- ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ለኮሌጁ የመደባቸውን ሓላፊ አልቀበልም ብለዋል
- ከኮሌጁ እንዲባረር የተወሰነበትን ዘላለም ረድኤትን ዋና ዲን ለማድረግ አስበዋል
- ደቀ መዛሙርቱና መምህራኑ ለከፍተኛ ተቃውሞ እየተዘጋጁ ነው
- ፓትርያሪኩ ለአቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ የማደር ዝንባሌ እየታየባቸው ነው
በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን መልክ መያዝና እልባት ማግኘት ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ውሳኔን በተግባር ተፈጻሚ ለማድረግ ያለመቻልልምሾነት ነው፡፡ ችግሩ ከሁሉ በፊት፣ ከፍተኛ አመራሩ በመግለጫው ያስቀመጠውን ያህል ለውሳኔው ተፈጻሚነት አለኝ የሚለውን ቆራጥ አቋም አጠያያቂ የሚያደርግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይኸው ‹‹ጥርስ አልባነት›› የሚያረጋግጥልን÷ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና ጥቅመኞችአስተዳደራዊ መዋቅራችንን በማይናቅ ደረጃ እንደተቆጣጠሩትና በአንዳንድ አብነቶች ተስፋ ሰጪ መነሣሣቶች እየታዩበት በሚገኘው የለውጥ ርምጃ ላይ በቀጣይነት የሚጋርጡትን ስጋትና ዕንቅፋት ነው፡፡ ጥቂት አስረጅዎችን እንጥቀስ፡-
የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔዎች የተፈጻሚነት ጅምር ሚዛን
የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ችግር የመልካም አስተዳደር ዕጦት መኾኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡ በቀድሞው 1፡4 አስተዳደራዊ መዋቅር/አደረጃጀት የነበረው ምደባ ጥናት ተደርጎለትና መስፈርት ወጥቶለት የተካሄደ ባለመኾኑ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ እንደመጣ ተመልክቷል፡፡ በመኾኑም ሀ/ስብከቱ ወደቀድሞው አንድነቱ ተመልሶ በአስተዳደር ችሎታቸው ጠንካራ በኾኑ አንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስና እርሳቸውን የሚረዳና በሥራ ችሎታው ብቁና ጠንካራ በኾነ አንድ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ በርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወስኗል፡፡
በዚህም መሠረት በጅማ ሀ/ስብከታቸው ጉልሕ የልማት ውጤቶችን በማስመዝገብና የቤተ ክርስቲያንን ሰላም በመጠበቅ በዞኑ የመንግሥት አስተዳደር ከፍተኛ ግምት የተሰጠው እንቅስቃሴ ያደረጉት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው በቅ/ሲኖዶሱ ተመድበዋል፡፡ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በበኩላቸው የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሾመዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱንም በቂ ሥልጣን በሚሰጣቸው ከ7 ‐ 10 በሚደርሱ የወረዳ (ክፍለ ከተማ) ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ለማዋቀር/ለማደራጀት በአስተዳደር ጉባኤ አባላትና ብፁዕነታቸው ባደራጁት የባለሞያ ቡድን ጥናት እየተካሄደ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በፓትርያሪኩ የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ንግግር ላይ እንደሰማነው የሥ/አስኪያጅ ምደባና ሥያሜው በሀ/ስብከቱ፣‹‹ተጠያቂነትና ሓላፊነት ያለው ጠንካራና ግልጽ የአስተዳደር ሥርዐት ለመዘርጋት›› በመኾኑ የመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ምደባና ሥያሜ አግባብነት መገምገም ያለበት በዚህ ዐይን መኾን ይኖርበታል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቁ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት በትምህርት ዝግጅታቸውና በሞያ ልምዳቸው ለክህነታዊ አገልግሎቱ (መስበክ፣ መዘመር፣ መቀደስ) የበረቱ እንደኾኑ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፤ ያምኑባቸዋልም፡፡
ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ነቀርሳ የኾነውን የመልካም አስተዳደር ችግር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ መግለጫ ላይ በተመለከተውና ሀ/ስብከቱን በመልካም አስተዳደር አርኣያነት በሚያስጠቅስ ክሂልና ቁርጠኝነት ለመፍታት፣ የመጋቤ ሐዲስ ይልማ የሥራ አስኪያጅነት ምደባና ሥያሜ ያለው ፍቱንነት ግን ብዙዎችን በጥያቄ ሣጥን ውስጥ የተወ ኾኗል፡፡ በመግለጫው እንደተባለው÷ የሥራ አስኪያጅነት መስፈርት ወጥቶ ውድድር አለመካሄዱ ምደባና ሥያሜው ክህነታዊ አገልግሎቱን መልካም አስተዳደር ለማስፈን ከሚያስፈልገው ሞያና ልምድ ጋራ በማቀናጀትና የሀ/ስብከቱን መሠረታዊ ችግር ከግንዛቤ በማስገባት የተፈጸመ ስለመኾኑ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡
ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅነት የተደረገው ሹመትም ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ኹኔታው ምናልባትም በ፳፻፪ ዓ.ም የተቋቋመው ‹‹አጣሪ ኮሚቴ›› በሪፖርቱ እንዳስቀመጠው፣ ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ክርስቲያኖችን ያማከለ በመንበረ ፓትርያሪክም ይኹን በአህጉረ ስብከት የማማከር ሞያዊ ድጋፍ የሚሰጡ አባላት ያሉበት በመንበረ ፓትርያሪክ የቅ/ሲኖዶስ አማካሪ ምክር ቤት፤ በአህጉረ ስብከት ደግሞ የመንበረ ጵጵስና አማካሪ ኮሚቴ ማቋቋም›› አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሳያጎላው አልቀረም፡፡
* * *
ከቤተ ክርስቲያን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣመውን አሳፋሪና አሳዛኝ ብልሹ አሠራር የሚያርምና የሚያስወግድ÷ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ በእንክርዳዱ ላይ አስተማሪ ሕጋዊ ርምጃ የሚወስድ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእይና ተልእኮ በግልጽ የሚያሳይ ስትራተጂያዊ ዕቅድ የሚቀይስ፣ ሕግና ደንብ የሚያሻሽልና አስተዳደሩን በአዲስ መልክ የሚያዋቅር፤ የፋይናንስ አሠራሩን ዘመናዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ የሚያደራጅ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ተቋቁሟል፡፡
ዐቢይ ኮሚቴው÷ ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሁለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አምስት ምሁራን ምእመናን በአባልነት የሚገኙበት ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የዐቢይ ኮሚቴውን አባላት በጽ/ቤታቸው ጠርተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሥራ መመሪያቸው የኮሚቴው አባላት በሂደት ሊገጥሟቸው በሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ሳይፈቱ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋቸዋል፡፡ ኮሚቴውን በፍጥነት ለማቋቋም መቻሉ የሚያስደስት ነው፡፡
ነገር ግን ከ‹‹ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን›› በኮሚቴው አባልነት ከተካተቱት አንዱ የኾኑትን መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ ኤልያስን በማሳያነት እንውሰድና ግለሰቡ በርግጥ የተወከሉበትን ዘርፍ ለመወከል ይበቃሉ ወይ? ዐቢይ ኮሚቴው ስትራተጂክ ዕቅድ ለመቀየስ፣ ሕጎችንና አሠራሮችን ለማሻሻል ተለይቶ ለተሰጠው ተልእኮስ ይመጥናሉ ወይ? ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ እንዳሳሰቡት ዐቢይ ኮሚቴው የተጣለበትን አደራ ከትችት ነጻ ኾኖ በአግባቡ ለመወጣት ያስችለዋል ወይ?
በትምህርት ዝግጅትና በሞያ ብቃት ከእርሳቸው የተሻሉና የላቁ ሊቃውንት ባሉበት ኹኔታ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት፣ ከአስተዳደር መምሪያና ከቊሉቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያዎች ዋና ሓላፊነት ካለባቸው አቅም ማነስና ብልሹ አሠራር ጋራ ሲዘዋወሩ የቆዩትን ግለሰብ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሂደት የሚወስን እጅግ አስፈላጊ ርምጃ›› ለተሰኘው ተግባር ማጨት ትእምርታዊነቱን ትልቅ ምፀት ያደርጋዋል ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡
ዐቢይ ኮሚቴው ዝርዝር ሥራውን የሚሠሩ የኤክስፐርቶች ቡድን በማደራጀት በባለሞያዎችና ሥራውን በበላይነት በሚቆጣጠረው የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲያሳልጥ ታቅዷል፡፡ ተስፋችን÷ የዐቢይ ኮሚቴው ሥራ በሂደቱ አሳታፊና በውጤቱም ከቅ/ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን አሠልጥኖ በማብቃት (mentoring) የለውጡ መሪና ባለቤት የማድረግ አካሄድ እንደሚኖረው ነው፡፡
የቤተ ክህነታችን አመራርና አስፈጻሚ የለውጡ መሪና ባለቤት ለመኾን በሚያደርገው ተሳትፎ የሚሸጋገርለትን ዕውቀትና ክህሎት ከራሱ ጋራ አዋሕዶና ለረጅም ጊዜ ይዞ ይሠራበት ዘንድ እንደ መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ በዘመን ከገፉ ሓላፊዎች ይልቅ÷ በዕድሜያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሞያ ልምዳቸውና ለለውጥ ባላቸው አዎንታዊ አመለካከት ለዐቢይ ኮሚቴው ሥራ በተሻለ የሚቀርቡቱ ዳግም ይመረጡ ዘንድ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህን ተልእኮ ለመቀበልና ለማስፈጸም የሚበቁ ወጣትና ጎልማሳ ባለሞያዎች ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድርጅቶችና መምሪያዎች ውስጥ አሉ፡፡
በዚህ ረገድ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለፈው ሳምንት ያካሄደውን የሀገር አቀፍ አጠቃላይ ጉባኤ ምሥረታ በማዘጋጀትናያጸደቀውን የመምሪያውን ስትራተጅያዊ ዕቅድ በመቅረጽ ጉልሕ ሚና ከተጫወቱ የመምሪያው አገልጋይ ምሁራን መካከል ሁለቱ በዐቢይ ኮሚቴው እንዲካተቱ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ መመረጣቸው በምሳሌነት የሚጠቀስና ምርጫው እዚያው ሳለም የወጣቶቹን ተምኔት የሚያሳካ (self – fulfilling prophecy) ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን መዋቅር እንዲያጠና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ጋራ በማቀናጀት ባቋቋሙት የባለሞያ ቡድንም የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በግል የሚያደርጉት አስተዋፅኦ አነቃቂነት ያለው ነው፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን በመንፈሳዊ ኮሌጆቻችንና በነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር እንዲሁም በመምሪያዎችና ድርጅቶች ውስጥ የለውጥ ንቅናቄውን በግንባር ቀደምነት ለማገዝ አቅሙም ፍላጎቱም ያለው የሰው ኀይል ፍተሻ በቅጡ ሊካሄድ ይገባል፡፡
አቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ ፈጣሪ?
የቤተ ክህነታችንን ብልሹ አሠራር ለማረምና ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት በሥርዐቱ ላይ የሚያተኩር እንጂ ግለ ሰዎችን ለማደንና ለመጉዳት እንዳልኾነ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡ ይኹንና የዐቢይ ኮሚቴው አንዱ ተግባር በፍትሐዊ ምርመራ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ ማቅረብና እንክርዳድ ኾነው በተገኙት ላይ አስተማሪና ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ መኾኑን አልሸሸጉም፡፡
ከዚህ አኳያ እንደ መዝገብ ጥበብ ዮሐንስ ኤልያስ ባሉት ላይ የምናተኩረው ታዲያ፣ እርሳቸውን በግለሰብ ደረጃ ለይቶ ለማጥቆር አልያም ከ‹‹ሙስና ጌቶች›› የበለጠ ጥፋት ስለፈጸሙ አይደለም፡፡ ይልቁንም በአንድ በኩል፣ ለውጡ በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ፍጹም መታየት የለበትም›› ለተባለው ሙሰኝነት ያለውን የፍጹምነት ትእምርታዊ ዋጋ ለመጠበቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ፣ለውጥን መኾን ከሚገባው አቅጣጫ ይልቅ እንዲኾን በሚፈልጉት አቅጣጫ በመውሰድ ለማብተክ ከሚሞክሩ አማሳኞች (saboteur) አስቀድሞ መከላከል ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ለዚህም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በአስተዳደሩ መካከል የተቀሰቀሰውን ውዝግብ ለመፍታት በተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ውስጥ መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ ያራመዱትንና በልዩነት የወጡበትን አቋም መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡
እንደሚታወሰው ሁሉ ውዝግቡ የተፈጠረው÷ የኮሌጁ የትምህርት አመራር ብቃትና አግባብነት ባላቸውባለሞያዎች እንዲመራ፣ የኮሌጁ አገልግሎት ለኮሌጁ በሚመደበው በጀት መጠን እንዲሻሻል ደቀ መዛሙርቱ ጥያቄያቸውን ጠንክረው በማቅረባቸው በአንጻሩ ደግሞ የኮሌጁ አስተዳደር በተለይ የበላይ ሓላፊው ባሳዩት ግትርነት ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በጥያቄያቸው/ተቃውሟቸው ለትምህርት አመራሩ ብቃትና አግባብነት የሌላቸው ሓላፊዎች ከቦታቸው እንዲወገዱ፣ የኮሌጁ በጀትና የገቢ ምንጭ በጥቅም ትስስር ከመመዝበር ድኖ የሕንጻው ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ የዶርሚተሪው፣ የምግብ ቤቱና የቤተ መጻሕፍቱ አገልግሎት እንዲሻሻል ነው፡፡ ጥያቄው በቅንነት ከተወሰደ ኮሌጁ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ እና ትውፊት እንዲጠበቅ፣ የመምህራኑን አቅም በማሳደግ የትምህርት ጥራቱን ለመጠበቅና በቂ ግንዛቤና ዕውቀት ያዳበሩ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት›› የሰነቀውን ርእይ ለማሳካት የሚረዳ ነው፡፡
ከፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከፖሊስ በመውጣጣት የተቋቋመው አምስት አባላት የሚገኙበት ኮሚቴ ለሦስት ሳምንታት ያህል በኮሌጁ በአካል እየተገኘ÷
- የኮሌጁን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ መምህራንንና ተማሪዎችን ሰብስቦ የትምህርት አመራሩንና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ተፈጽመዋል ስለተባሉ ሕገ ወጥ አሠራሮች በማነጋገር፣
- ተቃውሞ የቀረበባቸውን ሓላፊዎች የትምህርት ማስረጃዎች፣ አወዛጋቢ የፈተና ውጤት የሰጡባቸውን ሰነዶችና ከዚህም ጋራ በተያያዘ በተማሪዎች ላይ ደርሰዋል የተባሉትን አካላዊና ሞራላዊ በደሎች በመመርመር፣
- የዶርሚተሪውን፣ ምግብ ቤቱንና ቤተ መጻሕፍቱን ሕንጻዎችና አገልግሎቶች በመመልከት፣
የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄዎች አግባብነት ሲያጣራ ቆይቷል፡፡ የማጣራቱ ሂደት ደቀ መዛሙርቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ ስለመኾኑ አረጋግጧል፡፡ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ግን በአጣሪ ኮሚቴው የተረጋገጠውን ችግር ከነመፈጠሩም ለማሰብ አይፈልጉም፤ አንዳችም ሓላፊነት ለመውሰድም አይፈቅዱም፡፡
በማጣራቱ ሂደት የታየው አስገራሚው ጉዳይ÷ ይዞታቸው የተዳከሙና የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ ሕንጻዎች ይዞታ፤ በብልሽታቸው የጤንነት ስጋት የሚፈጥሩና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ የመማርያ ክፍሎች፣ የካፊቴሪያ፣ የዶርሚተሪ፣ የቤተ መጻሕፍትና የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች ገጽታ ብቻ አይደለም፡፡
ለኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ቀራቢ ለኾኑ አንዳንድ ሠራተኞች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር መምሪያ ሳያውቀው የሚከፈለው ደመወዝከተቀመጠው ስኬል በላይ መኾኑ አሳፋሪ ነው፡፡ የጠ/ቤ/ክህነቱን አከፋፈል ስኬል በተመለከተ መረጃውን ለአጣሪ ኮሚቴው ያቀረቡት የአጣሪ ኮሚቴው አባል መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ መረጃ በሰጡበትና ስሕተት ኾኖ በተገኘው በዚህ የኮሌጁ አሠራር ላይ ግን አቋም ለመውሰድ መቸገራቸው ተገልጧል፡፡
ከሓላፊነት እንዲነሡ ጥያቄ የቀረበባቸው ሁለት ሓላፊዎች በድኅረ ምረቃ (ሁለተኛ) ዲግሪ አለን ያሉትን የትምህርት ማስረጃ አጣሪ ኮሚቴው አግኝቶ ለማረጋገጥ ለሁለት ሳምንታት ያህል መለማመጥና መጠበቅ ነበረበት፡፡ በመጨረሻ ኮሚቴው አስጨንቆ ስለያዛቸው አካዳሚክ ዲኑ በቴዎሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ በሚል ያቀረቡት ማስረጃ በመርሐ ግብሩ የወሰዷቸውን ኮርሶች ዝርዝር አሟልቶ የማይገልጽ፣ ‹‹ሊታመን የማይችልና ተቀባይነት የሌለው›› ኾኖ መገኘቱ ተዘግቧል፡፡
የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ዘላለም ረድኤት ግን ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይኾኑ ከመቅረታቸውም በላይ ተቃውሞ ባቀረቡባቸው የደቀ መዛሙርት ተወካዮችና በአጣሪ ኮሚቴው አባላት ፊት የማጣራቱን ሂደት ረግጠው መውጣታቸው ተነግሯል፡፡ የኮሚቴው ምንጮች እንደገለጹት፣ ዘላለም ረድኤት በነገረ ክርስቶስና በክብረ ቅዱሳን አስተምህሮም ሕጸጽ እንደተገኘባቸው በደቀ መዛሙርቱ ክሥ ቀርቦባቸዋል፡፡
ኮሚቴው በዚህ አኳኋን ለሦስት ሳምንት ማጣራት ሲያካሂድ ከሰነበተ በኋላ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ባቀረበው የመፍትሔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡ ሕንጻዎቹና በውስጣቸው ለሚገኙ መገልገያ ዕቃዎች አስፈላጊው እድሳት፣ ጥገናና ቅያሪ (የተማሪዎች ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ ሳይቀር) እንዲካሄድ፣ የተነቃቀለው የቤተ መጻሕፍቱ ወለል እንዲስተካከልና ከንግድ ካፊቴሪያው የኩሽና ግድግዳ ጋራ የተያያዘው የቤተ መጻሕፍቱ ግድግዳ ተለያይቶ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡
ያልተሟላ የትምህርት ማስረጃ ያቀረቡት አካዳሚክ ምክትል ዲኑ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በማስተማር ብቻ እንዲሠሩ፣ የተጠየቁትን የትምህርት ማስረጃ ለማቅረብ ፈቃደኛ ካለመኾናቸውም በላይ የሃይማኖት ሕጸጽ ክሥ የቀረበባቸው የቀን መርሐ ግብር ሓላፊው ዘላለም ረድኤት ከኮሌጁ እንዲባረሩ፣ በማንኛውም የአገልግሎት ቦታ ከመመደባቸው በፊት ስለ ሕጸጻቸው በሚመለከተው አካል እንዲጠየቁ፣‹‹ምክትል ዋና ዲን›› የሚለው ቦታ በሙሉ ሓላፊነት በሚሠራ ዋና ዲን እንዲተካና ተገቢው ሰው እንዲመደብበት ኮሚቴው በአብላጫ ድምፅ ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል፤ ሪፖርቱም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቀርቦ የጋራ ምክክር ከተካሄደበት በኋላ የመፍትሔ ሐሳቡ ተቀባይነት ማግኘቱ ተመልክቷል፡፡ አፈጻጸሙ ግን በሐሳቡ ላይ የመስማማትን ያህል የቀለለ አልኾነም፡፡
የኮሚቴው ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲተላለፍ በአቋም የተለዩት መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ፣ በተለይ በሓላፊዎቹ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ያለበቂ ምክንያት መቃወማቸው እንደሚወራው ከጥቅምና ወገንተኝነት አንጻር እንጂ በመርሕ የተደገፈ አቋም እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታዲያ ኮሚቴው የማጣራት ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የቊሉቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ሓላፊ የነበሩት መዝገበ ጥበብ ዮሐንስ ሰሞኑን የአስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው መመደባቸው በምን መመዘኛ ተለክቶ ነው?
የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ለኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳብ ያሳዩት ተቃውሞ በአቋም ከመለየት አልፎ በተግባርም የተንጸባረቀ ነው፡፡ ይኸውም በዜናችን እንደገለጽነው ከኮሌጁ ምክትል ዋና ዲንነት ተነሥተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ም/ሥ/አስኪያጅ በኾኑት ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም ምትክ የቤቶችና ሕንጻዎችና አስተዳደር ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ተመድበው ነበር፡፡
አቡነ ጢሞቴዎስ ግን ‹‹ምደባው ከእኔ ዕውቅና ውጭ የተደረገ ነው፤ የምፈልገውን ሰው ከውስጥ አሳድጋለኹ እንጂ የተመደቡትን ሓላፊ አልቀበልም፤›› በሚል በፓትርያሪኩ ላይ ቀጥተኛ ጫና በመፍጠራቸው በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ የተወሰነው የመልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ ምደባወደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊነት እንዲዛወር፣ የዚሁ መምሪያ ሓላፊ የኾኑት መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ ደግሞ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ እንዲኾኑ ተደርጓል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎችና ድርጅቶች የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ በኮሌጁ የተከታታይ(ማታ) መርሐ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪያቸው አግኝተዋል፤ በኮሌጁ መመደባቸውም ጥቂት የማይባሉ የኮሌጁን ማኅበረሰብ አባላት አስደስቶ ነበር፤ ደስታው ከአንድ ቀን በላይ አልዘለቀም እንጂ፡፡ የዶ/ር አባ ኀይለ ማርያምን መነሣት ‹‹ዕድገት ነው›› በሚል ያልተቃወሙት አቡነ ጢሞቴዎስ የመልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ መመደብ ምነው አልተስማማቸው?
የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ‹‹ከውስጥ አሳድጋለኹ›› በሚል በያዙት ዕቅድ ከኮሌጁ እንዲባረር የተወሰነበትን ዘላለም ረድኤትን በም/ዋና ዲንነት ለማሾም ማሰባቸው እየተነገረ ነው፡፡ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ የኮሌጁ ም/ዋና ዲን ኾነው እንዲሠሩ የተሰጣቸው የቀደመው ምደባ ተፈጻሚ አለመኾኑ ‹‹ለአቡነ ጢሞቴዎስ ያልተገባ ተደጋጋሚ ተጽዕኖ የማደር ዝንባሌ ነው›› በሚል ፓትርያሪኩንና የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱን አስተችቷል፡፡
ከዚህ ባልተናነሰ የሚያሳስበው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ ከተጠያቂነት ውጭ መስለው በሚታዩት በአቡነ ጢሞቴዎስ ‹መልካም ፈቃድ› እና ሌሎች ተላላኪዎቹ ልመና ዲንነትን ለመቀዳጀት የከጀለው የዘላለም ረድኤት ተስፈኝነት ነው፡፡ ነገሩ ከምኞት አልፎ እውን ከኾነ የጥያቄያቸውን ምላሽ በከፍተኛ ትዕግሥት ሲጠባበቁ የቆዩትን ደቀ መዛሙርትና መምህራን ቁጣ ቀስቅሶ ወደ አላስፈላጊ የግጭት ምዕራፍ እንዳያሸጋግረው ተሰግቷል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ በአፈጻጸም ልምሾነትና በጥርስ አልባነት ከመደንበሽ እንታደገው ስንል ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ መልእክት አለን፡፡ አንድ የፓፓዎች ዜና መዋዕል አሰናጅ፣ “Charisma has to be changed to structure” ብለዋል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment