መ/ር ጳውሎስ መልአከ ሥላሴ |
(መ/ር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ/ PDF):- በቀድሞ ዘመን ማዶ ለማዶ በመንደር ተለያይተው በቅርብ ርቀት ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ
ክፍሎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ታዲያ ባልታወቀ ምክንያት ቅሬታ ፈጥረው በሆነው ባልሆነው ምክንያት እስከ መካሰስ ደርሰው ነበር፡፡ ልዩነታቸውም እየሰፋ ሲመጣ አንዱ ለሌላው መጥፎ ስም መስጠት ጀመረ፡፡ ከአሉባልታዎቹም መካከል፡- የታችኛው መንደር የላይኛዎቹን፤ “እዚያ ማዶ ያሉት ቡዳ ናቸው” ሲሉ፡- በላይኛው መንደር ያሉትም በተራቸው፤ “ታች መንደር ያሉት ቡዳ ናቸው” እየተባባሉ እርስ
በርሳቸው ይተማሙ ነበር፡፡ በሌላ መንደር የሚኖረው ሕዝብም ሁለቱን በቡዳነት ፈርጆ የሚቀርባቸው እስኪያጡ ድረስ ራሳቸው ባመጡት ጣጣ ገለልተኞች ሆነው ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡
ከቀኖች
በአንደኛው ቀን ከታችኛው መንደር አንድ የመሸበት መንገደኛ ወላጆቹ “ቡዳ” እንደሆኑ ከነገሩበት ላይኛው መንደር ደረሰ፤ እንዳይገባ ፈራ፤ አልፎ ከሄደ ደግሞ መሽቷልና የጅብ እራት ሊሆን ነው፡፡ ስለዚህም ጥቂት ካመነታ በኋላ፣ “ጅብ ከሚበላኝ ቡዳ ቢበላኝ አይሻልምን? ቡዳውንስ በጸበል እድናለሁ፤ ጅብ ከበላኝ መሞቴም አይደል? ደግሞስ ቡዳ ይሁኑ፣ አይሁኑ፣ ሰማሁ እንጂ የበሉት የለ? እንዲያውም በዚሁ አጋጣሚ ጉዱን ልወቅ” በማለት አማራጭ ያጣለትን ማደር እውነቱን ማረጋገጫ አድርጎ ሊጠቀምበት በማሰብ ፍርሃቱን አስወግዶ ወደ መንደሩ ገባ ይልና፤ “የእግዚአብሔር እንግዳ፣ የመሸበት መንገደኛ ነኝ፤ አሳድሩኝ” ይላል፡፡ በተሰጣቸው መጥፎ ስም ምክንያት እንግዳ የናፈቁት የመንደሩ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸው ልብን በሚነካ ሁኔታ ተቀብለው፣ እግሩን አጥበው፣ ጥሩ እራት አዘጋጅተው በክብር አስተናገዱት፡፡ በመስተንግዷቸው ውስጡ በጣም የተነካው እንግዳም ለጊዜውም ቢሆን “ቡዳ ናቸው” የሚለውን ነገር ዘንግቶ ነበር፡፡
ኋላ
ላይ ግን የቀረበለትን የማር ጠጅ እየተጎነጨ ሞቅታ ቢጤ ስለተሰማው፣ “እናንተዬ እዚያ ላይኛው መንደር ያሉት ሰዎች ቡዳ ናቸው ይባላልሳ! እውነት ነው እንዴ?” ሲል ወደራሱ
መንደር እየጠቆመ ጠየቀ፤ በድንገትም የቤቱ ደስታ በዝምታ ተዋጠ፤ በመካከል ግን አንድ ሸምገል ያሉ አባት፣ “እኛ እነሱን ቡዳ ናቸው እንላለን፤ እነሱም እኛን ቡዳ ናቸው ይሉናል፤ የእነሱን እንግዲህ እግዜር ይወቀው፤ እኛም አናውቀውም፤ የእኛን ግን አንተ ዛሬ መጥተሃልና አዳርህን አይተህ ነገ ትመሰክራለህ” በማለት መለሱለት፡፡ ያም እንግዳ ሌሊቱን ሙሉ “አውጣኝ፣ አውጣኝ” እያለ ሲጸልይ አደረ፡፡
በቅድስት
ቤተ ክርስቲያናችን አሁን እየታየ ያለው የሁለት ሲኖዶስ ውዝግብም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከደርግ መውደቅ ጋር ተያይዞ በአገራችን የተከሰተው ሁኔታ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንም እንግዳ ነገር እንድታስተናግድ አደረጋት፡፡ እርሱም የደርግ መንግሥት አልፎ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም 5ኛ ፓትርያርክ መረጠች፤ በዚህ መካከል ከፍተኛ ውዝግብና ሁለት ሲኖዶስ ተፈጠረ፡፡ አንደኛው ሌላኛውን ሕገ ወጥ እያለ መጥራትም ጀመረ፡፡ “ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት” ፣ “የሐዋርያት ጉባዔ በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” የሚለውን መርህ
የምታውጀዋን ቤተ ክርስቲያንም አዋጇን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር ገጠማት፡፡ ሐዋርያት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት አንድ ጉባኤ (ሲኖዶስ) እንደሆነ ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ የእኛዎቹ ግን አንድ ቤተ ክርስቲያን ሆነው ሁለት ሲኖዶስ ሆኑ፡፡ አንደኛው የሀገር ቤቱ፣ ሁለተኛው ደግሞ ስደተኛው፡፡
ወንጌሉ፤
ቅዳሴው፤ ስብከቱ፤ ማኅሌቱ፤ ሰዓታቱ አንድ ነው፡፡ በሁሉም አገልግሎት አንድ ናቸው፡፡ ሁለት ሲኖዶስ ሆነው ግን ተከፈሉ፡፡ በእነርሱ መከፋፈል ምክንያት ሕዝበ ክርስቲያኑም ተከፋፈለ፤ የሁለቱን መለያየት የጠላ ደግሞ የተሻለ የሠራ መስሎት በሌላ መልኩ ተገነለጠ፡- “ገለልተኛ” በሚል፡፡ ይህ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማይፈልጉና መከፋፈሏን
ለሚመኙ ደስታ ሆነላቸው፡፡ የተገነጠሉ ሁሉ፣ “እንደነ እገሌ ነው የሆንነው” በማለት ለተሳሳተ መንገዳቸው ቀድመው የተሳሳቱትን ምሳሌ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ይገነጣጥሏት ጀመሩ፡፡
ቤተ
ክርስቲያን እየደረሰባት ካለው ፈተና አንጻር አሁን ያለችበትን መልካም ደረጃ ስንመለከት፤ “የሲዖል ደጆች አይችሏትም” የሚል ቃል ኪዳን ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡ በዚህ ደስ ቢለንም በየጊዜው በሚከሰተው ፈተና ግን ማዘናችን አልቀረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድ አለመሆን ነጥቆ በረር ለሆኑት ደፋሮች እና በውድቀቷ መክበር ለሚሹ ምቹ ሁኔታን ፈጠረላቸው፡፡ እነርሱም ወሬ በማራገብ ልዩነቱን አሰፉት፡፡ ልዩነታቸውም በሃይማኖት፣ በሥርዓት ባስ ሲልም በፖለቲካ ሳይቀር እየተወነጃጀሉ የቤተ ክርስቲያንን ፈተና አበዙት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፣ “እለ ከርሶሙ አምላኮሙ”፣ “ሆዳቸው አምላካቸው” የሆነባቸው በሥጋ ብቻ የሚያስቡና ለጥቅም የሚሮጡ ግለሰቦችም ከአንዱ ሲያኮርፉ ወደ ሌላው ሄዶ ወሬ በማቀበል ክፍተቱን አሰፉት፡፡ አንደኛው ሲኖዶስ ሌላኛውን ሲያጎድፍ ልዩነቱ በዝቶ በአደባባይ እስከ መወጋገዝ ደረሱ፡፡ በዚህ ሁኔታ አንድነቱ ቢኖር ኖሮ ብዙ ሊሰሩባቸው የሚገቡ ሃያ የሚያስቆጩ ዓመታት አለፉ፡፡
የብዙኃኑ
ምኞት የነበረውን የልዩነትን ጉዳይ በዕርቅ የመፍታት ሙከራ ተጀምሮ ሳለ በመካከሉ የእግዚአብሔር ጥሪ ሆነና፣ ቀድመው የተሾሙት በሕይወት እያሉ ኋላ ላይ የተሾሙት ተጠሩ፡፡”ዘቦቱ ኲሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ” ሁሉ በእርሱ
ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ አንድስ እንኳን የሆነ የለም” ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር የፈቀደው ሆነ፡፡ አሁን ችግሩ ትንሽ ቀለል ያለ መስሎ ታየ፤ ምክንያቱም የሁለት ፓትርያርክ በሕይወት መኖር ለእርቁ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ ይታሰብ ስለነበረ ነው፡፡
ከብፁዕ
ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ በብዙዎች ዘንድ የነበረው ግምት፣ አስቀድሞ የተጀመረው ዕርቀ ሰላም በፍጥነት ይከናወናል የሚል ቢሆንም እንደታሰበው አልተጓዘም፡፡ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ 5ኛ ብለን ወደ 4ኛ አንመለስም በሚል ሰበብ ዕርቀ ሰላሙን ወደጎን በመተው አዲስ የፓትርያርክ ምርጫ በጥር ወር ለማካሔድ ዝግጅቱን አጠናቀቀ፡፡ የተከፈለችው ቤተ ክርስቲያን አንድ እንድትሆን የሁላችንም ናፍቆት ስለሆነ፣ አሁን ያለው ሁኔታ የሚያስጨንቅ እና ምጥ ውስጥ የሚከት ሆኗል፡፡ አንድነትን የሚያመጣውም በፍቅርና በይቅርታ የተመላ የአባቶቻችን ልብ በመሆኑ በቀደሙት አባቶች ተተክተው የእረኝነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ኃላፊነትን የተቀበሉ አባቶች ምሳሌነታቸውን እንዲያሳዩ ይጠበቃል፡፡ ለፍቅር ሲባል ማንኛውንም መሥዋዕትነት መክፈል እንደሚገባ የሚያስተምሩ አባቶች ትምህርታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ያስፈልጋል፡፡ በቀጣዩ ዘመንም በአባቶቻቸው የሚተማመኑ ልጆች እንዲፈጠሩ፣ በሃይማኖት ጠንካሮች በአገልግሎትም ደስተኞች እንዲሆኑ በዚህ ጊዜ ከማንኛውም ነገር በፊት ለዕርቀ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም የሚመኘውን እና እግዚአብሔርም የሚወደውን አንድነት ያሳዩ ዘንድ ያሻል፡፡
ስለዚህም
አባቶች የቁጥር ጉዳይ ከአንድነት አይበልጥምና ለዕርቀ ሠላሙ ሊከፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ምሳሌነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ከደረሰው ለከፋ አደጋ ልትጋለጥ ትችላለች፡፡ ለምሳሌ፡- የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ስድስተኛ ፓትርያርክ ከመረጠ በኋላ በምን ሁኔታ ነው ዕርቁ የሚቀጥለው? ይህ ራሱ ክፍተቱን የሚያሰፋ እንጂ አንድነቱን የሚያመጣ አይደለም፡፡ ስድስተኛ ፓትርያርክ ከተመረጠ በኋላ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የደረሰው ጥሪ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስም መድረሱ አይቀርምና እሳቸው ሲያልፉ፤ ስደተኛውም ሲኖዶስ የራሱን ፓትርያርክ መምረጡ አይቀርም፡፡ ያኔ ለመሰብሰብ የሚያስቸግር የመበተን ፈተና ሊመጣ ነው፡፡ ስለዚህ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ብፁዓን አባቶች ችግሩን ከወዲሁ በዕርቀ ሰላም እልባት ቢሰጡት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ይሆናል፡፡ በተጨማሪ ዕርቀ ሰላሙ የሚጠቅመው ከምእመናኑ ይልቅ ለአባቶች መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ዕርቅ የመንፈሳዊ ስብዕና ደረጃቸውን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የአባትነት አርአያነታቸውንና መንፈሳዊ ብቃታቸውን እንዲሁም ለመንፈሳዊ አንድነትና ለመነኮሱለት የአብነት ዓላማ የቆሙ መሆናቸውን ያመለክታል፤ ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የመልካም ታሪክ ባለቤት ያደርጋቸዋል፡፡
በዚህ
ጉዳይ ደግሞ የሕዝቡም ሐሳብ አንድ መሆኑን አባቶች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ሁለቱም ሲኖዶሶች አንዱ ሌላውን መናፍቅ ነው እያሉ በአደባባይ ተወጋገዙ፡፡ የዕርቀ ሰላም ድርድሩ ሲጀመር ልዩነቱ የሥልጣን መሆኑ እና የሃይማኖት አለመሆኑ ታየ፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው መንፈሳዊነት ብቻ ነው፡፡ መንፈሳዊነት ሲኖር እኔነት ይቀራል፤ ግትርነት እና አልሸነፍ ባይነትም ይወገዳል፤ ቁጥር ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ያን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አንድ ትሆናለች፤ አባቶችም ቡራኬያቸው የሚናፈቅ፣ መስቀላቸውንም ለመሳለም ሁሉም የሚሻማው ይሆናሉ፡፡
በስደተኛውም
ሆነ በሀገር ውስጥ ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ድርድር በመልካም ሁኔታ እንዲፈጸም የተወሰነ የጾም አዋጅ ቢታወጅ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ዕርቀ ሰላሙ በኮሚቴ ሳይሆን በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ዕንባና ጸሎት ቢታገዝ ሁኔታው ይፋጠናል፡፡ አስታራቂ ኮሚቴ የተባሉትም ለማስታረቅ የሚበቃ መንፈሳዊ ሰብዕና ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ሁሉም ባይሆኑ የተወሰኑት ይታወቃሉ፡፡ የማይታወቁትንም ቢሆን በዚህ ዘመን ማንነታቸውን ለማወቅ በቅርበት ማየት አይጠበቅም፡፡ ሆኖም እነዚህን አባቶች ወደ አንድነት ለማምጣት እርስ በርሳቸው የተቧደኑ ሰዎች ብቻ በቂ ናቸው ማለት ይቸግራል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፡-
1. በሕይወታቸው
አብነት(ምሳሌ) ሊሆኑ የሚችሉ፤
2. በሃይማኖታቸው
ነውርና እንከን የሌለባቸው (ከመናፍቅነትና ከተሐድሶ ሐሜት የጸዱ)፤
3. ጥቅመኛነት
የማያታልላቸውና ለገንዘብ የማያጎበድዱ፤
4. ለመታወቅና
ራሳቸውን ለመካብ የማያስቡ፤ ማለትም ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስቀድሙ ቢሆኑ፡፡
በአጠቃላይ ከየትኛውም ጎራ ያልሆኑና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው መሆን ይኖርባቸዋል እንጂ የታራቂዎች ዘመድና ወዳጅ ስለሆኑ ብቻ አስታራቂዎች መባላቸው ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም የለውም፡፡ ሸምጋዮችን ለመሸምገል (አስታራቂ የሆኑ አባቶችን ለማስታረቅ) ራሱን የቻለ ሽምግልና ይጠይቃል፡፡ የሲኖዶሱን መከፋፈል እንጀራቸው ያደረጉና አገልግሎታቸውን ከጥቅም ጋር ያዛመዱ፣ ሀገር ቤት ሲመጡ የዚህ፣ ባህር ማዶ ሲሄዱ የዚያ… ብቻ ደህና ለተከፈለበት ሰልፍ አሳማሪዎች፤ ሲላቸው ደግሞ በተመቻቸው ሚዲያ እየቀረቡ ራሳቸውን ለማሳወቅ የሚሮጡ፣ አንድ ጥግ ይዘው በቆሙበት ዐውደ ምሕረት ሞቅታ በተሰማቸው ቁጥር ሌላኛውን እየነቆሩ ልዩነቱ እንዲሰፋ ሚና የሚጫወቱ ሰዎች ዛሬ አስታራቂ ሆነው ማዕከላዊ (ገለልተኛ) ነን ቢሉ የማይታመንና የሚያሳፍር ነው፡፡
የሦስት
ሺህ ዓመት ታሪክ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለመፍታት የተሰበሰቡ ሽማግሌዎች ቢያንስ ንጹሓን ባይሆኑ እንኳን አዳፋ መሆን የለባቸውም፡፡ እንደሚታወቀው ዛሬ ራሳቸውን ሽማግሌ አድርገው የቀረቡት አደራዳሪዎች ትናንት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ አስተማራቸውና፤ ሰርተፍኬት ሰጣቸው፤ ዛሬ ባሉበት ሀገር ስደተኛው ቀጠራቸው፤ ዐውደ ምሕረት ላይ ሲወጡ የሀገር ቤቱን እየኮነኑ የመንግሥትን (የሰማዩን መንግሥት እንደሆነ ይታወቅልኝ) ወንጌል የሥጋ ጥቅማቸው ማጋበሻ አደረጉት፡፡ ምዕመናኑ አንድ፤ ቤተ ክርስቲያንዋም አንዲት ሆና ሳለ፤ ያገለግሉት የነበረው ትውልድ እንኳ ሳያልፍ ዛሬ ደግሞ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው አስታራቂ ነን ብለው ተነሱ፡፡ ታዲያ እነዚህ አደራዳሪ ናቸው ወይስ ተደራዳሪ?
አባቶችን
እናውቃቸዋለን፡፡ የዋሆች ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ለአደባባይ የበቃውም በየዋህነታቸው ነው፤ ግትር የሆኑትም በክፋት ሳይሆን የዋህነታቸው በዝቶ ነው፡፡ የዋሆች ባይሆኑ ኖሮ ትናንት አንድ ጥግ ይዘው ሲተቿቸው እና ሲያንጓጥጧቸው የነበሩ ዛሬ ራሳቸውን ሽማግሌ አድርገው ፊታቸው ላይ በሽንገላ ከንፈር “አባታችን” እያሉ ሲጥመለመሉ ባልተቀበሏቸው ነበር፡፡ እነሱም የአባቶችን የዋህነት ተጠቅመው በጉዳዩ ትከሻ ላይ ተንጠልጥለው የራሳቸውን ስም ለማስጠራት መነሳታቸው አሳዛኝ የታሪክ ተወቃሽነት የሚያስከትል መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉንም አያካትትም፡፡ በስነምግባራቸውና በሃይማኖታዊ አቋማቸው የተመሰከረላቸው መልካም አባቶች በመካከላቸው መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም ቅን አሳቢዎቹ የተሰለፉት ከቅጥረኞች ጎን ስለሆነ ራሳቸውን ከተኵላዎቹ መለየት አለባቸው፤ ባጭሩ እንክርዳዱ ከስንዴው ይለይ፡፡ ቀድሞውንም ሕዝቡ ሳያውቃቸው ቀርቶ ሳይሆን ትኩረቱ ዕርቀ ሰላሙ ላይ ስለሆነ እስከ መከር ይቆይ ብሎ ነው፡፡ አሁን መከሩ ደርሷል፤ ስለዚህ እርቁን እንዳያጨናግፉ ይታጨዱ፡፡ ውስጥ ያሉት መልካሞቹ የቀበሮ ባህታውያንን ያስወግዱና ለአንድ ወገን ያላደላ ሚዛናዊ ጉዞ ያድርጉ፤ የገዳም አባቶችንና የዋሃን ምዕመናንን ይዘውም መንፈሳዊ ጉዞ ያድርጉ፡፡
አጭር
መልዕክት ለሀገር ቤቶቹም ለስደተኞቹም…
ለሀገር
ቤት አባቶች
· በቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት ከአዲስ አበባ ወደ ሀገረ አሜሪካ ልዑካንን በመመደብ ያለመሰልቸት ለዕርቅ መመላለሳችሁ ለአንድነቱ ያላችሁን ሙሉ ፈቃደኝነትና ጉጉት ያሳያል፡፡ የለፋችሁበት እንዲሳካ ከዚህ በታች ያሉት ነገሮች ተግባራዊ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡
1. የፓትርያርክ ምርጫውን ከእርቁ ባታስቀድሙ፤
2. ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት በየገዳማቱ ለሚገኙ አበውና፤ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የተወሰነ የጾም አዋጅ ብታውጁ፤
3. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፤ ማኅበረ ካህናትን፤ ሰባክያነ ወንጌል አገልጋዮችንና ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ምሁራንን በየደረጃ በማሰባሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ብታወያዩ የተሻለ ይሆናል፡፡
ባህር
ማዶ ላላችሁት
· የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ለዕርቅ ጥረት ማድረግ የጀመረው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሉስ እረፍት በፊት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እርሳቸው በሕይወት እያሉ እርቁ ቢሳካ ኖሮ 20 ዓመታት የቆዩበትን መንበር ይልቀቁልን እንደማትሉ ይታመናል፡፡ መቼም አንተ ተዋርደህ እኔ ከብሬ እንታረቅ ብሎ ድርድር የሚጀምር በታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የተጀመረው ዕርቀ ሰላም በመልካም ሁኔታ እንዲፈጸም፡-
1. የቅዱስነታቸውን የአቡነ መርቆርዮስን ወደ መንበራቸው መመለስን የዕርቅ ድርድር ውስጥ ባታስገቡ፡፡ የምትታረቁት ለሹመት አይደለምና፡፡ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስም በተደጋጋሚ አሜሪካ ድረስ በመመላለስ ለዕርቀ ሰላሙ እና ለአንድነቱ ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ የቅዱስነታቸው አቡነ መርቆርዮስን አባትነት አምኖ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም፡፡ ዕርቁና ሹመቱ ተለያይተው ቢታዩ
መልካም ነው፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ የሚጠላ የለም፤ ለዚህ ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈጠረ ቅሬታ ካለ ቅድሚያ እሱን መፍታት ይኖርባችኋል፡፡ ያ ደግሞ ራሱን የቻለ ጊዜ ይፈልጋልና ይህንን በመሳሰሉት ምክንያት የሥልጣንን ጉዳይ ሳይሆን በቅድሚያ እናንተ ብትስማሙና የሹመቱን ጉዳይ
ለመንፈስ ቅዱስ ብትሰጡ መልካም ነው፡፡
2. የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከላይ እንደተጠቀሰው አሜሪካን ድረስ ልዑካን መድቦ ለበርካታ ጊዜያት ሲመላለስ ገንዘብ፣ ጊዜና የሕይወት ዋጋ መክፈሉ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ለሰላሙ ጉዳይ ከዋሽንግተን ዲሲ ተነስተው አዲስ አበባ ሲደርሱ በአየር ግጭት (መዛባት) ምክንያት ወዲያውኑ ሕይወታቸውን ያጡት ታላቁ ሊቅ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የማይረሱ አባት ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን በማሰብ በተለሳለሰ ሁኔታ የልባችሁን በር ለዕርቁ ብትከፍቱና ሁኔታዎች በፍጥነት እንዲስተካከሉ ብትተባበሩ መልካም ነው፡፡ ደግሞስ ሁሌ ከዚህ ብቻ መኬዱ ለምንድን ነው? ለምን እናንተስ
ኢትዮጵያ በመምጣት ለዕርቁ ያላችሁን ፍላጎት አታሳዩም? ምን አልባት ከመንግሥት ጋር ያለውን መቃቃር እንደ ምክንያት ትጠቅሱት ይሆናል፡፡ መቼም ሁላችሁም ከመንግስት ጋር እንዳልተቃረናችሁ ግልጽ ነው፡፡ እጃቸውን ፖለቲካ ውስጥ ያላስገቡ አዳዲስ ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳት እንዳሉ ይታወቃል፤ ነገር ግን እስካሁን ከእናንተ ወደዚህ የመጣ ልዑክ የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ለዕርቁ ከፍተኛ ፍላጎት የሚታይበት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ነው ቢባል ማጋነንም ማድላትም አይሆንም፤ ምክንያቱም ገንዘብ፣ ጊዜና ሕይወት ከፍሏልና፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከእናንተ ከባህር ማዶዎቹ አባቶች የአባትነት መዓዛ ይፈልጋል፡፡ እንደ ሀገር ቤቶቹ እናንተም የዕርቁ ጉዳይ ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነ ዋጋ ክፈሉ፡፡ ሀገራቸው መግባት የሚችሉ ልዑካን ከዚያም ይምጡ፡፡
3. በተደጋጋሚ እንደሚጠየቀው የቅዱስነታቸው የአቡነ መርቆርዮስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ከአንደበታቸው ቢሰማ የተሻለ ነው፡፡ በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች እሳቸውን ደብቀው የሚደራደሩባቸው ጉዳይ ግልጽ አይደለም፡፡ እናንተም በሩን ዘግታችሁ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጋር ለዕርቁ የመጡ አባቶችን አለማገናኘት ራሱ ሌላ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ፓትርያርኩን ከአዲስ አበባ
አሜሪካ ድረስ ያለ መሰልቸት ከሚመላለሱት ብፁዓን አበው ጋር እንዲገናኙ አድርጉ፤ የእሳቸውም ስሜት እና ፍላጎት ከአንደበታቸው ይሰማ፡፡
4. በመጨረሻ በአገር ቤትም
ሆነ በባህር ማዶ ያላችሁ አበው፡- ዕርቅን የማይፈልግ ከእግዚአብሔር አይደለምና ለእርቁ ከምንም በፊት ቅድሚያ ቢሰጥ የተሻለ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ አቡነ መርቆርዮስ ቢመጡ እሰየው ነው፤ ያ ካልሆነ ግን ዕርቅ አይሆንም አይባልም፡፡ በአደባባይ የተወጋገዛችሁትን በአደባባይ ፍቱት፤ ውግዘቱ ይነሳ፡፡ እዚህ ያሉት ባህር ማዶ ሲሄዱ የፈለጉበት ቤተ ክርስቲያን ያገልግሉ፣ ያስቀድሱ፣ ወዘተ... የአጵሎስ፣ የኬፋ ማለት ይብቃ፡፡ እዚያም የውጭዎቹ ጋር የሚያስቀድሱትና የሚቀድሱት ተሳትፎዋቸው ሀገር ቤት ሲመጡ አይቋረጥ፡፡ የተሰደዱት ሀገር ቤት የሚገቡበት አማራጭ ቢታጣ እንኳን ቢያንስ ቢያንስ መተቻቸቱና መነቃቀፉ ቀርቶ እንደ ሁለት ሀገረ ስብከትም ሆነው ቢሆን በጸሎት በመተሳሰብ ያገልግሉ፡፡ ህዝቡን ከንትርክ ያሳርፉት፡፡ ዕርቅ፣ ዕርቅ የሚባልበትም ዓላማ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ስትገለገል ለማየት ነው፡፡ ለዚህም የእናንተ አብነታችሁ ያሻል፡፡
ለአንባቢዎች
፡-
“ጸልዩ
በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር”“በእግዚአብሔር ዘንድ የቀናችና ርትዕት ስለምትሆን አንዲት ቅድስት
የሐዋርያት ጉባኤ ስለሆነች ቤተ ክርስቲያን ሰላምን ለምኑ”፤
እግዚአብሔር
የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ያጽናልን!!!
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment