*እስክንድር ገብረ ክርስቶስ
ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ ፶፱ኛ ዓመት ቁጥር ፻፶፰ ግንቦት እና ሰኔ ፳፻፭ ዓ.ም
/መጠነኛ አርትዖት ተደርጎበት የቀረበ/
በቤተ ክህነታችን አሠራርና አደረጃጀት ውስጥ የሚታየውን የሙስናና የጎጠኝነት ችግሮች በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳናት በመጠቀም ያልጠቆመው ያላመላከተውና በመረጃ በማስደገፍ ይፋ ያላደረገው ብልሹ አሠራር ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዎች እጅጉን በተቃራኒው መንገድ የሚገለጹት የብልሹ አሠራር ምንጮች እንዲወገዱም ምንጮችን እየጠቀሰና መረጃዎችን እያስደገፈ፣ ‹‹ኧረ በሕግ አምላክ! ቤተ ክርስቲያኒቱን እናድናት››በማለት መልእክቱን አስተላልፎአል፤ ሰሚ አላገኘም እንጂ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በልዩ ልዩ ወቅቱ ያስተላለፏቸው መልእክቶች ቤተ ክርስቲያናችን ከሙስና፣ ጎጠኝነት፣ መድልዎና ጥላቻ የጸዳች እንድትኾን ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም የሚያመላክቱ መኾናቸውን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ይህን አቋም በእጅጉ እንደሚጋሩት የጽሑፉ አዘጋጅ ስለሚያምን የቅዱስነታቸውን መልእክቶች መነሻ በማድረግ ስለችግሮቹ አስከፊነት ጥቂት ማለቱ አስፈላጊ ኾኖ አግኝቶታል፡፡
ወደ ዋናው የጽሑፌ መልእክት ከመግባቴ በፊት÷ ቤተ ክህነቱ ተቋማዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፤ ብልሹ አሠራር፣ ሙስናና አድልዎ ይወገድ የሚል ጠንካራ አቋም ይዘው ለውጥ ለማምጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደረጉ መሪዎችን ለአብነት ማንሣት የጽሑፌን ሐሳብ ስለሚያጠናክር ጥቂት ለማለት ወደድኹ፡፡
ለአብነት ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅተው ሲያበቁ የጥናቱ ጠቃሚነት በቅጡ ሳይጤን በግፍ ከቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲለቁ የተገደዱትን አቶ በድሉ አሰፋን እናንሣ፡፡ አቶ በድሉ አሁን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ከሚመሩት ተቋም አንጻር ያስመዘገቡት ውጤት በትክክልም የለውጥ ሰው መኾናቸውን፣ ኋላቀር አሠራር ጠላልፎ ሊጥለው የደረሰውን የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በተግባር በመለወጥ ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ሠርተው አሳይተውናል፡፡ እኒያን የተግባር ሰው ያጣው ቤተ ክህነታችን ቁጭት ውስጥ ገብቶ ለለውጥ እንዲዘጋጅ የሚያነሣሣው ጠፍቶ አባቶችን ካባቶች የሚያለያይ ነግሦበት ከረመ፡፡ በመሠረቱ አቶ በድሉ የጨለማው ቡድን ሰለባ መኾናቸውን ስንቶቻችን እናውቅ ይኾን?
ከአቶ በድሉ በኋላ የመጡ በርካታ ምሁራን በተለያዩ መንገዶች ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ መለወጥ ሲያነሡ እንደ ተናዳፊ እባብ ጭንቅላታቸውን እየተመቱ ሐሳባቸው ከንቱ ቀርቷል፡፡ እዚህ ላይ ለውጥ የማይገባቸው፣ ስለለውጥ የሚያስቡቱን አስቀድመው መቀጥቀጥና ማስቀጥቀጥ መደበኛ ሥራቸው የኾኑ በቤቱ አጠራር የጨለማው ቡድን አባላት በመባል የሚታወቁ ፀረ ለውጥ፣ ፀረ ዕድገትና የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ የተፀናወታቸው ምሁራን ነን ባዮች በቤተ ክህነቱ ነግሠው ቆይተዋል፡፡ አሁንም የንግሥና ዘመናቸውን ለማራዘም ከተራ ድብትርና አውጥተው እዚህ ያደረሷቸውን አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኘሬዝዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ም/ቤት ለሰላም የክብር ኘሬዝዳንትን በመካድ መልካም ሥራና ርኅራኄአቸውን ደግነትና ሥራ ወዳድነታቸውን እንኳን ለመመስከር ሲቸገሩ እንመለከታቸዋለን፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ከጳጳሳት፣ ከመንግሥት ሰዎችና ከሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለ ድርሻ አካላት ጋራ እንዳይስማሙ በየወቅቱ አዲስ አጀንዳ በመፍጠርና በማቀበል የጨለማውን ሲኖዶስ በመምራት ያልኾነ ምክር ይመክሯቸው የነበሩ፣ የአቶ በድሉን ጥናታዊ ጽሑፍ በመስረቅ ያዘጋጁ መስለው ለመታየት የሞከሩ ማን እንደኾኑ ሊቃነ ጳጳሳቱም ኾኑ የቤተ ክህነት ሠራተኞች ጠንቅቀው ያውቋቸዋል፡፡
በቅርቡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ልዑል ሰገድ ግርማም ስለ ለውጥ አስፈላጊነት፣ ስለዘመናዊ አስተዳደርና ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ልትመራበት ስለሚገባው ዘመናዊ አስተዳደር በጋዜጦቻችንና በመጽሔቶቻችን ጠቋሚ ገላጭና አስተማሪ ጽሑፎችን በመጻፍ ወደ ለውጥ የሚያመራቸውን እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምሩ የጨለማው ቡድን ሰብሳቢና አባላቱ ልክ ዛሬ እንደሚሉት፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በአቶዎች አትመራም፤ አቶዎቹ በጠበጡን›› በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ የነርሱና የነርሱ መሰሎች እንጂ የአቶዎች አይደለችም በማለት በስእለትና በዐሥራት በኵራት ከአቶዎቹ (ከምእመናን) የተሰበሰበውን ገንዘብ በመዝረፍ የሠሩት ሳያንሳቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ከምእመናን አስተዋፅኦ ለመለያየት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
እጅጉን የሚገርመው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አማካሪ በመኾን የጨለማውን ቡድን በመምራት ቅዱስነታቸውን በእባብ መርዝ የተለወሰ የተስፋ ዳቦ በማሳየት ሲያስቱ የነበሩት የጨለማው ቡድን ግንባር ቀደም መሪዎች መጨረሻ ላይ ለአቶ ልዑል ሰገድ ግርማ ከቤተ ክህነት መልቀቅ ምክንያት ነው የተባለውን ጥናታዊ ጽሑፍ በጋራ አርቅቀውና በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ፈርመው ሲያበቁ እነርሱ ከነገሩ ንጹሕ እንደኾኑ በማስመሰል ቤተ ክርስቲያኒቱ በአቶዎች እንደ ተደፈረች በማስወራት የጨለማ ተውኔታቸውን በመሪ ተዋናይነት የሠሩት ዛሬ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ለመክበብና ለመቆጣጠር የሚጥሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከትቢያ አንሥተው ሰው ያደረጓቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች እንደኾኑ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ የጨለማው ቡድን÷ የለውጥ፣ የዕድገት፣ የዘመናዊ አሠራር ፀር ከመኾኑም በላይ አሉባልታ፣ ወሬ፣ ሽብር በመንዛት ለለውጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ማኰላሸት ተቀዳሚ ተግባሩ እንደኾነ ካለፏት ዓመታት እንቅስቃሴውና ከፍ ሲል ከዘረዘርናቸው አብነቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
ይህ አስተሳሰቡና ግብሩ በጨለማ የሚመሰለው ቡድን ዋና ዓላማ፣ በእርሱ ዙሪያ የተሰበሰቡ ኔትወርኮችን በማስተባበር ለለውጥና ለሥራ የሚደረጉ መልካም ሥራና ውጤቶችን ጥቀርሻ መቀባት ሲኾን ጥቅምና ሙስና የሚገኝባቸውን መሥመሮች ሁሉ በይዞታነት በመቆጣጠር ሙስና ጠሏና ተቃዋሚዋ ቤተ ክርስቲያናችን በሙስና መገለጫነትና በብልሹ አሠራር ተጠቃሽነት እንድትታወቅና መልካም ስሟ እንዲዋረድ በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱ በልዩ ልዩ ጊዜያት ያስመዘገበቻቸው መልካም የሥራ ውጤቶች ሁሉ በሕዝብ ዘንድ ተገቢውን ዕውቅና እንዳያገኙ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የጨለማው ቡድን በመባል የሚታወቁ ስብስቦችን አጠቃላይ አቋም ስንመለከት÷ ለድኃው የማያዝኑ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለግል ጥቅማቸው እንዲያም ሲል ለቡድናቸው ህልውና የቆሙ፣ አብዛኛዎቹ የቡድኑ አባላት በሥልጣን ዘመናቸውም ኾነ አሁን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማስመዝገብ ያልቻሉ፣ ይልቁንም በመጥፎ ተግባራቸው የጥንታዊቷ፣ የብሔራዊቷና፣ የታሪካዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር የመጥፎ ሥራ መገለጫዎች እንዲኾኑ አፍራሽ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የጨለማው ቡድን ባለፏት ዓመታት የለውጥ ተግዳሮቶች ኾኖ የቆየው፡፡
ወደ ቀደመው ነገሬ ስመለስ፣ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡ ለውጥ መምጣት የሚጀምረው ደግሞ ለውጥ ያስፈልጋል የሚል ጠንካራ አቋምና እምነት ካለው አመራር ሲመነጭ እንደኾነም ግልጽ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እስከ አሁን ያሳዩት አቋም ተቋማዊ ለውጥ ለቤተ ክርስቲያን ግድና አስፈላጊ መኾኑን ያረጋገጠ ነው፡፡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም በቤተ ክህነቱ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚፈልጉና ይህ ጠንካራ አቋማቸው እንደኾነም አይጠረጠርም፡፡
በተዋረድ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ የመምሪያ ሓላፊዎችም ቢኾኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ጊዜውም አሁን እንደኾነ ያምናሉ፤ ሠራተኛውም ለውጡ ይዞለት የሚመጣውን መሠረታዊ ጥቅም ስለሚገነዘብ ለውጡን ይጠላዋል ተብሎ አይታመንም፡፡ ለውጡ የማይዋጥላቸውና ለውጥ የማይፈልጉት የጨለማው ቡድን አባላት ብቻ እንደኾኑም ከላይ ተመልክተናል፡፡ በመኾኑም ከጨለማው ቡድን በአንጻሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ለውጥ መምጣት አለበት ብሎ የሚያምነው አካል በጥቂቱ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህን ምቹ ኹኔታ በመጠቀም የግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተቋማዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ፣ ወቅታዊና ጠቃሚ መኾኑ በጽኑ ከታመነበትም ለውጡን ለማምጣት ይቻል ዘንድ መለወጥ ያለባቸው አሠራሮች፣ ለለውጥ መሰናክል የኾኑ ተግዳሮቶች፣ የሙስና አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ተቆጥረው መውጣትና መጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ነጥብ በነጥብ ከተዘረዘሩ በኋላ አስተሳሰብና ድርጊቶቹን በመሠረቱ ለመቀየር፣ መልካም አስተዳደርና ዘመናዊ መዋቅር ለመዘርጋት የሚያስችል ስትራተጅያዊ ዕቅድ ማዘጋጀትና ማጽደቅ ሥራውም በታቀደ አግባብ እንዲፈጸም ማድረግ ለውጡን ለማምጣት ያስችላል፡፡ እዚህ ላይ የለውጥ ተግዳሮቶችን በመዘርዘር ጥቂት ፍንጮችን መስጠት ይቻላል፡፡
የሙስና አስተሳሰብና ድርጊቶች
ሙስና የሚመጣው ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደኾነ ይታወቃል፡፡ መልካም አስተዳደርን በተቋም ደረጃ ማረጋገጥ፣ ማስፈን ከተቻለ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የሥራ ሂደት መፍጠር ከተቻለ ሙስናን መቀነስ ይቻላል፡፡ ሙስና በቤተ ክርስቲያናችን እንዲስፋፋ ዕድል የፈጠረለት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያለው የአሠራር መዋቅር ባለመዘርጋቱ እንደኾነ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ስለኾነም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማዕከል ያደረገ ወጥ የሥራ ሂደት ከተፈጠረና ሞያና ሞያተኛን ያገናዘብ የቅጥርና የዝውውር ሥርዐት ከተዘረጋ እንዲሁም የደመወዝ ክፍያ ሥርዐቱም ወጥነት ያለውና ሞያን ያማከለ እንዲኾን ማድረግ ከተቻለ ሙስናን መቀነስ ይቻላል፡፡
ይህን ሥርዐት በመዘርጋትም ያለአግባብ መበልጸግን መከላከል ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ ካለፉት ዐሥር ዓመታት ወሳኝ በኾነ የሥልጣን ዕርከን ላይ የነበሩ ሓላፊዎች ሀብት እንዲፈተሽና ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ መኾኑ እንዲረጋጥ ቢደረግ በርግጠኝነት በቅርቡ በሙስና ወንጀል ወኅኒ ከወረዱ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የሚቀላቀሉ የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች እንደማይታጡ መገመት አያዳግትም፡፡ ለዘጠኝና ዐሥር ዓመታት ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣን ይዘው የሚጠቀስ ሥራ ያልሠሩ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በርከት ያሉ መኖሪያ ቤቶችን በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸውም ስም የገነቡ የቤተ ክህነቱ ምሁራን ነን ባዮችንም ማግኘት ይቻላል፡፡
ስለኾነም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዐት በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ በመጀመሪያ ሙሰኞችን ማጋለጥ፣ በሕግ መጠየቅና ማስቀጣት የሙስና ምንጭ የኾኑ የአሠራር ቀዳዳዎችን በሙሉ በመዝጋት ጥናትን መሠረት ያደረገ የአሠራር መዋቅርን መፍጠር ይገባል፡፡ ይህን ከማድረግ ጎን ለጎን ከተቻለ ከቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ጀምሮ ተሿሚዎች ሁሉ ሀብትና ንብረታቸው ቢመዘገብ ሙሰኝነትን በቀጣይነት ከመዋጋት አንጻር መልካም ይኾናል፡፡ በመጨረሻም በሙስና ዙሪያ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እስከ አጥቢያ ድረስ በማካሄድ መጽሐፍ ቅዱስ አስተሳሰቡንና ድርጊቱን በግልጽ የሚኮንነውን ሙሰኝነት በተግባር የሚቃወምና የሚኮንን አመራር መፍጠር ይቻላል፡፡
ለውጥና አስፈላጊነቱ
ከቤታችን ተጨባጭ ኹኔታ አንጻር ሲመዘን ለውጥ አስፈላጊ እንደኾነ በአንደበታቸው የሚመሰክሩ፣ ተግባራዊና ውጤት ሊያመጣ የሚችል ጥናት እንዲደረግ በዘመናዊ አሠራር የሠለጠኑ ባለሞያዎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ የሚደግፉና ዘወር ብለው ደግሞ፣ ‹‹ይህን ሐሳብ ተቀብለን ተግባራዊ ካደረግነው ቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ላይ ትወድቃለች፤ አዲስና የተማረ የሰው ኀይል ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያስፈልጋትም፤ ባለው የሰው ኀይል ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤›› በማለት አባቶችን የሚያሳስቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ መሳይ ጠላቶች በሚመጥናቸው ቦታ ሊቀመጡ ይገባቸዋል፡፡
በመሠረቱ የዘመናዊ አሠራር ውጤት የኾነው ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማእከል ያደረገ አሠራር መዘርጋት የሚቻለው በቤተ ክርስቲያንም በዘመናዊው ትምህርትም ዕውቀት ያላቸውና ቅን አስተሳሰብን ያዳበሩ ለውጥ ፈላጊዎችን ማስተባበር ሲቻል እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በተንኮል የበለጸጉና በኪራይ ሰብሳቢነት ጐዳና ተጉዘው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከገቢያቸው ጋር በማይመጣጠን መልኩ በርካታ መኖሪያ ቤቶች የገነቡ የጨለማው ቡድን ሰብሳቢዎችን ይዞ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ግን የዋህነት ነው፡፡
አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን በአደረጃጀትና አሠራር መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ካልቻለች፣ የምትመራው ምእመን በተለያየ መንገድ የሠለጠነና በሠለጠነ መዋቅር ውስጥ የሚያገለግል ስለኾነ ተመሪው ከመሪው በሚበልጥበት ኹኔታ ረጅም ርቀት ለመጓዝ አዳጋች ይኾናል፡፡
በመሠረቱ ታቦታትን፣ ጥንታዊ ቅርሶችንና ንዋየ ቅድሳትን ዘርፎ የሚሸጥና የሚደራደር የካህን ደላላ ቁጥር በተበራከተበት ኹኔታ ሙዳይ ምጽዋት የሚሠብር፣ በስእለት የተሰጠውን ገንዘብ ለራስ ጥቅም የሚያውል ሙሰኛ ካህን በሠለጠነበት፣ በአጠቃላይ የረቀቀ የሙስና ስልት በቤተ ክርስቲያን እየነገሠ በሄደበት ኹኔታ በሙስና ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ የጀመረ፣ በዘመናዊ አሠራር ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘትና መስጠት የሚችል ሕዝብን መምራት በውኑ ይቻል ይኾን? ከተቻለስ ምን ያህል ርቀት ይወስደን ይኾን; የሚለውን ማጤንና ቤተ ክርስቲያኒቱን መታደግ በተለይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ይጠበቃል፡፡ ችግሩንና ችግሩ ይዞት የሚመጣውን ውጤት አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ከእምነቱ ተከታይ ምሁራን የሚጠበቅ ይኾናል፡፡
ሲጠቃለል ቤተ ክርስቲያናችንን በመጪው ትውልድ ውስጥ ያለአንዳች እንከን ለማስቀጠል፣ ቤተ ክህነታችን ትውልዱ የተቀበለውና የሚወደው ተቋም ለማድረግ ከተፈለገ በአሠራር በአደረጃጀትና በአገልግሎት አሰጣጥ እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብና የሚተገበር ዕቅድ በማዘጋጀት ለለውጥ መሥራት የግድ እንደሚል በመገንዘብ በዚህ ዙሪያ ጠንከር ያለ ውሳኔ ማስተላለፍ የግድ ይላል፡፡
ተግዳሮት
ዘመኑ እንደሚያመላክተን ለውጥን መቀበልና በለውጥ ውስጥ መጓዝ የግድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደራዊ መዋቅሯ ውስጥ ቀስ በቀስ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችላትን ሥራ መሥራቷ የማይቀር ይኾናል የሚል ተስፋ አለ፡፡ ተስፋ ብቻ ሳይኾን ለውጥና ዘመናዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ ከቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤና ከብፁዓን አባቶቻችንም እየተገለጸ ነው፡፡ ይህ ጥሩና በጎ ነገር ነው፡፡ ወደ ለውጥ በምናደርገው ጉዞም ተግዳሮት በመኾን ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉትን መለየትና ማወቅ ደግሞ የግድ ይላል፡፡
በዚህ ረገድ!
- ለውጥ ምን ያደርጋል!
- ዘመናዊ አሠራር በቤተ ክርስቲያን ለምን ያስፈልጋል፤
- የጥንቱ አሠራር እጅግ በጣም ጥሩ ነው፣ ስላልተጠቀምንበት ነው እንጂ፤
- አስተዳደሩ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባላቸው ብቻ መመራት አለበትና ወዘተ የሚሉ ተግዳሮቶች በጨለማው ቡድን አባላትና ለውጥን በማይፈልጉ ጥቂት ሰዎች መነሣቱ አይቀርም፡፡ ይህን ለማረምና ለማስተካከልም የጨለማውን ቡድንና አመራሩን ከክፏ ሥራው እንዲታቀብ ማድረግ
- ባልተመጣጠነ ገቢ በርካታ የመኖሪያ ቤት የገነቡ አመራሮችን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ ማድረግ
- በአመለካከትም በተግባርም ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮችን መለየት
- ለለውጡ ቀና አመለካከት የሌላቸውን የሥራ ሓላፊዎች በለውጥ ምንነት ዙሪያ በማሠልጠን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት
- ወሬና አሉባልታ አመላላሾችንና አናፋሾችን ማሥታገስና አለማስተናገድ
- በመረጃ በተደገፈ ጉዳይ ዙሪያ ብቻ መነጋገር የለውጡን ተግዳሮት ለማስቆም ቁልፍ ሥራዎች ይሆናሉ፡፡
ተቋማዊ አስተሳሰብና እምነት የሌላቸውን፣ በጎጥና በመንደር አስተሳሰብ ውስጥ የተዘፈቁትን በማጋለጥና መሥመር በማስያዝ እንዲሁም ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ ተግዳሮቶችን የተገነዘበ የስትራተጂያዊ ዕቅድ፣ የመዋቅርና ዝርዝር አሠራር ሰነድ በማዘጋጀት መንቀሳቀስ ካልተቻለ አበው፣ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” እንዲሉ የለውጥ ጉዟችን ከንግግር ማሣመርያነት የማይዘልና በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታዩ ችግሮች ሳይፈቱ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍበት ኹኔታ ይፈጠራልና በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል፡፡
*አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ሓላፊ ናቸው፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment