭፍራዎች
ከመንበራቸው ላይ አስቀምጠው ዝም ማሰኘት አይችሉም ብለን ተስፋ አናደርግም። የምንመለሰው ለመታገል ነው ካሉ፥ በድርድሩ ጊዜ በሩ ገርበብ ብሏል። ጠላትን ከዚህ የተሻለ የጦር ሜዳ አስተካክልልን አይሉትም።

ሲኖዶስ፤

ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት አንድ ሲኖዶስ፥ አንድ አመራር ብቻ ነው። ይኸንን ሕግ ሁለት ሲኖዶስ የፈጠሩት፥ አዲስ አበባ ያሉት ካህናትና ስደተኞቹ ካህናት፥ ያውቁታል። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለነው ሕዝበ ክርስቲያን፥ ካህናቱን ጨምሮ፥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች ነን። የምናደርገው ትግል ሀገራችን ነፃ ሆና በነፃነት እንድንኖርባት ነው እንጂ፥ ይኸን
ካላገኘን ብለን በተሰደድንበት ዓለም፥ ኢትዮጵያዊ መንግሥትና ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስቲያን ልናቋቁም አይደለም። ስለዚህ፥ የተሰደዱትን ካህናት የምጠይቃቸው፥ "የእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ" እያሉ ሕዝብ ማስጨነቃቸውንና የመከፋፈል ምክንያት መሆናቸውን ትተው፥ የድዮስጶራው ሕዝብ ወያኔን ሲቃወም ተጨማሪ ኀይል እንዲሆኑ ነው። "የእኛን ሲኖዶስ
ተከተሉ" ማለት የሃይማኖት ስደተኞች ሳንሆን፥ የሃይማኖት ስደተኞች ሁኑ፤ ከኢትዮጵያው ሕዝበ ክርስቲያን ተለዩ" ማለት ነው። ብዙዎች የሚከተሏችሁ ወያኔ የተጠቃላቸው መስሏቸው፥ ቢቸግራቸው ነው እንጂ፥ ኢትዮጵያ ካለው ሕዝበ ክርስቲያን መለየት ፈልጎ አይደለም።

የአንድ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ማእከል ከሕዝቡ ማእከል መሆን እንዳለበት መካድ አይቻልም። ስለዚህ፥ በሕዝብ ማህል ያለውን የኢትዮጵያውን ጭቁን ሲኖዶስና የቤተ ክርስቲያንን አመራር ታግሎ፥ ከወያኔ እጅ ነፃ አውጥቶ፥ ከመውሰድ ይልቅ፥ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋም ሕጋዊ አለመሆኑን ሲኖዶስ አቋቋሚዎች ያውቁታል። መፍትሔ አድርገው ያዩት፥
የኢትዮጵያውን ሲኖዶስ "ሕገ ወጥ" እነሱ ያቋቋሙትን "ሕጋዊ" ማለት ነው። ግን ሁለቱም ሕገ ወጥ ናቸው። ልዩነቱ የኢትዮጵያው ሲኖዶስ "ሕገ ወጥ" የሆነው መንግሥት አስገድዶት ሲሆን፥ የውጪዎቹ ካህናት ሲኖዶስ ያቋቋሙት በስደተኛው ሕዝብ ብዛትና ብሶት በመጠቀም ነው።

በወያኔ ጭቆና የተሰደደው ሕዝብ ብዙ ባይሆን፥ ስዱዳን ጳጳሳት ምንም ብዙ ቢሆኑ ብቻቸውን ሲኖዶስ አያቋቁሙም ነበር።
በሲኖዶስ ስም የተደራጁት ለአገልግሎት እንዲመቻቸው ብቻ ከሆነ፥ ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ሳያቋቁሙ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠትና ሕዝበ ክርስቲያኑን አስተባብሮ የወያኔን ክንድ መመከት ይቻላል። ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ማቋቋም ግን፥ ሕዝብ ስለሚከፋፍል መንበሩን ከመልቀቅ የከፋ ሌላ ጥፋት መጨመር ነው።

የድዮስጶራው መንፈሳዊ ችግር፤

የድዮስጶራው ሕዝበ ክርስቲያ የሚኖረው ኢትዮጵያ ካለው ሕዝበ ክርስቲያን የተለየ ችግር በሚያስከትል በተለየ የባህል አካባቢ ነው። ይኸ ልዩ የባህል አካባቢ የሚያመጣውን ችግር የሚረዱለት ካህናት ያስፈልጉታል። ስለዚህ፥ የድዮስጶራው ካህናት ድርጅት አቋቁመው፥ የሕዝቡን ችግር ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ በየጊዜው እየተሰበሰቡ መመካከር፥ እርስ
በርሳቸው መማማር፥ ልምድ ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ተናጋሪ እየጋበዙ ልምዱን እንዲያካፍላቸው መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል። ያንን ድርጅት "መካናዊ (ሀገረ ስብከታዊ) ሲኖዶስ" ወይም "ረክበ ካህናት ጉባኤ" ሊሉት ይችላሉ። ቀኖና ነው። የሚከፋፍለንን ሲኖዶስ በዚህ በሚያስተባብረን ሲኖዶስ ስም ቢጠሩት፥ ያስከብራቸዋል። ሁላችንም እንከተላቸውና፥
"ከፋፋይ " የሚለው አስከፊ ታሪካቸው ይፋቅላቸዋል።

ኑዛዜ፤

ስደተኞቹ ጳጳሳት (አባ ይስሐቅ፥ አባ መልከጼደቅ፥ አባ ዜና ማርቆስ፥ አባ ኤልያስ) አንድ ጊዜ፥ ኒው ዮርክ ከተማ ስብሰባ አድርገው በማግስቱ፥ ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለተሰበሰብነው ነገሩን። በዚህ ጊዜ፥ "ጥቂቶች ብዙዎችን አይወክሉም፤ ይኸ እንዴት ይሆናል? በሚገባ አስባችሁበታልን? " የሚል ጥያቄ ሳነሣ፥ ዶክተር በላቸው ዓሥራት ፖለቲካዊ ጥቅሙን ካስረዳ በኋላ፥ አባ ገብረ ሥላሴ ተነሥተው፥ "በወያኔ ስር ያሉት ጳጳሳትም ከእኛ ጋር ናቸው"
አሉ። ይህን ሲኖዶስ ኢትዮጵያ ያሉት ጳጳሳት ከደገፉት፥ ወያኔን የሚያጠቃ ኃይል ካለው በማለት ደግፌው ነበር። አሁን ሳየው አንዱንም ተስፋ አልፈጸመልንም። እንዲያውም፥ ገደል የሚያገባ መንገድ ይዞ መጓዝ ስለሆነ እንመለስ።


የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. I got it so much worthy and contemporary article on the verge of our church canon situation. May God Bless you Getachew Haile (prof.)

    ReplyDelete